Tuesday, January 15, 2013

የቆቅ ትዳር



                                                                   

                                             ማክሰኞ ጥር 7/2005 የምሕረት ዓመት

         ከወደ አውሮፓ የሰማሁት አንድ ነገር ትዝ ይለኛል፡፡ ልጅቱ እና ልጁ በእጮኝነት የአራት አመታት እድሜ አስቆጥረዋል፡፡ በእነዚህ ጊዜያት ሁሉ በአንድ እጅ የመብላትና በአንድ አፍ የመናገርን ያህል የፍቅር ቅርበትና መዋደድ ነበራቸው፡፡ ታዲያ ለመጋባት ወስነው ቀን ይቆርጣሉ፡፡ በዚያም ቀን የቤተክርስቲያኑ አዳራሽ በታዳሚ ጢም ብሎ ሙሽራውና ሙሽሪት ለቀለበትና ለፊርማ ስነ ሥርዓት ወደተዘጋጀው መድረክና ይህንን ወደሚያስፈጽሙት የሃይማኖት አባት በእርጋታ ይቀርባሉ፡፡ ድንገት ባል ፊርማውን በተዘጋጀው ምስክር ወረቀት ላይ አስፍሮ እንደጨረሰ የሚስቲቱ ተራ ሲደርስ ቬሎዋን ሰብስባ ከፍ ባለ ድምጽ “አንተ አታገባኝም . . . . አዎ! አንተን አላገባም” እያለች ከአይን ያውጣሽ በሚያስብል ድፍረት በእድምተኛው መሐል ተወራጭታ ወጣች፡፡ ግን ምክንያቷ ምን ይመስላችኋል?

         የጥርን ወር መበሰር ተከትሎ አንድ ነገር ያስተዋላችሁ ይመስለኛል፡፡ የጋብቻ ስነ ሥርዓት ! እንደ እግዚአብሔር ሰው በሁለት ሰዎች አንድ ሥጋ መሆን ደስታ ሲሰማን፤ በትዳር ውስጥ ለሚፈጠረው የከፋ ችግር በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የጦሱ ሰለባ መሆናችንን ስናስብ ደግሞ ሥጋትና ሀዘን ይከብበናል፡፡ ውድ የቤተ ፍቅር ብሎግ ተከታታዮች ጋብቻን በተመለከተ ብዙ ችግሮች እንዳሉ ያለ ነጋሪ የምናውቀው ሐቅ ነው፡፡

         የአንድን ወንድና የአንዲትን ሴት ትዳር የተሻለ ውበትና ሰላም የሚሰጥ ጥቂት መፍትሔ በልባችሁ እንዳለ ከተሰማችሁ አልያም በዚህ ርዕስ ዙሪያ እኔ ላካፍል የምችለው አሳብና ገጠመኝ አለኝ የምትሉትን ከታች ባለው አስተያየት መስጫ ውስጥ በመፃፍ እንድትወያዩበትና ቆቅማ የሆነውን ግን ጥበብ የሌለውን የትዳር ኑሮ እንታደግ በማለት እንጋብዛለን፡፡ በሚቀጥለው ጽሑፍ ስንገናኝ ከላይ የጠየቅናችሁን ጥያቄ መልስና ሰፋ ያለ ማብራሪያ ለማቅረብ እንሞክራለን፡፡ በጸሎት አግዙን!

                                                               - ይቀጥላል -  
        

Tuesday, January 8, 2013

እንደ ገና ዳቦ . . .




                                    ማክሰኞ ታህሳስ 30/2005 የምሕረት ዓመት

       አንድ ቂመኛ ሰው “ክፉውን በመልካም እንጂ በክፉ አትቃወም” የሚለውን የፍቅር ትምህርት በመቃወም “እንዴት ይህ ሊሆን ይችላል?” በማለት ቡዳሃን (የቡድሂዝም እምነት መስራች) ጠየቀው፡፡ እርሱም ካደመጠው በኋላ “አንድ ሰው ለጓደኛው ስጦታ አዘጋጅቶ ወሰደ፡፡ ነገር ግን ጓደኛው ስጦታውን አልቀበልህም አለው፡፡ በዚህ ጊዜ ይህ ስጦታ ለማን የሚሆን ይመስልሃል?” አለው፡፡ ወጣቱም “ለዚያው ለራሱ ነዋ!” ሲል መለሰ፡፡ ቡዳሃም “መጥፎና ጠማማ ሰው ሰማይን በምራቁ ለማበላሸት ተንጋሎ እንደሚተፋ ሰው ነው፡፡ የጠማማው ሰው ምራቅ ተመልሶ ራሱን ያረክሰዋል እንጂ ሰማይን ማርጠብ አይችልም፡፡ ክፉም እንዲሁ በክፋቱ ሌላውን ከሚጎዳ ይልቅ ራሱን በይበልጥ ሲጎዳ ይኖራል” በማለት ቂመኛውን ሰው አስተማረው፡፡
       ከቡድሂዝም ትምህርት መካከል የማስታውሰውንና ከክርስትና አስተምህሮ ጋር በእጅጉ አንድ የሆነውን ክፍል እንዳስታውስ ያደረገኝ በአገራችን የተለመደ አንድ አባባል ወደ አእምሮዬ ስለመጣ ነው፡፡
“አንተም ክፉ ነበርክ ክፉ አዘዘብህ
እንደ ገና ዳቦ እሳት ነደደብህ፡፡” ይሰኛል፡፡
ሰውየው “የእጅህን ይስጥህ” የሚለው ርግማን እንደተፈፀመበትና ተመጣጣኝ ዋጋ እንደተከፈለው ሌላኛው ወገን “እሰይ” በሚሰኝ እርካታ ውስጥ ሆኖ የተናገረው ቃል እንደሆነ የኃይለ መለኮት ሹም ለነበሩት በዛብህ የተገጠመው ይህ ግጥም ያስረዳናል፡፡

Tuesday, January 1, 2013

የእድሜ በረከት




                                                                                                                              

                                 ማክሰኞ ታህሳስ 23/2005 የምሕረት ዓመት


        እግዚአብሔርን እናመሰግነው ዘንድ ካሉን ምክንያቶች ሁሉ የላቀው ምክንያት ይመስለኛል፡፡ መቼም ሰው ነንና ስለ በላነው ምግብ እንጂ ስላላመጥንበትና ስለዋጥንበት እድሜ ለማመስገን ግንዛቤውም ሆነ ፍላጎቱ የለንም፡፡ እረ እንደውም! ለምንበላውና ለበላነው ለማመስገንም እንፈተናለን፡፡ ማን ነበሩ “ማምሻም እድሜ ነው” ያሉት፡፡ እውነታቸውን ነው ሰው ጥርሱ ያኘከውን፣ አፉ ያመላለሰውን፣ ምላሱ ያጣጣመውን በጉሮሮው የሚያወርደው እድሜው ካለው ነው፡፡ ብዙዎች በአፍና በጉሮሮ ድንበር ላይ በተፈጠረ ፍጥጫ በአይን ተሰናብተውን መቃብር ወርደዋል፡፡ አደራ! የምለውን ከምግብ አንፃር ብቻ እንዳታዩብኝ፡፡ ምክንያቱም ወሬም ያንቃል፡፡ በዚህ የተጎዱ ብዙ ናቸው፡፡ ጌታ ከዚህ ውርደት ይጠብቃችሁ፡፡
         አሁን ምን እያሰብኩ መሰላችሁ የምጽፈው ጣቶቼ በአድማ እንቢ ቢሉ (ባረገው ለምትሉ ይቅር ይበላችሁ)፣ አንደበት ለመናገር ባይታዘዝ፣ ጆሮም ቢተባበራቸው በየትኛው መንገድ እንገናኝ ነበር? መቼም የአይን ጥቅሻ ወረቀት ላይ አይሰፍር? ግን ከዚህ ሁሉ ሥጋት በላይ እድሜው ባይኖርስ? እንኳን ማውራት መሰማማት፣ እንኳን መተያየት መደባበስ፤ መተሳሰብም ሲዳላ ይሆን ነበር (እየዬ ሲዳላ ነው እንዲሉ)፡፡
         ገንዘብና ቁሳቁስ እንደ ትልቅ በረከት በሚቆጠሩበት ማኅበረሰብ መካከል እድሜን እንደ በረከት ማውራት “ከሌለህ የለህም” በሚለው አሳብ ላይ ጅሐድ እንደማወጅ ነው፡፡ መቼም ይህ ብሒል ምንጩ ስለደረቀ በዚህ አንጣላም፡፡ እስቲ አንድ ጊዜ ወንዶች ብቻ “እድሜያችሁ ስንት ነው?” . . . እሺ ጥግ ላይ ያለኸው . . . “ሴቶችን ለምን አትጠይቅም?”፡፡ እሺ እህቶችስ “እድሜያችሁ ስንት ነው?” . . . እሺ መሐል ያለሽው . . . “የእኛ እድሜና ደመወዝ አይጠየቅም”፡፡ የተቀበልነውን መካድ ሰጪውን አያሳስተውም፡፡ የሆነልንን አለመመስከራችን አድራጊውን ከክብር አያሳንሰውም፡፡ ብዙ ከተቀበለ ግን ብዙ ይጠበቅበታልና ስለ እድሜያችሁ ጌታን አክብሩት፡፡
         እየተማርን፣ እየለበስን፣ እየሠራን፣ እየበላን፣ እየወጣን እየገባን፣ በጎ ብቻ ሳይሆን ክፉም እያቀድን ያልከፈልንበት ትልቅ ሀብት እድሜ ነው፡፡ ትላንት አጥታችሁ ዛሬ ያገኛችሁ፣ ትላንት አግኝታችሁ ዛሬ ያጣችሁ፤ ትላንት ተወዳችሁ ዛሬ የተተዋችሁ፣ ትላንት ተጠልታችሁ ዛሬ የተፈቀራችሁ፣ ትላንት ተገፍታችሁ ዛሬ የተከበራችሁ፣ ትላንት ታቅፋችሁ ዛሬ የተዋረዳችሁ እድሜ ባይኖራችሁ ይህንን ፈረቃ እንዴት ታዩት ነበር? እንኳንም ኖረን ከፋን፣ እንኳንም ኖረን ተጠላን፣ እንኳንም ኖረን አጣን፣ እንኳንም ኖረን ታማን፣ እንኳንም ኖረን ተንገዳገድን፤ እንኳንም ኖራችሁ ተሰደዳችሁ፣ እንኳንም ኖራችሁ አለቀሳችሁ፣ እንኳንም ኖራችሁ ሁሉ ሆነ፡፡ “. . . . ሞቴን እመርጣለሁ” ለማን ብላችሁ? እድሜ ውድ ነው! እስኪንጠፈጠፍ ትጉ፣ እስኪሟጠጥ በርቱ፡፡ ታዲያ አደራ ሰጪውን እያመሰገናችሁ!
         አንድ ሰው ሞቶ ቀብር ሄደን መቃብሩ ሥፋራ ስንደርስ አንድ ሰው አለፍ ብሎ ቆሞ ሲቃ እየተናነቀው፣ ጎንበስ ቀና እያለ፣ እንደ መቀነት እጁን ወገቡ ላይ ጠምጥሞ ያለቅሳል፡፡ እኔም ምናልባት በሰው ሀዘን ላይ የራሱን እያዘነ ይሆን በማለት የጆሮዬን ኃይል ጨመርኩ፡፡ ብዙ ጊዜ ሀዘን ላይ ምን ይገርመኛል መሰላችሁ አባታችሁ ሞቶ ለእናታቻው የሚያለቅሱ፣ እህታችሁ ሞታ ለወንድማቸው የሚያነቡ ሰዎች (እነዚህ ሁሉ የሌሏቸውስ? ለምትሉኝ ለቅም አያታቸው)፡፡ ታዲያ እንዲህ ያሉ ሰዎች ሀዘን ቤቱን የለቅሶ ቢፌ (እንደ ምግቡ ያለ) ያስመስሉታል፡፡ አንድ ሞቶባችሁ ምን አልባት ለማረጋገጥ ቀሪዎቹን መቁጠር ይጠበቅባችኋል፡፡ ወደ ወጣቱ ስንመለስ አብዝቶ እያለቀሰ አንድ ነገር ይላል፡ -“ምን አለ ጥቂት ብትታገሽኝ፣ ምን አለ ኖረሽ በተበሳጨሁ፣ ምን አለ ቆመሽ ሳስታምምሽ በኖርኩ . . . .” ወጣቱ ከነባልንጀሮቼ አስለቀሰን፡፡ ለካ የወዳጅ ጭቅጭቁም ይናፍቃል፣ ለካ የአፍቃሪ ቁጣውም ያሳርፋል፣ ለካ የባልንጀራ ተግሳጹም አምሮት ነው . . . . በእርግጥም ያ ቀን ብዙ አስተማረን፡፡
1. እድሜ ዕድል ነው፡-  እያንዳንዱ ቀን ወደ ግባችን፣ ወደ ስኬታችን፣ ወደ መሻታችን እንደርስበት ዘንድ ትልቅ ስጦታ ነው፡፡ የስጦታው ሕልውና ደግሞ በሰጭው እግዚአብሔር እጅ ላይ ነው፡፡ የእኛ ድርሻ በተሰጠን እድሜ በአግባቡ መጠቀም ነው፡፡ ሞትን የሚፈራ በእድሜው ያልተጠቀመ ብቻ ነው፡፡ እድሉን ያላባከነ ሞትን በደስታ ይጋፈጣል፡፡ ሰዎች እድል እንዲሰጡን ብዙ ጊዜ ደክመናል፡፡ ብዙዎች ከስህተታቸው ለመማር፣ የበደሉትን ለመካስ እድሉን ሳያገኙ በምኞት አልፈዋል፡፡ እግዚአብሔር እንዴት ያለ ነገር እንዳደረገልን ልብ በሉ! በእድሜ ባርኮናል፡፡ ስሙ ብሩክ ይሁን፡፡
2. ኃላፊነት ነው፡- ኃላፊነትን ከቁሳቁስ ጋር ያያዙ እድሜያቸውን ከስረው የማይከተላቸውን ሰብስበው ያልፋሉ፡፡ በእድሜአቸው አመሻሽ ላይ ጸጸት እንደ እግር እሳት ያንገበግባቸዋል፡፡ በማይመልሱት ትላንት ይቆዝማሉ፡፡ የማይለውጡትን ያመነዥጋሉ፡፡ ዛሬ በዋዛ ላለፋቸው ነገ ኪሳራ ነው! ጌታ ለተፈጠርንለት ነገር ኖረን እንድናልፍ ይርዳን፡፡  
3. ሀብት ነው፡- በዓለም ላይ ትልቁ የሀብት ስፍራ መቃብር ነው ሲባል ሰምቻለሁ፡፡ ሰዎች እውቀታቸውን፣ ልምዳቸውን፣ ፍቅራቸውን፣ መፍትሔያቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ቃላቸውንና ተግባራቸውን ሁሉንም ይዘው ከአፈር ጋር ኑሮ ይመሰርታሉ፡፡ ውጤቱ ሞት ቢሆንም ምክንያቱ ግን የእድሜ ማብቃት ነው፡፡ እድሜ ሲያበቃ ምክር የለውም፡፡ ጅምሩ እንደተጀመረ፣ ዝርክርኩ እንደተዝረከረከ፣ የጎደለው እንደጎደለ ብቻ ሁሉም ባለበት ነው፡፡ እድሜ ሀብት ነውና የሥጋቸውን እየሰጡ በነፍሳችሁ ለመጫወት ከሚከጅሉ ተጠበቁ፡፡ ኢየሩሳሌም ውስጥ የአይሁድ ሰንበት ከመግባቱ ጥቂት ደቂቃዎች በፊት ረቢው (መምህሩ) በከተማውና በየገበያው እየዞረ መለከት ከነፋ ገዥ ለሰጠው ብር መልስ እንኳ ሳይቀበል እየሮጠ ይሄዳል፡፡ ሻጭም እየሸጠ መለከት ከተነፋ ዕቃውን አይቀበልም፡፡ ተወዳጆች ሆይ እድሜያችሁን ዘርዝሩት!  
ከልቤ ምስጋና፡-
           አባት ሆይ እንኳንም አሰብከን፣ እንኳንም ፈጠርከን፣ እንኳንም በሰው መሐል ሰው ሆነን ተገኘን፡፡ ስምህ ይባረክ! ይህንን ቢጤያችን ሰው ሥልጣን ቢኖረው ኖሮ እንደማያደርገው እናውቃለን፡፡ ወላጅ እንኳ ልጁን የሚወልደው ነገን ስለማያውቅ ነው፡፡ አንተ ግን የዛሬ ማንነታችንን ቀድመህ እያወከው ፈጥረኸናል፡፡ የሥጋ ወላጆች በባለገ ልጃቸው ተጸጽተው በማኅፀን ሳለህ በሟሟህ ብለው ይቆጫሉ፡፡ አንተ ግን የመንፈስ አባት (አበ ነፍስ) ሁሉን ችለህ ሁሉን ተሸክመህ አለህ፡፡ ጌታ ሆይ መኖራችን በሰዎች አለመቻል ነው፡፡ ዛሬ ቢችሉ የሚጠሉን፣ ዛሬ ቢችሉ ኖሮ የሚያጠፉን፣ ዛሬ ቢችሉ ታሪካችንን የሚያበላሹ፣ ዛሬ ቢችሉ ኖሮ ካንተ የሚለዩን አድፋጮች ብዙ ናቸው፡፡ አንተ ግን መቻልህን ለማዳን አድርገኸዋል፡፡ ሰውን ወዳጅ ሆይ ጸጋህ አቁሞናልና ምሕረትህ እድሜ ሰጥቶናልና ስምህ ይቀደስ፡፡ 

Tuesday, December 25, 2012

ሥራህን ሥራ!




                                         ማክሰኞ ታህሳስ 16/2005 የምሕረት ዓመት

           ጌታ ለእያንዳንዱ ሰው ሥራ ሰጥቶታል ያንን መሥራት የእርሱ ፈንታ ነው፡፡ ቢቻለው እሱን ማገድ የዲያቢሎስ ሥራ ነው፡፡ በእርግጥ ሥራውን እግዚአብሔር እንደሰጠህ ያህል ሰይጣን ሊያግድህ ይሞክራል ሌላ ነገር በበለጠ ደስ የሚያሰኝ ሊያቀርብልህ ይጥራል፡፡ በዓለማዊ ተስፋዎች ያባብልሃል የሃሜት ጎርፍ ያስወርድብሃል በሐሰተኛ ክስ ያሰቃይሃል ለክብርህ እንድትከላከል ያደርግሃል ደራሲያን እንዲጠይቁህ እጅግ ስመ ጥር ሰዎች በክፉ እንዲናገሩህ ይጠቀምባቸዋል፡፡
           ጲላጦስ፣ ሄሮድስ፣ አናንያ፣ ቀያፋ በአንተ ላይ ያድማሉ ይሁዳም በአጠገብህ ቆሞ በሰላሳ ብር ሊሸጥህ ይከጅላል፡፡ አንተም “ይኸ ሁሉ የመጣብኝ ለምንድን ነው?” በማለት ይደንቅሃል ይኸ ሁሉ የመጣብህ ሰይጣን በዘዴ ከሥራህ ሊስብህና እግዚአብሔርን ከመታዘዝ ሊያሰናክልህ መሆኑን ልትገነዘብ አትችልምን?
           ሥራህን ሥራ አንበሳው ቢያጓራ ፍንክች አትበል፣ የሰይጣንን ውሾች ለመውገር አትቁም፣ ጥንቸሎቹንም  በማባረር ጊዜህን አታጥፋ፣ ሥራህን ሥራ ዋሾቹ ይዋሹ ጠበኞቹ ይጣሉ ማኅበረኞቹ ይወስኑ፣ ደራሲዎቹ ይድረሱ፣ ሰይጣንም የፈለገውን ያድርግ አንተ ግን ምንም ነገር እግዚአብሔር የሰጠህን ሥራ ከመፈፀም እንዳያግድህ ተጠንቀቅ፡፡
           ገንዘብ እንድታተርፍ አልተላክም፣ እንድትበለፅግም አላዘዘህም፣ ሰይጣንና አገልጋዮቹ የሚነዙትን የሐሰት ወሬ እንድታስተባብል አልተጠየክም እነዚህን ሁሉ ነገሮች ብታደርግ ሌላ ሥራ ልትሠራ አትችልም፤ ይህም ብቻ ሳይሆን ለራስህ እንጂ ለጌታ አልሠራህም፡፡
           ሥራህን ሥራ ዓላማህ እንደ ኮከብ የፀና ይሁን፣ ተወው ዓለም እንደፈለገው ይነታረክ ይጨቃጨቅም፡፡ ጥቃት ይደርስብህ፣ ትበደል፣ ትሰደብ፣ ትታማ፣ ትቆስል፣ ትናቅ ይሆናል፡፡ ኃይለኛ ያጎሳቅልህ፣ ወዳጆችህ ይተዉህ፣ ሰዎች ይንቁህ ይሆናል፡፡ አንተ ግን የፀና ውሳኔ በማያወላውል ቅናት በመጨረሻ ላደርገው የሰጠኸኝን ሥራ ፈፀምኩ ለማለት እስክትችል ድረስ የሕይወትህን ዓላማና የተፈጠርክበትን ግብ ተከተል፡፡

Tuesday, December 11, 2012

ሰው አያክፋችሁ (ካለፈው የቀጠለ)



                                               
                                            ማክሰኞ ታህሳስ 2/2005 የምሕረት ዓመት

           ባለፈው ክፍል የአንዳችን እንቅስቃሴ በሌላው ሕይወት ላይ በበጎም ሆነ በክፉ ያለውን ከፍ ያለ ተጽእኖ ለመዳሰስ ሞክረናል፡፡ ሁላችንም ብንሆን በሰው ላይ የምንፈርድበት ብቻ ሳይሆን በእኛም ውስጥ የሚፈረድበት ኑሮ አለን፡፡ ብዙዎች ለራሳቸው እንኳ ደግመው ሊያስቡት ከሚያንገሸግሻቸው ነገር ጋር ይኖራሉ፡፡ እንዲህ ካለው ጠባይና አኗኗር ጋር ተፈጥረው ግን አይደለም፡፡ አብዛኛው ሰው ያከፋው ነው፡፡ ጥላቻን የሚያግቱ፣ ተንኮል የሚያስቀጽሉ፣ ዓመጽ የሚያሰለጥኑ እንደ ምድር አሸዋ በዙሪያችን ናቸው፡፡
           ባል ያከፋቸው ሚስቶች ጥሩ እናት መሆን ሲያቅታቸው፣ አሳዳጊ ያከፋቸው ልጆች ጥሩ ባልንጀራ መሆን ሲሳናቸው፣ ጓደኛ ያከፋቸው ወጣቶች መልካም አባት መሆን ሲቸገሩ፣ ኅብረተሰቡ ያከፋቸው ሰዎች በቅን መምራት ሲተናነቃቸው አስተውለናል፡፡ ክፉ የምንለው ያከፋነውን ነው፡፡ ርኩስ የምንለው ያረከስነውን ነው፡፡ ጠፋ የምንለው ያባረርነውን ነው፡፡ ከሀዲ የምንለው ያስካድነውን ነው፡፡ ጌታ ሆይ ይቅር በለን!
           የሮም ንጉሥ የነበረውን ኔሮን ቄሳር ክርስቲያኖችን እንደ ጧፍ ለኩሶ እንደ ሻማ በማቅለጥ፤ ከአንበሳና ከነብር ጋር በማታገል ይዝናና የነበረ ክፉ መሪ እንደነበር ታሪክ ያስታውሰናል፡፡ ኔሮን ወደ ሥልጣን የመጣበትን መንገድ ስንመለከት፤ እናቱ አግሪፒና በ12 ዓመቷ የ15 ዓመት ዕድሜ በነበረው በኋላም ንጉሥ በሆነው ወንድሟ ካሊጉላ ትደፈራለች፡፡ በ13 ዓመቷ ትዳር መስርታ የልጇ የኔሮን ጥብቅ ወዳጅ ሆናለች፡፡ አግሪፒን አጎቷ የነበረውን ንጉሥ ክላውዴዎስ (ቀዳማዊ) ከማግባቷ በፊት ሁለተኛ ባሏን በመድኃኒት ገድላለች፡፡ ከዚያም ክላውዴዎስን በመርዝ በመግደል ኔሮ ዙፋኑን ወርሶ ወደ ንግሥና እንዲመጣ አድርጋለች፡፡ ጨካኙን ኔሮን ስናስብ እንዴት ባለ ሁኔታ ውስጥ እንዳደገ ልብ ማለት ትምህርት ያተርፍልናል፡፡
        በዓለማችን ላይ ከተነሡ አያሌ ዓመፀኞች ጀርባ ያለው ነገር በኔሮን ቄሳር ካየነው ብዙም የሸሸ አይደለም፡፡ በወላጅ፣ በጓደኛ፣ በወዳጅ፣ በፍቅረኛ ዓላማቸውን የሳቱ፣ ከሕሊናቸው የተጣሉ፣ የሕይወት ታሪካቸው ጥላሸት የተለቀለቀ፣ ራሳቸውን እየፈሩ የሚኖሩ፣ የማንነት መቃወስ የገጠማቸው ከእነርሱ ስህተት በላይ ሰው አክፍቷቸው ነው፡፡
         በአገራችን የገጠሩ ክፍል ዛሬም ድረስ ሙሉ ለሙሉ ጠርቶአል በማይባልበት ሁኔታ ደም የመቃባት ክፉ ውርስ አለ፡፡ ለዚህ መባባስ እንደ አንድ ምክንያት ተደርጎ የሚቀርበው ደግሞ ወገኑ ሞቶበት ደም ያልመለሰ ወንድ እንደ ነውረኛ መቆጠሩና ሚስት ለማግባት እሺታን መነፈጉ ነው፡፡ እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ ሰው ሸሽቶ ካልሆነ በቀር አብሮ ሆኖ ሕሊናውን መጠቀም አይችልም፡፡ ባይወድም ይከፋል፡፡ አቅም ባይኖረውም ይሸፍታል፡፡ ታዲያ እድሜ ሰጥቷችሁ ከዓመታት በኋላ ብትገናኙ ያ መልካምነት ሞቶ ተቀብሮአል፡፡ ያ ትህትና አፈር ትቢያ ሆኖአል፡፡ ያ ርኅራሄ ላይመለስ እርቆ ሄዶአል፡፡ ለልቡ ተጠግታችሁ “ምነው? ምን ገጠመህ?” ብትሉት ልክ እንደ ሙሾ አውራጅ እየተንሰቀሰቀ “ሰው አከፋኝ” ይላችኋል፡፡ ሰው አያክፋችሁ!
         ሕይወት ቅብብሎሽ ናት፡፡ አንዱ ትውልድ ሲሄድ ያን ተከትሎ ሌላው ይመጣል፡፡ ታዲያ ይህኛው ሲከፋ ለመጪው ውርስ ሆኖ ይቀራል፡፡ ከዚያም ክፉና ደግ ምርጫ ሳይሆን የውርስ ቅብብሎሽ ይሆናል፡፡ በእርግጥም እውነታው እንዲሁ ነው፡፡ ከማይጠፋው ዘር የተወለዱ ሁሉ የማይጠፋ ነገር ሲቀባበሉ ይኖራሉ፡፡ ያለ ምርጫቸው በሰው ምርጫ፣ ያለ ፍላጎታቸው በሰው ፍላጎት፣ ያለ ውዴታቸው በሰው ግዴታ የኑሮ አቅጣጫቸው የተወሰነ ያላለቀ ነገር (unfinished business) አላቸውና ዛሬም ከብርቱ ፈተና ጋር ናቸው፡፡

መፍትሔ

         እኔ ከሞትኩ . . . አይነት ኑሮ ለምድሪቱ ጭንቅ ነው፡፡ የሆነ ቦታ የሚጨክን ሰው ያስፈልጋል፡፡ ከአያት ከቅድመ አያት የመጣ ነገር ሁሉ ለልጅ ልጅ አይተላለፍም፡፡ እኛ የተጫነንን ሌሎች ላይ መጫን የለብንም፡፡ እኛ የመረረን ሌሎችንም እንዲመራቸው ቸልተኛነት ልናሳይም አይገባም፡፡ የከፉብንን በመክፋት፣ የጠሉንን በመጥላት፣ ያንገላቱንንም በማንገላታት ምድሪቱን በጨለማ ልንለውሳት አይገባም፡፡ እናም እንደ ብርሃን ልጆች በመመላለስ ክፉውን እንዋጋ፡፡ ጸጋ ይብዛላችሁ!  

Tuesday, December 4, 2012

ሰው አያክፋችሁ



                                        ማክሰኞ ሕዳር 25/2005 የምሕረት ዓመት

        በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ከመልካምነት ይልቅ ክፋት ዓለምን እንደገዛ እናስተውላለን፡፡ አለመታዘዝ ያመጣውን ውድቀት ተከትሎ የሰው ዝንባሌ “የማልወደውን ክፉን ነገር አደርጋለሁና ዳሩ ግን የምወደውን በጎውን ነገር አላደርገውም” (ሮሜ. 7÷19) ወደሚል ሙግት ገብቶአል፡፡ ከመምረጥ ጀምሮ እስከ ድርጊት ድረስ ሰዎች በብርቱ ይፈተናሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜም ከነ አካቴው ሁሉን እርግፍ አድርጎ የመተው ውሳኔ ላይ ይደርሳሉ፡፡ ማለትም በጎም መጥፎም ያለመሆንና ያለማድረግ! ሰው ግን ከሁለት አንዱን ነው፡፡ ከእነዚህ ራሱን የሚያገልበት ሌላ ሦስተኛ ክልል የለም፡፡ ልክ እንደ አንድ ቀን ሁለት ገጽታ ብርሃንና ጨለማ ነው፡፡ በብርሃን እንመላለሳለን ወይም በጨለማ እንመላለሳለን፡፡ ክርስትና ግን እንደ ብርሃን ልጆች መመላለስ ነው፡፡ ከክፉ መራቅ ሰላማችንን የሚጸናበት ዋስትና ነው (ኢሳ. 48÷22)፡፡  
         በታሪክ ከተነሡ እጅግ ክፉና አምባገነን መሪዎች መካከል አንዱ ሂትለር ነው፡፡ በየዘመናቱ ብዙ አስጨናቂዎችን ሰዎች ርደውና ተንቀጥቅጠው አስተናግደዋል፡፡ ብዙዎች ሞተው፤ አንዳንዶች ደግሞ አጉል ነዋሪ ሆነው በዚያ አረመኔያዊ ሥርዓት ውስጥ አልፈዋል፡፡ አንዳንዴ ባለፈው የአገራችን ሥርዓት ውስጥ ጨካኝ የነበሩና የገዛ ጎረቤታቸውን በቁም የቀበሩ ሰዎች በዚህኛው ሥርዓት ውስጥ ሲሽቆጠቆጡ ስናያቸው የሥርዓቱ ለውጥ ጭካኔያቸውን እንዳዳፈነው እንጂ እንዳጠፋው አይሰማንም፡፡ የዚያ አምባገነናዊነት ግርሻት ያየለበባቸው ደግሞ ለዚህኛው ሥርዓት ተቆርቋሪ መስለው በዚያኛው አመጽ ይገለጣሉ፡፡ እናም ራሳቸውን ያረካሉ፤ ክፋት ያስገብራልና ዘመን ቢቀያየርም ክፉውን አያስረጀውም፡፡ እግዚአብሔር ግን ይለውጣል!
         ለዚህ ጽሑፍ ርዕስ ያደረኩትን ቃል ያገኘሁት ለልቤ እጅግ ቅርብ ከሆነ አባት (ከአንዱ እግዚአብሔር) ምክር መካከል ነው፡፡ ዘመኑ መካሪም ተመካሪም የሰለቸበት ነው፡፡ ከዚህ ይልቅ ሰው ሁሉ ወደ ልቡ አሳብ ተጠምዷል፡፡ ምን አልባት “ደግሞ በዚህ ዘመን ምን በጎ መካሪ አለ?” ልትሉ ትችላላችሁ፡፡ ነገር ግን ሰው አያስተውልም እንጂ እግዚአብሔር በአንድ በሌላም መንገድ ይመክራል፡፡ አንዳንዴ ሳት ብሏቸው እንኳ ጥሩ እንደማይናገሩ ከምናስባቸው ሰዎች ሕይወት ያለባቸው ቃላት ሲወጡ እናስተውላለን፡፡
         እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ ይረግምለት ዘንድ ባላቅ የከፈለበትን የበልዓም አንደበት መርቆበታል (ዘኁ. 22)፡፡ በእርግጥ ተደላድለን ውሸት ከምንናገር እግዚአብሔር ጠምዝዞን ለእውነት ብንመሰክር ይበልጣል፡፡ በየአደባባዩ የሚጠፋውን መብል እያሰቡ፣ ሕሊናቸውን አራቁተው ሆዳቸውን እየሞሉ በዚህ ዓለም ከንቱ መለፍለፍ የተጠመዱ ሁሉ ከበለዓም ስሕተት (ይሁዳ 11) ሊማሩ ያስፈልጋቸዋል፡፡   
        የስነ ልቦና ባለሙያዎች እንደሚያስረዱት ልጆች እያለን ከቤተሰቦቻችና ከማኅበረሰቡ ጋር የነበረን ግንኙነት (Attachment) ወደ ማወቅ ደረጃ ከመጣን በኋላ በቀጣይ ኑሮአችን ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ (በጥሩም በመጥፎም) ያሳድራል፡፡ የአንድ ሰው ክፋት የብቻው ክፋት፣ የአንድ ሰው መልካምነት የብቻው መልካምነት አይደለም የሚል መከራከሪያ የሚቀርበውም ለዚህ ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ የምንመለከተው ወንጀል ተባባሪና አሰልጣኝ ያለው ነው፡፡ በጣም ጨዋ እንደነበሩ የምናውቃቸውን አልባሌ ቦታ ስናገኛቸው አድራሻ ለመለወጥ ያበቃቸው ክፉ ባልንጀርነት እንደሆነ እናያለን፡፡  
        ሰውና ሁኔታ ያከፋው ካልሆነ በስተቀር ማንም ክፉ ሆኖ የተፈጠረ የለም፡፡ ወድጄ መሰለህ እንዲህ ያለ ጠባይ የያዝኩት፣ አመል ያወጣሁት በማለት የሚናገሩ ወገኖች ብዙ ናቸው፡፡ ማንም በጥረት የተበላሸ የለም፡፡ አንዳንዱ እንጀራ በልቶ ለማደር፣ ሌላው ከሰው ተመሳስሎ ለመኖር፣ አንዳንዱ የእጁን ላለማጣት ብቻ ሁሉም ለከፋበት ምክንያት ያቀርባል (ምንም እንኳ ምክንያት ባይታደግም ግን እኮ ከፀሐይ በታች ባለው ኑሮ ምክንያተኝነት ስልጣኔ ነው እንጃ እንግዲህ አንዱን ምረጡ)፡፡    
      በጭካኔውና በአረመኔነቱ ከምናውቀው ሂትለር ጀርባ ያለውን ታሪክ በአጭሩ ለመመልከት ብንሞክር፤ እናቱ ክላራ ከእርሷ በ23 ዓመት እድሜ ለሚበልጣት ለአጎቷ የልጅ ልጅ ሦስተኛ ሚስት የነበረች ስትሆን በትዳር በቆየችባቸው ጊዜያት ሁሉ ባለቤትዋን ትጠራው የነበረው “አጎቴ” እያለች ነበር፡፡ ግንኙነታቸው የተጀመረውም በአጎቷ ቤት በቤት ሠራተኛነት ታገለግል በነበረበት ጊዜ ነው፡፡ ታዲያ ሂትለር ልጅ እያለ እናቱ ክላራ ብቸኛ ጓደኛው ነበረች፡፡
         አስራ ስምንት ዓመት ሲሞላው እናቱ በካንሰር ሞተችበት፡፡ በዚህም ምክንያት ለከፍተኛ የልብ ስብራትና ለበለጠ ብቸኝነት ተጋለጠ፡፡ አንዳንድ የታሪክ ምሁራን እንደሚያስረዱት ሂትለር በሴሜቲኮች በተለይም በአይሁዶች ላይ ጥላቻና የበቀል ስሜት ያደረበት የሚወዳት እናቱ አይሁዳዊ በሆነ ዶክተር የተደረገላት ሕክምና ውጤት አልባ በመሆኑ ነው፡፡ እንግዲህ በግፍና በሰው ሰቆቃ ራሱን ያረካ የነበረው አዶልፍ ሂትለር ወደዚህ የክፋት ጣሪያ የደረሰው በዚህ መንገድ ነው፡፡ እናንተስ እንዴት ታዩታላችሁ?
                መልካም የምንሆነው ለራሳችን ብቻ ብለን አይደለም፡፡ ሌሎችንም ከእሳት ነጥቆ ለማውጣት እውነተኛ መንገድ ስለሆነ ጭምር ነው፡፡ በጎ ነገር ዘር ነው፡፡ ዘር ደግሞ ከተዘራ በኋላ እንደ ዘራነው ልክ አይሆንም፡፡ ስለዚህ በጎነታችንም ሆነ ክፋታችን መሐን ሊሆን አይችልም፡፡ በጎ የዘራችሁ ደስ ይበላችሁ!
                                                          - ይቀጥላል -

Tuesday, November 6, 2012

የማታውቂው ባዶ



                                         ማክሰኞ ጥቅምት 27/2005 የምሕረት ዓመት


          ባል ከሚስቱ የሚደብቃት ምንም ነገር የለም፡፡ አሳቡን የምታስብ፣ የልብ ምቱን የምትመታ፣ ንግግሩን የምታወራ እስክትመስል የገንዘብ ብቻ ሳይሆን የኑሮ ወጪና ገቢውንም ታውቃለች፡፡ ነገር ግን ሚስትን ጨምሮ ማንም የማያየው ቁልፉም በእርሱ እጅ ብቻ የሆነ አንድ መሳቢያ አለው፡፡ ሚስት እንዲያሳያት የጠየቀችው ቢሆንም እምቢታው ግን አላስቻላትም፡፡ ብዙ ጊዜ ክልከላውን ብታከብርለትም አንዳንዴ ግን አክርራ ትጠይቀዋለች፡፡ ታዲያ አንድ ቀን የመሳቢያውን ቁልፍ ረስቶ ከቤት ይወጣል፡፡ ሚስትም የዘወትር ትጋቷ ምላሽ ያገኝና ከኮቱ ኪስ ቁልፉን ወስዳ መሳቢያውን ታየዋለች፡፡
          ባል ከሥራ መልስ ወደ ቤት ሲመጣ ሚስት ፊቷ ፍም እስኪመስል ታለቅሳለች፡፡ የተደናገጠው ባል ምክንያቷ ምን እንደሆነ ቢጠይቃት “ለባዶ መሳቢያ ይህንን ያህል ጊዜ ያስለመንከኝ ለምንድነው?” የሚል መጠይቃዊ ምላሽ ያገኛል፡፡ ባልም ትህትና በተሞላበት አነጋገር “የማታውቂው ባዶ እንኳ ይኑረኝ ብዬ ነው” አላት፡፡    
         ድብቅነት አንዱ የኑሮ መስፈርት እየሆነ መጥቶአል፡፡ ለዚህም እንደ ምክንያት የሚቀመጡት ማሳመኛዎች ብዙ ናቸው፡፡ አብዛኞቹ ድብቅነት አያስፈልግም! የሚል አቋም ሲኖራቸው እንደ መከራከሪያ የሚያቀርቡትም አሳብ ደግሞ “ድብቅነት ሕይወትን ከባድና ውስብስብ ያደርጋታል” የሚል ይሰኛል፡፡ አንዳንዶች ደግሞ እንደ አስፈላጊነቱ ድብቅነት መኖር አለበት ባይ ናቸው፡፡ እንደ መከራከሪያነት ከሚያቀርቡት ምሳሌ መካከል ሰይጣንን ያጣቅሳሉ! ምክንያቱም ውድቀቱ የእግዚአብሔርን መደበቅ ተከትሎ የመጣ ነው፡፡ ስለዚህ ቢያንስ ሰውን ለመፈተንና በጎውን አቅርቦ ክፉውን ለማራቅ የምንሸሽገው ባዶ እንኳ ያስፈልገናል የሚል ነው፡፡ ሌሎች ደግሞ “ድብቅነት ምን ጊዜም አስፈላጊ ነው” የሚል አመለካከት ያላቸው ናቸው፡፡ እነዚህ “በተኩላ ዓለም በግ መሆን ለእራስ በገዛ እጅ መቃብር መቆፈር ነው” የሚሉ አሉታውያን (ጠርጥር) ናቸው፡፡ እናንተስ?   
          እውቀት በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ቋሚ ጥማት ነው፡፡ የሚሰወረን ነገር ባይኖር የሁላችንም መሻት ነው፡፡ ስለ ሰው ማወቅ ብቻ ሳይሆን የሰውንም ማወቅ እንፈልጋለን፡፡ ድብቆች ብንሆንም ከሰው የተገላለጠ ነገር እንጠብቃለን፡፡ ነገር ግን ተግባራዊ በሆነ መንገድ የአብሮነት ኑሮአችን የተያያዘበት ሰንሰለት ብዙ መሰብሰብ ጥቂት መገለጥ ነው፡፡ በአካባቢያችሁ ያሉ ሰዎች “ምነው ሰሞኑን በዛህ/ሽ?” ብለዋችሁ አያውቁም? ይህ በሌላ መንገድ “አይኔ ሰልችቶሃል” ማለት ነው፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን እንዲህ ስላለው ሁኔታ “እንዳይሰለችህ እንዳይጠላህም እግርህን ወደ ባልንጀራህ ቤት አታዘውትር” (ምሳ. 25÷17) በማለት ምክሩን ይለግሰናል፡፡
          በሰው ታሪክ ውስጥ አንዱ ለሌላው ግልጽ አለመሆንና ነገሮችን መሸሸግ ውድቀትን ተከትሎ ወዲያው በዔደን ገነት ውስጥ የተስተዋለ ሐቅ ነው፡፡ የአዳምና ሔዋን መተፋፈር አንዳቸው ለሌላቸው እንዳይገለጡ አደረጋቸው፡፡ ደግሞም እግዚአብሔርን ተጠያቂ ወደ ማድረግ የመራቸውንም ምክንያት ስንመረምረው የጋራ መወያየት የታየበት ሳይሆን የየግል ልብ ወለድ እንደሆነ እናስተውላለን(ዘፍ. 3)፡፡ አዳም ለመብላት የሚስቱን ቃል ቢሰማም ለመፍትሔ ግን አልሰማትም፡፡ ሔዋንም ለማብላት ቃላትን ለአዳም ብትናገርም ለመፍትሔ ግን አላናገረችውም፡፡ ይህንን ተከትሎ ነው እንግዲህ ቃየን አቤልን ተደብቆ የገደለው፡፡ እንዲህ ያለው የድብቅነት ዝንባሌ እኛም ጋር የደረሰው በቅብብሎሽ ነው፡፡   
          ሰው የቱንም ያህል ድብቅ ቢሆን ከሰው የሚያስቀረው እንጂ ከእግዚአብሔር የሚሰወረው ነገር የለም፡፡ አይኖቹ እንደ እሳት ነበልባል በሆኑት ጌታ ፊት ሁሉ የተራቆተ ነው፡፡ እግዚአብሔር የማያውቀው ድርጊት ቀርቶ የማያውቀው ባዶ እንኳ የለንም፡፡ ውድ የቤተ ፍቅር ብሎግ ተከታታዮች በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ በተረዳችሁበት መንገድ ያላችሁን አሳብ እንድትገልፁና ለውይይት እንድትሳተፉ በትህትና እንጋብዛለን፡፡