Showing posts with label ልዩ ልዩ. Show all posts
Showing posts with label ልዩ ልዩ. Show all posts

Monday, September 26, 2016

መልሱ ላይ ጥያቄ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!


ሰኞ መስከረም 16 ቀን 2009 የጸጋ ዓመት

‹‹ፍቅርም እውነትም ማን ነው?››

       ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የመስቀል አደባባዩ ትልቁ ደመራ፤ ትንንሽ ደመራ ልጆች በየአካባቢው መታየታቸው እየተለመደ መጥቶአል፡፡ ይህ ሊሆን የቻለበትን ብንመረምር ደግሞ ብዙ ምክንያቶችን ልናገኝ እንችላለን፡፡ ነገር ግን ሁሉም ሰው በቀላሉ የሚያስተውለውን ለማየት ብንሞክር ሃይማኖታዊ መልክና ዓለማዊ መልክ ብለን በሁለት ልንከፍለው እንችላለን፡፡

      ከእምነት ጋር በተያያዘ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የመስቀሉን ቃል ይዞ ታሪካዊ የሆነውን ተዛምዶ በማስከተል በዓል የሚያደርጉትን ልብ ስንል፤ ከዚህ ውጪ የሆነው ደግሞ መጠጥ ማሻሻጫ፤ የሥጋን ጥያቄ በመንፈሳዊ ሽፋን ማርኪያ፤ ከአላፊ አግዳሚው ገንዘብ መሰብሰቢያ፤ መዝፈን መጨፈሪያ፤ ይህንንም የሚመስል ሁሉ ነው፡፡

      ለዚህ ጽሑፍ የመጻፍ ግፊት ኃይል የሆነኝ ዛሬ ማለዳ በተንቀሳቀስኩበት አካባቢ ዓይኖቼ የተመለከቱት ጽሑፍ ነው፡፡ ምሽት ሊለኮስ አንድ መጠት ቤት ፊት ለፊት የተደመረ ደመራ ጉልላት ላያ፤ የተመሳቀለውን እንጨትና ጉንጉን አበባ ታኮ በነጭ ወረቀት በጥቁር እስክርቢቶ የተጻፈ ‹‹ፍቅርም እውነትም ማን ነው?›› የሚል ትልቅ ጥያቄ ላይ ዓይኖቼ አረፉ፡፡ አሥር ደቂቃ ቆሜ ብዙ አሰብኩ፡፡ ነገር ግን ቀለል አድርጌ ላየው በሞከርኩ ቁጥር ዙር እየከረረ፤ ነገሩ እየከበደ መጣብኝ፡፡ እናም ውስጤ ‹‹መልሱ ላይ ጥያቄ›› የሚል ርዕስ ተፈጠረ፡፡

    ፍቅር እና እውነት በክርስትና ውስጥ እጅግ መሰረታዊ ነገሮች ናቸው፡፡ መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያው ጳውሎስ በኩል ‹‹ . . በተጠራችሁበት መጠራታችሁ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እለምናችኋለሁ›› ባለበት ክፍል ‹‹ . . እውነትን በፍቅር እየያዝን በነገር ሁሉ ወደ እርሱ ራስ ወደሚሆን ወደ ክርስቶስ እንደግ›› (ኤፌ. 4፡15) ይለናል፡፡ እውነት ያመንበት መሰረት ሲሆን፤ ፍቅር ደግሞ ያመነውን በተግባር የምንገልጥበት መንገድ ነው፡፡ እውነት ኖሯቸው ፍቅር የሌላቸው እውነቱን የብቻቸው ከማድረግ ጀምሮ ሌላውን ለመጉዳት ጭምር ሊያውሉት ይችላሉ፡፡ ፍቅር ኖሯቸው እውነቱ የሌላቸው ደግሞ ሚዛን በሌለው ፍቅር እውነትን እየረገጡ ይበድላሉ፡፡

Monday, September 5, 2016

‹‹መስሚያው ጥጥ››

 በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!


ሰኞ ነሐሴ 30 ቀን 2008 የምሕረት ዓመት

        ከበርሃማው የመልክዓ ምድር ክልል አንዱ፤ ከጥቂት መልካሞች እንደ እድለኛ  ያደኩበትን የድሮውን ሳስታውስ ከማረሳቸው ሰዎች መካከል የድጓ መምህር የኔታ ብርሃኑ አንዱ ነበሩ፡፡ ሰው ለእግዚአብሔር በማይታጭበት፤ በልዩ ልዩ ሱስ መጠመድ እንደ ነቄ በሚያስቆጥርበት፤ ለሕያው አምላክ ማድላት ፋራና ፈሪ በሚያሰኝበት መዝሙረ ዳዊት ሁለቴ ዘልቆ ማጠናቀቅ እንደ ብርቅ በሚታይበት ማኅበረሰብ፤ እንደተረዱት መጠን ለእግዚአብሔር አገልግሎት ወንዶችን ያቀርቡ ዘንድ የኔታ በትጋት ያስተምሩን ነበር፡፡

        አንድ ቀን የሰኞ መስተጋብ ላዜም በተለመደው ሰዓት ወደ መቃብር ቤታቸው ስሄድ፤ በበሩ ትይዩ ባለው ሽቦ አልጋቸው ላይ በቁጭ አቀርቅረው ትልቅ መጽሐፍ ያነባሉ፡፡ ወደ ውስጥ ለመዝለቅ ፈቃዳቸውን በሚጠይቅ ዜማዊ አነጋገር የኔታ . . የኔታ . . እያልኩ በተደጋጋሚ ከስተውጪ ወደ ውስጥ ገርበብ ባለው ብረት በር በኩል እጣራለሁ፡፡

Wednesday, November 25, 2015

የኔታ፡ ኢየሱስ



    እሮብ ህዳር 15 ቀን 2008 የምሕረት ዓመት

ሀ ሁ አቡጊዳ ፊደልን ሊቆጥሩ
ከምምሩ የኔታ ፊት ተኮለኮሉ፤
ትንሽ ምላሶች ይንጫጫሉ
ከወረኛ ዓለም እንዲቀላቀሉ፤
እኒያኛው የሥጋ የኔታ
ዘርግተው የፊደል ገበታ፤
ሲያሻቸው ሲተኙ ሲያንቀላፉ
ሲሻቸው ሕጻናት ሲያስለፈልፉ፤
 ብላቴኖቹ ፊደል ቆጥረው ሲጨርሱ
የምምሩም እግሮች አብረው ተነሡ፤
. . . ሌላኛው የኔታ የጠልጣላ ነፍሴ
ቢያሳስባቸው መዳን መቀደሴ፤
የተግባር ትምህርት ሲጀምሩ
እጆቻቸው በምስማር ተቸነከሩ፡፡

                                       /ከቤተ ፍቅር ቤተሰብ የተላከ/
                      ‹‹ . . . ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ፤›› /ቆላ. 4፡3/!

Wednesday, November 18, 2015

የፍቅር ዘመቻዎች


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

                                     እሮብ ህዳር 8 ቀን 2008 የምሕረት ዓመት

1. ሁሉንም ሰው አክብር - ክርስቶስ በሁሉም ሰው ውስጥ ይኖራል፡፡ የሌሎች ሰዎችን ስሜት አክብር - እነርሱ የአንተ ወንድሞችና እኅቶች ናቸውና፡፡

2. ስለ እያንዳንዱ ጥሩ አስብ - በማንም ላይ መጥፎ ነገርን አታስብ፡፡ በመጥፎ ሁኔታዎች ውስጥ እንኳን ቢሆን ጥሩ ነገሮችን ለማግኘት ሞክር፡፡

3. ሁልጊዜም ስለ ሌሎች ጥሩ ተናገር - በማንም ላይ ዘለፋን አታድርግ፡፡ በንግግር ካልተገለፀ ቃል የሚመነጨውን ማንኛቸውም ጉዳት አርም፡፡ በሰዎች መካከል ውዝግብና አታካራ እንዲፈጠር ምክንያት አትሁን፡፡

Friday, August 21, 2015

ፍቅር እና ጀበና


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

አርብ ነሐሴ 15 ቀን 2007 የምሕረት ዓመት

እዚያ . . . ቡና ጠጡ፤
አሉባልታ አድምጡ።
ብዬ ከወዳጆቼ ተሰባስቤ፤
ለወሬ ተሰናድቶ ቀልቤ።
የሰው ሥጋ ስንቋደስ፤
ስንቀቅል ስንጠብስ።
ከፍም የተገናኘው ሸክላ፤
በእሳቱ ነበልባል ሲበላ።
ድንገት . . . እፍ . . . እፍ . . . ኧረ ገነፈለ፤
ቡናው ከጀበናው ዘለለ።
እኛ ስናወራ እሳቱ አይሎ፤
ጀበናው የውስጡን አወጣ አግተልትሎ፡፡
እዚህ . . . ቡና ጠጡ፤
ቃሉን አድምጡ። 
ብዬ ወዳጆቼን ሰብስቤ፤
ለቃሉ ተሰናድቶ ቀልቤ።
የሰው ነፍስ ስንናጠቅ፤
ከክፉ ሥራ ስናላቅቅ።
ከፍም የተገናኘው ሸክላ፤
በሳቱ ነብልባል ሲበላ።
ድንገት . . . እሰይ . . . እሰይ . . . ገነፈለ፤
ፍቅር ከጀበናው ዘለለ።
ከተሰባሪው ገል ገላ፤
ከእኔነቴ ሸክላ።
የመለኮት እሳት በዝቶ፤
ውስጤን አግሎ አፍልቶ።
እንደ ፈሳሽ ምንጭ፤
ከሰዎች ሲሰራጭ።
የሕይወት ቡና ቢያጠጣ፤
ከሸክላነታቸው ሸክላ ወጣ።
እናንተም የፍቅሩ ቁራሾች፤
የመለኮት እሳት ተካፋዮች።
ከፍቅር ጀበና ገንፍሉ፤
ከሸክላነታችሁ ውጡና ዝለሉ።

                                 ‹‹ . . . ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ፤›› /ቆላ. 4፡3/!