Thursday, April 12, 2012

የኃጢአተኞች ወዳጅ




          እግዚአብሔር ስሙን እንዲቀድስ ክብሩን እንዲወርስ በጽድቅ የፈጠረው ሰው ፈቅዶ ኃጢአተኛ ቢሆንበት እውነትና ምሕረቱን ጽድቅና ሰላሙን አስማምቶ በማዳን ዳግመኛ የራሱ ሊያደርገን ወደደ፡፡ እግዚአብሔር ሰውን በአርአያውና በምሳሌው ፈጠረው አዳም ከውድቀት በኋላ በመልኩና በምሳሌው ልጅ ወለደ ኃጢአተኝነትም በዚህ መንገድ ለሰው ሁሉ ደረሰ፡፡ (ዘፍ. 5÷3) እግዚአብሔር አብ ለበደለ ሰው የሚወደውን አንድያ ልጁን ወደ ዓለም ሰደደ፡፡ እርሱም በሰው መካከል በመገለጥ በሞት ላይ ስልጣን ያለውን ዲያቢሎስ በሞት እንዲሽር በሕይወታቸውም ሁሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነፃ እንዲያወጣ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ፡፡ (ዕብ. 2÷14) መዳን የሚጠይቀውን ሁሉ ዋጋ ለመክፈል አንዱ ስለ ሁሉ ሊሞት ሞትን ዓላማ እኛን አድራሻ አድርጎ መጣ፡፡     
“የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጥቶአልና፡- እነሆ በላተኛና የወይን ጠጅ ጠጭ ÷ የቀራጮችና የኃጢአተኞች ወዳጅ አላችሁት፡፡ (ሉቃ. 7÷34)”

          የጉንዳን መንጋ ላይ ቆሞ የሰፈሩበትን ጉንዳኖች እንደሚያራግፍ ምስኪን ሰው ኃጢአትን በልቡ ሞትንም በጀርባው ተሸክሞ ለዘመናት ከኩነኔ በታች ለተንከራተተው ጽድቁ እንኳ እንደ መርገም ጨርቅ ለተቆጠረቅ የሰው ዘር በክርስቶስ በምጣት ታላቅ የምስራች ሆነ፡፡ ተገለጠ፡፡ በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ለሚያምኑ ሁሉ በእርሱ በማመን የሚገኘው በሕግና በነቢያት የተመሰከረለት የእግዚአብሔር ጽድቅ ያለ ሕግ ተገልጧል፡፡ በነፍስ በሥጋ በመንፈስም ለታሰሩት መፈታት፣ ለዕውሮች ማየት፣ ለተጠቁት ነፃ መውጣት፣ ለድሆችም የወንጌል መሰበክ በክርስቶስ ሰው መሆን የሆነ ነው፡፡ በገነት ሰውን የተሸሸገበት ድረስ ሄዶ ወዴት ነህ? በማለት የሕይወትን ጥሪ ያሰማ አምላክ (የሸሸነው ጽድቅ) ያለንበት ድረስ መጣ፡፡ በበደልና በኃጢአታችን ሙታን የሆንነውን በማይለካ ፍቅሩ ወደደን፡፡

         በመዳፍህ የያዝከው ዕንቁ ከእጅህ ወጥቶ ጭቃ ውስጥ ወደቀ፡፡ ጭቃውን ብትጠላውም ለዕንቁው ያለህ ፍቅር ግን አይቀንስም፡፡ ስለዚህ አንጽተህ ዳግም የራስህ ልታደርገው ንጹሕ ለመሆን የሚጠይቀውን ሁሉ ዋጋ ትከፍላለህ፡፡ ካሉት መቶ በጎች የባዘነውን አንዱ ፍለጋ ዘጠና ዘጠኙን ትቶ እንደተሰማራ ባገኘውም ጊዜ ካልባዘኑት ይልቅ በአንዱ መገኘት ደስ እንደሚሰኝ መልካም እረኛ ክርስቶስ በቃል ከሚሰማው ነቀፋ በተግባር እስከሚታየው መከራ ሁሉን ስለ እኛ ሲል ተቀበለ፣ ለመዳንም የሚያስፈልገውን ሁሉ ዋጋ መስቀል ላይ ከፈለ፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋና በደም አቋም በዚህ ምድር በተመላለሰበት ወራት የሞት ቀንበር ለከበደበት፣ የኃጢአት ሸክም ለሚያንገዳግደው የሰው ዘር ባሳየው ርኅራኄ፣ በለገሰው የማይነጥፍ ፍቅር የኃጢአተኞች ወዳጅ ተብሏል፡፡ ሕሙማን (ኃጢአተኛ) እንደሆኑ ለሚያምኑ ሁሉ ክርስቶስ መድኃኒት ነው፡፡ አይሁድና ፈሪሳውያን ግን ከዘላለም ሞት ሊያድን የመጣውን ጌታ የኃጢአተኖች ወዳጅ፣ የግፉአን ባልንጀራ እያሉ ያሙት ነበር፡፡ መልካም መሆናችን ላለመታማት ዋስትና የለውም፡፡ በጎነታቸው በክፋት እየተመዘነ፣ መውደዳቸው የጥላቻን ያህል ዋጋ እየጠነፈገ፣ እንደ ማር የጣፈጠ ንግግራቸው ሕይወት የሆነ ምክራቸው እንደ ሬት እየተቆጠረ ኖረው ያለፉ እውነተኞችን ታሪክ ያስታውሰናል፡፡ ጌታም የጥላቻ ጉልበት ያደቀቃቸውን፣ የገዛ ነውራቸው ያሳፈራቸውን፣ የሰው ፊት የገፋቸውን በልቡ ተቀብሎ በቤታቸው ስለተስተናገደ ክፉዎች በጎውን ያሙት ነበር፡፡

            ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈው መልዕክቱ “አሳቾች ስንባል እውነተኞች ነን ያልታወቁ ስንባል የታወቅን ነን የምንሞት ስንመስል እነሆ ሕያዋን ነን” (2ቆሮ. 6÷9) ይላል፡፡ የብዙዎቻችን ጥረት ክፉ ላለመሆን ሳይሆን ክፉ ላለመባል ነው፡፡ ስለዚህ ሌሎች ስላሉን እንጂ ስለሆነው፣ ስለሚወራብን እንጂ ልባችን ስለሚያወራልን ግድ አይለንም፡፡ በመባልና በመሆን መካከል ግን ሰፊ ልዩነት አለ፡፡ ሰዎች እኛን በሚያሙበት ክፉ ነገር ውስጥ አለመገኘት በመልካም መታማት ነው፡፡ መርቆ መረገም፣ ወድዶ መጠላት፣ አቅፎ መገፋት፣ አጉርሶ መነከስ፣ በጎ ውሎ መሰደድ የክርስቲያን ክብሩ ነው፡፡ ክርስቶስም በመልካምነቱ ታምቶአል፡፡ ሐዋርያው በጊዜው ሰዎች ስለሚሉትና እርሱ ስለሚኖረው ኑሮ ሲያስረዳ አሳቾች ይሉናል እውነተኞች ነን፣ ያልታወቁ ይሉናል የታወቅን ነን በማለት ኑሮውንና ሐሜታውን ለይቶ ያሳየናል፡፡ ተወዳጆች ሆይ እኛ ስንባል ስንታማ ምን ዓይነት ሰዎች ነን? ንፉግ ስንባል ለጋስ፣ ክፉ ስንባል ደግ፣ ጠላት ስንባል ወዳጅ ነን ወይ? ሰዎች እኛን በሚያሙበት ነገር ውስጥ ከተገኘን ችግሩ ያለው እነርሱ ጋር ሳይሆን እኛ ጋር ነውና አካሄዳችንን ማስተካከል አለብን፡፡ ከዚህ ውጪ ከሰው ለሚመጣው ማንኛውም ሀሜትና ወቀሳ ይልቅ እግዚአብሔር ስለ እኛ በሚለው ነገር ላይ ማረፍ አለብን፡፡ በሕይወት ትልቁ ቁም ነገር ሌሎች ስለ እኛ የሚሉት ሳይሆን እግዚአብሔር የሚለው ነው፡፡

          ኃጢአተኛ እንደሆናችሁ ለሚሰማችሁ ሁሉ ጌታን የሚያህል ወዳጅ አላችሁና ከሞት ጋር የጀመራችሁትን ግብግብ አቁሙ፡፡ በደጃችሁ ቆሞ ለሚያንኳኳውም በመክፈት ምላሽ ስጡ፡፡ ሕሙማንን ሊፈውስ የእግዚአብሔር ልጅ በውርደት ተገልጧል፡፡ ከተለያየ ክፉ ልማድና ዓለማዊ አሠራር መላቀቅ ያቃታችሁ እናንተን ከዚህ የሚታደግ መድኃኒት ተገልጧልና በዚህ ደስ ይበላችሁ፡፡ የኑሮ ቀንበር የነውር ሸክም የከበደባችሁ ልባችሁን መሰላቸት የሞላው ሁሉ ነገር የማይታኘክ መራራ የሆነባችሁ እናንተን ሊያሳርፍ የኃጢአተኞች ወዳጅ የሆነ ጽድቅ ተገኝቷልና በእምነት ቅረቡ፡፡ ጌታ ሆይ ለፍቅርህ ተመን ልኬት የለውምና አንተ በምታውቀው መጠን ተመስገን!!!         

Wednesday, April 11, 2012

ሰነፍ እርቅ




         ሐይቅ እስጢፋኖስ (ኢየሱስ ሞዓ) አካባቢ ከገዳሙ ትንሽ ራቅ ብሎ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁት ነው፡፡ ለብዙዎቻችሁም አዲስ ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ አገራችን የመፈቃቀር፣ አብሮ የመብላት፣ እንግዳ የመቀበል ታሪክ ብቻ ያላት አይደለችም፡፡ ደም የመቃባት፣ የገዛ ወገንን ገሎ የመሸለል፣ አቂሞ ለበቀል ዱር የመሸፈትም ታሪክ የተሸከመች ናት፡፡ ስለ ፍቅር አብዝቶ በሚነገርበት፣ አብሮ መኖርና መደጋገፍ እንደ ስልጣኔ በሚቆጠርበት ዓለም ዛሬም ድረስ በሞት የሚፈላለ፣ጉ ለጥፋት የተሰማሩ መኖራቸውን ማስተዋል እጅጉን ለልብ ሀዘን ነው፡፡

       
  አካባቢው ላይ በተገኘንበት ወቅት አንድ ሰው ተገድሎ ፀጥታ አስከባሪዎች ስፍራውን በብርቱ ይጠብቃሉ፡፡ ከመጠየቅ እንደተረዳነው ምክንያቱ የሟች ቤተሰቦች የገዳይን ወገን እንዳይገሉ ለመጠበቅ መሆኑን ተረዳን፡፡ በአንድ ሰው ስህተት ሙሉ ቤተሰብ መጨነቁ፣ ነፃነት አጥቶ የቤት ውስጥ እስረኛ መሆኑ፣ በሞትኩ አልሞትኩ ሥጋት መሸበሩ እንኳን ለባለቤቶቹ ለታዛቢውም የሚጨንቅ ነበር፡፡ ማኅበረሰቡ ግን አብሮት እንዳደገ የቤት እንስሳ በጉዳዩ አለመገረሙ ያስገርም ነበር፡፡ እኛም ያለበደሉ ሞት በደጁ የሚያደባበትን ቤተሰብ ሊታደግ የሚችለው መፍትሔ ምንድነው? በማለት ጠየቅን፡፡ የተሰጠን መልስ ግን ለሌላ ጥያቄ የሚጋብዝ ነበር “የሰነፍ እርቅ”፡፡ እንደተነገረን ከሆነ የሰነፍ እርቅ ማለት ገዳይ በሕግ ጥላ ስር ከሆነ በኋላ ጉዳዩ በፍርድ ቤት እየታየ በዚህ መሐል የገዳይ ቤተሰቦች በሟች ወገን ጥቃት (ግድያ) እንዳይደርስባቸው ለጊዜው የሚደረግ መገላገያ ነው፡፡ ስለ ዋስትናው የጠየቅናቸው አባት እንደነገሩን “በሰነፍ እርቅ አስገደለኝ” የሚባል አባባል እንዳለ ጠቅሰው የሟች ቤተሰብ እርቁን ሊያፈርስ፣ የገዳይን ቤተሰብ ሊገድል እንደሚችልና በብዛት እንዲህ ያለው ነገር ሲከሰት እንደሚስተዋል አስረድተውናል፡፡ በማከልም የሟች ቤተሰብ ውሉን አፍርሶ ቢገኝ በሕብረተሰቡ ዘንድ ነውር እንደሆነ ነግረውናል፡፡ ከዚህም ጋር አያይዘው ልብን የሚነካ ታሪክ ማለትም የሰነፍ እርቅ ከተደረገ በኋላ ስለሞተ ሰው አጫውተውናል፡፡ ብዙ ጊዜ የሰነፍ እርቅ ሲከናወን ካሳ ስለማይካስና ሽምግልናው ገዳይ ተገኝቶ መጸጸቱን የማያሳይበት በመሆኑ ዘላቂነቱ አጠራጣሪ እንደሆነም መረዳት ችለናል፡፡

          ደም በደም፣ ወንጀል በበለጠ ወንጀል፣ ቅያሜ በከፋ በቀል የሚመለስበት አገር ላይ እየኖርን መሆኑን ማወቃችን ምን ያህል በጸሎት መትጋት እንዳለብን የሚጠቁም ይመስለኛል፡፡ አንዱ በዘራው ሌላው እያጨደ፣ አንዱ በበደለ ሌላው እየካሰ፣ አንዱ ባጠፋ በጅምላ እየተላለቅን መኖራችን እውነት በልባችን ላይ ስፍራ እንደተነፈገ የሚያስረዳ ነው፡፡ እንዲህ ያለውን ነገር ለመቀየር የተለያዩ ቤተ እምነቶች በጋራ መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡ በግለሰብ ደረጃ ደግሞ ለይቅርታ ያለንን አመለካከት ማስተካከልና ማሳደግ አለብን፡፡ የእግዚአብሔር ቃል “ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ” (ቆላ. 3÷13) ይላል፡፡ የይቅርታችን መሠረት እግዚአብሔር በልጁ በኩል ለእኛ ያሳየን (የሚወደውን አንድያ ልጁን በመስጠት) ይቅርታ ሲሆን እኛ ለሌሎች ይቅርታ እንድናደርግ የሚያስችለን ኃይል (ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቷልና) ደግሞ በመስቀል ላይ ሆኖ ለወጉት ምሕረትን የለመነው ጌታ ነው፡፡ ያንን የመስቀል ላይ ምሕረት በደም የሆነ ይቅርታና ስርየት ዕለት ዕለት የሚያስታውሰን ደግሞ ቅዱሱ የእግዚአብሔር መንፈስ ነው፡፡

          ክርስቶስ እኛን ይቅር ያለን በበደላችንና በኃጢአታችን ሙታን፣ ከፍጥረታችንም የቁጣ ልጆች ሳለን ነው፡፡ የኃጢአት ደመወዝ ሞት እንደመሆኑ የዘራነውን ማጨድ ፍትሃዊነት ሆኖ ሳለ ክርስቶስ ግን የማይገባንን ሕይወት ሰጥቶ የሚገባንን ሞት እርሱ ሞተልን፡፡ (ኤፌ. 2÷1-6) ዛሬ በእኛ ላይ የሚሆንብን ነገር እኛ በእግዚአብሔር ላይ ከሠራነው በደል አይበልጥም፡፡ ብዙው ተትቶልን ጥቂቱን ይቅር ማለት ካልቻልን ግን እጀ ነካሽ፣ ወጪት ሰባሪዎች ነን፡፡ እግዚአብሔር ሰነፍ እርቅ የለውም ይቅርታና ምሕረቱ ለዘላለም ነው፡፡ በዚህም ይጸጸት ዘንድ እግዚአብሔር ሰውን አይደለም፡፡

         ይህንን ርዕስ ያነሣሁበት ምክንያት ለምክርና ለተግሳጽ የሚሆን ጥቂት ቁም ነገር ስላገኘሁበት ነው፡፡ በእኛስ ሕይወት ሰነፍ እርቅ አይስተዋል ይሆንን? ፆም እስኪፈታ የይምሰል ታርቀን በነገር የምንፈስክ ስንቶቻችን ነን? ካንጀት ሳይሆን ካንገት፣ የልብ ሳይሆን የአፍ እርቅም ሰነፍ እርቅ ነው፡፡ ከፊል ቂም ከፊል ይቅርታ፣ ከፊል ኩርፊያ ከፊል ሰላምታ፣ ከፊል መንፈግ ከፊል መቸር ባጠቃላይ ይግደልሽ እያሉ ይማርሽ እንደሚባለው ያለ አይነት ነው፡፡ እግዚአብሔር የእርሱ የሆኑትን፣ በእውነትና በመንፈስ የሚያመልኩትን እንዲህ ይላል “እንግዲህ መባህን በመሠዊያው ላይ ብታቀርብ በዚያም ወንድምህ አንዳች በአንተ ላይ እንዳለው ብታስብ በዚያ በመሠዊያው ፊት መባህን ትተህ ሂድ አስቀድመህም ከወንድምህ ጋር ታረቅ በኋላም መጥተህ መባህን አቅርብ፡፡ (ማቴ. 5÷23-24)  ክርስቶስ ለእኛ ያሳየውን ይቅርታ ስንረዳ እኛም ሌሎችን ይቅር የማለት ጉልበት እናገኛለን፡፡ ይቅር ማለት ይብዛላችሁ!!

Monday, April 9, 2012

ሰው ለቤቱ



         የመጽሐፍ ቅዱሳችን የመክፈቻ ክፍል በሆነው የዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ ብዙ ከመለኮት ለሰው የተላለፉ ለትምህርትና ለተግፃጽ ልብንም ለማቅናት የሚያገለግሉ መንፈሳዊ መልእክቶች እንዳሉ እናውቃለን፡፡ ከዚህ ርዕስ ጋር በተያያዘ የምናነሣው ከያዕቆብ ታሪክ የተወሰነውን ክፍል ይሆናል፡፡ ይስሐቅና ርብቃ ያዕቆብና ዔሳው የሚባሉ ልጆች እንደነበሯቸው እነርሱም ገና በማህፀን ሳሉ ይጋፉ እንደነበር ያም መገፋፋት ወደ ማስተዋል ከመጡ በኋላም በኑሮአቸው እንደተገለጠ ዜና መዋዕላቸው ያስረዳናል፡፡

       ይስሐቅ በእድሜው ምሽት፣ በዘመኑ መጨረሻ፣ አይንን በሚይዝ እርጅና ውስጥ ሆኖ በኩሩንና የሚወደውን ልጁን ዔሳውን በመጥራው “ከመሞቴ በፊት እንድመርቅህ ወደ ዱር ሂድ አድነህም ጣዕም ያለውን ምግብ አዘጋጅተህ አብላኝ” አለው፡፡ ርብቃ ይህንን ትሰማ ስለነበር እርሷም በተራዋ የዔሳውን እግር ጠብቃ ለምትወደው ልጇ ለያዕቆብ በወንድሙ ምትክ በረከትን መቀበል እንደሚችል ለዚህም አደን መውጣት እንደማያስፈልገው ይልቁንም በቤት ካሉት ጠቦቶች መካከል የሰቡና የጣሙትን ሁለት እዲያመጣ አዘዘችው፡፡ ያዕቆብ የእናቱ ብልሀት የተቃኘ ማታለል አልዋጥ ቢለው “ወንድሜ ሰውነቱ ጠጉራም ነው የእኔ ገላ ደግሞ ለስላሳ ነው ታዲያ አባቴ ይህንን ባረጋገጠ ጊዜ በበረከት ፈንታ መርገምን አተርፋለሁ” አላት፡፡ ርብቃ ግን መርገሙ በእኔ ላይ ይሁን በማለት ያዘዘችውን እንዲፈጽም ነገረችው፡፡

        በዚህ ቤተሰብ ውስጥ ከምናስተውለው ነገር አንዱ መለያየትን ነው፡፡ በያዕቆብና በዔሳው መካከል ግፊያ የጀመረው ገና በማኅፀን ሳሉ ቢሆንም ያ ባለማስተዋል የነበረ ነው፡፡ ወደ ማስተዋል ከመጡ በኋላ ግን የምናየው መለያየት የቤተሰብ ተጽእኖ ውጤት ነው፡፡ እናትና አባት ለልጆቻቸው እኩል ፍቅር ባለማሳየታቸው በወንድማማቾቹ መካከል ዛሬ ድረስ ያልጠፋ መለያየትና ጠላትነትን አትርፏል፡፡ በእኛም አገር እንዲህ ያለው የቤተሰብ መሐል መለያየት ጎልቶ የሚስተዋል ችግር ነው፡፡ አንድ ሰው የአካባቢውና የቤተሰቡ ውጤት እንደመሆኑ ችግሩ ተሸጋጋሪ፣ ጉዳቱ ሁለንተናዊ ነው፡፡ እየሰማን ካደግነው ይትባህል መሐል “ሴት ልጅ አባቷን ወንድ ልጅ እናቱን ይወዳል” የሚለው ተጠቃሽ ነው፡፡ ከዚህም ስር ሰደድ ብሒል የተነሣ በአንድ ቤት ውስጥ ሁለት ዓይነት ጽንፍ፣ በተለይ በእናትና በአባት አለመግባባት ወቅት ይስተዋላል፡፡ ቤተሰብ አርአያነቱ መጀመሪያ ለቤቱ ሰዎች እንደመሆኑ በመልካም ምሳሌ መሆን እንዲሁም  ሚዛናዊነቱን የጠበቀ ፍቅር ለልጆች ማሳየት አግባብ ነው፡፡

          ያዕቆብ የእናቱን ምክር ሰምቶ በድምጽ ራሱን በሰውነቱ ደግሞ ወንድሙ ዔሳውን መስሎ ቆመ፡፡ ይስሐቅ የያዕቆብን ዔሳው አለመሆን ቢጠራጠረውም ከዚህ ያለፈ አቅም አልነበረውም፡፡  ልብንና ኩላሊትን በሚመረምረው እግዚአብሔር ፊት ግን ሰው በሁለት ማንነት ሊቆም  ከመታወቅስ ሊያመልጥ እንዴት ይችላል? ያዕቆብ ሁሉን በእናቱ ምክር ቢያደርገውም አጨዳውን ግን ከእናቱ ጋር አላጨደውም፡፡ እንደውም ያዕቆብ የወንድሙ ቁጣ እስኪበርድ ድረስ ወደ አጎቱ ላባ ዘንድ ከሸሸ በኋላ እናቱ የሞተችው ዳግመኛ ሳይተያዩ ነው፡፡ ያዕቆብ አባቱ ቤት የዘራውን ማታለል አጎቱ ቤት ዐሥራ አራት ዓመት በመታለል እንዲሁም የገዛ ልጆቹ ዮሴፍን ለምድያም ሰዎች ወደ ግብጽ ሸጠውት ልብሱን በደም ነክረው በማምጣት ልጅህ ሞቷል በማለት በእርጅናው አታለሉት፡፡ “ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳል” (ገላ. 6÷7) ተብሎ እንደተፃፈ ያዕቆብ የዘራውን አጨደ፡፡

            ኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ ሠላሳ ቁጥር ሠላሳን ስናነብ ግን ያዕቆብ ወደ ልቡ እንደተመለሰና “እኔ ደግሞ ለቤቴ የምሠራው መቼ ነው?” በማለት የአጎቱን ቤት ጥሎ እንደሄደ እናስተውላለን፡፡ እግዚአብሔር የቃል ብቻ ሳይሆን የሕይወትም መምህር ነው፡፡ ስለዚህ ሁኔታን መንገር ብቻ ሳይሆን በሁኔታ ውስጥም ያሳልፈናል፡፡ ያዕቆብ ባለፈባቸው የኑሮ ብርቱ ሰልፎች ውስጥ ምን ያህል እንዳጣ አስተውሎ የአጎቱን የተመለስ ልመናና የአደርግልሃለው ማባበያ እንቢ አለ፡፡ ያዕቆብ ዕድሜውን ለራሱ ለመሰብሰብ ቢተጋበትም እኔነቱ ያስገኘለት ነገር ግን የለም፡፡ በዚህም የእግዚአብሔር ጸጋ ምን ያህል ሰፊ እንደሆነ እናገናዝባለን፡፡

          የእግዚአብሔር ቃል በግልጥ እኛ የመለኮት ቤት እንደሆንን ይናገራል፡፡ (2ቆሮ. 6÷16) ቤትን ስናስብ ደግሞ ብዙ ነገሮች ወደ ሕሊናችን ይመጣሉ፡፡ ዞረን ዞረን የምንሰበሰብበት፣ ክፉውንም ደጉንም የምናሳልፍበት፣ ከፀሐይ ንዳድ ከበረታ ብርድ የምንሸሸግበት፣ ቢከፋን ማኩረፊያ፣ ቢመቸን ማረፊያችን ነው፡፡ ነገር ግን ቤትን ቤት ሊያሰኙ፣ መኖርም ሊያስችሉ፣ መንፈስና ቀልብን ሊስቡ የሚያስችሉ አስፈላጊ ነገሮች አሉ፡፡ የመጀመሪያው ንጽሕና ነው፡፡ ሰው የቤት ዕቃ ስለማሟላት ለማሰብ የቤቱን ንጽሕና በቅድሚያ ሊያስተውል ግድ ነው፡፡ ንጹሕ ባልሆነ ቤት ስለተሟላ የቤት ዕቃ ማውራት ግብዝነት ነው፡፡ በቁሙ ቤትን ያለ ንጽሕና ማሰብ አለኝ እያሉ ለመኖር ካልሆነ በቀር ከቤቱ ተጠቃሚ መሆን አይቻልም፡፡

           እኛ የሕያው እግዚአብሔር ቤት መሆናችንን ከተረዳን የቤቱ ንጽሕና እንዲጠበቅ መትጋት አለብን፡፡ ልብሳችን ላይ ቁሻሻ ማየት የሚያስቆጣን ከሆነ ልባች ላይ የሚገላበጠው የኃጢአት ብዛት ምነው አያስከፋንም? መልካምነት የሚጀምረው ከቤት ነው፡፡ ለቤታችን ንጽሕና ሳንቆረቆር ለመንደር ንጽሕና ዘብ መቆም የራስን እያሳረሩ የሰው ማማሰል ነው፡፡ ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን እውነትም በእኛ ዘንድ አይኖርም፡፡ (1 ዮሐ. 1÷8) ኃጢአት ደግሞ ለእግዚአብሔር ጽድቅ ጠላት ነው፡፡ ኃጢአትም ከዘላለም ሞት ፍርድ በታች ማብቂያ ለሌለው ኩነኔ ተላልፎ ተሰጥቷል፡፡ ሰው ከዚህ ኃጢአት የሚነፃበት ከፍርድም ነፃ የሚሆንበት ኃይል ያስፈልገዋል፡፡ የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ እንደሚያነፃ መረዳት ደግሞ እንደቆሸሹ ለሚያምኑ ሁሉ የሚያጠራ ውሃ ነው፡፡ (1ዮሐ. 1÷7) በሰማይና በምድር ፊት እግዚአብሔርን እንደበደልነው ሲሰማን ወደ ምሕረቱ የምንቀርበው በንስሐ ሲሆን እግዚአብሔር ለእኛ ይቅርታን የሚሰጠን ደግሞ አንድ ጊዜ ከፈሰሰው የልጁ ደም የተነሣ ነው፡፡ ስለዚህ የምንነፃበት እያለ ቆሽሸን የምንቀደስበት እያለ ረክሰን የምንድንበት እያለ ተኮንነን የሚቀበለን የምሕረት እጅ እያለ ተቅበዝብዘን መኖር የለብንም፡፡ ኃጢአትን በመሰወር ውስጥ ልማት የለም በመናዘዝና በመተው ግን በረከት አለና ተወዳጆች ሆይ ንጽሕና ይጠበቅ!!

           ሁለተኛው ፀጥታ ነው፡፡ ዛሬ ዓለም ላይ ጮኸው የሚሰሙት በፀጥታ ውስጥ የተከናወኑ ተግባራት ናቸው፡፡ እንደዚህ ዘመን መደማመጥ የጠፋበት አሳብ የተደበላለቀበት የሚመስለውን ከሆነው መለየት ያስቸገረበት ጊዜ የለም፡፡ ሕይወትን ለኪሳራ የሚዳርጋት ትልቁ ነገር ጽሞና የለሽ ትጋት ነው፡፡ ሰው ያገኘውን ካጣው የያዘውን ከበተነው ያተረፈውን ካጎደለው በፀጥታ ካልመረመረና ካለየ እድገት እንዴት ሊኖር ይችላል? ፀጥታ በተሳሳተ መንገድ ሮጦ የተሳሳተ ነገር ከማጨድ ይጠብቃል፡፡ እግዚአብሔር ለሕይወታችን ያለውን አሳብ ልንሰማውና ልንረዳው የምንችለው ፀጥታን መለማመድ ስንችል ነው፡፡ አለዚያ እየሮጡ መታጠቅ እየሮጡ መፈታት ይሆናል፡፡

          ከኃጢአት ቀጥሎ ለሕይወታችን መታወክ ምክንያት የሚሆነው ለኑሮ መጨነቅ ነው፡፡ እግዚአብሔር እኛን ወደዚህ ምድር ያመጣን አስቀድሞ የሚያስፈልገንን በመፍጠር ነው፡፡ ዛሬ ጭንቀት ስናመርት የምንውለውም ከእኛ ቀድመው ለተፈጠሩት ነገሮች ነው፡፡ የሠራን እግዚአብሔር ነው ለኑሮአችንም ከእርሱ በላይ ሊያስብ የሚችል የለም፡፡ መጨነቅ የማያስረዝሙትን ፀጉር ሲጎትቱ መኖር ነው ይህ ደግሞ ለውጥ በማይመጣበት መልኩ ራስን መጉዳት ነው፡፡ ክርስቲያን ወደ መኖር ባመጣው በአንድ ልጁ በክርስቶስ ኢየሱስ ባዳነው አምላክ ያረፈ አሳቡም በዘላለም ሕይወት የተሞላ ነው፡፡ ቃሉ “እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉ” ይላል፡፡ ግን ጥለናል ወይ?

        የሕይወት ፀጥታ የመጣንበትን ያለንበትንና መዳረሻችንን አጥርተን እንድናይ ይዳናል፡፡ እግዚአብሔር የሰላም አምላክ እንጂ የሁከት አምላክ ስላይደለ ከእርሱ ጋር ለመገናኘት ፀጥታ ብርቱ ነው፡፡ ስለዚህ በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ፡፡ አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል፡፡ (ፊል. 4÷6) ተወዳጆች ሆይ በልባችሁ ግድግዳ ላይ የተሰቀለውን ማስጠንቀቂያ አንብባችሁታልን? እንዲህ ይላል “ፀጥታ ይከበር”፡፡ ለበረከት ሁኑ!!

Thursday, April 5, 2012

መጽናናት




     በአዲሱ እለት አጥቢያ ላይ ከእንቅልፌ ስነቃ ልክ የመከራ ወጀብ ወደ እኔ እንደሚመጣ መስሎ ተሰማኝ፡፡ ማየት የቻልኩት ሁሉ ከችግር ቀጥሎ የሚመጣ ሌላ ተግባር ነው፡፡ እናም ጮኼ ማልቀስ ጀመርኩ አቤት ጌታዬ ከእኔ የምትፈልገው ምንድን ነው?” ከከፍታው የመጣው ምላሽ ምንም ሳይሆን በጣም ቀላል ምላሽ ነበር፡፡ አንድ ያልተጠበቀ ነገር ግን እውነተኛ ምላሽ፡፡ ከእኔም ሆነ ከእናንተ የሆነ የሚፈልገው ነገር አለ፡፡ ሁሉንም ነገርሲል መለሰልኝ፡፡ እንደ አዳኝህና እንደ መሪህ ሁልጊዜም በመንገድህ ሁሉ አብሬህ እንዳለሁ የአንዲቷ ፀጉርህ ዘለላ እንኳን ወዳጅ፤ እኔ እንደሆንኩ እንድታውቅ እፈልጋለሁ፡፡

     በመልካም ጊዜያትም ሆነ በክፉዎቹ በእውነትና በመንፈስ እንድታገለግለኝ፣ ተደሰትክም ተከፋህም በምስጋና መሥዋዕት እንድታከብረኝ እፈልጋለሁ፡ በእያንዳንዷ እለት እምነትህ እየጠነከረ እንዲያድግ ለምንለሚሉት ጥያቄዎችህ መልስ ባይኖርህም እንኳን በእኔ እንድታምን እፈልጋለሁ፡፡ ያጋጠመህን አስቸጋሪ ነገር እንድትኖርበት ስትጠራ፤ የእኔን ፍቅር እንድትማርና እቅፌም እንዲሰማህ እፈልጋለሁ፡፡ ማንም ሆነ ምንም በልብህ ያለኝን ቦታ እንዲወስድ አልፈልግም፡፡ ልታደርገው በሚገባህ በማንኛውም ነገር ውስጥ ቀዳሚና ትልቅ ድርሻ እንዲኖረኝ እፈልጋለሁ፡፡ ምንም ነገር አያናውጽህ በቃል ኪዳኔም ጽና በስተመጨረሻም ሁሉ ነገር ተከናውኖልህ ታያለህ፡፡ እስኪ አስብ?

W ሕመም የማይሰማህ ቢሆን ፈዋሽ መሆኔን እንዴት ታውቃለህ?

W በመከራ ውስጥ ካላለፍክ ነፃ አውጪ መሆኔን እንዴት ልታውቅ ትችላለህ

W ብስጭት ካልተሰማህ እንዴት ሆሃ ምቹ እንደሆንክ ታውቃለህ

W ፈተናዎች ከሌሉብህ እንዴት አድርገህ ራስህን ጽኑ እኔን አሸናፊ ብለህ ልትጠራ ትችላለህ?

W ስህተቶችን ጭራሽ ካልሠራህ ይቅር ባይ መሆኔን እንዴት ማወቅ ይቻልሃል?

W ሁሉን የምታወቅ ከሆነ ጥያቄዎችህን ሁሉ እንደምመልስልህ በምን ታውቃለህ?

W ጭራሽ ያልተሰበርክ ብትሆን ኖሮ ሙሉ ላደርግህ እንደሚቻለኝ ከወዴት ታውቃለህ?

W የማልቀጣህ ቢሆን እኔ እንደምወድህ፣ አንተም ልጄ እንደሆንክ እንዴት ትረዳለህ?

W ኃይል ሁሉ ቢኖርህ በእኔ ላይ መደገፍን እንዴት ልትማር ትችላለህ?

W ሕይወትህ ፍጹም ቢሆን ኖሮ ከእኔ የምትፈልገው ምን ይኖር ነበር?

        አየህ ውድ ልጄ በሁሉም ነገር ውስጥ ሁሉ ነገርህ እንድሆን እና ወደቅህም ጸናህም በእኔ መኖር ላይ እንድትደገፍ እፈልጋለሁ፡፡ ከእኔ የምትፈልገው ምንድነው? ለሚለው ጥያቄህ መልሴ ሁሉንም ነገርየሚል ነው፡፡ ልክ አንተ ለእኔ ሁሉ ነገር እንደሆንክ ሁሉ፡፡ ከግርግርና ከፈተና የጸዳ ቀለል ያለ ሕይወትን መፈለግ ለብዙዎቻችን አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ይልቁንስ የማንረዳው ነገር ቢኖር ያለ ውጣ ውረድ የምንኖርባት ሕይወት ያን ያህል የሻትነውን ነገር ከግቡ ለማድረስ እንደማታስኬደን ነው፡፡

     ደስታን ለማድነቅ ሐዘን ያስፈልጋል በትንሽ ስጦታ ውስጥ እርካታን ለማግኘት መሰላቸት ይኖራል፡፡ ይህም እያንዳንዱን አስፈላጊ ሥራ የምናደርግበትን፣ አዳዲስ አሳቦችን የምናፈልቅበትን እና አስቀድመን የያዝነውን ጸጋ የምንናፍቅበት እድል የሚፈጥርልን ነው፡፡ ቢሆንም ግን ልብ ልንለው የሚገባን ነገር ሕይወት የተመሠረተችው እኛ በከፊል በምናደርገው ነገር ላይ ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔር ለሰው በሚያደርገው ሙሉ ነገር ላይ መሆኑን ነው፡፡ ሙሉ እኛነታችን ይህንን ታላቅ እውነት እስካልተቀበለውና እስካልኖርንበት ድረስ መልካምነትና ሰላም በሙላት በእኛ ውስጥ ሊኖር አይችልም፡፡ እርሱ ብቻውን እውነተኛ አዳኝ ነው፡፡ ስለዚህ በዋናነት በራሳችን ላይ የምንደገፍ ከሆነ ሕይወት የማይገፋ እየሆነብን ይመጣል፡፡ የእግዚአብሔር ጸጋ ሕልውናችን ነው፡፡ በእርሱ ላይ እንሄዳለን፡፡ እርሱንም እንተነፍሳለን፡፡ በእርሱም ውስጥ ኖረን በእርሱም ውስጥ እንሞታለን፡፡

Tuesday, April 3, 2012

ስመ አበሮች



          ሰው ማኅበራዊ እንደመሆኑ ከግለኝነት ይልቅ እርስ በእርስ የሚገናኝባቸው ጉዳዮች የበዙ ናቸው፡፡ ከሁሉም የበረታው ግን የዓላማ ዝምድናና ግንኙነት ነው፡፡ ክርስትና በሥጋ ካለው ዝምድና እንዲሁም ከማኅበራዊ መስተጋብር የጠነከረና ስር የሰደደ ነው፡፡ የሥጋ ዝምድና በሞት የሚፈታ መቃብርን የማያልፍ ሲሆን መንፈሳዊው ቤተሰባዊነት ግን በሞት ላይ ሕያው ከመቃብርም አልፎ ለዘላለም ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ግብረ አበር ሲባል እንሰማለን ይህ ከወሬ፣ ከምክር፣ አቅጣጫም ከመጠቆም ባለፈ ራስን ደምሮ በተግባሩ መሳተፍን የሚያሳይ ነው፡፡ ስለዚህ የአንዱ ተጠያቂነት ሌላውንም ተጠያቂ ያደርጋል፣ የአንዱ ኪሳራ ሌላውንም ይነካል፣ የአንዱ እንባ ሌላውንም ያስነባል፡፡ እዚህ ላይ አፍንጫ ሲመታ አይን ያለቅሳል ነው፡፡ የአንዱ ሞት ለሌላውም የሞት ያህል ነው፡፡ በደስታውም እንዲሁ ነው፡፡ የእገሌ ሳቅ ለእገሊትም ደስታ ነው፡፡ የአንዱ ማትረፍ ለሌላውም ትርፍ ነው፡፡ በጋራ ትግል የጋራ ድል በጋራ ድካም የጋራ ሽንፈት መቀበል የግብረ አበርነት ጠባይ ነው፡፡

           የስም አበርነትን ስንመለከት አለሁ ግን አልተሳተፍኩም፣ አባል ነኝ ግን አልተባበርኩም፣ ይመለከተኛል ግን አልተመለከትኩም የሚል ዓይነት ነው፡፡ በተደከመበት ላይ ንግግር፣ በተለፋበት ላይ ድርድር፣ ባለቀ ነገር ላይ መሸለል አይነተኛ ጠባያቸው ነው፡፡ ስም አበሮች አቀብሎ ሸሽ ዓይነት ናቸው፡፡ ዋጋ መክፈሉ ላይ የሉም ዋጋ ሲሰጥ ግን ማልዶ ሰልፈኛ ናቸው፡፡ ሥራውን ስትሠሩ፣ ድካሙን ስትደክሙ፣ ተግዳሮቱን ስትጋፈጡ አጠገባችሁ የሉም፡፡ ነገር ግን የድመት አፍንጫ የንስር ዓይን አላቸው፡፡ ከተግባሩ በኋላ ሲወራ አብሮ ይወራላቸዋል እንደውም የእነርሱ ሊልቅ ይችላል፡፡ በክርስትናውም ዓለም የስም ተሳትፎአቸው ያየለ ሥራውና ተግባሩ ላይ ግን ደካሞች የሆኑ፣ ብዙ የሚወራላቸው ጥቂቱም የሚበዛባቸው አሉ፡፡ ባለቀ ሥራ ላይ መራቂዎች፣ በግንባታው ላይ ግን የሩቅ ታዛቢዎች ብዙ ናቸው፡፡

         ተወዳጆች ሆይ ከስመ አበሮች ወይስ የግብረ አበሮች ናችሁ? መልካም ነገር በስም ሳይሆን በግብር ሲተባበሩት፣ በሩቅ ሳይሆን ቀርበው ሲኖሩት ጣዕም፣ ውበትና ለሌላው የሚተርፍ በረከት አለው፡፡ ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ የሚሉት ሁሉ መንግስቱን እንደማይወርሱ፣ በቃልና በአንደበት ብቻ የሚዋደዱም ፍቅር የሆነውን ጌታ እንደማያከብሩ፣ ሕጉን የሚሰሙ ዳሩ ግን የማይፈጽሙ እንደማይባረኩ ባለቤቱ ተናግሯልና ለጽድቅ ስመ አበር ከመሆን ግብረ አበር መሆን ያስፈልገናል፡፡

          ክርስትና ነኝ ሲሉትና ሲሆኑት አንድ አይደለም፡፡ ዛሬ የሚፋንኑት የግብር ሳይሆን የስም አበሮች ናቸው፡፡ ስለ ፍቅር የሚያወሩ ግን ፍቅርን ከስም ባለፈ በግብር የማያውቁት ደግሞም የማይገልጡት፣ ለመውደድ አይደለም ለመወደድ እንኳን ልባቸው የማይታዘዝላቸው፣ ርኅራኄን በስም ብቻ የሚያውቁት ነፍሳቸው ለባልንጀራ የማይራራላቸው ላማጡት የጨከኑ፣ ይቅርታን በርቀት ያውም በስም የተግባቡት የስም አበሮች የግብር ባይተዋሮች፣ ስለ መሆን ብዙ የሚያብራሩ ጥቂት የማይኖሩ የሕይወት ተላሎች ቤት ይቁጠራቸው፡፡ በስም ባልና ሚስት በተግባር የጧሪና ተጧሪ ኑሮ የሚኖሩ የዘወትር ርእሳቸውና ጭቅጭቃቸው በጀት የሆነ የግብረ አበር ያለህ ይላሉ፡፡ መንፈሳዊውም ዓለም የስም ሳይሆን የተግባር ጥያቄው እያየለ መጥቷል፡፡ ተወዳጆች ሆይ እግዚአብሔርን እንደ እግዚአብሔርነቱ የምንገልጠው በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባርም ነውና እውነትን በስም ብቻ ሳይሆን በግብርም እንድንተባበር ጸጋው ይብዛልን!!!