ማክሰኞ የካቲት 25 ቀን
2006 የምሕረት ዓመት
ጌታ ሆይ÷ አንተ ታላቅ ነህ÷ ውዳሴም ያለ ገደብ ይገባሃል፤ ኃይልህ ታላቅ÷
ጥበብህም የማይለካ ነው፡፡ የፍጥረትህ ደካማ ክፍል የሆነው የሰው ልጅ÷ ሟችነቱንም ከራሱ ጋር የተሸከመው የሰው ልጅ÷ የኃጢአቱን
ምስክርነት÷ የአንተንም የትዕቢተኞችን መቃወም ማስረጃ የተሸከመው የሰው ልጅ÷ አንተን ነው ማወደስ የሚፈልገው፡፡ እንግዲህ ይህ
የፍጥረታት ደካማ ክፍል የሆነው የሰው ልጅ ሊያወድስህ ይፈልጋል፡፡
‹‹ከጌታ ከራሱ በስተቀር ማን ነው ሌላ ጌታ፤ ወይስ ከእግዚአብሔር ውጭ እግዚአብሔርስ ማን ነው?›› እጅግ ታላቅ፣ እጅጉን
የላቀ፣ እጅግ ኃያል፣ እጅግ ሁሉን ቻይ፣ እጅጉን መሐሪ፣ እጅግ ጻድቅ፣ እጅግ የተሰወርክ እጅግ የቀረብክ፣ እጅግ ውብና እጅግ ብርቱ፣
ጽኑና የማትጨበጥ፣ የማትለወጥና ሁሉን የምትለውጥ፣ አዲስ ሆነህ የማታውቅ፣ የማታረጅ፣ ሁሉን የምታድስ፣ እነርሱ ሳያውቁት ትዕቢተኞችን
የምታስረጅ፣ ምንጊዜም የምትሠራ፣ ምንጊዜም የምታርፍ፣ የምትሰበስብ፣ ምንም የማያሻህ፣ እየደገፍክ የምትይዝ፣ የምትሞላ፣ የምትከላከልም፣
የምትፈጥር፣ የምትመግብ፣ የምታጠናቅቅ፣ የምትፈልግ፣ ምንም ሳይጎድልህ፡፡
አንተ ታፈቅራለህ ነገር ግን ያለ ስሜት ነው፤ ቅናትህ መሥጋት የለበትም፡፡ ጸጸትህ ቁጭት አያውቅም፡፡ ቁጣህም የተረጋጋ
ነው፡፡ ሥራዎችህን እንጂ እቅድህን አትቀይርም፤ ፈጽሞ ሳይጠፋብህ፤ ያገኘኸውን ትጨብጣለህ፡፡ ምንም ባያሻህም በማግኘትህ ትደሰታለህ፡፡
ስስትን ባታውቅም፤ ብድርን ከነወለዱ ትፈልጋለህ፡፡ ባለእዳ እስክትሆን አብዝተው የሚከፍሉህ፤ ለመሆኑ ያንተ ቢኖረው ካንተ ያልሆነ
ሊኖረው የሚችል ማን ነው? ለማንም ባለ እዳ ሳትሆን እዳህን ትከፍላለህ ስትመልስም ምንም አይጎድልብህም፡፡ ኦ አምላኬ ሕይወቴ ቅዱሱ
ትፍስሕቴ ሆይ ምን እያልን ይሆን? ስለ አንተ ሲናገር ሰው ምን ማለት ይችላል? ስለ አንተ አብዝተው እንኳን የሚናገሩ እንደ ዲዳ
ናቸው - ስለ አንተ የማይናገሩ ወዮላቸው!





