Friday, September 16, 2016

የተደረገልን /3/


                በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

 ሐሙስ መስከረም 6 ቀን 2009 የጸጋ ዓመት

       መጽሐፍ ‹‹በኢየሱስ ክርስቶስም በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ›› (ሮሜ 3፡24) ሲል፤ ክርስቲያን የጽድቅን ሥራ አይሠራም ማለት አይደለም፡፡ የጸደቀ ዛፍ ያለ ፍሬ ሊሆን እንደማይችል፤ ከሥሩ በግንዱ በኩል ቅርንጫፎች እየተመገቡ ያፈራሉ፡፡


      ‹‹ጻድቅ በእምነት ይኖራል ተብሎ እንደ ተጻፈ የእግዚአብሔር ጽድቅ ከእምነት ወደ እምነት በእርሱ ይገለጣልና›› (ሮሜ 1፡17) ተብሎ እንደተጻፈ፤ በእምነትና በጽድቅ ሥራ እያደግን፤ እርሱ ጽድቃችን ጌታ ኃጢአትን እንደሚጠላ ከበደል እየራቅን የምንኖር እንሆናለን፡፡ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ደኅንነትን ያገኙና ጽድቅ የሆነላቸው ሁሉ ኃጢአትን ባለማድረግ መርኅ ውስጥ እየኖሩ (1 ዮሐ. 2፡1)፤ በሚሆነው ድካማቸው በዳኑበት በዚያው ደም በንስሐ ይታጠባሉ (1 ዮሐ. 1፡7)፡፡


     ሐዋርያው ጳውሎስ ሰዎችን ሁሉ የሚያድን የእግዚአብሔር ጸጋ እንደ ተገለጠ በተናገረበት ክፍል ‹‹ይህም ጸጋ›› በማለት የጸደቅንበት ያው ጸጋ በቀጣይ ተግባራዊ ኑሮአችንን በተመለከተ ምን እንደሚሠራ ያስረዳናል፤ ‹‹ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት ክደን፤ የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን፤ ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል፤ . . ›› (ቲቶ 2፡11-13)፡፡ በጸጋ የሆነው ጽድቅ፤ ጽድቅን በጸጋው በኩል እንድናደርግ የሚያስችለን ነው፡፡
              
         ቅድስና

      ‹‹መቀደስ›› ማለት መለየት ነው፡፡ የዚህም መሠረቱ ቅዱሱ እግዚአብሔር ሆኖ፤ የምንቀደሰው ‹‹በእውነትህ ቀድሳቸው፤ ቃልህ እውነት ነው›› (ዮሐ. 17፡17) ተብሎ እንደ ተጻፈው በክርስቶስ ነው፡፡ ቅድስና በአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ በሁለት መንገድ ተገልጿል፡፡ አንደኛው ከሥፍራ አንጻር ያለው የክርስቲያኖች መቀደስ ሲሆን፤ ይህም በሐዋርያው ጴጥሮስ መልእክት ውስጥ ‹‹በመንፈስም እንደሚቀደሱ›› የተባለው ነው (1 ጴጥ. 1፡1-2)፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በተግባራዊ ኑሮ መቀደስ ነው፡፡ ይህም ‹‹ትቀደሱም ዘንድ ፈልጉ›› የተባልነው ነው (ዕብ. 12፡14)፡፡

     ሐዋርያው ጳውሎስ በቆሮንቶስ መልእክቱ መጀመሪያ ኢየሱስ ክርስቶስ ቅድስና እንደተደረገልን ተናግሯል፡፡ ከሰማያዊ ስፍራ አንጻርም ሆነ ከተግባራዊ የምድር ኑሮ አንጻር ሊኖረን የሚችለው ቅድስና መሠረቱ ክርስቶስ እንደ ሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ የተቀመጠ ግልጥ አሳብ ነው (ዮሐ. 17፡17-19)፡፡ እያንዳንዱ የምእመናን የእለት ከእለት ኑሮ መለኮታዊ ሚዛን ክርስቶስ ነው፡፡ በመለኮት መንግሥት ሰው የሚጠበቅበት የቅድስና ልክ ‹‹ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ›› (ሉቃ. 1፡35) ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፡፡       

   ቅዱስና ያለ ተንኮል፤ ነውርም የሌለበት፤ ከኃጢአተኞችም የተለየ የሆነው (ዕብ. 7፡26) መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ጊዜ ፈጽሞ የእርሱን ሥጋ በማቅረብ እንደተቀደስን (ዕብ. 10፡10)፤ እንዲሁም የዘላለም ፍጹማን የሆንበትን ክርስቶስ የሆነልንን እንረዳለን (ዕብ. 10፡14)፡፡ ከእግዚአብሔር የቅድስና ባህርይ ጋር ከማይስማሙ ማንኛቸውም የአሁኑ ዓለም ነገሮች መለየት የሚቻለው በክርስቶስ ነው፡፡

     ኃጢአተኛው የሰው ዘር በእግዚአብሔር ፊት ቅድስና የሆነውን ሁሉ ለማድረግ በራሱ  አቅሙና ችሎታው የለውም፡፡ ዳሩ ግን ‹‹ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ›› (ኤፌ. 4፡24) እንደተባለ፤ በቅድስና የምንኖርበት መንገድ ግልጥ ተደርጎአል፡፡ እውነተኛ ምእመናን በክርስቶስ ሆነው ለእግዚአብሔር የሆነውን ቅድስና የሚለማመዱ ናቸው፡፡

   ተወዳጆች ሆይ፤ ‹‹አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል፤›› (ዮሐ. 14፡25) እንደተባልን፤ በክርስቶስ ክርስቲያን የሆኑ ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በቅድስና ይኖራሉ፡፡ ቅዱሱ መንፈስ በእኛ ውስጥ የመሥራቱ መሰረት ግን በክርስቶስ ላይ ያለን እውነተኛ እምነት ነው፡፡ ለዚህም የእግዚአብሔር ቃል በእጅጉ ያስፈልገናል (ሮሜ 10፡17)፡፡ ለምን እግዚአብሔር ቅድስናን በክርስቶስ እምነት አደረገው የሚል ልብ ቢኖር፤ አሁንም ‹‹ . . ሥጋን የለበሰ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት እንዳይመካ›› የሚል ነው፡፡

No comments:

Post a Comment