Thursday, September 12, 2013

ዘመንሰ፡ የተዋጀ ይዋጃል


                                                ሐሙስ መስከረም 2/ 2006 የምሕረት ዓመት

        ዘመንን ያመጣ፣ ለዘመኖቻችን ዳርቻን ያበጀ፣ በእድሜ በረከት፤ በእርጅና ሽበት የሚባርክ፣ ሕፃናቱን አስተዋዮች፣ ጎበዛዝቱን ብርቱዎች የሚያደርግ እግዚአብሔር ብሩክ ነው፡፡ ተናግሮ የሚቀር፣ ትቶት የሚሆን፣ ይዞት የሚወድቅ፣ ጥሎት የሚነሣ፣ ዓይቶት የሚሰወር፣ ወድዶት የሚጠላ፣ ሰጥቶት የሚነፈግ፣ ምሕረት አድርጎለት የሚኮነን፣ ጠግኖት የሚሰበር፣ እንባ ታብሶለት የሚያዝን፣ ደግፎት የማይጸና አንድስንኳ የሌለ እግዚአብሔር አብ ስሙ ይቀደስ፡፡ እኛን ፈልጎ በአድራሻችን የመጣ፣ ሰው ሆኖ ሰዎችን የረዳ፣ ወደ ምድር ወርዶ ወደ ሰማይ ያደረሰን፣ ተዋርዶ ክብርን ለእኛ ያመጣ፣ ራሱን ባዶ አድርጎ ወደ እግዚአብሔር ሙላት ያሻገረን፣ እስከ መስቀል ሞት ታዝዞ በደሙ ያዳነን፣ ለእኛ ጽድቅ የደከመ፣ ለእኛ ትንሣኤ የሞተ፣ በረከታችንን መንፈሳዊ፤ ስፍራችንን ሰማይ ያደረገልን ኢየሱስ ጌታችን ነው፡፡

        የኩነኔውን ዘመን በምሕረት የቀየረ፣ ለዘላለም ያመለጥንበት ዐለት፣ ምድረ በዳውን የምናቋርጥበት ምንጭ፣ ፈተናዎቻችንን የምናልፍበት መውጫ፣ ይገለጥ ዘንድ ባለው ክብር ፊት የምንቆምበት ጽናት መድኃኔዓለም ስሙ ብሩክ ይሁን፡፡ የሚያጽናና ደግሞም የሚያጸና፣ የቃሉን ደጅ የሚከፍት፣ ፍቺውን የሚያበራ፣ መንፈሳዊ ፍሬዎችን እንድናፈራ የሚረዳን፣ ለሙሽራው እንደ ሙሽሪት የሚያስጌጥ፣ ድካማችንን የሚያግዝ፣ በጸጋ የሚያስተባብር፣ ለቤተክርስቲያን ሁለንተናዊ እድገት የሚተጋ መንፈስ ቅዱስ ይባረክ፡፡ እንዴት እንድንጸልይ ለማናውቅ በማይነገር መቃተት የሚናገር፣ ዓለማዊነትን ክደን የተባረከው ተስፋችንን እንድንናፍቅ የሚያበረታን፣ የእግዚአብሔር መንፈስ፥ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ፥ የምክርና የኃይል መንፈስ፥ የእውቀትና እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ ለዘላለም ይመስገን፡፡ አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ፣ አንድ አምላክ አሜን፡፡   

         ወዳጆቼ እንኳን አደረሳችሁ! ትላንት ዛሬ፣ ቅድም አሁን፣ ምሽት ንጋት ስለሆነላችሁ የምታምኑት ጌታ ይባረክ፡፡ ቀኑ በስሙ ይቀደስላችሁ፡፡ ዘመኑ በእርሱ እጆች ላይ ይለቅላችሁ፡፡ ሊመጡ ያሉት ቀናት እንደሚገባ ኖራችሁባቸው እንዲያልፉ ጸጋው ያግዛችሁ፡፡ ዛሬ ብዙ ለመናገር፤ እናንተም ብዙ ለመስማት እንዳልተዘጋጃችሁ ይሰማኛል፡፡ ቢሆንም ጥቂት የእግዚአብሔርን አሳብ እንጨዋወት፡፡ ጌታ ለደቀ መዛሙርቱ ባስተማራቸው ጸሎት ላይ “ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን” (ማቴ. 6፥10) ብለን እንድንለምን አዝዞናል፡፡ በሰማያት ያለው የእግዚአብሔር ፈቃድና የልቡ ምክር በዚህ ምድር ላይ ሊከናወንበት የሚችለው ትልቁ ስፍራ ክርስቲያን ነው፡፡


          አባታችን ሆይ ብለው ሊጸልዩ የሚችሉት ከእግዚአብሔር የተወለዱ ብቻ ናቸው፡፡ የአባት ፈቃድ ዳር የሚደርሰው በልጆቹ ነው፡፡ ወንጌል ወደ ምድር ዳርቻዎች ሁሉ ሊደርስ የሚችለው በክርስቶስ በማመን የዘላለም ሕይወት ባገኙ ወንድሞችና እህቶች አማካኝነት ነው፡፡ በሰማይ ያለው የእግዚአብሔር ፈቃድ በእኛ በኩል ወደ ሰዎች ሁሉ ካልደረሰ ባላመኑት መካከል ፈቃዱ አይከናወንም፡፡ እግዚአብሔር ለዚህ ዓለም ብቸኛ መፍትሔ ባደረገው ልጁ በክርስቶስ የሚያምኑ ሁሉ የአምላክ ፈቃድ ምድሪቱን እንዲገዛ ትልቅ ኃላፊነት አለብን፡፡ ዘወትር ያለማቋረጥ በመጸለይ የእግዚአብሔር ፈቃድ ወደ ሰዎች ሁሉ እንዲደርስና በእኛም ሕይወት እንዲፈጸም ትጋት ልናሳይ አግባብ ነው፡፡  

          ሐዋርያው፡- “ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ” (ኤፌ. 5፥16) በማለት ክርስቲያን በዘመን ላይ ያለውን ትልቅ ድርሻ በምክር ይገልፃል፡፡ ተወዳጆች ሆይ ክርስቲያን በዚህ ዓለም ስርዓት ስር ባሪያ የሚሆን ሳይሆን በእያንዳንዱ የዚህ ዓለም ሁኔታ ውስጥ ተጽእኖ በመፍጠር ጌታን የሚያከብር ነው፡፡ ነገንና ከነገ ወዲያን ስናስብ መልካም ብቻ ሳይሆን ክፉ ቀኖችም እንዳሉ ሚዛናዊ ሆነን እናስባለን፡፡ መንፈሳዊ ሰው ደግሞ ክፉዎቹን ቀኖች ይዋጃል፡፡ መዋጀት የሚለው ቃል መግዛት የሚለውን ትርጉም ይይዛል፡፡ ከክርስቲያን አንፃር ዘመንን መዋጀት ጊዜና ሁኔታውን ለእግዚአብሔር ክብር ማስገዛት ነው፡፡

         ክርስቶስ ደሙን አፍስሶ ከኃጢአትና ከሞት እንደዋጀን ሁሉ ዘመንን መዋጀት ዋጋ ያስከፍላል፡፡ በመዋጀት/ በመግዛት ውስጥ ልንከፍለው ግድ የሚሆን ዋጋ አለ፡፡ ልናምን ብቻ ሳይሆን ደግሞ ላመነው ዋጋ ልንከፍልለት ተጠርተናል፡፡ እንደ ተዋጀ ክርስቲያን ሌሎችን መዋጀት የዚህ እውነት አንድ አካል ነው፡፡ ክፉዎቹን ቀኖች በጎ ለማድረግና እንደ እግዚአብሔር ቃል ዘመኑን ለመዋጀት የሚጠቅሙንን ነጥቦች ነቢዩ ዳዊት ይነግረናል፡-“በጎንም ዘመን ለማየት የሚወድድ ማን ነው? አንደበትህን ከክፉ ከልክል፥ ከንፈሮችህም ሽንገላን እንዳይናገሩ። ከክፉ ሽሽ መልካምንም አድርግ ሰላምን እሻ ተከተላትም” (መዝ. 33፥12-14)፡፡ 
      
1.     በአንደበት አለመበደል፡- በልባችን የተሰወረውን የምናሳይበት አደባባይ አንደበት ነው፡፡ በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ አንደበት ከተብራራበት መንገድ አንዱ “አንደበት እሳት” (ያዕ. 3፥6) የሚል ነው፡፡ በሰው ዘንድ ካሉት ነገሮች ሁሉ አንደበት ትልቁን ስፍራ ይይዛል፡፡ ልናቀና ልንሰብርበት፣ ልናከብር ልንበድልበት፣ ልናሳርፍ ልናስከፋበት . . . . የሚሆን ኃይል ነው፡፡ ወንጌል ብንመሰክርና ሰዎችን ብናጽናና በዚሁ በአንደበት ነው፡፡ ክርስትናን ከምንኖርበት አንዱ መንገድ ምስክርነት ነው፡፡ አንደበታችንን ለእግዚአብሔር ማስገዛት ማለት በጎውን የምስራች፣ መልካሙን ወሬ ለሰዎች መናገር ነው፡፡

       ብዙ ሰዎች በሰው ቃል ተሰብረዋል፡፡ በሰው አንደበት ንግግር ተመርረዋል፡፡ ዓለምን ውበት የሚያሳጣ፣ በሕዝቦችና በመንግስታት መካከል ጸብን የሚያጭር፣ ሕሊናን የሚያረክስ ነገር ቢኖር ክፉ ንግግር ነው፡፡ ምድሪቱን የሚያስጨንቅ ክፉ ወሬ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ሰዎች በዚህ ሁኔታ ውስጥ እንደ መፍትሔ በመታየት ተጽእኖ መፍጠር አለባቸው፡፡ አልጫ በሆነው የዓለም ስርዓት ላይ እንደ ጨው፣ ጨለማ በወረሰው የምድሪቱ ኑሮ ላይ እንደ ብርሃን መታየት ዘመኑን የምንዋጅበት ሂደት ነው፡፡

      ሰይጣን ሕይወታችንን የሚዋጋው አንደበታችንን እየተከተለ ነው፡፡ ዲያቢሎስ የልባችንን ማወቅ አይችልም፡፡ ታዲያ ዓለሙን የሚጫወትበት እንዴት ነው? ብንል ከወሬያችን እየተረዳ ነው፡፡ ልብና ኩላሊትን የሚመረምር የሚለው ለእግዚአብሔር እንጂ ለሰይጣን አይጠቀስም፡፡ ጠላት ግን ባወራነው ክፉ ይዋጋናል፡፡ እግዚአብሔርን በመከራ ውስጥ እንኳ ማመስገን፣ በጊዜውም ያለ ጊዜውም ስንፍናን አለመናገር፣ በሁኔታዎች ላይ ቃሉን ማወጅ ለሰይጣን ብርቱ ፈተና መሆን ነው፡፡ ተወዳጆች ሆይ አንደበታችሁን ከክፉ ጠብቁ፡፡ መልካሙን የምስራች ወደ ሰዎች በማድረስ፣ ለመፍትሔ በማውራት፣ በጎውን በመግለጥ አፋችሁን ለጽድቅ ክፈቱ፡፡ በመስበክ ቢሆን በመዘመር ሰዎች የዚህን ዓለም ከንቱ ነገር በመናገር የሚያሳልፉትን ጊዜ መቀነስ፣ በአንድም በሌላም መንገድ ሰዎች እግዚአብሔርን እንዲያወሩ መርዳት የአዲሱ ዓመት ተግባራችን ይሁን፡፡ ጸጋው ያግዘን፡፡

2.    ሽንገላ አታውሩ፡- ሽንገላ እውነቱን እውነት ውሸቱንም ውሸት አለማለት ነው፡፡ እንዲህ ያለው ነገር ቤተክርስቲያንን ባሪያ ማድረጉ ልብን ያሳዝናል፡፡ ዛሬ ዛሬ ነውሩ አለመሸነጋገል እየሆነ መጥቷል፡፡ ለሽንገላቸው የሚጠቀሙበት የእግዚአብሔርን ቃል መሆኑ ደግሞ በደሉን ያከፋዋል፡፡ እናንተ ግን ወዳጆቼ ፈጽሞ አትሸንግሉ፡፡ ለእግዚአብሔር መታመን ከምናሳይበት መንገድ ዋናው ነገር እውነቱን እውነት ውሸቱን ውሸቱ እያሉ ወደ ፊት መጓዝ ነው፡፡ በተለይ በእግዚአብሔር አሳብ ላይ ውሸትና ተረት አለመሸቃቀጥ ተገቢ ነው፡፡ በአንደበታችን ከምንበድልበት ነገር ሽንገላ የከፋው ነው፡፡ ዘመንን መዋጀት፣ በጎን ዘመን ማየት የምንሻ ሁሉ አለመሸነጋገል መመሪያችን መሆን አለበት፡፡
       
         ሽንገላ ሰዎች ያላቸውን አቅም እንዳይጠቀሙና ለለውጥ እንዳይታዘዙ የሚያደርግ ማነቆ ነው፡፡ ሰው ባለው ሳይሆን እንዳለው በሚሰማው ነገር እረክቶ ቁጭ እንዲል ጠፍሮ የሚይዝ ትብታብ ነው፡፡ ውኃ ሲወስድ እያሳሳቀ ነው እንዲሉ ሽንገላ እያሳሳቃቸው ሊያውቁ የሚገባቸውን ሳያውቁ፣ ሊይዙ የሚገባቸውን ሳይዙ፣ ሊያስተካክሉ የሚገባቸውን ሳያስተካክሉ ዘመን ያለፈባቸው አልፎም ተርፎ ሞት የቀደማቸው ብዙ ናቸው፡፡ እውነተኛ የሆኑ ሁሉ ነፍሳቸው ሽንገላን አጥብቃ ትጸየፈዋለች፡፡

3.    ክፉውን መሸሽ፡- ቆመን የምንታገለው ብቻ ሳይሆን ሸሽተን የምናሸንፈው ነገር መኖሩን መረዳት ትልቅ ጥበብ ነው፡፡ ሽሽት በብዙ የእግዚአብሔር ሰዎች ሕይወት ውስጥ ተግባራዊ የተደረገ መርኅ ነው፡፡ በአዲስ ኪዳን ሳይቀር እንድንሸሻቸው የታዘዝንባቸው ነገሮች አሉ፡፡ ፈተናዎቻችንን ብርቱ ከሚያደርጉ ነገሮች አንዱ ቆሞ መደራደር ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ግን ለክፉ ተግባር እንደ መፍትሔ ከሚያቀርበው መካከል ሽሽት ይጠቀሳል፡፡ አብዛኞቻችንን ሽሽት ስፍራን መልቀቅ ብቻ እንደ ሆነ ልናስብ እንችላለን፡፡ ዳሩ ግን የሽሽት የመጀመሪያው እርምጃ በልብ መፋታት ነው፡፡ ከዚያ እግር ይከተላል፡፡ ይህ ቅደም ተከተል ባልተጠበቀበት ጊዜና ሁኔታ ሁሉ ግን እንደሸሸነው በሚሰማን ነገር ዳግም መያዝ ይመጣል፡፡ በሚያስጨክነው ጨክነን፣ ልንተወው የሚገባንን ትተን፣ ማቄን ጨርቄን ሳንል ክፉውን መሸሽ ያስፈልጋል፡፡

        ክፉውን መሸሽ ዘመናችንን ከምንዋጅበት፣ ሊመጡ ያሉትን ቀናትና ወራት ውብት ከምንሰጥበት ነገር አንዱ ነው፡፡ ባለፈው ዘመን ክፉ ባልንጀራ የነበረን ከዚያ ሽሹ፣ ባለፈው ዓመት በአመጸኞች ጉባኤ ላይ የተቀመጥን ከዚያም ሽሹ፣ ከዝሙት ሽሹ፣ ከጣዖት ማምለክ ሽሹ . . . ጌታ አቅም ይሁነን፡፡ ወደ እግዚአብሔር በመቅረብ ብቻ ሳይሆን ከክፉውም በመራቅ አምላካችንን እንድናከብር ቅዱስ መንፈሱ ይርዳን፡፡

4.    መልካሙን ማድረግ፡- የነገር ሁሉ መጠቅለያው ተግባር ነው፡፡ ለሰዓታት ያወራነውን ለደቂቃ ማድረግ ካልቻልን ሞት እርሱ ነው፡፡ “ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያሳታችሁ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ” (ያዕ. 1፥22) ተብሎ እንደ ተፃፈ የእግዚአብሔርን ቃል በመስማትና በማንበብ ብቻ ሳይሆን በማድረግም የምንደሰት መሆን ይገባናል፡፡ ዘመኑን የምንዋጀው በምንናገረው ብቻ ሳይሆን በምናደርገውም ጭምር ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ብርሃን ካወራ በኋላ ዓይነ ስውር ያበራ ነበር፡፡ ስለ ትንሣኤ ካወራ በኋላ ሙት ያስነሣ ነበር፡፡ እንደ ክርስቲያን የተናገርነውን የምናደርገው፤ የምናደርገው የምንናገረውን እንዳያበላሸው (እንዳይጠፋፉ) መጠንቀቅ አለብን፡፡  
       
       ከምድሪቱ ጩኸት አንዱ የተግባር ያለህ! የሚል ነው፡፡ መልካም መነገሩ፣ መልካም መወራቱ በራሱ በጎ ቢሆንም ተግባር ግን ሊገልጸው ይገባል፡፡ ሰዎች ብዙ ከምንነግራቸው ጥቂት ብናደርግላቸው ይመርጣሉ፡፡ ለራበው ሰው ወሬ ብታወራለት በጆሮው ሳይሆን በሆዱ ይሰማሃል እንዲሉ መፍትሔ በማንሆንበት ሁኔታ እንዳንገኝ ጌታ ይርዳን፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ እኛን የተቤዠን እሰቀላለሁ ብሎ ብቻ ሳይሆን ተሰቅሎ፣ እሞታለሁ ብሎ ብቻ ሳይሆን ሞቶልን ነው፡፡ በቃልም በኑሮም ጌታ ብርቱ ነበር፡፡ ተወዳጆች ሆይ እኛስ? ልብ በሉ! የተዋጀ ይዋጃል፣ የዳነ መፍትሔ ይሆናል፣ ያመለጠ ያስመልጣል፣ ብዙ ከተቀበለ ብዙ ይጠበቅበታል፡፡


1 comment:

  1. Big thank you bra awesome job.to me it looks like i was seating in front of mirror to groom my self.I learn a lot.thanks &God bless you.

    ReplyDelete