Thursday, February 16, 2012

የምስጋና ዋጋ



   ጥንታዊ በሆነ አንድ ገዳም ውስጥ የነበረን ሃይማኖታዊ ስርዓት በምሳሌነት እናንሣ። የዚህ ስነ ስርዓት አንዱ መሰረታዊ ነገር በውስጡ የሚኖሩ ባህታውያን ዝም ማለት አለባቸው የሚል ሲሆን የመናገር እድል የሚዘጋጅላቸውም በሁለት ዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ በዚያን ጊዜ ታዲያ ሁለት ቃላቶችን እንዲናገሩ ይፈቀድላቸው ነበር፡፡
     አንድ ወጣት ይህን ስርዓት ከጀመረ በኋላ የሁለት ዓመቱን የአመክሮ ጊዜ ሲያጠናቅቅ አበምኔቱ ሁለት ቃላትን ይናገር ዘንድ ጋበዙት፡፡ እርሱም “የምግቡ መጥፎነት” ሲል ተናገረ። ከሁለት ተጨማሪ ዓመታት በኋላ እንደገና ሁለት ቃላት የመናገሩን እድል አገኘ። ታዲያ ይህንን አጋጣሚ “የመኝታው መቆርቆር” ለማለት ተጠቀመበት፡፡
    ከሁለት ዓመታት በኋላ ለሦስተኛ ጊዜ የገዳሙ መሪ ጋር ሲደርስ ተስፋ መቁረጥ በሚታይበት መንፈስ ውስጥ ሆኖ እንዲህ ሲል ተናገረ፡- “እኔ ለቅቄያለሁ”፤ የገዳሙም አበምኔት ወደ ወጣቱ እየተመለከቱ፡- “ታውቃለህ! ያልከው ሁሉ እኔን ትንሽ እንኳን አልደነቀኝም፡፡ እዚህ ከደረስክበት ጊዜ አንስቶ እያደረክ ያለኸው ማማረር፣ ማማረር፣ ማማረር . . . . ብቻ ነው” አሉት። ወደእኛ ሕይወት እንምጣና ኑሮን በሁለት ቃላቶች እንድንገልጸው እድሉ ቢሰጠን ምላሻችን ምን ይሆን ነበር? ትኩረትህ በአሜኬላዎቹ በጉብታዎቹና ፍትሃዊ ባለመሆን ላይ ይሆን ነበር? ወይስ መልካም ትክክልና ተወዳጅ በነበሩት ሁኔታዎች ውስጥ ለመኖር ቆርጠህ ትነሣ ነበር?
    ለልባችን ከጣፋጩ ይልቅ የመረረው ቅርብ የሆነበት ምስጢር አለማመስገን ነው፡፡ አእምሮን ከሚያልፍ ሰላም ርቀን የሕሊናችን ትኩሳት አልበርድ ያለውም ብዙ ተቀብሎ ጥቂት ከማያመሰግን ሰብእናችን የተነሣ ነው፡፡ ኑሮ ከምግብ መጣፈጥ፣ ከመኝታ መመቸት፣ ከቦታ መደላደል፣ ከሥጋ መቀማጠል የዘለለ ቁም ነገር አለው፡፡ በዚህም ምድር ሳለን ከዚህ ከፍ ያለ ዓላማና ጉዞ ከሌለን እጅግ ምስኪኖች ነን!  
    እግዚአብሔርን በማመስገን፣ ስሙን በማክበር፣ ቃል ኪዳኑን በማመን፣ ጌትነቱን በማምለክ፣ ተስፋውን በመጠባበቅ የኖሩ በእሳት ውስጥ እንኳን ለአምላካችን አምልኮ ለንጉሣችን ውዳሴ ነበራቸው፡፡ የሁኔታ ለውጥ፣ የምቾት መጓደል፣ የጨካኞች ዛቻ፣ የሐሰተኞች ተንኮል የማያቀልጠው ልብ፣ የማያቆሽሸው ሕሊና እርሱ አመስጋኝ ነው፡፡ እግዚአብሔርን ለማመስገን ፈቃዱንም ላለማማረር ከበቂ በላይ ምክንያት አለን፡፡ የምናስወጣውና የምናስገባው አየር፣ ያለፈልን ሌሊት የተቀበልነው ማለዳ፣ ለዘላለም ኑሮ የተያዘልን ቀጠሮ . . . . የተባረከ ጥቂት ምክንያታችን ነው፡፡ ዛሬ ለመቀበል ትላንት የተደረገልንን በማሰብ ማመስገን ጤናማነት ነው፡፡ የሰጭውን ልብ ከሚያራሩ ነገሮች አንዱ ያለፈውን ውለታውን ማሰብ መቻላችን ነው፡፡ ተወዳጆች ሆይ የምስጋና ዋጋው የሚብራራው ባመሰገንበት መጠን ነውና አመስግኑ!
    አንድ ጊዜ የሰማሁትን ሌላ ምሳሌ ላካፍላችሁ፡፡ ሁለት ሰዎች እግዚአብሔርን ተመሳሳይ ነገር ለመኑት፡፡ እግዚአብሔርም ለአንዱ ሰጥቶ ሌላውን ከለከለው፡፡ ያልተቀበለውም ሰው በአምላኩ ፊት ቆሞ “ለባልንጀራዬ ሰጥተህ እኔን የነሳኸኝ ስለምንድነው” በማለት ሞገተ፡፡ ጌታም አምላክም የሆነው ሲመልስ “እርሱን ብከለክለው ኖሮ ከእኔ ይርቅ ነበር ስለዚህ በመስጠት በእቅፌ እንዲቆይ አደረኩት፡፡ አንተ ደግሞ ብሰጥህ ኖሮ በሰጠሁህ ረክተህ ሰጭውን እኔን ትተህ ትለየኝ ነበር፡፡ ስለዚህ አንተን በመከልከል የእኔ አደረኩህ፡፡” አለው፡፡ እግዚአብሔር ሲሰጠን ልክ የሚሆነውን ያህል ሲከለክለንም እውነተኛ ነው፡፡ እርሱ የሚሰጠንን ማንም መልአክ እንኳን እንደማይሰጠን እርሱ የከለከለንንም ከማንም አናገኘውም፡፡ “በጎ ስጦታ ሁሉ ፍጹምም በረከት ሁሉ ከላይ ናቸው÷ መለወጥም በእርሱ ዘንድ ከሌለ በመዞርም የተደረገ ጥላ በእርሱ ዘንድ ከሌለ ከብርሃናት አባት ይወርዳሉ፡፡” (ያዕ. 1÷17)፡፡ አሜን!

Tuesday, February 14, 2012

የወዳጅ ወጣ ገባ



    ሰው በሰው ብቻ ሳይሆን በራሱም ማዘዝ ይቸግረዋል፡፡ መሄድ እየፈለግን የምንቆምበት፣ መሥራት እየፈለግን የምንሰንፍበት፣ መስጠት እየፈለግን የምንነፍግበት፣ በጎ መናገር ሽተን ክፉ ስናወራ የምንውልበት ጊዜ የእድሜያችንን አብላጫ ይወስዳል፡፡ የእኔ ነው ያልነው የሰው የሆነብን፣ አቋሜ ነው ያልነው የተንሸራተተብን፣ ጨበጥኩት ያስኩት ያልነው ነፋስ መዝገን የሆነብን፣ አለ ያልነውን አለመኖር የለም ያልነውን ሕልውና እየተፈራረቀው የተቸገርን፣ ገባ ያልነውን ወጥቶ ወጣ ያልነውን ገብቶ እያገኘነው ግራ የገባን ብዙ ነን፡፡ ወዳጅ የልባችንን እልፍኝ ብቻ ሳይሆን ጓዳ ጎድጓዳውን የሚያውቅ፣ መልካሙን ብቻ ሳይሆን መጥፎውንም የሚረዳ፣ በደስታ ቀን ከብቦ የሚስቅ ብቻ ሳይሆን በሀዘንም ቀን ታጥቆ የሚያለቅስ ነው፡፡ ወዳጅ በጆሮ ሳይሆን በልብ የሚሰማ፣ ከአፍ ሳይሆን ከልብ የሚያደምጥ፣ ከሚደርሱ በፊት ቀድሞ የሚደርስ፣ ከሚቀርቡ በላይ አብዝቶ የሚቀርብ፣ ከሚያውቁ በላይ በጥልቀት የሚያውቅ፣ የማይነገር ያለስስት የሚነገረው፣ የማይታይ ያለመሽኮርመም የሚገለጥለት የማይካፈልን የሚያካፍሉት የልብ ነው፡፡

    ወዳጄ ነው! ማለት የቃሉን ያህል የሚቀል ኃላፊነትን ያዘለ አይደለም፡፡ ለዚህም ነው ጠላቴ በምንለው ከሚደርስብን ጉዳት በላይ የወዳጅ ማቁሰል የሚያንዘፈዝፈን፤ የአፍቃሪ መክዳት አቅል የሚያስተን፡፡ ወጡ ስንል በረንዳ ላይ፤ ገቡ ስንል በር ስር ገብተው አይገቡ ወጥተው አይወጡ ነገር በጉጉት የሚንጡ “አለ የለም፣ ገባ ወጣ፣ ሄደት መለስ፣ ሞቅ ቀዝቀዝ፣ በተን ስብስብ ” ግን ወዳጅ የምንላቸው የየእለቱ የቤት ሥራ ናቸው፡፡ እንዲህ ያለውን ሕመም ዘመናዊ ሐኪም፣ የባሕል መድኃኒት፣ የሥጋ ዘመድ፣ የሀብት ብዛት፣ የስልጣን ከፍታ፣ የእውቀት ጥልቀት አይረዳውም አይፈውሰውምም፡፡

ሰውየው ሚስቱ በመግቢያ ሰዓት እየወጣች በመውጫ ሰዓት እየገባች፤ እንተኛ ሲል እየተሰማራች፣ እንሥራ ሲል እየተጋደመች መከራውን አይኑ ፈጦ ታበላዋለች፡፡ እራት በመብያ ሰዓት ጉሊት ለመሸመት ትወጣለች አንዱን ጥላ ሌላውን አንጠልጥላ በዋል ፈሰስ በያዝ ለቀቅ በሩ ክፍቱን ያመሻል፡፡ ታዲያ ባል ቢቸግረው “ገብተሽ አልቀሽ እንደሆን በሩን ልዝጋው ወይ?” ማለት ጀመረ፡፡ አንዳንዴ ወደ ልባችን አልገባ ካሉን በላይ መግባት ጀምረው ገብተው ያላለቁት ዋጋ ያስከፍሉናል፡፡ በተናጉ ትዳሮች በተበተኑ ጋብቻዎች ላይ ከምናስተውለው የችግር ምክንያት አንዱ ገብቶ አለማለቅ ነው፡፡ አንዳንዶች በቸልተኝነት ሌሎች ደግሞ በብልጣብልጥነት እንዲህ ያለውን ስህተት ይፈጽማሉ፡፡ ብልጦቹ ገብተን ካለቅን ፍቅር ይቀዘቅዛል፣ መዋደድ ይሰለቻል፣ አብሮነትም ይታክታል ይላሉ፡፡ ስለዚህ ለእነርሱ ትዳርን የሚያቆመው ምሰሶ፤ የእድሜውም ዋስትና እንደ ቀብድ እየተሸራረፉ መግባት ነው፡፡ ዛሬ ስለ አይናቸው ያስጠኑናል እሱን አጣጥመን ስንጨርስ ደግሞ ተከታይ አፍንጫን ያብራሩልናል፡፡ አምስቱን የስሜት ሕዋሳት ሲያስጠኑን ብቻ ዐሥር ልደታችንን እናከብራለን፡፡ እንደነዚህ ያሉ ሰዎች በአንዴ የምንናገርለት ሙሉ ነገር የላቸውም፡፡ ስለ ልባቸው ስንጠየቅ እኛ ገና የምላሳቸው አልገባንም፡፡ ስለዚህ ልባቸው ወደ ልባችን ገብቶ እስኪያልቅ ድረስ የምንናገርላቸው አይኖረንም፡፡ በእርግጥም ገብተው ካላለቁ ምን ማውራት ይቻላል? ያለ በቂ መጠናናት የሚፈጸም ትዳርም ሆነ የዓላማ ወዳጅነት የማይጠግ ቁስል ሲያክሙ መኖር ነው፡፡

አዎ! የወዳጅ ወጣ ገባ ማለት ደስታም ሀዘንም፤ ማጣት ማግኘትም ነው፡፡ የወደዳችሁት እንደወጣ የተሰማችሁ መግባትም አለና የሻከረው ልባችሁ በዚህ ተስፋ ይለስልስ፡፡ ወዳጅ በሕይወታችሁ እልፍኝ እንደተሰበሰበ የተሰማችሁም መበተን አለና በዚህ አትመኩ፡፡ ብትወዱ ግን ብዙ ነገሬ ስለሆነው ወዳጄ ጥቂት ልንገራችሁ፡፡ ከገባ የማይወጣ ከያዘ የማይለቅ ካቀፈ የማይገፋ ከሳመ የማይነክስ ቃል ከሰጠ ቃሉን የማያጥፍ ፍቅሩን በቃል ሳይሆን በተግባር እያብራራ የሚደግፍ መታማት መነቀፋችሁ መሰደብ መሰደዳችሁ የማያሸሸው እግራችሁን ሊያጥብ የታጠቀ ሊያቆማችሁ የወደቀ ሊፈውሳችሁ የደቀቀ ሊያከብራችሁ የተዋረደ ለአርነታችሁ የታሠረ መለያው መስቀል የሆነ በአባቱ ቤት ብዙ መኖሪያ ያለው በዚያም ሥፍራን ያዘጋጀላችሁ ትንሣኤና ሕይወት መንገድና እውነት ክርስቶስ ኢየሱስ ነው! በእርሱ ዘንድ ብቻ ገባ ወጣ የለምና በደጅ ቆሞ ለሚያንኳኳው እንቢ እንዳትሉ ተጠንቀቁ!

ተወዳጆች ሆይ በእንባ መጥታችሁ ከነሀዘን፣ በድካም መጥታችሁ ከነመዛል፣ በሕመም መጥታችሁ ከነበሽታችሁ፣ በጥያቄ መጥታችሁ ያለ እረፍት፣ የማትመለሱበት ፊትና ዙፋን የጌታ ነው! መዋደድ ይብዛላችሁ፡፡

Monday, February 6, 2012

እሺታ ያለ ቦታው


  
    ሕይወት የእያንዳንዱ እለት ውሳኔዎቻችን ድምር ውጤት እንደመሆኗ በየቀኑ ፈቃደኝነታችንን የምናሳይባቸውና በእንቢታ የምናልፋቸው ነገሮች መኖራቸው ግድ ነው፡፡ ከዚህም በመነሣት ኑሮ እሺ ብቻ ሳይሆን እንቢም እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ በእርግጥም በማስተዋል ሆነን ካየነው የሚጥም እንዳለ ሁሉ የሚመር፣ የሚወራ እንዳለ ሁሉ የማይነገር፣ የሚገለጡበት እንዳለ ሁሉ የሚሸሸጉት፣ እሺታ እንዳለ ሁሉ በእንቢታ የሚለዩት መኖሩ ኑሮ ሚዛናዊነትን እንደሚጠይቅ ያስረዳናል፡፡ ለብዙዎቻችን በቦታውና በሰዓቱ እንቢ ማለት አለመቻል ብርቱ ፈተናችን ነው፡፡ ለጥቅማችን እንቢ ከምንል በእሺታችን ብንጎዳ እንመርጣለን፡፡ ነገር ግን መልካሙን በሙሉ ፈቃድ መታዘዝ እንጂ ሁሉንም እሺ ማለት ትክክል ሊሆን አይችልም፡፡ ምንም እንኳን የምንኖረው ሁሉ በተፈቀደልን ዓለም ላይ ቢሆንም በዚያው ልክ ደግሞ ሁሉም አይጠቅመንም፡፡
     በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔርን እሺ ማለት የምድርን በረከት እንደሚያበላ ስናነብ በአዲስ ኪዳን ደግሞ ሰይጣንን እንቢ (መቃወም) ማለት ከራሱ ከእግዚአብሔር ጋር እንደሚያጣብቅ ያስረዳናል፡፡ በቦታው ካልሆነ እሺታ፤ በጊዜው የሆነ እንቢታ የተሻለ ነው፡፡ እሺታችንን እውነተኛ የሚያደርገው እሺ የምንልበት አሳማኝ ምክንያት እንደመሆኑ፤ እንቢታችንም በዚህ ጎዳና ካለፈና እውነት ካለው አግባብነቱ አጠያያቂ ሊሆን አይችልም፡፡ ስለዚህም ከከንቱ እሺታ በእውነትና በመንፈስ የሆነ እንቢታችን ዋጋው ትልቅ ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች እንቢ ማለት አለመቻላቸውን እንደ ጽድቅ ሲቆጥሩት እንታዘባለን፡፡ እንዲህ ያሉ ሰዎች ኃጢያትን  እየሠሩ እንቢ ባለማለታቸው ብቻ መልካም ያደረጉ የሚመስላቸው ናቸው፡፡ ጥቂት ጊዜ ወስዳችሁ እንቢ ማለት ባለመቻላችሁ አልያም እንቢ ለማለት ፈቃደኛ ባለመሆናችሁ በሕይወታችሁ ውስጥ ስለገጠማችሁ ኪሳራ አስቡ፡፡ ፈቃዳችሁም ከሆነ በአስተያየት መስጫው ላይ አካፍሉን፡፡
    እውነተኛ በሆነ መንገድ እንቢ ማለት ያልተቻላቸው ሰዎች ከሁሉም ዓይነት እያነሱ ሁሉንም ለማስደሰት ነፍሳቸውን እያስጨነቁ ከእንቢና ከእሺ ሌላ እየፈለጉ የሚኖሩ ሆነዋል፡፡ በዚህም መንገድ የሚከፍሉት ዋጋ የሚያገኛቸው ኪሳራ ሁለንተናዊ ነው፡፡ በአግባቡ እንቢ ማለት አለመቻል የኑሮን ሌላ ጎን ለማወቅ ፈቃደኛ አለመሆንም ነው፡፡ ሙሴ የፈርዖን የልጅ ልጅ መባልን በእምነት እንቢ ብሎ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራን ለመቀበል ባይመርጥ፣ ዮሴፍ ከጲጥፋራ ሚስት የኃጢአት ገበታ ራሱን ባይሰበስብ የዝሙት ግብዣዋን ንቆ ባይሸሽ (እንቢ ባይል) ዛሬ ስለ እነርሱ የምናነበው ምን ሊሆን ይችል ነበር? ይህንን ባላደርግ እመርጣለሁ፣ ይህንን መሥራት እፈልጋለሁ፣ ይህንን ወድጄዋለሁ ይህን ደግሞ ጠልቼዋለሁ ማለትን መፍራት የለብንም፡፡ እውነተኛ እንቢታ የወዲያው ቢሆንም ውጤቱ ግን የእድሜ ልክ ነው፡፡ ሰዎች የማንፈጽመውን ተስፋ ከምንሰጣቸው ላንተገብረው እሺ ከምንላቸው ይልቅ በወቅቱ ለምንመልስላቸው እንቢታ ዋጋ ይሰጣሉ፡፡   
     ተወዳጆች ሆይ እንቢ ማለት ባለመቻላችሁ እንደ ሞኝ ተቆጥራችሁ፣ ከደካሞች ተደምራችሁ፣ ከሰው ትኩረት ተነፍጋችሁ፣ በመከራ ወጀብና አውሎ እያለፋችሁ፣ ኃጢአትን በውድም በግድም ተለማምዳችሁ፣ በአንደበት በድላችሁ ይሆን? ባላመንበት ነገር እሺ ብለን፣ ለቤተሰብ ደስታ ብቻ ስንል ካላረፍንበት ሰው ጋር ተሞሽረን፣ ከማንወደው ተግባርና የኑሮ ዘይቤ ጋር እየተሟገትን ይሆን? የምላችሁ ይህንን ነው “የእንቢታም ትክክል አለው” አልያ ግን “እንቢ አያውቁ” የብዕር ስማችን መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ ልብ በሉ! እስከ ሞት እሺ የማንለው፣ እስከ ስኬት የምናዘገየው፣ በይደር የማናቆየው ጉዳይ ሊኖረን ያስፈልጋል፡፡ “እሺ እሺ አብዝታ ቀረች ተንከራታ” እንደተባለው እንዳይሆንብን ከዓመፃ ጋር አለመተባበር ክፉውንም በእንቢታችን መኮነን ክርስትና ነውና ለዚህ መትጋት ይኖርብናል፡፡
                  ክፉውን እንቢ ብትሉ ለሐሰትም ባትታዘዙ የሰማይን በረከት ትበላላችሁ!