Saturday, December 17, 2011

ሕይወት ሲካፈል



የምትጋጠመው   -     ግጥሚያ
የምትቀበለው     -     ስጦታ
የምትጋራው      -     ጀብዱ
የምትጋፈጠው   -      መከራ
የምትወጣው     -     ሐዘን
የምትከውነው   -     ግዴታ
የምትጠቀምበት  -     አጋጣሚ
        የምትፈጽማት   -     ጉዞ
        የምትጠብቃት   -     ቃል ኪዳን
        የምታሟላት      -     ጉድለት
የምትንከባከባት   -    ፍቅር
        የምታሳካት       -     ግብ
        የምታወድሳት     -     ውበት
        የምትፈታት       -     እንቆቅልሽ ናት!

ሞት የሚሆነው ለሞቱ ሰዎች ብቻ ነውና በሕይወት ያለ ሰው ሞትን ያስንቃል፡፡  ከሞት በኋላ ሊሆን ለሚችለው ነገር ከሚኖርህ አሳብ በበለጠ ከሞት በፊት ስለሚሆኑት ነገሮችና መሆን ስለሚገባህ አስብ ምክንያቱም ያ ውጤት ነውና፡፡ ከሞት በፊትም ቀድመህ አትሙት፡፡ ኑርልን!
 ሻማ ብርሃኑን ካልሰጠ በቀር ሊያበራ አይችልም፡፡ የሚታየው በራሱ ብርሃን ነውና፡፡ ለሌሎች ብርሃንን በመስጠት ያበራል፡፡ ታዲያ ለምን ብርሃንህ እንዲያበራ አትፈቅድለትም፡፡ ራስህንና የራስህን ለሌሎች አካፍል በቃ! አካፍል አሁንም  አካፍል ደግሞ አሁንም አካፍል . . . ምን እንደሚሆን ታውቃለህ? በረከት ጓዙን ጠቅሎ በአንተ ውስጥ ይከትማል፡፡ አትኩሮት፣ ፍቅርና ደሰታን ስጥ፡፡ በየዕለቱ ስጥ፡፡ ለመስጠት አስቸጋሪ ቢሆንም እንኳን አንተ ግን ስጥ፡፡ ምንም ምላሽ ሳትጠብቅ ስጥ፡፡ መቀበል ብትፈልግ እንኳን ስጥ፡፡ ትልልቅ ዋጋ የሌላቸውን ነገሮች እንኳን ቢሆን ስጥ፡፡ መስጠትህንና ማካፈልህንም አታቋርጥ፡፡

Thursday, December 15, 2011

ለጭንቀት


ለጭንቀት  -  በጣም ተብረቅራቂ
ለንዴት  -  በጣም ለጋስ
ለፍርሃት  -  በጣም ጠንካራ
የመከራን መኖር አምኖ ለመቀበል   -    በጣም ደስተኛ ሁን፡፡
እውነተኛ ደስታ ከነፍስ፣ ከመንፈስና ከሥጋ ጤንነት ይቀዳል!
በተጨነቅህ ጊዜ፡ -
1.          ፈጽሞ ለብቻህ አትጨነቅ- ችግሮችህን ለሚያወያይህ ወዳጅ ንገር፡፡ ይህም መንገድ የተጨነቅህበትን ምክንያት በትክክል ለማየት ይረዳሃል፡፡ ከሌሎች መጽናናትንም እንድታገኝ ያደርግሃል፡፡
2.          እውነታውን አግኝ- የጭንቀትህን መሠረት ፈልግ፡፡ ችግርህን ምክንያት ከሌለው ውጥረትህ እንድትለየው ይረዳሃልና፤ የሚያስጨንቁህም ነገሮች በወረቀት ላይ ለማስፈር ሞክር፡፡
3.          ተግባራዊ ሁን- ጊዜህን ወይም ደግሞ በመጨነቅ የምታጣውን አቅም አታባክን፡፡ ችግሩ በሚጠይቀው መልኩ ለመፍታት ሞክር፡፡ ቸል ብትል ግን ለወደፊቱ የከፋ ውጥረት ውስጥ ሊከትህ ይችላል፡፡
4.          ለጤናህ ከፍተኛ ዋጋ ስጥ- ይኽውም ከራስህ፣ ከእግዚአብሔርና ከአካባቢህ ጋር የሚኖርህ ትክክለኛ ግንኙነት ነው፡፡
5.          ዛሬን ብቻ ኑር- ወደፊት ስለሚሆነው ወይም ደግሞ ባለፈው ስለሆነው ነገር ፈጽሞ አትጨነቅ፡፡ ይልቁንም ደግሞ አሁን እየሆነ ባለው ነገር ላይ አትጨነቅ፡፡
6.          አዎንታዊ አስተሳሰብ ይኑርህ- ኑሮ አእምሮ ውስጥ ነው፡፡ ሁልጊዜም ቢሆን በአሉታዊ አስተሳሰቦች ከመተከዝ ይልቅ በነገሮች መልካም ጎን ላይ አተኩር፡፡ የደስታም ለዛ ይኑርህ፡፡ በትንንሽ ነገሮች መደሰትም ልመድ፡፡
7.          ጥቂት ዕረፍ- ችግሮችህን የምታጤንበት፣ መፍትሔ ላይ የምትደርሰበት፣ ሁሉን ከሚያውቀው ጌታ ጋር የምትነጋገርበት፣ ጭንቀትህንም የምትሰናበትበት ቢያንስ ግማሽ ሰዓት በእረፍት የማሳለፊያ ጊዜ ይኑርህ፡፡ እየሮጥክ የገጠመህን እየሮጥክ አትፈታውምና፡፡
8.          በሥራ ቆይ- በመሥራት የምናሳልፈው ጊዜ ከጭንቀት ለመዳን ሁነኛ መፍትሔ ነው፡፡ ራስህን በሥራ ላይ ማቆየትህ በአእምሮህ ውስጥ ያሉት አሉታዊ አስተሳሰቦች እንዲጠፋ ያደርጋቸዋል፡፡ እየተማርክ ከሆነም በትምህርትህ ይበልጥ ቀጥል፡፡ ስንፍና የሰይጣን ትልቁ ዙፋን ነውና፡፡
9.          ስጦታዎችህን አስብ- የበታች እንደሆንክ እየተሰማህ በተጨነክበት ጊዜ ሁሉ የተቸሩህን ስጦታዎች አስብ፡፡ የዚያን ጊዜ የተሻለ ስሜት ይሰማሃል፡፡
በመጨረሻም የሁሉ መጀመሪያ፣ በሂደቱም ላይ ጌታ የሆነውን እግዚአብሔር አስብ፡- በሚያስፈልግህ ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ለእርሱ አሳውቅ፡፡ እርሱ ስለ አንተ ያስባልና በአንዳች አትጨነቅ (ፊልጵ. 4፡6) ።
ከጭንቀትህ የተነሣ በምሽት ለመተኛት ትቸገራለህ፤ ራሳቸውን የሚያሳርፉበት ቀርቶ የሚያስጠጉበት እንኳን የሌላቸውን አስብ፡፡
በሥራህ ደስ የማይል ቀን ያጋጥምሃል፤ ላለፈት ዘመናት ዛሬንም ጨምሮ እንኳን ሥራ አጥቶ የተቀመጠውን ሰው አስብ፡፡
ወዳጅነትህ ወደ ከፋ ጎዳና እያመራ ስለሆነ ተስፋ ቆርጠሃል፤ ማፍቀርና በምላሹ ደግሞ መፈቀር ምን ዓይነት እንደሆነ ጭራሹኑ የማያውቁትን ሰዎች አስብ፡፡
የምትወደውን አንድ ሰው በሞት ስላጣህ ቀኑ ጨልሞብሃል፤ ሙሉ ቤተሰቡን አንድ ቀን የቀበረውን ብቸኝነት እንደ ሳማ ቅጠል የሚለበልበውን እርሱን አስበ፡፡
በሕይወትህ ባጋጠሙህ ጭንቀቶችና በገጠምካቸው ፈተናዎች ትማረራለህሁሉም የሆነው ስለኖርክ ነው፡፡ በመቃብር ሥፍራ ካሉት አንዱ እንኳን እንደ አንተ ደስታና ሐዘንን፣ ከፍታና ውድቀትን የማየትም ሆነ የማስተዋል አቅሙም አጋጣሚውም የለውም፡፡ ስለዚህ በምትኖርበት ጊዜ ሁሉ ላለፈው ለሚመጣውና እየሆነ ላለ መጨነቅን አቁም!