አርብ መጋቢት 30 ቀን 2008 የምሕረት ዓመት
(መልእክት ወደ
ፊልሞና)
‹‹እምጳውሎስ ሙቁሐ ለኢየሱስ ክርስቶስ፡ (ኤፌ. 3፡1)!››
‹‹አእሚርየ ከመ ትወስክ እንዘ አዘዝኩከ፤ ካዘዝሁህም
አብልጠህ እንድትሠራ ዐውቄ ጻፍኩልህ፡፡›› /ቁ. 21/
ፍቅርን
ለሚመለከቱ ቅን ልቦች የፊልሞና መልእክት መዋደድን ሊሞላን የሚችል ቅዱስ አሳብ የያዘ መጽሐፍ ነው፡፡ ግንኙነቶቻችንን የምንጠብቅበት
ሰማያዊ መመሪያና መለኮታዊ አካሄድን በጥልቀት እንረዳበታለን፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ በፊልሞና እና በአናሲሞስ መካከል የተፈጠረውን
መለያየት አስመልክቶ ‹‹ልቡን የሚያሳርፍ›› መፍትሔ እንዲመጣ በፍቅር
ዝቅ ማለቱን እንመለከታለን፡፡ በአገራችን የሰዎችን አለመግባባት ለመፍታት የሚያስተራርቁ ሰዎች ድንጋይ ጭምር ተሸክመው በመካከል
እንደሚቆሙ እናውቃለን፡፡
በዚህ አጭር መልእክት ውስጥ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ስም አሥር
ጊዜ ተጠቅሷል፡፡ ኢዮብ ‹‹ይኸው ስትሰድቡኝ አሥር ጊዜ ነው፤ ስታሻክሩኝም አላፈራችሁም›› (ኢዮ. 19፡3) እንዳለ፤ እንዲሁም
በልማድ ‹‹አሥር ጊዜ አትነዝንዘኝ›› እንደሚባል (ይህንን ለመጀመሪያ ጊዜ ያለው የመጽሐፉ ኢዮብ ይመስለኛል)፤ ሐዋርያው ለቆሮንቆስ
ምእመናን ‹‹ነገር ግን ወንድሞች ሆይ፤ ሁላችሁ አንድ ንግግር እንድትናገሩ በአንድ ልብና በአንድ አሳብም የተባበራችሁ እንድትሆኑ
እንጂ መለያየት በመካከላችሁ እንዳይሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ›› (1 ቆሮ. 1፡10) ያለውን እዚህም
ተግባራዊ እንዳደረገ ልናስብ እንችላለን፡፡



