Sunday, October 26, 2014

ከከፋን የከፋ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ጥቅምት 16 ቀን 2007 የምሕረት ዓመት

         ወንጌል ያስተማርኳትን አንዲት ሴት በቢሮዬ መንገድ ላይ አግኝቻት፤ በፀጉሯ መንጣት፤ በሰውነቷ መግዘፍ፤ በፊቷ መሸብሸብ ስገረም፤ ‹‹የነገርከኝ ቃል ግን አላረጀም›› አለችኝ፡፡ ታዲያ ስለ ባለቤቷና ልጆቿ እየጠየኳት፤ በመሐል ‹‹ምን ሆነህ ነው? ፊትህ ደህና አይደለም›› እያለች ምራቋን እጇ ላይ እንትፍ ብላ ለእኔ የማይታየኝን እሷ የምታየውን ከፊቴ ላይ ታብሳለች፡፡ በእርግጥ በጊዜው ያዘንኩበት ነገር ቢኖርም፤ ያ ከአሳቤ በስተ ውስጥ የነበረ ነው፡፡ ሴቲቱ ፊቴ ላይ ምን ታይቷት እየደጋገመች ምራቅ እንዳጠገበችው ባላውቅም፤ በጊዜው ግን ቅንነቷን እንዳደነቅሁ አስታውሳለሁ፡፡ ምንም እንኳን ለጭርት ወጪ ብታስወጣኝም ማለት ነው፡፡

           ሴቲቱ እንደ ከፋኝ እያወራች በምራቅ ጉንጬን አራሰችው፡፡ በጊዜው እኔ ያዘንኩበት ነገር እድሜው አጭር፤ ክብደቱ ቀሊል፤ መፍትሔው ግልጽ ነበር፡፡ ደግሞ ‹‹እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ አሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን።›› የሚለው የታመነ ቃል ልቤን ሞልቶት ነበር፡፡ የከፋኝን ለማስወገድ /በእርሷ ግንዛቤ/ ከከፋኝ የከፋ ነገር አደረገች፡፡ እንግዲህ ይህ ከሁለት አመታት በፊት የሆነ አጋጣሚ፤ በዚህ ርዕስ ዙሪያ ልጽፍ ሳስብ ትዝ አለኝ፡፡ ለመነሻም እንዲሆን አሰብኩ፡፡

Friday, October 17, 2014

አብርሃም እንዲህ አላደረገም


ጥቅምት 7 ቀን 2007 የምሕረት ዓመት

‹‹አብርሃም እንዲህ አላደረገም›› /ዮሐ 8÷40/!

       የተሻለ ሰምቶ የተሻለ መናገር፤ የበለጠ አይቶ የበለጠ መሥራት በሰው ልጆች ሕይወት ውስጥ የማይቋረጥ ቅብብሎሽ ነው፡፡ ይህንንም አበው ‹‹ትውፊት›› ወይም ጤናማ መወራረስ ይሉታል፡፡ ያለንን መቀባበል መልካም ነው፡፡ የምንቀበለው ሁሉ ግን መልካም ሊሆን አይችልም፡፡ ከእግዚአብሔር የተቀበልነውን ሕሊና ሥራ ላይ ከምናውልበት መንገድ አንዱ መምረጥ ስለሆነ፤ እንደ ባለ አእምሮ አስተውለን ልንመርጥ  ያስፈልገናል፡፡ የሚረባንን ከማይረባን መለየት የምንችልበት መንሽ ደግሞ ቅዱስ ቃሉ ነው፡፡

       መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹አባትህን ጠይቅ ይነግርህማል›› /ዘዳ 32÷7/ የሚል መጽሐፍ ብቻ አይደለም፡፡ ለአንዳንድ ልብ የመጽሐፉ ሙሉ ጭብጥ ከዚህ አይዘልም፡፡ ነገር ግን ‹‹ማስተዋል ይጋርድሃል›› /ምሳ 2÷11/ ተብሎ እንደ ተፃፈ፤ የቃሉን ሙሉ ገጽታ መመልከት ያስፈልጋል፡፡ በኑሮአችንም እንዲሁ ነው፡፡ ማስተዋል ከከንቱ ኑሮ፤ ውልና ማለቂያ ከሌለው ጥረት፤ ከስህተት ጎዳና ይጠብቃል፡፡ ምድሪቱ ላይ እኛን አድራሻ አድርጎ ከሚመጣ ከየትኛውም ክፉ ትግል፤ ከቅርብም ከሩቅም ባላንጣ መጋረድ በቃሉ ነው፡፡ ጌታ በሊቀ ካህናትነት ጸሎቱ ‹‹በእውነትህ ቀድሳቸው፤ ቃልህ እውነት ነው።›› /ዮሐ 17÷17/ እንዳለ፤ ከየትኛውም ጠላትነት የምንጠበቅበት አጥር ቅዱስ ቃሉ ነው፡፡ በዚህም ውስጥ የምናስተውለው ትልቁ ነገር ቅዱሱን እግዚአብሔር ነው፡፡

       ካለፉት በሕይወት ኖሮ መማር እጅግ ጤናማ ነው፡፡ ሌሎች ቀድመውን ካዩት መማር እየቻልን ‹‹እስክናይ›› ብለን ግትር አንሆንም፡፡ ነገር ግን የቀደሙን ያዩት ሁሉ ልክ፤ የሠሩት ሁሉ እጅግ በጣም ጥሩ እንደ ሆነ ማሰብ ደግሞ ጤናማ አይደለም፡፡ ኑሮአችን ከዘላለም እስከ ዘላለም ያው /መዝ 89÷2/ በሆነው እግዚአብሔር ይመዘናል፡፡ በተሰጠን የእውነት ቃል /ኤፌ 1÷13/ ሁሉም ይፈተሻል፡፡ ሐዋርያው ጴጥሮስ ‹‹ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከከንቱ ኑሮአችሁ በሚያልፍ ነገር›› /1 ጴጥ 1÷19/ ሲል፤ ውርስ ሁሉ ጤናማ አለመሆኑን ያስገነዝበናል፡፡ ከሙግቶቻችን አልፈን ማየት ካልቻልን ለእኛ መዳን እንዴት ጭንቅ ነው?

Tuesday, October 14, 2014

ቱንቢ (plumbline)



ጥቅምት 4 ቀን 2007 የምሕረት ዓመት

‹‹እንዲህም አሳየኝ እነሆም፥ ጌታ ቱንቢውን ይዞ በቱንቢ በተሠራ ቅጥር ላይ ቆሞ ነበር››
/አሞ 7÷7/

        በአዲስ ኪዳን መጻሕፍት የታሪክ ክፍል በሆነው የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ከምንማራቸው መንፈሳዊ ትምህርቶች መካከል ትጋት አንዱ ነው፡፡ ክርስቲያኖች በእግዚአብሔር ፊት የሚተጉበትን ነገር መመርመርና መመዘን አለባቸው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ስለሆነ አይመረመርም፡፡ የሰው ፍለጋና ጥረትም አያገኘውም፡፡ ዳሩ ግን ሥጋ ለባሽ ሁሉ ሕያውና ጻድቅ በሆነው በእርሱ በእግዚአብሔር ፊት ቃልና ኑሮው ይመዘናል፡፡ በእውነት ላይ የተመሰረተው ‹‹ይበል›› ተብሎ ይሁንታን ሲያገኝ፤ እንደ ዘላለም ምክሩና እንደ ጌታ ልብ ያልሆነው ሁሉ ግን ሁሉን እንደ ፈቃዱ በሚያደርግ ሉዓላዊ አምላክ ዙፋን ፊት በጽድቅ ይዳኛል፡፡

        እግዚአብሔር እውነቱን የሚለካ ሌላ እውነት የሌለ እውነተኛ፤ ጽድቁን የሚመዝን ሌላ ሚዛን የሌለ ጻድቅ፤ ቅድስናውን የሚተያይ ሌላ ቅድስና የሌለ ቅዱስ አምላክ ነው፡፡ ሁሉ በእርሱ ተፈጥሮአልና፤ ከሆነውም ሁሉ ያለ እርሱ የሆነ አንድ ስንኳ የለምና ሁሉን የሚመዝን እርሱ ነው፡፡ እውነተኛ አምላክ የሆነ እርሱ ብቻ /ዮሐ 17፣3/ የቃልና የኑሮአችን ቱንቢ በእጁ አለ፡፡ እርሱ እውነተኛ አምላክ ነው፡፡ ሁሉ በእርሱ ይመዘናል፡፡ ‹‹እግዚአብሔር የመረጣቸውን ማን ይከሳቸዋል? የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው፥ የሚኰንንስ ማን ነው?›› /ሮሜ 8፥33/ ተብሎ እንደ ተፃፈ፤ እግዚአብሔር ነገሮቻችንን ሊመዝን፤ ሊያጸድቅና ሊኮንን እውነተኛ ዳኛ ነው /መዝ 7÷11/፡፡

Saturday, October 4, 2014

ብዙ ኃይል


                            መስከረም 24 ቀን 2007 የምሕረት ዓመት

‹‹በጻድቅ ሰው ቤት ብዙ ኃይል አለ፤ የኃጥእ ሰው መዝገብ ግን ሁከት ነው።›› 
(ምሳ. 15÷6)፡፡

         በሰው ልጆች አኗኗር ውስጥ ኃይል እጅግ አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ በኃይል እጦትና እጥረት ሰዎች ያለ መብራት በጨለማ ይሄዳሉ፤ ያልበሰለ በጥሬው ይበላሉ፡፡ ሰዎች በአቅም ማነስ ምክንያት ለተግባር ብዙ ይቸገራሉ፡፡ ኃይል የማይገባበት የኑሮ ክፍል የለም፡፡ ብዙ ነገሮች በብዙ ኃይል ጭምር የሚተገበሩ ናቸው፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ በመንፈሳዊው ዓለም ስላለው ከፍተኛ ኃይል ይነግረናል፡፡ ጠቢቡ በዘመኑ ያስተዋለውን ባካፈለበት በዚህ ክፍል ላይ ጻድቅ ቤት ውስጥ ብዙ ኃይል እንዳለ ሲነግረን፤ በኃጢአተኛ መዝገብ ውስጥ ግን ሁከት አለ ይለናል፡፡

        ጠቢቡ ጻድቅና ኃጥእን፤ ቤትና መዝገብን፤ ኃይልና ሁከትን እነዚህን ሁለት ነገሮች ከሰው አንፃር በንጽጽር አቅርቦልናል፡፡ ጽድቅ የሚለው አገላለጽ በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነትን ያገኘ እውነተኛ ማንነትን ሲያሳይ፤ ኃጥእ የሚለው አገላለጽ ደግሞ ከእግዚአብሔር ጋር ጸብ ውስጥ ያለና መንገድ የሳተ  ማንነትን ያመላክተናል፡፡ ቤት ልንኖርበትና ልንጠለልበት ያለንበትን ክልል ሲያሳይ፤ መዝገብ አንድ ሰው የሚሰበስበውን የሚያኖርበትን ስፍራ ያመለክተናል፡፡ ብዙ ኃይል የሚለው አገላለጽ ጽድቅ የሚለውን አዎንታዊ ቃል ተከትሎ የመጣ እንደ መሆኑ በዚያው መንገድ የምንመለከተው ብርቱ ነገር ሲሆን፤ ሁከት ደግሞ የደፈረሰ ያልጠራ፤ ሰላም የሌለበትን ነገር ያስረዳናል፡፡