Thursday, March 20, 2014

የጉብዝና ወራት /ክፍል ሁለት/

                    Please Read in PDF: Yegubzna Werat

                       ሐሙስ መጋቢት 11 ቀን 2006 የምሕረት ዓመት


     ‹‹ልጆች ሆይ፥ ኃጢአታችሁ ስለ ስሙ ተሰርዮላችኋልና እጽፍላችኋለሁ። አባቶች ሆይ፥ ከመጀመሪያ የነበረውን አውቃችኋልና እጽፍላችኋለሁ። ጎበዞች ሆይ፥ ክፉውን አሸንፋችኋልና እጽፍላችኋለሁ።›› (1 ዮሐ. 2÷12-14)፡፡

         መንገድ እየሄድኩ ግርግር ተፈጠረና ፈንጠር ብዬ የሚሆነውን በአንክሮ እከታተል ጀመር፡፡ አንድ ወጣት እጅ ከፍንጅ አንዲት ጉብል ቦርሳ ውስጥ ተገኝቶ ኖሮ የጸጥታ አስከባሪዎች ከብበው ያናዝዙታል፡፡ ታዲያ በተጠየቅ ሂደቱ አንድ የሚያውቀው ሌላ መንገደኛ ድምጹን ከፍ አድርጎ ‹‹እንዴ! እኔ አውቀዋለሁ፡፡ እርሱ ሌባ አይመስለኝም፤ እንዲያውም የሚጥል በሽታ አለበት›› ብሎ መሰከረ፡፡ በዚህ ጊዜ ከጸጥታ አስከባሪዎቹ አንዱ፤ በበሰለ ነገር ላይ ደርሶ አስተያየት ለሰጠው መንገደኛ ‹‹ታዲያ ሴት ቦርሳ ውስጥ ነው እንዴ የሚጥለው?›› ብሎ ሲጠይቅ፤ በዙሪያው የቆመ ሰው ሁሉ ሳቀ፤ አንዳንዱም እኔን ጨምሮ ተሳቀቀ፡፡  

        ዶ/ር ኢዮብ ማሞ ‹‹እይታ /Mindset/›› በሚል መጽሐፋቸው ‹‹ስለምታስበው ነገር ተጠንቀቅ፤ አሳቦችህ ወደ ቃላት ይለወጣሉና፡፡ ስለምትናገረው ነገር ተጠንቀቅ፤ ንግግሮችህ ወደ ተግባር ይለወጣሉና፡፡ ስለምትተገብረው ነገር ተጠንቀቅ፤ ተግባሮችህ ወደ ልማድ (ባህርይ) ይለወጣሉና፡፡ ስለ ልማድህ ተጠንቀቅ፤ ልማድህ የሕይወት ፍፃሜህን ይወስናልና›› (ዶ/ር ኢዮብ ማሞ፤ 2005 ዓ.ም፤ እይታ (Mindset)፤ አዲስ አበባ) በማለት፤ አሳብና አመለካከት በእያንዳንዳችን ሕይወት ላይ ያለውን ጉልህ ተጽእኖ ይናገራሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔርን አሳብ የያዘ መጽሐፍ ነው፡፡ የፈጠረን አምላክ እንዴት እንድንኖር መመሪያ የሰጠንም በዚሁ ቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ ነው፡፡ ሰው አሳቡን፤ ንግግሩን እና ተግባሩን የሚያነፃው በመለኮት አዋጅ ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር የጠበቀ ግንኙነት ከሌለን የእግዚአብሔርን ፈቃድ ልንረዳና ልንታዘዘው አንችልም፡፡

Thursday, March 13, 2014

ቤተ ፍቅር

ቤተ ፍቅር መጽሔት ቁጥር ሦስት፡

‹‹ያንብቡ››


Saturday, March 8, 2014

የጉብዝና ወራት /ክፍል አንድ/

                                        Please Read in PDF: yegubzna werat 1
                                                            
      መግቢያ
                          ቅዳሜ የካቲት 29 ቀን 2006 የምሕረት ዓመት

        በአንድ አጋጣሚ ያገኘሁት ከሀገር ውጪ የሚኖር ሰው ስለ ሕይወት እየጠየኩት እንጨዋወታለን፡፡ ምን ዓይነት ውጥረት ውስጥ እያለፈ እንዳለና ከዚህ የተነሣ ትዳር ለመመስረት እንዳልቻለ ከወሬው መካከል ትኩረት ሰጥቶ፤ ስለዚህ ጉዳይ እየደጋገመ በቁጭት ይነግረኛል፡፡ እኔም ኑሮውን ባልካፈለው እንኳ ወሬውን ልጋራው ብዬ እህ . . እህ . . እያልኩ፤ አናቴን እየወዘወዝኩ አደምጣለሁ፡፡ ታዲያ በገረመኝ ሁኔታ በየጨዋታው መሐል ‹‹ተው እንጂ›› ስለው ‹‹ወጣትነቴን አያስጨርሰኝ እልሃለሁ›› እያለ መሐላ ቢጤ ጣል ያደርጋል፡፡ የፀጉሩን ለውጥ፣ የፊቱን ሽብሻብ፣ የወገቡን ጉብጠት፣ የትንፋሹን ቁርጥ ቁርጥ፣ ቢያቀኑት የሚንቋቋ ማጅራቱን፤ የእድሜውን የትየለሌነት እንኳን እኔ፤ በመነጽር ታግዞ የሚመለከትም አዛውንት ልብ እንደሚለው ግልጥ ነው፡፡ ልቤ ‹‹ምን ነካው?›› ለምዶበት ወይስ ያለፈ ናፍቆት ጸንቶበት ይሆን? እላለሁ፡፡ ልቡ ‹‹እስከ ዶቃ ማሠሪያው ንገረው›› አለው መሰል፤ እየደጋገመ ‹‹ወጣትነቴን አያስጨርሰኝ›› ይላል፡፡ እንደ መንደር ሰው ‹‹አይሻልህም ሕፃንነቴን›› ሊለው ሥጋዬ ዳዳ፤ መንፈስ ግን ልጓም ሆነበት፡፡

       እኔን ወንድሜ! አልኩኝ፡፡ ዛሬ ላይ ቆሞ ለትላንት መኖር፣ የያዙት ደብዝዞ ያለፈውን መከጀል፣ የተሸቃቀጠ ኑሮ፣ እድሜን የማያሳይ ድንግዝግዝ፤ ባልንጀራዬ አሳዘነኝ፡፡ እንደሚገባ ያልኖረበት፣ ተላላ ሆኖ ያለፈበት፣ በጭንቅ የሰበሰበውን በፌዝ የበተነበት፣ ምክር ሬት፣ ተግሳጽ ሞት የሆነበትን ለዛሬ መራራ የዳረገውን ወጣትነቱን ትኩር ብዬ ወደኋላ አየሁት፡፡ በኋላ በእንባ የነገረኝን ቀድሜ በመሐላው ደረስኩበት፡፡ ሙከራ ቅኝቱ፣ ስሜት መዘውሩ የነበረውን ወጣትነቱን አወጋኝ፡፡ የሽምግልና እድሜ ሸክም ማቅለያ ሳይሆን፤ ዕዳ ማቆያ የሆነውን የኑሮ እስታይል /ዘይቤ/ እንደሚገለጥ መጽሐፍ አስነበበኝ፡፡ ‹‹ብትችል ሰርዘው፤ ባትችል እለፈው›› እያለ አገላበጠልኝ፡፡ እንባ ያጋቱ ዓይኖቹ፣ የቁጭት ፍም የተከመረባቸው ጉንጮቹ፣ በጥርሱ መጅ የላመ ከንፈሩ፣ ደግፈኝ . . ደግፈኝ የሚለው አፍንጫው፣ በእጆቹ መዳፍ ልምዥግ የሚያደርጋቸው ጢሞቹ፣ የመፍትሔ ያለህ! የሚመታው ልቡ ሁሉም ፊቴ ተራቆተ፡፡

Tuesday, March 4, 2014

ማረፍን ማን ይሰጠኛል?

                                   Please Read in PDF: Marefn man yesetegnal?
                                                    

                              
                                            ማክሰኞ የካቲት 25 ቀን 2006 የምሕረት ዓመት

            ጌታ ሆይ÷ አንተ ታላቅ ነህ÷ ውዳሴም ያለ ገደብ ይገባሃል፤ ኃይልህ ታላቅ÷ ጥበብህም የማይለካ ነው፡፡ የፍጥረትህ ደካማ ክፍል የሆነው የሰው ልጅ÷ ሟችነቱንም ከራሱ ጋር የተሸከመው የሰው ልጅ÷ የኃጢአቱን ምስክርነት÷ የአንተንም የትዕቢተኞችን መቃወም ማስረጃ የተሸከመው የሰው ልጅ÷ አንተን ነው ማወደስ የሚፈልገው፡፡ እንግዲህ ይህ የፍጥረታት ደካማ ክፍል የሆነው የሰው ልጅ ሊያወድስህ ይፈልጋል፡፡

            ‹‹ከጌታ ከራሱ በስተቀር ማን ነው ሌላ ጌታ፤ ወይስ ከእግዚአብሔር ውጭ እግዚአብሔርስ ማን ነው?›› እጅግ ታላቅ፣ እጅጉን የላቀ፣ እጅግ ኃያል፣ እጅግ ሁሉን ቻይ፣ እጅጉን መሐሪ፣ እጅግ ጻድቅ፣ እጅግ የተሰወርክ እጅግ የቀረብክ፣ እጅግ ውብና እጅግ ብርቱ፣ ጽኑና የማትጨበጥ፣ የማትለወጥና ሁሉን የምትለውጥ፣ አዲስ ሆነህ የማታውቅ፣ የማታረጅ፣ ሁሉን የምታድስ፣ እነርሱ ሳያውቁት ትዕቢተኞችን የምታስረጅ፣ ምንጊዜም የምትሠራ፣ ምንጊዜም የምታርፍ፣ የምትሰበስብ፣ ምንም የማያሻህ፣ እየደገፍክ የምትይዝ፣ የምትሞላ፣ የምትከላከልም፣ የምትፈጥር፣ የምትመግብ፣ የምታጠናቅቅ፣ የምትፈልግ፣ ምንም ሳይጎድልህ፡፡

             አንተ ታፈቅራለህ ነገር ግን ያለ ስሜት ነው፤ ቅናትህ መሥጋት የለበትም፡፡ ጸጸትህ ቁጭት አያውቅም፡፡ ቁጣህም የተረጋጋ ነው፡፡ ሥራዎችህን እንጂ እቅድህን አትቀይርም፤ ፈጽሞ ሳይጠፋብህ፤ ያገኘኸውን ትጨብጣለህ፡፡ ምንም ባያሻህም በማግኘትህ ትደሰታለህ፡፡ ስስትን ባታውቅም፤ ብድርን ከነወለዱ ትፈልጋለህ፡፡ ባለእዳ እስክትሆን አብዝተው የሚከፍሉህ፤ ለመሆኑ ያንተ ቢኖረው ካንተ ያልሆነ ሊኖረው የሚችል ማን ነው? ለማንም ባለ እዳ ሳትሆን እዳህን ትከፍላለህ ስትመልስም ምንም አይጎድልብህም፡፡ ኦ አምላኬ ሕይወቴ ቅዱሱ ትፍስሕቴ ሆይ ምን እያልን ይሆን? ስለ አንተ ሲናገር ሰው ምን ማለት ይችላል? ስለ አንተ አብዝተው እንኳን የሚናገሩ እንደ ዲዳ ናቸው - ስለ አንተ የማይናገሩ ወዮላቸው!