Tuesday, November 6, 2012

የማታውቂው ባዶ



                                         ማክሰኞ ጥቅምት 27/2005 የምሕረት ዓመት


          ባል ከሚስቱ የሚደብቃት ምንም ነገር የለም፡፡ አሳቡን የምታስብ፣ የልብ ምቱን የምትመታ፣ ንግግሩን የምታወራ እስክትመስል የገንዘብ ብቻ ሳይሆን የኑሮ ወጪና ገቢውንም ታውቃለች፡፡ ነገር ግን ሚስትን ጨምሮ ማንም የማያየው ቁልፉም በእርሱ እጅ ብቻ የሆነ አንድ መሳቢያ አለው፡፡ ሚስት እንዲያሳያት የጠየቀችው ቢሆንም እምቢታው ግን አላስቻላትም፡፡ ብዙ ጊዜ ክልከላውን ብታከብርለትም አንዳንዴ ግን አክርራ ትጠይቀዋለች፡፡ ታዲያ አንድ ቀን የመሳቢያውን ቁልፍ ረስቶ ከቤት ይወጣል፡፡ ሚስትም የዘወትር ትጋቷ ምላሽ ያገኝና ከኮቱ ኪስ ቁልፉን ወስዳ መሳቢያውን ታየዋለች፡፡
          ባል ከሥራ መልስ ወደ ቤት ሲመጣ ሚስት ፊቷ ፍም እስኪመስል ታለቅሳለች፡፡ የተደናገጠው ባል ምክንያቷ ምን እንደሆነ ቢጠይቃት “ለባዶ መሳቢያ ይህንን ያህል ጊዜ ያስለመንከኝ ለምንድነው?” የሚል መጠይቃዊ ምላሽ ያገኛል፡፡ ባልም ትህትና በተሞላበት አነጋገር “የማታውቂው ባዶ እንኳ ይኑረኝ ብዬ ነው” አላት፡፡    
         ድብቅነት አንዱ የኑሮ መስፈርት እየሆነ መጥቶአል፡፡ ለዚህም እንደ ምክንያት የሚቀመጡት ማሳመኛዎች ብዙ ናቸው፡፡ አብዛኞቹ ድብቅነት አያስፈልግም! የሚል አቋም ሲኖራቸው እንደ መከራከሪያ የሚያቀርቡትም አሳብ ደግሞ “ድብቅነት ሕይወትን ከባድና ውስብስብ ያደርጋታል” የሚል ይሰኛል፡፡ አንዳንዶች ደግሞ እንደ አስፈላጊነቱ ድብቅነት መኖር አለበት ባይ ናቸው፡፡ እንደ መከራከሪያነት ከሚያቀርቡት ምሳሌ መካከል ሰይጣንን ያጣቅሳሉ! ምክንያቱም ውድቀቱ የእግዚአብሔርን መደበቅ ተከትሎ የመጣ ነው፡፡ ስለዚህ ቢያንስ ሰውን ለመፈተንና በጎውን አቅርቦ ክፉውን ለማራቅ የምንሸሽገው ባዶ እንኳ ያስፈልገናል የሚል ነው፡፡ ሌሎች ደግሞ “ድብቅነት ምን ጊዜም አስፈላጊ ነው” የሚል አመለካከት ያላቸው ናቸው፡፡ እነዚህ “በተኩላ ዓለም በግ መሆን ለእራስ በገዛ እጅ መቃብር መቆፈር ነው” የሚሉ አሉታውያን (ጠርጥር) ናቸው፡፡ እናንተስ?   
          እውቀት በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ቋሚ ጥማት ነው፡፡ የሚሰወረን ነገር ባይኖር የሁላችንም መሻት ነው፡፡ ስለ ሰው ማወቅ ብቻ ሳይሆን የሰውንም ማወቅ እንፈልጋለን፡፡ ድብቆች ብንሆንም ከሰው የተገላለጠ ነገር እንጠብቃለን፡፡ ነገር ግን ተግባራዊ በሆነ መንገድ የአብሮነት ኑሮአችን የተያያዘበት ሰንሰለት ብዙ መሰብሰብ ጥቂት መገለጥ ነው፡፡ በአካባቢያችሁ ያሉ ሰዎች “ምነው ሰሞኑን በዛህ/ሽ?” ብለዋችሁ አያውቁም? ይህ በሌላ መንገድ “አይኔ ሰልችቶሃል” ማለት ነው፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን እንዲህ ስላለው ሁኔታ “እንዳይሰለችህ እንዳይጠላህም እግርህን ወደ ባልንጀራህ ቤት አታዘውትር” (ምሳ. 25÷17) በማለት ምክሩን ይለግሰናል፡፡
          በሰው ታሪክ ውስጥ አንዱ ለሌላው ግልጽ አለመሆንና ነገሮችን መሸሸግ ውድቀትን ተከትሎ ወዲያው በዔደን ገነት ውስጥ የተስተዋለ ሐቅ ነው፡፡ የአዳምና ሔዋን መተፋፈር አንዳቸው ለሌላቸው እንዳይገለጡ አደረጋቸው፡፡ ደግሞም እግዚአብሔርን ተጠያቂ ወደ ማድረግ የመራቸውንም ምክንያት ስንመረምረው የጋራ መወያየት የታየበት ሳይሆን የየግል ልብ ወለድ እንደሆነ እናስተውላለን(ዘፍ. 3)፡፡ አዳም ለመብላት የሚስቱን ቃል ቢሰማም ለመፍትሔ ግን አልሰማትም፡፡ ሔዋንም ለማብላት ቃላትን ለአዳም ብትናገርም ለመፍትሔ ግን አላናገረችውም፡፡ ይህንን ተከትሎ ነው እንግዲህ ቃየን አቤልን ተደብቆ የገደለው፡፡ እንዲህ ያለው የድብቅነት ዝንባሌ እኛም ጋር የደረሰው በቅብብሎሽ ነው፡፡   
          ሰው የቱንም ያህል ድብቅ ቢሆን ከሰው የሚያስቀረው እንጂ ከእግዚአብሔር የሚሰወረው ነገር የለም፡፡ አይኖቹ እንደ እሳት ነበልባል በሆኑት ጌታ ፊት ሁሉ የተራቆተ ነው፡፡ እግዚአብሔር የማያውቀው ድርጊት ቀርቶ የማያውቀው ባዶ እንኳ የለንም፡፡ ውድ የቤተ ፍቅር ብሎግ ተከታታዮች በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ በተረዳችሁበት መንገድ ያላችሁን አሳብ እንድትገልፁና ለውይይት እንድትሳተፉ በትህትና እንጋብዛለን፡፡