Wednesday, September 25, 2013

ድመራ (+)


                        
       መስቀል መደመር ነው፡፡ በክርስቶስ ኢየሱስ ያገኘነውን ሕይወት በፍሬ የምንገልጥበት መንገድ! ከትላንት ዛሬ፤ ከዛሬ ነገ የተሻለና የበለጠ ሆነን የምንገኝበት ኃይል ነው፡፡ በክርስቶስ ያየነውን ርኅራኄ ለሌሎች የምንገልጥበት በረከት ነው፡፡ ጥልን ከመካከላችን የምናስወግድበት እርቅ ነው፡፡ በዚህ ዓለም መከራና ፈተና ፊት ትምክህት ነው፡፡ ለምድሪቱ የምናቀርበው መፍትሔ ነው፡፡ እግዚአብሔር ምን ያህል እንደሰጠን ብቻ ሳይሆን ምን ያህል እንደወደደን የፍቅሩን ብርታት፣ የቃል ኪዳኑን ጽናት፣ የተስፋውን ፍፃሜ የምናይበት አደባባይ፤ ከምድር ከፍ ከሰማይ ዝቅ ያለ ቃል ኪዳን፣ ዘመንና ኑሮ ለሁለት የተከፈለበት ውለታ፣ ምሕረትና እውነት፣ ጽድቅና ሰላም የተስማሙበት ማሰሪያ መስቀል (ድመራ) ነው፡፡

       የክርስትናውን መልክ ከሚያደበዝዙ ነገሮች መካከል ዋናው በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ የተገለጡትን አሳቦች በትክክል አለመተርጎምና አለመኖር ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ “የተሰቀለውን ኢየሱስን እንድትሹ . . . የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን . . . (ማቴ. 28÷5፣ 1 ቆሮ. 1÷3)” ተብሎ ተጽፏል፡፡ ለሰዎች መሻት ምላሽ የሚሆነው መሻታችን ሳይሆን ትክክለኛውን እርካታ ማቅረባችን ነው፡፡ የክርስቶስ መለያው መስቀል እንደ ሆነ ሁሉ የክርስትናውም መለያ መስቀል ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ስለ ምቾታችን እየተሟገትን የምንኖርበት ሳይሆን ክርስቶስን በመከራው የምንመስልበትና የመስቀሉን ኃይል በኑሮ የምንመሰክርበት ነው፡፡ ክርስትና ዛሬ ላይ እንዴት እንደደረሰ ታሪክ ስንመረምር ብዙ እውነተኛ ክርስቲያኖች ዋጋ እየከፈሉ፣ የተሰጣቸውን የወንጌል አደራ በደም ጭምር እየተወጡ፣ በቃልና በኑሮ እየታመኑ ነው፡፡ በረከት የምንደምረው ነው፡፡ እግዚአብሔር በመስቀሉ በኩል በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ የሠራው ሥራ ከንቱ በሆነችው ዓለም ፊት የምንቆጥረው ብልጥግናችን ነው፡፡

Thursday, September 19, 2013

የስንኝ ገበታ 1




            አርብ መስከረም 10/ 2006 የምሕረት ዓመት

ለእኔ ሲነጋ ለጠላት ጨልሟል፣
ጉልበቱ ቄጤማ ኃይሉም ከንቱ ሆኗል፡፡
ደኅንነት ዋስትና የያዘኝ መዳፍህ፣
ጌታ ነህ ኢየሱስ ማንም የማይደፍርህ፡፡


ከሰው የጨረሰ ልቡን ለሚያስታምም፣
ተስፋው ተጨልጦ ለመኖር ያጣ አቅም፡፡
 ትንሣኤና ሕይወት መንገድና እውነት፣
ክርስቶስ ኢየሱስ ፍቱን ነው መድኃኒት፡፡

Thursday, September 12, 2013

ዘመንሰ፡ የተዋጀ ይዋጃል


                                                ሐሙስ መስከረም 2/ 2006 የምሕረት ዓመት

        ዘመንን ያመጣ፣ ለዘመኖቻችን ዳርቻን ያበጀ፣ በእድሜ በረከት፤ በእርጅና ሽበት የሚባርክ፣ ሕፃናቱን አስተዋዮች፣ ጎበዛዝቱን ብርቱዎች የሚያደርግ እግዚአብሔር ብሩክ ነው፡፡ ተናግሮ የሚቀር፣ ትቶት የሚሆን፣ ይዞት የሚወድቅ፣ ጥሎት የሚነሣ፣ ዓይቶት የሚሰወር፣ ወድዶት የሚጠላ፣ ሰጥቶት የሚነፈግ፣ ምሕረት አድርጎለት የሚኮነን፣ ጠግኖት የሚሰበር፣ እንባ ታብሶለት የሚያዝን፣ ደግፎት የማይጸና አንድስንኳ የሌለ እግዚአብሔር አብ ስሙ ይቀደስ፡፡ እኛን ፈልጎ በአድራሻችን የመጣ፣ ሰው ሆኖ ሰዎችን የረዳ፣ ወደ ምድር ወርዶ ወደ ሰማይ ያደረሰን፣ ተዋርዶ ክብርን ለእኛ ያመጣ፣ ራሱን ባዶ አድርጎ ወደ እግዚአብሔር ሙላት ያሻገረን፣ እስከ መስቀል ሞት ታዝዞ በደሙ ያዳነን፣ ለእኛ ጽድቅ የደከመ፣ ለእኛ ትንሣኤ የሞተ፣ በረከታችንን መንፈሳዊ፤ ስፍራችንን ሰማይ ያደረገልን ኢየሱስ ጌታችን ነው፡፡

        የኩነኔውን ዘመን በምሕረት የቀየረ፣ ለዘላለም ያመለጥንበት ዐለት፣ ምድረ በዳውን የምናቋርጥበት ምንጭ፣ ፈተናዎቻችንን የምናልፍበት መውጫ፣ ይገለጥ ዘንድ ባለው ክብር ፊት የምንቆምበት ጽናት መድኃኔዓለም ስሙ ብሩክ ይሁን፡፡ የሚያጽናና ደግሞም የሚያጸና፣ የቃሉን ደጅ የሚከፍት፣ ፍቺውን የሚያበራ፣ መንፈሳዊ ፍሬዎችን እንድናፈራ የሚረዳን፣ ለሙሽራው እንደ ሙሽሪት የሚያስጌጥ፣ ድካማችንን የሚያግዝ፣ በጸጋ የሚያስተባብር፣ ለቤተክርስቲያን ሁለንተናዊ እድገት የሚተጋ መንፈስ ቅዱስ ይባረክ፡፡ እንዴት እንድንጸልይ ለማናውቅ በማይነገር መቃተት የሚናገር፣ ዓለማዊነትን ክደን የተባረከው ተስፋችንን እንድንናፍቅ የሚያበረታን፣ የእግዚአብሔር መንፈስ፥ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ፥ የምክርና የኃይል መንፈስ፥ የእውቀትና እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ ለዘላለም ይመስገን፡፡ አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ፣ አንድ አምላክ አሜን፡፡   

         ወዳጆቼ እንኳን አደረሳችሁ! ትላንት ዛሬ፣ ቅድም አሁን፣ ምሽት ንጋት ስለሆነላችሁ የምታምኑት ጌታ ይባረክ፡፡ ቀኑ በስሙ ይቀደስላችሁ፡፡ ዘመኑ በእርሱ እጆች ላይ ይለቅላችሁ፡፡ ሊመጡ ያሉት ቀናት እንደሚገባ ኖራችሁባቸው እንዲያልፉ ጸጋው ያግዛችሁ፡፡ ዛሬ ብዙ ለመናገር፤ እናንተም ብዙ ለመስማት እንዳልተዘጋጃችሁ ይሰማኛል፡፡ ቢሆንም ጥቂት የእግዚአብሔርን አሳብ እንጨዋወት፡፡ ጌታ ለደቀ መዛሙርቱ ባስተማራቸው ጸሎት ላይ “ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን” (ማቴ. 6፥10) ብለን እንድንለምን አዝዞናል፡፡ በሰማያት ያለው የእግዚአብሔር ፈቃድና የልቡ ምክር በዚህ ምድር ላይ ሊከናወንበት የሚችለው ትልቁ ስፍራ ክርስቲያን ነው፡፡

Wednesday, September 4, 2013

ዘመንሰ ለሊከ ውእቱ


 እሮብ ነሐሴ 29/ 2005 የምሕረት ዓመት
                                                 
        ተስዕለ አሐዱ እምነገሥት ወይቤ 
«እፎ ዘመን ሐለወት
         ወይቤልዎ «ዘመንሰ ለሊከ ውእቱ፤
          እስመ አንተ አሰነይካ ለሊከ ትሴኒ
             ወለእመ አንተ አህሰምካ ለሊከ ተሃስም፡፡
    ዘመንሰ ለሊከ ውእቱ . . . . »

ትርጉም፡-
ከነገሥታት አንዱ ለሊቃውንቱ እንዲህ የሚል ጥያቄ አቀረበላቸው፡-
ዘመን ማለት ምን ማለት ነው?”
ሊቃውንቱም፡- «ዘመን ማለት አንተ ነህ፣
አንተ ጥሩ ከሆንክ ዘመኑ ጥሩ ይሆናል፣
አንተ ክፉ ከሆንክ ዘመኑ ክፉ ይሆናል፡፡
ዘመን ማለት አንተ ነህ . . . »
      
       ጥሩ ዘመን ከተነሣ ጥሩ ሰዎች ይታወሳሉ፡፡ መጥፎ ዘመንም ከተወሳ መጥፎ ሰዎች ይዘከራሉ፡፡ ዘመኑ የትጋት ከሆነ ትጉ ሰዎች ይወደሱበታል፡፡ ዘመኑ የስንፍና ከሆነ ደግሞ ሰነፍ ሰዎች ይወቀሱበታል፡፡ ዘመን ጥሩም ሆነ ክፉ የሚሆነው ከእኛ ምግባር የተነሣ ነው፡፡ ጥሩ ከሆንን ጊዜው ጥሩ ሲሆን መጥፎ ከሆንን ግን ዘመኑ መጥፎ ይሆናል፡፡ ልክ እንደ መስታወት ራሳችሁን ይዛችሁለት ስትቀርቡ እድፉን እድፍ፣ ንጻቱን ንጹህ እንደሚለው ዘመን አደባባይ ነው፡፡ ገዥና ሻጭ፣ ትጉና ሰነፍ፣ አስተዋይና መሃይም፣ ብርቱና ድኩም፣ ዝንጉና ባለ ራዕይ . . . . ለሁሉም የእኩል እድል ዘመን ነው፡፡

ዘመን ሰውን ይመስላል
ሰውም ዘመኑን፡፡