Friday, October 2, 2015

‹‹የመጽናናት ሁሉ አምላክ››


      (2 ቆሮ. 1፡3)
 
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
 
አርብ መስከረም 21 ቀን 2008 የምሕረት ዓመት
 
          በቅዱሱ መጽሐፋችን ‹‹አጽናኑ፤ ሕዝቤን አጽናኑ፡ ይላል አምላካችሁ፡፡›› /ኢሳ. ፡1/ ተብሎ እንደተጻፈ፤ ክርስቲያኖች በፈተናና በመከራቸው እርስ በእርስ የሚጽናኑበት ‹‹የርኅራኄ አባትና የመጽናናት ሁሉ አምላክ›› እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ 
 
          እርሱ አምላካችን የዘላለም አምላክ፤ የምድር ዳርቻ ፈጣሪ፤ የማይደክም የማይታክት፤ ማስተዋሉም የማይመረመር፤ ሰማያትን የፈጠረ የዘረጋቸው፤ ምድርንና በውስጥዋ ያለውን ያጸና፤ በእርስዋ ላይ ለሚኖሩ ሕዝብ እስትንፋስን፣ ለሚሄዱባትም መንፈስን የሚሰጥ ነው፡፡   

Saturday, September 19, 2015

ከማያምንም የከፋ፡


ቅዳሜ መስከረም 8 ቀን 2008 የምሕረት ዓመት 

         ‹‹ነገር ግን ለእርሱ ስለ ሆኑት ይልቁንም ስለ ቤተ ሰዎቹ የማያስብ ማንም ቢሆን፥ ሃይማኖትን የካደ ከማያምንም ሰው ይልቅ የሚከፋ ነው።›› /1 ጢሞ. 5፡8/፡፡

        ቤተ፡ ሰብ፤ የብዙ ነገሮች መሠረት እንደ ሆነ በብዙዎች ዘንድ ይነገራል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም እንዲሁ ለቤተ፡ ሰዎች ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣል፡፡ በብሉይ ኪዳን ቤተ፡ ሰብ የሚለው፤ በአዲስ ኪዳን ቤተ ሰዎች በማለት ተጽፎ እናነባለን፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ትኩረት ከሰጣቸው ነገሮች አንዱ በቤተ፡ ሰዎች መካከል ያለው ግንኙነት ተጠቃሽ ነው፡፡

        የመጽሐፍ ቅዱሳችን የመጀመሪያ ክፍል የዘፍጥረት መጽሐፍ ስለ ስድስት ቤተ፡ ሰዎች ማለትም አዳም፤ ኖኅ፤ አብርሃም፤ ይስሐቅ፤ ያዕቆብና ዮሴፍን ቤተሰባዊ ኑሮ የሚተርክና ለኪዳኑ ታማኝ የሆነውን እግዚአብሔር የሚያሳየን ድንቅ መጽሐፍ ነው፡፡ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ እንደ አቤል ያለውን የእምነት ሰው፤ ደግሞም እንደ ቃየል ያለውን የሞት ልጅ የምናገኝበት ብዙ ትኩረትና ማስተዋላችንን የሚጠይቅም ክፍልም እንደሆነ ልብ እንላለን፡፡

Sunday, September 13, 2015

ዘመን እንደ ዮሐንስ


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

ቅዳሜ መስከረም 1 ቀን 2008 የምሕረት ዓመት  

           በቤተ፡ ክርስቲያን 2008 የምሕረት ዓመት ‹‹ዘመነ ዮሐንስ›› ይባላል፡፡ በአዲስ ኪዳን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ወንጌላቱ በተቀመጡበት ቅደም ተከተል በአራት ዓመት አንድ ጊዜ አንዱ ወንጌላዊ ዘመኑ ይሰየምበታል፡፡ ብዙ ሰዎች ልብ ባይሉትም ዘመን በተፈራረቀ ቁጥር አንዱ ወንጌላዊ ለሌላው እየተቀባበለ ዓመቱ በወንጌል ጸሐፊዎቹ ስም ይጠራል፡፡

Friday, August 21, 2015

ፍቅር እና ጀበና


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

አርብ ነሐሴ 15 ቀን 2007 የምሕረት ዓመት

እዚያ . . . ቡና ጠጡ፤
አሉባልታ አድምጡ።
ብዬ ከወዳጆቼ ተሰባስቤ፤
ለወሬ ተሰናድቶ ቀልቤ።
የሰው ሥጋ ስንቋደስ፤
ስንቀቅል ስንጠብስ።
ከፍም የተገናኘው ሸክላ፤
በእሳቱ ነበልባል ሲበላ።
ድንገት . . . እፍ . . . እፍ . . . ኧረ ገነፈለ፤
ቡናው ከጀበናው ዘለለ።
እኛ ስናወራ እሳቱ አይሎ፤
ጀበናው የውስጡን አወጣ አግተልትሎ፡፡
እዚህ . . . ቡና ጠጡ፤
ቃሉን አድምጡ። 
ብዬ ወዳጆቼን ሰብስቤ፤
ለቃሉ ተሰናድቶ ቀልቤ።
የሰው ነፍስ ስንናጠቅ፤
ከክፉ ሥራ ስናላቅቅ።
ከፍም የተገናኘው ሸክላ፤
በሳቱ ነብልባል ሲበላ።
ድንገት . . . እሰይ . . . እሰይ . . . ገነፈለ፤
ፍቅር ከጀበናው ዘለለ።
ከተሰባሪው ገል ገላ፤
ከእኔነቴ ሸክላ።
የመለኮት እሳት በዝቶ፤
ውስጤን አግሎ አፍልቶ።
እንደ ፈሳሽ ምንጭ፤
ከሰዎች ሲሰራጭ።
የሕይወት ቡና ቢያጠጣ፤
ከሸክላነታቸው ሸክላ ወጣ።
እናንተም የፍቅሩ ቁራሾች፤
የመለኮት እሳት ተካፋዮች።
ከፍቅር ጀበና ገንፍሉ፤
ከሸክላነታችሁ ውጡና ዝለሉ።


                  

Friday, August 14, 2015

ስፍራችሁን ያዙ

(ካለፈው የቀጠለ)

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

አርብ ነሐሴ 8 ቀን 2007 የምሕረት ዓመት

      ‹‹ነጽር ኀበ አይ መካን አዕረጋ ለቤተ ክርስቲያን ዘከመ ይእቲ ኩለን ሰሐባ በጥበብ እምሉዓሌ፡፡ ወክመዝ አዕረጋ ኀበ ልዕልና ዐቢይ÷ ወለዝንቱ ዘውእቱ እምኔነ አንበሮ ዲበ ዝንቱ መንበር÷ ወለነሂ ዓዲ ለቤተ ክርስቲያን ስሐበነ እግዚአብሔር ኀቤሁ በከዊኖቱ ርእሰ ዚአነ እስመ ውስተ መካን ኀበ ሀሎ ርእሰ ህየ ይሄሉ ሥጋ ቤተ ክርስቲያን አካሉ እንደ መሆንዋ መጠን ወዴት ከፍ ከፍ እንዳደረጋት አስተውል፡፡ ከላይ ሆኖ በጥበብ ወደ እርሱ አቀረባት እንደዚህ ወዳለ ክብርም አወጣት ከእኛ ወገን የሆነውን /ከመለኮት ጋር የተወሐደውን/ ትስብእትንም በዚያ ዙፋን በቀኙ አስቀመጠው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የሆንነውን እኛንምርስቶስ ራሳችን በመሆኑ እግዚአብሔር ወደ እርሱ ሳበን÷ ራስ ካለበት ሕዋሳት ይኖራሉና››      

/ሃይማኖተ አበው ዘዮሐንስ አፈወርቅ፤ 67÷39/ 

Monday, June 29, 2015

ስፍራችሁን ያዙ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!ሰኞ ሰኔ 22 ቀን 2007 የምሕረት ዓመት

በዚህ ምድር ላይ እጅግ አስፈሪው ሰው ክርስቶስ የሌለውን ማንነት የያዘ ነው፡፡ ለምድሪቱ እግዚአብሔር እንደሌለው ሰው ያለ ሥጋትና ሽብር፤ የሁከት ርዕስና የክፋት ሥር የለም፡፡ ለአመፃ ጉልበት በሚሆኑ፤ ለከንቱ ኑሮ አቅም በሚፈጥሩ፤ ሰውን ከባህርዩ ውጪ ነውርን በሚያለማምዱ ብዙ ነገሮች መሐል በምንመላለስበት የዚህ ዓለም ስርአት፤ ማምለጥ የደኅንነት አምላክ በሆነው በእግዚአብሔር ነው፡፡
‹‹አምላካችንስ የደኅንነት አምላክ ነው፤ ከሞት መውጣትም ከእግዚአብሔር ነው።›› /መዝ. 67፡20/ እንደተባለ፤ ደኅንነት ከእግዚአብሔር፤ ከሞት ማምለጥም ሁሉን ከሚችል አምላክ ነው፡፡ ነቢዩ በሌላ ስፍራ ‹‹እግዚአብሔር ከመቅደሱ ከፍታ ሆኖ ተመልክቶአልና፥ ከሰማይ ሆኖ ምድርን አይቶአልና የእስረኞችን ጩኸት ይሰማ ዘንድ፥ ሊገደሉ የተፈረደባቸውን ያድን ዘንድ›› /መዝ. 101፡19-20/ እንዳለ፤ መዳን በእርሱና ከእርሱ ካልሆነ በቀር ሥጋ ለባሽ ሁሉ ከዘላለም ፍርድና ኩነኔ ሊያመልጥ አይችልም፡፡

Sunday, April 19, 2015

በዚያ አይፈልጓችሁ


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
እሁድ ሚያዝያ 11 ቀን 2007 የምሕረት ዓመት
‹‹ሕያውን ከሙታን መካከል ስለ ምን ትፈልጋላችሁ? ተነሥቶአል እንጂ በዚህ የለም።››
 /ሉቃ. 24፡5/
         የብሉይ ኪዳን መጻሕፍ የሚጀምረው የእግዚአብሔርን ሉዓላዊነት በማወጅ ነው፡፡ ‹‹በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ።›› /ዘፍ. 1፡1/፤ እግዚአብሔር የበላይ የሌለበት ሉዓላዊ አምላክ ነው፡፡ እርሱ እንደሚያይ የሚመለከት ሌላ፤ እርሱ እንደሚያውቅ የሚረዳ ሌላ፤ እርሱ እንደሆነው የሚገኝ ሌላ የለም፡፡
         ‹‹ብቻውን ተአምራትን የሚያደርግ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ›› /መዝ. 71፡18/፤ ‹‹እርሱ ብቻውን ታላቅ ተአምራትን ያደረገ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና›› /መዝ. 135፡7/፤ ‹‹እርሱ ግን ብቻውን ነው፤ እርሱንስ የሚመስለው ማን ነው? ነፍሱም የወደደችውን ያደርጋል።›› /ኢዮ. 23፡13/፤ የሚሉት መዝሙራት እግዚአብሔር ብቻውን የበላይ ገዥ አምላክ መሆኑን ያስረዱናል፡፡
         ነቢዩ በሌላ ስፍራ ‹‹እግዚአብሔር ታላቅ ነው፤ እጅግም የተመሰገነ ነው፤ ለታላቅነቱም ፍፃሜ የለውም፡፡ ትውልደ ትውልድ ሥራህን ያመሰግናሉ፤ ይልህንም ያወራሉ፡፡ የቅድስናህን ግርማ ክብር ይነጋገራሉተአምራትህንም ይነጋገራሉ፡፡ የግርማህንም ኃይል ይናገራሉታላቅነትህንም ይነጋገራሉብርታትህንም ይነጋገራሉ፡፡›› /መዝ. 144፡3-6/ ይላል፡፡ ስለ እግዚአብሔር ከተነጋገርን ብርታትና ታላቅነቱን እንነጋገራለን እንጂ እርሱ ድካም የለበትም፡፡ በዘመናት የማይቀያየር፤ በሁኔታዎች የማይዝል ግርማ የእግዚአብሔር ነው፡፡ ይታጣል ይሞታል ተብሎ ለእርሱ አይሠጋም፡፡