ሐሙስ ነሐሴ 5 ቀን 2008 የምሕረት ዓመት
‹‹አንድ ትንሽ ልጅ በእጁ የሠራት ጀልባ ከዕለታት በአንዱ ቀን ተሰረቀችበት፡፡ እንዲህ ከሆነ ከብዙ ቀናት በኋላ፤ ዕቃ እያስያዘ ገንዘብ በሚያበድር ሰው ሱቅ በኩል ሲያልፍ ጀልባውን አያት፡፡ በደስታ ወደ ሰውየው ሮጦ ‹‹ያቺ የእኔ ትንሽ ጀልባ ናት›› አለው፡፡ ዕቃ አስይዞ አበዳሪውም ‹‹የለም፤ እኔ ስለገዛኋት የእኔ ናት›› ብሎ መለሰለት፡፡ ‹‹አዎ፤›› አለ ትንሹ ልጅ፤ ‹‹ግን የእጄ ሥራ ስለሆነች የእኔ ናት›› በማለት አስረዳው፡፡ ‹‹እንግዲያውስ›› አለ ዕቃ አስይዞ አበዳሪው፤ ‹‹ሁለት ዲናር ከሰጠኸኝ ልትወስዳት ትችላለህ›› አለው፤ ጀልባውን ዳግም የራሱ ለማድረግ በብርቱ የፈለገው ልጅ የተጠየቀውን ለመክፈል የጉልበት ሥራዎችን በመሥራት ገንዘቡን አገኘ፡፡
ከዚያም ወደ ሱቁ በመሔድ ገንዘቡን ከፍሎ ጀልባውን አስመለሰ፡፡ በመጨረሻም ጀልባውን በእጆቹ አቅፎ እየሳመ ‹‹አንቺ ውድ ትንሽ ጀልባ፤ እወድሻለሁ፡፡ አንቺ ሁለቴ የእኔ ነሽ፡፡ በፊት ሠራሁሽ፤ አሁን ደግሞ ገዛሁሽ›› አለ፡፡ /William Moses Tidwell, Pointed
Illustrations (Kansas City, Mo.; Beacon Hill Press, 1951) P. 97/.
ከላይ ያነበብነው ታሪክ የወጣ ሲመለስ፤ የጠፋ ሲገኝ፤ የወደቀ ሲነሣ . . ያለውን ደስታና እርካታ ቆም ብለን እንድናስብ ይጋብዘናል፡፡ ሁሉም ነገር ላይ ‹‹የማይዘልቅ›› የሚል በተለጠፈባት የአሁኗ ዓለም የኑሮ ሥርዓት ውስጥ ባትጠፉ እንኳ የጠፋ ፈልጋችሁ እንደምታውቁ ግልጥ ነው፡፡ የተወደደው ባለ መድኃኒቱ ሉቃስ (ቆላ. 4፡14) በጻፈው የወንጌል ክፍል፤ ከዘኬዎስ መጎብኘት ጋር በተያያዘ ‹‹ኢየሱስም፡- . . የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቶአልና›› /ሉቃ. 19፡9/ ተብሎ ተጽፎ እናነባለን፡፡ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ፈላጊም አዳኝም›› ነው፡፡






