Tuesday, June 26, 2012

ማን ያግባሽ? (ክፍል ሦስት)



ከሁለተኛው አስተያየት የቀጠለ፡ -  
         መጋባትን በአግባቡ የፈጸሙ ሰዎች ትዳር ውስጥ ልዩነትን ወደ አንድነት፣ መራራቅን ወደ ቅርበት ሲያመጡት እንመለከታለን፡፡ ምክንያቱም አንዱ በሌላው ውስጥ ብቻ ሳይሆን ሌላውም በአንዱ ውስጥ ስፍራን አግኝቶአል፡፡ ሳይጋቡ የገቡ የልብ ጥምረት፣ የአሳብ መስማማት አይስተዋልባቸውም፡፡ አካላዊ ሕብረት ጎልቶ ቢታይም የመንፈሳዊ ውስጠታቸው ነፀብራቅ መሆን ግን አይችልም፡፡
       ከሙሽራው ክርስቶስ ጋር ያለንን ጥምረት ቅዱስ መጽሐፍ ሲነግረን “እኛ ግን የክርስቶስ ልብ አለን” ይላል፡፡ በእርሱ ብንኖር እርሱ ደግሞ በእኛ ለመኖሩ መሠረቱ የጌታን ልብ መያዛችን ነው፡፡ የሙሽራይቱ ለሙሽራዋ የሚኖራት ትልቁ ክብር እንደ ልብዋ ሳይሆን እንደ ልቡ አሳብ መኖሯ ነው፡፡ የክርስቶስ አካል (ቤ/ን) ብልቶች እንደመሆናችን መንፈስ ቅዱስ ለክርስቶስ ለማጨት ሕይወታችንን በሚጎበኝበት ሁኔታ ውስጥ ትልቁ ጥያቄ ማን ያግባሽ? የሚለው ነው፡፡ እግዚአብሔር ፈቃዳችንን ተጠቅሞ በሕይወታችን ውስጥ በፍቅርና በኃይል ይሠራል እንጂ ነፃ ፈቃዳችንን ለመጣስ  አንዳች ነገር አያደርግም፡፡ ጌታ ከገዛ እውነቱ ይጣላ ዘንድ አመፀኛ አይደለም!
         ስለ መታጨት ስናስብ ከመጽሐፍ ቅዱስ የዘፍጥረት ምእራፍ ሃያ አራት ታሪክ ተጠቃሽ ነው፡፡ አብርሐም ለልጁ ለይስሐቅ ሙሽሪትን ለመፈለግ ሎሌውን እንደላከ የምናስተውልበትን ክፍል እናነባለን፡፡ አብርሐም ልጁን በሞሪያም ለመሥዋዕትነት ካቀረበ (በአባቱ ሕሊና ከተሠዋ) በኋላ በምሳሌነቱ የልጁን ትንሣኤ ከተመለከተ ከዚያም ሚስቱን ከቀበረ በኋላ እንደ ተስፋው ቃል እውነተኛ ወራሽ ለሚሆነው ብቸኛ ልጁ ይስሐቅ ሚስትን ያጋባው ዘንድ ሎሌውን ላከ፡፡
          ሎሌው የናኮር ከተማ ወደምትገኝበት መስጴጦምያ ተጓዘ፡፡ በዚያም ርብቃ ውኃ ልትቀዳ ስትመጣ በመንገድ አገኛት፡፡ ሎሌውም ውኃ አጠጪኝ በሚል የመግባቢያ ቃል ስለ ውኃ አጣጯ ይስሐቅ ነገራት፡፡ አባቱ አብርሃም ለልጁ ያልሠጠው አንዳችም ነገር እንደሌለ ከእርሱም ጋር ብትጋባ የእዚህ ሁሉ ክብርና ባለ ጠግነት ተካፋይ እንደሆነች አወጋት፡፡ አባት ለልጁ መልካም ሚስትን ለማዘጋጀት ሎሌውን እንደላከ ሎሌውም ለይስሐቅ መልካሚቱን እንደወሰደ የታጨችይቱም ያላየችውን ነገር ግን የሰማችለትን፣ ያላገኘችውን ነገር ግን ተስፋ የተሰጣትን ቃል አምና አዎንታዊ ምላሽ ስትሰጥ እናስተውላለን፡፡
        ለጸጋው ቃል አደራ የተሰጠን ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ እንደ አባት ፈቃድና መመሪያ ለአንድ ልጁ ለክርስቶስ ታጭተናል፡፡  ሎሌው ከአብርሃም እንደወጣ መንፈስ ቅዱስ ከአብ ሠርፆአል (ዮሐ. 15÷26)፣ ስለ ወልድም ወልድ ካለው ወስዶ ይነግረናል (ዮሐ. 16÷12)፡፡ ርብቃ (ቤተ ክርስቲያን) ከስም ሁሉ በላይ የሆነውን ስም ደግሞም ከሰማይ በታች እንድንበት ዘንድ የተሰጠንን ስም የያዘውን፣ ከአለቅነትና ከሥልጣንም ከኃይልም ከጌትነትም ሁሉ በላይ በዚህ ዓለም ብቻ ሳይሆን ሊመጣ ባለውም ዓለም ጌታ የሆነውን በአባት ዘንድ እንዳለ ክብር ያለውን ክብር  ብታስተውል ደግሞም እሺ ብትል በሠርጉ እራት ላይ እድል ፈንታ ይሆንላታል፡፡ በወርቅና በብር ያይደለ በደሙ የሆነ ጥሎሽ ለእርሷ ራሱን አሳልፎ ሰጥቶአል፡፡ እንዲህ ባለ ፍቅርና መከራ ለወደደን መታጨት እርሱ ያግባኝ ብሎ ለአንድ ወንድ ክርስቶስ መለየት ክብሩ በዋጋ የማይተመን ነው፡፡
           ቤተ ክርስቲያን የታጨችለትን ልታስተውል ደግሞም ፍቅሩን ልታከብር ይገባታል፡፡ ከሀብት፣ ከሥልጣን፣ ለዚህ ዓለም ከሚመች ከንቱ መለፍለፍ ተረትና መጨረሻ ከሌለው የትውልዶች ታሪክ፣ በእውነት ላይ ዓመጽ እነዚህን ከመሳሰል ተጨማሪ ወንዶች (ማመንዘር) ልትርቅ ይገባል፡፡ ለሁሉም የሆነው አንድ ሙሽራ የአንተ የአንቺ ሙሽራ ነው ወይ? ከነፍሳችን ጋር ሊዋሃዱ የሥጋ ምኞት፣ ዓለምና ዲያቢሎስ በዙሪያችን ያደባሉ ታዲያ ማን ያግባሽ? ማስተዋልን እንድናተርፍ ጌታ ይርዳን፡፡
                                                                                ኃይሉ ወ/ማርያም

3. ቤተ ፍቅር የምታነሷቸው የመወያያ ርዕሶች ተመችተውኛል፡፡ ማን ያግባሽ? የሚለው ጥያቄ በሌላ ጎኑ ማን ያግባህ? የሚል ጥያቄም እንደሆነ በማመን ያለኝን አመለካከት እገልፃለሁ፡፡ ለመንደርደሪያ ያክል ባለፈው ባስነበባችሁት አስተያየት ላይ ትህትና የተባለች አልያም የተባለ ሰው የሰጠውን መደምደሚያ ወድጄዋለሁ፤ በአብላጫውም አመለካከት እስማማለሁ፡፡
        እንደ እኔ አመለካከት ከሆነ ገንዘብ እንዲሁም አፍ ለትዳር ጣዕም አስፈላጊ ነገሮች ናቸው፡፡ ሀብቱ ልቡ አፉም ልቡ የሚለው እንዳለ ሆኖ መነጣጠል በሌለበት ሁኔታ ቁሳዊና አሳባዊ ነገሮችም ለትዳር ጤናማነት ወሳኝ ናቸው፡፡ እግዚአብሔር ራሱ አዳምን (እንኳን ሔዋንን ረዳት አድርጎ መፍጠር ይቅርና) ከመፍጠሩ በፊት ስለሚኖሩበት፣ ስለሚበሉት፣ ስለሚዝናኑበት፣ ስለሚሠሩት አስቦና አሰናድቶ በአለቀ ነገር ላይ ነው የሞሸራቸው፡፡ ይቅርታ አድርጉልኝና ጎጆ ውስጥ እንጨርሰዋለን በሚል የጅምር ጋጋታ ላይ ትዳር መመስረት ጉዳቱ እንጂ ጥቅሙ አይታየኝም፡፡
         ሰው ሥጋና ነፍስ (መንፈስ) እንደመሆኑ ብር ያለው ያግባሽ? የሚለው ከስግብግብነትና ከንዋይ አፍቃሪነት በፀዳ መንገድ መሟላት አለበት፡፡ ይህንን ቀለል ባለ እገላለጽ ስናስቀምጠው የመተዳደሪያ ጉዳይ በትዳር ውስጥ የመጨቃጨቂያ ርእስ አይሁን ማለት ነው፡፡ አፍ ያለው ያግባሽ? የሚለውም ጥያቄ ማታለልና ማደናገርን የሚያጣራ ጆሮ ካለን አስፈላጊ ነው፡፡ አሳባቸውን ወደ ውስጥ እንጂ ወደ ውጪ መግለጽ የማይችሉ መታለላችን ጨዋ በሚል ሽፋን የሚያሞካሻቸው፣ ማስተዋላችን ደግሞ የሚኮንናቸው ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ እንዲያውም የሕሊናዋን የማታወራ፣ የተሰማትን የማትገልጥ ሴት ከገጠመቻችሁ እንዲሁም አይኑ ቁልጭ ቁልጭ አፉ ዝም ጭጭ የሚል ወንድ ከገጠማችሁ እንደነዚህ ያሉት ከባድ የቤት ሥራ ናቸው፡፡
       አሳቤን ስጠቀልል ሔዋን የተሞሸረችው ለእንስሳት መጠሪያቸውን ለሚሰይመው፣ መኖሪያው ዔደን ገነት ለሆነው፣ ከእግዚአብሔር ጋር የአባትና የልጅ ሕብረት ላለው አዳም ነው፡፡ በእርግጥም ሔዋንን ማን ያግባሽ? ብለን ብንጠይቃት አዳም ከማለት ውጪ ሌላ ምላሽ አይኖራትም፡፡ ምክንያቱም ያለው አንድ ወንድ ብቻ ነዋ! ምናልባት በዙሪያቸው ከእጽዋት መካከል የወንዴ ዘር አልያም ከእንስሳቱ ዘንድ ወንድ ካልሆነ በቀር ለአማራጭ ተቀናቃኝ አልነበረም፡፡ ምናልባትም ሲመስለኝ ከሠይጣን የሆነ ነገር ግን እንደ ሰው ያለውን ምክር የሰማችው ለብቸኛው አዳም ልብዋ አማራጭ ያገኘ መስሎት ይሆናል፡፡ ዛሬ ግን አማራጩ ብዙ ነው፡፡
      በአካል ቀጭን፣ ወፍራም፣ ረዥም፣ አጭር፣ ቀይ፣ ጥቁር እንዳለ ሁሉ በአስተሳሰብ፣ በኑሮ ዘይቤ እንዲህ የሚመደቡ ወንድም ሴትም ባሉበት ዓለም እንደመኖራችን ማን ያግባሽን አቅልሎ ማየት አይቻልም፡፡ እኔ ግን በመጠን ኑሩ ስለሚል ቃሉ ብር ካላት አፍም ካላት የተመጠነችውን ማግባት መልካም ነው እላለሁ፡፡ ክብረት ይስጥልኝ!
                                                                                   ሀብተ ወልድ

4. እግዚአብሔር ጸጋውን ያብዛላችሁ፡፡ ርእሱን እንደተመለከትኩ ውስጤ ጥያቄ ስለተፈጠረብኝ ይህንኑ ለመግለጽና ምላሻችሁን ብታካፍሉኝ በማለት ጥያቄዬን እንደሚከተለው እገልጣለሁ፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለሁ ፍቅር ጀምሬ ነበር ይህም ብዙ ሳይቆይ ተለያየን በልቤ ውስጥ አኑሮ ያለፈው ነገር ግን ቀላል አልነበረም፡፡ ዩኒቨርስቲ ከገባሁም በኋላ ከአንድ ልጅ ጋር ተቀራርበን ተመርቄ እስክንለያይ ድረስ ዘለቅን ከዚያ በኋላ ግን ሊዘልቅ አልቻለም፡፡ አሁን ታዲያ ከሁለቱም ጋር በነበረኝ የፍቅር ጊዜ ከሁለቱም የወደድኩላቸውን ጨምቄ አንድ ሰው በልቤ ስያለሁ ማለትም አሁን ማግባት የምፈልገው እንደዚህ አይነት ሰው ሁነ፡፡ ይህም ሌላ ከማንም ጋር እንዳልቀራረብና የሚመጣልኝንም የፍቅር ግብዣ ትኩረት እንድነፍግ አድርጎኛል፡፡ እድሜዬ እየገፋ ቢሆንም ማስተካከል ግን አልቻልኩም፡፡ ምን ትመክሩኛላችሁ? በትዳር አጋር ምርጫ ላይ የእግዚአብሔር ፈቃድስ ምን ይመስላል?
                                                                                      ሕሊና
                                                              

                                                       ይቀጥላል

Friday, June 22, 2012

ማን ያግባሽ? (ክፍል ሁለት)



          በመጀመሪያው ክፍለ ንባባችን አንባቢዎች አሳባችሁን እንድትገልጹ በመጋበዝ በይቀጥላል ቀጠሮ እንዳጠናቀቅን የሚታወስ ነው፡፡ በዚህ መሰረት ከተላኩልን አሳቦች መካከል መርጠን ከዚህ በታች እናስነብባለን፡፡

1. ስለ እውነት ለመናገር ርዕሱን ስመለከት ጥያቄው ለእኔ ብቻ የቀረበ ያህል ተሰምቶኛል፡፡ ቤተ ፍቅር በዚህ ርእሰ ጉዳይ የምንወያይበትን አሳብ ስላቀረባችሁ በግል ደስ ብሎኛል፡፡ ለዚህ ምክንያቴ ደግሞ በጋብቻ ላይ ያለው ፈርጀ ብዙ ችግር ነው፡፡ ወደ ትዳር የገቡትን ስናይ “ላም . . . ወልዳ እንዳትልሰው እሳት እንዳትተወው ልጅ ሆነባት” አይነት ነው፡፡ መጋባት ለመረዳዳት መሆኑ ቀርቶ ለመጎዳዳት ሆኗል፡፡ ብዙዎችም እናርፋለን ብለው እሳት ላይ ተጥደዋል፡፡ ታዲያ የቤተሰብና የሕብረተሰብ ምንጭ ስለሆነው ትዳር መወያየት፣ ትውልድ ስለሚቀረጽበት ተቋም መነጋገር አገብጋቢ ጉዳይ ይመስለኛል፡፡
       ቀጥታ ወደ አሳቤ ስገባ እንደ እኔ አመለካከት ብር ያለውን አልያም አፍ ያለውን ማግባት የትዳርን ዝልቀትና ጣዕም አይወስነውም፡፡ ለመኖር እጅግ አስፈላጊው ነገር ያለው ባለን ላይ ሳይሆን በሆነው ላይ ነው፡፡ ጥሩ ስብእና ኖሮት ሀብት ካለው በያዘው ላይ በጥበብ የሚያዝ እንጂ የሀብቱ ሎሌ አይሆንም፡፡ እንደዚሁ መደመጥ በቃል ብዛት የሚመስለውም አፈኛ ትልቁ ቋንቋ አሳብ እንደሆነ ያስተዋለ ስብእና ካለው የትዳሩ ምሰሶ በዚያኛው ሀብት በዚህኛው አፍ መሆኑ ቀርቶ እውነተኛ ልብ ይሆናል፡፡ ይህ ድምዳሜዬ በመነሻ ካስነበባችሁን የጥበበኛው አባት መደምደሚያ ጋር በአብላጫው ይመሳሰላል፡፡
        በዙ ጊዜ ሃይማኖተኛ በሆኑ ሰዎች ዘንድ የሚስተዋለው አንድ አቅጣጫ ብቻ ነው፡፡ ልጁ አልያም ልጅቷ መንፈሳዊ የሆነ አልያም የሚመስል ነገር በእነርሱ ዘንድ ማየታችን ብቻ! ሕይወት ከብዙ አቅጣጫ መመልከትን ትጠይቃለች፡፡ ለዚህ አጋርነት የምንመርጠው ሰው አስተዳደግ፣ ለትዳር ያለው ምልከታ፣ ለደስታና ለሀዘን፣ ለማግኘትና ለማጣት ያለው አተያየት፣ ለወላጆቹ ያለው ፍቅር ወዘተ መስተዋል ይገባቸዋል፡፡ እንዲህ ማድረግ መጠራጠር አይመስለኝም፡፡ እኔ እንዲህ ያለውን ሒደት መጠበብ ነው የምለው ወይም በኋላ መማቀቅ እንዳይመጣ ቀድሞ መጠንቀቅ፡፡ እኔን ማን ያግባሽ ካላችሁኝ “ሀብቱም አፉም ልቡ የሆነ” የሚል ምላሽ አለኝ፡፡ ቤታችሁ የፍቅር ይሁን!!
                                                                            ትህትና ለገሰ

2. ሙሽራው ክርስቶስ ለእጮኛው ያቀረበው ጥያቄ አድርገን ብንመለከተው በነፍሳችን ብዙ የምናተርፍ ይመስለኛል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “በእግዚአብሔር ቅንዓት እቀናላችኋለሁና እንደ ንጽሕት ድንግል እናንተን ለክርስቶስ ላቀርብ ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለሁና . . .” (2ቆሮ. 11÷2) በማለት የታሰብንለትን ክብር ያስተዋውቀናል፡፡ ትዳር ባለበት በየትኛውም ዘመን እንዲህ ያለው የመተጫጨት ሂደት መኖሩ ሲታሰብ ልብን ፈገግ የሚያደርግና ለመደነቅ የሚያበቃ የበዛ ምክንያት ባይሰጥም ከሁሉ ለሚበልጥ ጌታ እጮኛ የመሆን ነገር ግን ከመታሰብ የሚያልፍ ተግባራዊ ደስታ አለው፡፡ አንድ ታላቅ ንጉሥ ሎሌውን ወደ ትንሽ መንደርና የድንኳን ቤት ልኮ በዚያ ውስጥ የምትኖርን ጎስቋላና ምስኪን ሴት ለልጁ ሚስትነት ቢያጫት ምንኛ ድንቅ ነው?
        በማግባትና በመጋባት መካከል ልዩነት መኖሩ ለሚያስተውሉ ሁሉ ግልጽ ይመስለኛል፡፡ ማግባት የአንደኛውን ወገን የማሳመን ኃይል የሚያጎላ ሲሆን መጋባት ግን በሁለት ሰዎች መሐል ያለን የጋራ መግባባት (መስማማት) የሚያሳይ ነው፡፡ ይህ ሐቅ በተግባራዊው ኑሮ ላይም በድምቀት ይስተዋላል፡፡ በአንድ ሰው የፍቅርም ሆነ የኃይል ተጽእኖ ስር የወደቁ ትዳሮች በገቡ እንጂ ባላገቡ አጋሮች የዘወትር ልሰናበት ጥያቄ የተወጠሩ ናቸው፡፡ መጋባትን በአግባቡ የፈጸሙ ሰዎች ትዳር ውስጥ ልዩነትን ወደ አንድነት፣ መራራቅን ወደ ቅርበት ሲያመጡት እንመለከታለን፡፡ ምክንያቱም አንዱ በሌላው ውስጥ ብቻ ሳይሆን ሌላውም በአንዱ ውስጥ ስፍራን አግኝቶአል፡፡    
                                                                
                                                                ይቀጥላል

Tuesday, June 19, 2012

ማን ያግባሽ?


   
     ጋብቻ ለመመስረት ያሰበ አንድ ወጣት ከቤተሰብና ከጓደኞቹ ጋር ተማክሮ ከጨረሰ በኋላ የመንፈስ አባቱ ዘንድ በመሔድ ይህንን ውሳኔውን አስረዳቸው፡፡ ጥበበኛውም አባት ለማግባት ያለውን ጉጉት በልጁ ፊት ላይ እያስተዋሉ አሳቡ መልካም እንደሆነ ገልጸው ማስታወሻና ብዕራቸውን በማውጣት “ስለ ልጅቷ ትንሽ ነገር ንገረኝ” በማለት ጥያቄ አቀረቡለት፡፡ እርሱም እንዲህ አለ “ትውልዷ ከነገስታት ዘር እድገቷም በምቾት መሐል ነው” አለ፡፡ እኚህም አባት በሙሉ ልብ ሆነው በያዙት ማስታወሻ ላይ ዜሮ ጻፉ፡፡ ወጣቱም ስለ ልጅቷ ማብራራቱን ቀጠለ፡-
“በጣም ውብ ናት” አለ፡፡ እርሳቸውም ሌላ ዜሮ ጻፉ፡፡
“በጣም ዝነኛ ናት” አለ፡፡ ደግመው ሌላ ዜሮ ጻፉ፡፡
“በጣም ሀብታም ናት” አለ፡፡ ጥበበኛውም ሌላ ዜሮ ጻፉ፡፡
“በጣም ምሁር ናት” አለ፡፡ አሁንም ሌላ ዜሮ ጻፉ፡፡
“በጣም ዘመናዊ ናት” አለ፡፡ ተጨማሪ ሌላ ዜሮ ጻፉ፡፡
በመጨረሻ ግን የረሳውን አንድ ነገር ነገራቸው “ልባም እንዲሁም ሕይወቷ ለእግዚአብሔር ክብርና ምስጋና የተሰጠ ነው” አላቸው፡፡ ጥበበኛውም አባት ፊታቸው ላይ ፈገግታ እየተነበበባቸው አስቀድሞ ከጻፉአቸው ስድስት ዜሮዎች ፊት አንድ ቁጥርን ጽፈው  “በል ሂድና አግባት” አሉት፡፡  ወጣቱም በደስታ ከፊታቸው ሄደ፡፡
       ማስተዋል የጎደለው ፍቅር ጥልቀት የሌለው መሳሳብ ውጤት ነው፡፡ ብዙ ጊዜም በሌላው ሰው አካላዊ ገጽታና ውጫዊ አቋም ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ምንም እንኳን መማረክ ወደ ፍቅር የሚመራ አንደኛው መንገድ ቢሆንም እውነተኛ ፍቅር ግን በአካላዊ ውበት፣ በአፋዊ መስፈርት ከመሸነፍ ያለፈ ነው፡፡ አካላዊ ውበት የጊዜያዊ ጉጉት መገለጫ ሲሆን ፍቅር ግን በሌላው ውስጥ ያለውን መልካሙን ነገር በመሻት ትዕግስትን መሰረት የሚያደረግ ነው፡፡ ይህም የትኛውንም ልብ የመንካት፣ በላቀና በጠለቀ መንገድ የመግዛት ጉልበት ነው፡፡
         ማንኛውም ሰው በዘመኑ የሚያሳልፋቸው ትልልቅም ይሁን ትንንሽ ውሳኔዎች አሉ፡፡ ሕይወትም በዚህ የዕለት ተዕለት ቋሚ የመምረጥና የመወሰን ተግባር ላይ የተመሰረተች ናት፡፡ ጋብቻ የእኛን ትልልቅ ውሳኔ ከሚፈልጉ ነገሮች አንዱ ነው፡፡ የምናመልከውን እንመርጣለን፣ የምንኖርበትን አካባቢ እንመርጣለን፣ የልባችንን የምናካፍለው ባልንጀራ እንመርጣለን፣ በትዳር አጋር የሚሆነንን እንመርጣለን፣ በአጠቃላይ መሆን የምንፈልገውን እንመርጣለን፡፡ በእርግጥ ምርጫችንን ከምንኖረው በላይ ተጽእኖ ወደ ኑሮአችን የሚያመጣውን መኖራችን ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን በዚህም ውስጥ ከእውነት ጋር ያለን ትስስር ሊደበዝዝ አይገባም፡፡ ምርጫችን ውስጥ ሞትም ሕይወትም፣ ደስታም ሀዘንም፣ ክብርም ውርደትም አለ፡፡ መርጠን ዘመናችንን የእንባ ልናደርገው መብቱ የእኛ ነው፡፡
         ብዙ ጊዜ ከትዳር ጋር ተያይዞ የሚነሣ መጠይቃዊ አባባል አለ፡፡ ልጅቱን ሀብት ያለው ያግባሽ ወይንስ አፍ ያለው? ብለው ቢጠይቋት አፍ ያለው አለች፡፡ ምነው? ቢሏት አፍ ያለው ብር ያለውን ሀብቱን ያስጥለዋል አለች እየተባለ ይነገራል፡፡ መኖር ከሚጠይቃቸው መሠረታዊ ነገሮች መካከል አፈኝነት (ተናጋሪ) እንደ አንድ አስፈላጊ ነገር እየተቆጠረ መምጣቱን የማያስተውል ያለ አይመስለንም፡፡ አንድ አባት ሲመክሩ “ልጄ ዓለምን የሚያስተዳድሩት ቅኖች ሳይሆኑ አፈኞች ናቸውና ቀን በሚያመጣው አትደነቅ” ብለዋል፡፡
        ዛሬ ዛሬ ለከፍታው ለመቆጣጠር አፈኛ እንደመሆን ያገለገለ ነገር የለም፡፡ (በሥጋ አተያይ) ከቤተሰብ ጀምሮ በአካባቢያችን፣ በሥራ ቦታ፣ በማኅበራዊ አብሮነቶች፣ በመንፈሳዊው ሕብረት ውስጥ እንኳን ሳይቀር አፈኞች ባለ ብዙ ትኩረት ባለቤት ናቸው፡፡ እንደ ፍሬያማ ዛፍ ከነመልካምነታቸው ያቀረቀሩ በሰው ልብ ውስጥ መታየታቸው ትንሽ ነው፡፡
       ዓለማችን ላይ ብርቱ ተናጋሪዎችና አሳማኞች እንዳሉ እናውቃለን፡፡ ሰው ገድሎ ጽድቅን የሚሰብኩ አሳምነው ያሉትን የሚያስፈጽሙ ተናጋሪዎችን ምድራችን እያስተናገደች ነው፡፡ የጠነከረውን ልብ እንደሚፈረካክሱ፣ ዐለት የሆነውን አሳብ እንደሚያለዝቡ የሚነገርላቸውም ጥቂት አይደሉም፡፡ ዳሩ ግን ዕለት ዕለት ሽቅበት እንጂ ማሽቆልቆል ለማያውቀው የሰው ልጆች ጥያቄ ምላሽ መሆን አልቻለም፡፡ ዓለም አፈኞች አሏት ቅኖች ግን የሏትም፣ ብዙ የሚናገሩ አሏት ጥቂት የሚተገብሩ ግን ድሀ ናት፣ የምላስ ቸሮች የልብ ቀማኞች፣ አፈ ጮሌ ልበ ጩቤዎች የመልክዓ ምድራችን አብላጫ እድምተኞች ናቸው፡፡
      ከእያንዳንዱ አመጽ ጀርባ ያለው ትልቁ ኃይል ገንዘብ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በትምህርቱ ገንዘብን ሌላኛው ጌታ አድርጎ እንዳቀረበውና እንዳስጠነቀቀን ቅዱስ መጽሐፍ ይነግረናል፡፡ (ማቴ. 6÷24) ጥበብና ማስተዋል የበዛላቸው ሁሉ ምድራችን የሀብት እጥረት እንደሌለባት ይናገራሉ፡፡ በእርግጥም ዓለማችን የፍትህና የፍቅር እንጂ የንዋይ እጦት ችግርተኛ አይደለችም፡፡ ሰው ከሀብቱ ማስተዋልን ካልተማረ ልንገለገልበት በሚገባው ነገር መገልገያ መሆን አይቀርም፡፡ ብዙ ሀብት ጥቂት ማስተዋል፣ ብዙ ንብረት አነስተኛ ፍቅር፣ ብዙ ገንዘብ ትንሽ ርኅራኄ በሌላቸው ባለ ጠጎች ድሆች ለጥቂቶች ኑሮ ማገዶ ሆነዋል፡፡ 
       ሀብት ካለው ይልቅ አፍ ያለውን ለመምረጥ የወሰነችው ልጅ፤ ከአፈኛው ይልቅ ብራሙን የምታስቀድመውም ልጅ ሁለቱም ለምርጫቸው የሚያጣቅሱት ምክንያት አላቸው፡፡ ነገር ግን የእኛን አሳብ ከማስነበባችን በፊት እናንተ በርእሱ ዙሪያ የታያችሁንና የተሰማችሁን በአድራሻችን እንድትልኩልን አልያም አስተያየት በመስጫው ላይ እንድትጽፉልን መጋበዙ የተሻለ ሆኖ ስላገኘነው ትሳተፉ ዘንድ በአክብሮት እንጋብዛለን፡፡
ይቀጥላል


Friday, June 15, 2012

ምክር


  
        የፈለከውን ነገር ሁልጊዜ ላታገኝ ትችላለህ፡፡ ያገኘኸውን ነገር መውደድን ግን ተለማመድ፡፡ መሻትህ ሁሉ ላይኖርህ ይችላል ያለህን መንከባከብ ግን አትርሳ፡፡  ኑሮዬ ይበቃኛል ማለት ስለ ግብህ ማሰብ አቆምክ ማለት አይደለም፡፡ በዚህ ውሳኔ ማረፍ ቅሬታን ያርቅልሃል እምነት ማጣትን ያስወግድልሃል ተስፋ መቁረጥንና የተዛባ አመለካከትህንም ያስተካክልልሃል፡፡
      አሳብህም ልብህም ሰፊ ይሁን አመለካከቶችህ ሁሉ ሕያው እግዚአብሔርን በመተማመን ቅዱሱን መንፈስ ክንድ በማድረግ ላይ የተመሰረቱ ይሁኑ፡፡ ሥራህንና ቃልህን ለማዛመድ ትጋ፡፡ የልብህና የእጅህ  እርስ በእርሳቸው እንዳይጣረሱ ጥረት አድርግ፡፡ ምድራችን ስለፍትህ በሚያወሩ ግን ደግሞ ለሕግ በማይገዙ ፍቅርን በሚሰብኩ ግን በፍቅር ለመኖር ምንም ጥረት በማያደርጉ የጌታን  ቃል በሚያደምጡ ግን ደግሞ ቃሉን በማይኖሩ ሰዎች የተሞላች ናት፡፡
       ልብ በል ወሳኙ ነገር የምትኖርበት ቦታ ሳይሆን  አኗኗርህ ነው፡፡ ከምታምንበት ነገርም በላይ ዋጋ ሊሰጠው የሚገባው ባመንክበት ነገር እንዴት ትኖራለህ የሚለው ነው፡፡ ሁላችንም በሕይወት ያለነው ደስተኞች እንድንሆን ነው፡፡ ለዚህም የእግዚአብሔርን ድምጽ አድምጥ ለኑሮህ ብልጥግና ፍቃዱን ተከተል ስኬታማ ለመሆንም በእውነት ላይ ቁም፡፡  እኛ ቀብረን የምናዝነውን ሀዘን ቆመው፣ እኛ ርቦን የምንሰቃየውን ስቃይ ጠግበው፣ እኛ አጥተን የምናነባውን እንባ አግኝተው የሚያነቡት ብዙ ናቸው፡፡ ልዩነቱ እኛ ሁሉን ለእርሱ ክብር ማድረጋችን ነውና ሁኔታዎችህን ሁሉ ለእርሱ ክብር ማድረግን መልመድ ይገባሃል፡፡  
       ማንም ሰው ከጠባቡ ግለኝነት ሕይወት ወደ ሰፊው ጠቅላላው የሰው ልጅ ምልከታ ከፍ እስኪል ድረስ መኖርን ተማረ አይባልም፡፡ ማለዳ ማለዳ አዲስ ትርጉም ባለው መንገድ ለመኖር ራስን መመልከታችን ወደ ፊት ከመመልከት ጋር ሊዋሐድ ይገባዋል፡፡ ያለህን ስትሰጥ ጥቂት ሰጥተሃል ራስህን ስትሰጥ ግን ያኔ በእውነት ሰጥተሃል እንደሚባለው የእኛን ብቻ ሳይሆን እኛንም ለሌሎች ማካፈል አለብን፡፡ ለምሳሌ ማየት ለተሳነው ሰው መመልከት ቢችል ኖሮ ሊያከናውን የሚችለውን እኛ ብናከናውንለት፣ መራመድ ለማይችል ቢራመድ ኖሮ ሊሠራው የሚችለውን እኛ በመራመድ ብንሠራት፣ መናገር ለማይችለው መናገር ቢችል ኖሮ የሚያስረዳውን አፍ ሆነን ብንናገርለት ይህ ራስን ማካፈል ነው፡፡ በፍቅር መግዛት በጥላቻ ከመግዛት፣ ብቸኝነትን ከመንከባከብ ሕይወትን ማጋራት አብዝቶ የተሻለ ነው፡፡ በትህትና ልንሠራው የምንችለውን መልካም ነገር በሸካራ ቃላቶች ልናውከው፣ በግለኝነት ልናፍነው አይገባም፡፡
       እርግጠኝነት ያለው ፍቅር የሕፃናት ነውና ለእነርሱ በእርጋታ ንገራቸው፡፡ እንክብካቤን የሚፈልግ ፍቅር ያለው በአዛውንቶች ዘንድ ነውና በእድሜ ለገፉ በእርጋታ ንገራቸው፡፡ ርኅራኄን የሚፈልግ ፍቅር ያለው በድሆች ዘንድ ነውና ለእነርሱ በእርጋታ ንገራቸው፡፡ በከንቱ የሚተጋ ፍቅር ያለው በኃጢአተኞች ዘንድ ነውና ለስሁታን በእርጋታ ንገራቸው፡፡ ሕያውና ዘላለማዊ ፍቅር ያለው በጌታ ዘንድ ነውና የሰውን ዓመጽ ለማሸነፍ ሕይወቱን ለሰጠው ለእርሱ በእርጋታ ተናገር፡፡ የጉብዝና ወራት ፍቅር ያለው በወጣቶች ዘንድ ነውና ለእነርሱም በጥበብ ተናገር፡፡ ጌታ የማያየው የለምና በምታየው ተስፋ አትቁረጥ፣ እርሱ የማይሰማው የለምና በምትሰማው አትመረር፣ እርሱ የማይደርስበት የለምና ባልያስከው ነገር አትቆጭ፣ ጌታ ከምናየው ከምንሰማው ራሳችን ለራሳችን ከምንነግረው በላይ ነውና ልብህ በዚህ ይጽና፡፡ መዋደድ ይብዛላችሁ!!

Tuesday, June 12, 2012

ጅቡም ይበላል (ክፍል አራት)



  ክቡር ከበደ ሚካኤል ከፃፉት ግጥም መካከል የተወሰነውን ለማጠቃለያ እንደ መግቢያ እንጠቀምበት፡፡
ድንበሬን ማን ገፍቶት አይሉም አይሉም፤
ሚስቴንስ ማን ነክቶአት አይሉም አይሉም፤
አጥሬን ማን ጥሶት አይሉም አይሉም፤
         ጊዜው ከደረሰ ይደረጋል ሁሉም፡፡
         አማራጭ ከሕይወታችን ጋር በብርቱ የተሳሰረ ነገር እንደሆነ በአንድም በሌላም መንገድ መተማመን ላይ እንደደረስን አምናለሁ፡፡ ሰው ነፃ ፈቃድ ያለው ፍጥረት በመሆኑ የመምረጥ መብቱ የተጠበቀ ነው፡፡ ሰው ነፃ ፈቃድ ባይኖረው ኖሮ ዛሬ ድረስ በገነት የአትክልት ስፍራ አጥሮ በታሰረ ገመድ የሚንገላታ እንስሳ ከመሆን አይለይም ነበር፡፡ ምክንያቱም ሰውና መላእክትን ከሌሎቹ ፍጥረታት የሚለያቸው አንዱ ነገር ነፃ ፈቃድ ያላቸው መሆኑ ነው፡፡ መከራ በምንሰማውና በምናየው ልክ በሆነባት ዓለም ላይ አማራጭ ማጣት ነፃ ፈቃድ ላለው የሰው ልጅ ቢለዋ ተሰጥቶ ሥጋ እንደመከልከል ነው፡፡
         ከላይ ለመንደርደሪያነት ያነሣነው ግጥም የሚነግረን ጊዜው ከጠየቀ ሰው የማይሆነውና የማይከውነው ነገር እንደሌለ ነው፡፡ ስለ ሕይወት የተለያዩ ሰዎች የተለያየ አመለካከትና እይታ እንዳላቸው እናስተውላለን፡፡ ጥቂቶቹን ለመመልከት ያህል “ሕይወት ሽክርክሪት ናት፤ አንዳንዴ ከፍ፤ ሌላ ጊዜ ዝቅ ትላለህ፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ዝም ብለህ ትሽከረከራለህ” ሌላ ደግሞ “ሕይወት እጅግ ፈጣንና ኃይሉን ሁሉ ልንጠቀምበት እንደማይቻለን አስር ማርሽ እንዳለው ብስክሌት ናት” በተጨማሪም “ሕይወት በካርታ ጨዋታ ትመሰላለች፤ በእጅህ ላይ ባሉት ካርዶች መጫወት ይኖርብሃል” የሚል የተለያዩ አመለካከቶችን ማስተዋል እንችላለን፡፡
        ከሁላችንም ገሃዳዊ ኑሮ በመነሣት ለሕይወት ማብራሪያ ብንፈልግ ሕይወት ምርጫ እንደሆነች እንረዳለን፡፡ ሰዎች በአደጉ አገሮች ላይ ለመኖር ያላቸውን ጉጉት ከሚያንረው ምክንያት አንዱ የአማራጭ መኖር ነው፡፡ በዚያው መጠን ደግሞ በታዳጊ አገሮች ላይ ለመኖር ፍላጎት የማጣት ስሜት የሚስተዋለው በአማራጭ ማነስ አልፎም ተርፎ አለመኖር የተነሣ ነው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ሰው ከራሱ ጋር ላለመኖር ውሳኔ ላይ የሚደርሰውም በጊዜው ለገጠመው ነገር ልብን የሚሞላ፤ ሚዛን የሚደፋ አማራጭ መፍትሔ አለማግኘቱ ቢኖርም እንኳን አለማስተዋሉ ነው፡፡
           ሕይወት ከግምታችን እንዲሁም ስሜታችን ከሚነግረን ከፍ ያለ ነገር ትፈልጋለች፡፡ ለዚህም ደግሞ ትክክለኛ መሻቷን የሚሞላና ለማንኛውም ነገር ዘላቂ የሆነ አማራጭ ትፈልጋለች፡፡ ሰው ይህንን ከሰው ምላሽ ሊያገኝለት አይችልም፡፡ ሥጋ ለባሽ ሁሉ እንዲህ ላለው ጥያቄ ከእውቀቱ፣ ከንብረቱ፣ ከሥልጣኑና ከዝናው ዘላቂ መፍትሔ ሊያወጣ አይቻለውም፡፡
          ነቢዩ እንዳለ “እግዚአብሔር የርስቴ እድል ፈንታና ጽዋዬ ነው÷ ዕጣዬንም የምታጠና አንተ ነህ፡፡ ገመድ ባማረ ስፍራ ወደቀችልኝ ርስቴም ተዋበችልኝ፡፡ (መዝ. 15÷5) እንዳለ አማራጭ ወደሌለው ምርጫችን፣ መፍትሔውን የሚያስንቅ መፍትሔ ወደሌለ የዘላለም መፍትሔያችን፣ መድኃኒትነቱን የሚያህለው ወደሌለ መድኃኒት ዘወር ማለት ግድ ይሆናል፡፡ ከሁከት ለመውጣት የሞከርናቸው አማራጮች ሁሉ የማባባስን ያህል ከሆኑብን እርሱ ጌታ አእምሮን የሚያልፍ ሰላም አለው፡፡ ኑሮ አታካች ሆኖብን ሲነጋ መቼ በመሸ ሲመሽ መቼ በነጋ ለምንል እርሱ የበጎ ስጦታ የፍጹም በረከት ጌታ ነው፡፡ ነውርን መሸከም፣ ኃጢአትን መታገስ ላዛላችሁ እርሱ በምህረቱ ባለጠጋ ነው፡፡ ሀዘን ልባችንን ለሸረሸረው እርሱ ለዘላለም የማንታወክበት ደስታ ነው፡፡
           ወንጌላዊው ማርቆስ አማራጭ ያለችውን ሁሉ አስሳ በመጨረሻ ሞትን ፊት ለፊት መጠበቅ ዕድል ፈንታዋ ስለሆነባት ሴት ታሪክ ያስነብበናል፡፡ (ማር. 5÷25) ጌታ ከምኩራብ አለቆች አንዱ ታናሽቱ ልጁ ታማ እንዲፈውስለት ለመነው፡፡ ጌታም እሺታውን በተግባር ሊፈጽም በመንገድ ሳሉ ስሟ ያልተጠቀሰ አንዲት ሴት ከአሥራ ሁለት ዓመት ጀምሮ ደም ይፈሳት በዚህም በሽታ በብርቱ ትሰቃይ ነበርና የልብሱን ጫፍ ብነካ እድናለሁ በሚል እምነት ቀረበች፡፡ ከታሪኳ እንደምንረዳው ወደ ብዙ  መድኃኒት አዋቂዎች ዘንድ እንደሄደች ነገር ግን ከዕረፍት ይልቅ ስቃይ እንደበዛባት፤ ገንዘብዋንም ሁሉ ከስራ ከመሻል ይልቅ እንደባሰባት እንረዳለን፡፡
           በምኩራብ አለቃውና በዚህች ሴት መካከል ሰፊ ልዩነት አለ፡፡ እርሱ ባለ ሥልጣን ሲሆን እርሷ ከተራው ሕዝብ መሐል ናት፡፡ እርሱ በኅብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ግምትና ክብር የሚሰጠው ሰው ሲሆን እርሷ ደግሞ ትኩረት የተነፈገች፣ ለማኅበራዊ ሕይወት እንኳን መጠጊያ ያጣች፣ ችግሯን በማባበል የተጠመደች ናት፡፡ (ዘሌ. 15÷19) ግን ለሁለቱም ያለ ልዩነት ጌታ ያስፈልጋቸው ነበር፡፡ እርሱ ሥልጣኑ የማይፈታው፤ እርሷ ደግሞ ገንዘብዋ የማይፈውሰው ችግር ነበረባቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ የሚሆን አማራጭ መፍትሔ በዙሪያቸው አልነበረም፡፡ በሚበልጠው (በሞት) የተፈተነ መሳይ የሌለው አማራጫችን ጌታ ግን ብቸኛ መድኃኒት ሆናቸው፡፡
            ኢያኢሮስ ለአሥራ ሁለት ዓመታት የአይኑ ማረፊያ፣ የቤቱ ድምቀት የሆነች ልጁን ሲያጣ፤ ሴቲቱ ደግሞ ለአሥራ ሁለት ዓመታት ስታንቀላፋ እያባተተ፣ ስትነቃ ልብዋን እያዛለ ያሰቃያት ከነበረው በሽታ የተነሣ ለመኖር ያላት ጉጉት ተሟጦ ተስፋ ቆርጣ ነበር፡፡ የእግዚአብሔር ቃል የሴቲቱን የግል ጥረት ውጤት “ባሰባት እንጂ አልተሻላትም” በሚል ነው፡፡ ልብ ብለን ካስተዋልን ሴቲቱ ከፍለጋዋ ስትመለስ ዋናዋ ላይ አይደለም የቆመችው ይልቁንም ባሰባት(ኔጌቲቭ) ከምርጫዋ ዕድል ፈንታዋ ይህ ነበረ፡፡ ጉልበት ሳላት፣ ገንዘብ ሳላት ጌታን አላገኘችውም፡፡ አማራጮችዋ ሁሉ ሲሟጠጡ፣ የረገጠችው ደጅ ሁሉ ለመፍትሔ ዝግ ሲሆን፣ እርሷና ሞት ፊት ለፊት ሲፋጠጡ ግን ቀጠሮ የማይሰጥ መድኃኒት አገኛት፡፡ ሄዳ ያንኳኳችው ሲዘጋ የሞት መድኃኒት ወደ ሕይወቷ አንኳኩቶ መጣ፡፡ እርሱ ክርስቶስ ከማንኛውም ሁኔታ ጋር ብንፋጠጥ፣ የትኛውንም አይነት የኑሮ ተግዳሮት በእድሜያችን ብናስተናግድ መቼም የማይታጣ ምርጫችን ነው፡፡
          ገንዘብ እንደሌላችሁ ለሚሰማችሁ ጌታ ብል የማይበላው መዝገብ ነው፡፡ ጤና እንዳጣችሁ ለሚሰማችሁ ክርስቶስ የሞት መድኃኒት ነው፡፡ መጠለያ እንደሌላችሁ ለሚሰማችሁ ሁሉን የሚችል ጌታ አምባ መጠጊያ ነው፡፡  እንደተጠላችሁ እንደተተዋችሁ ለምታስቡ እርሱ በዘላለም ፍቅር የሚወድ ደግ ሳምራዊ ነው፡፡ ፍርሃትና ጭንቀት እንደ አውታር ለወጠራችሁ እርሱ አእምሮን ሁሉ የሚያልፍ ዕረፍት ነው፡፡ ተወዳጆች ሆይ ክርስቶስ ላለው ክርስቲያን አማራጭ ማጣት ጥያቄው አይደለም!

Friday, June 8, 2012

ጅቡም ይበላል (ክፍል ሦስት)


       
       በዚህ ክፍል ካለፈው የቀጠለ አስተያየት እናቀርባለን፡፡ እስካሁን የልባችሁን አሳብ ላካፈላችሁን ደግሞም አስተያየት ለላካችሁልን ሁሉ የእውነት እናመሰግናለን፡፡ በመጀመሪያ ባለፈው ክፍል ከኢኮኖሚና ከፖለቲካ አንፃር እንየው በማለት ወደጋበዘን ወንድም አስተያየት በማስከተልም ሌላ ሁለት አስተያየቶችን እንመለከታለን፡፡
       ፍትሕ፣ ነፃነት፣ ሰላም፣ እኩልነት እነዚህ ሁሉ በምንም የማንደልላቸው ርሀቦች ናቸው፡፡ የእነዚህን መጓደል እንጀራ አይተካውም፡፡ ራሳችን ለራሳችን የምንነግረው ማንኛውም ሽንገላም ከብዝነት አያሳርፈውም፡፡ ሰዎች እነዚህ ካልተከበሩላቸው የአሳብና የአካል ትግላቸው አይቋረጥም፡፡ ሰው አማራጭ ካጣ ቀይ መስመር፣ ነጭ መስመር የሚባል ወሰን አይወስነውም፡፡ ለእርሱ ልኬቱና ድንበሩ እውነትና ፍትሕ ነው!
       መሪዎች ጠንቅቀው ሊያውቁት ደግሞም በጥበብ ሊመላለሱበት አግባብ የሆነው ነገር ቢኖር የሕዝቦች ሕሊናዊና አካላዊ ፍላጎት በቅጡ ምላሽ ካላገኘ ብሶት እንደ ፍግ እሳት ውስጥ ውስጡን እየነደደ፤ አይነካም ያሉት እንደሚነካ፣ አይደፈርም ያሉት እንደሚደፈር፣ አይሻርም ያሉት እንደሚንኮታኮት ነው፡፡ ምክንያቱም የጊዜ እንጂ የሰው ጀግና የለውምና ነው፡፡ እንዲህ ያለው ነገር አገርን በመምራት ደረጃም ብቻ ሳይሆን ቤተሰብን በመምራት ውስጥም ይሠራል፡፡ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት ባልቻሉ አባቶቻቸው ስም ላለመጠራት ጥረት የሚያደርጉ ልጆችን አስተውለናል፡፡ ከከፋ ጅቡም ይበላል!
      ዛሬ ብዙዎች የደከሙበትና የሚሟገቱለትን ፖለቲካ የኢኮኖሚው አለመረጋጋትና የዋጋ መናር እያበላሸው ነው፡፡ ምክንያቱም የራበው ሰው የሚሰማህ ከልቡ በጆሮው ሳይሆን ከአንገት በሆዱ ነው እንዲሉ ልብ ያለው ልብ ይበል በማለት ልለፈው፡፡ ክብረት ይስጥልኝ!
                                                                                           ፈታሒ
4. ቤተ ፍቅር ስለ አማራጭ፣ አመራጭ ስለማጣትና አማራጭ ካልተገኘ እንኳን በጅብ የተነከሰው በግ ቀርቶ ጅቡም ሊበላ ይችላል… ለምን ሲባል ደግሞ ‹‹ወገኔ እዬዬም ሲደላ ነው›› ሲባል አልሰማህም እንዴ የሚለው በማኅበረሰባችን የእለት ተእለት ኑሮ ውስጥ የሚንጸባረቀው የቆየው ብሂል በአያ ጅቦና በበጊቱ ተረክ የቀረበውን ታሪክ የሚያጠናክር ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ቤተ ፍቅር በታሪክ አሰደግፋ ያቀረበችው ጽሑፍ ብዙ ሊያነጋግረንና ሊያወያየን እንደሚችል ባምንም ግን አማራጭ በራሱ ፍጹም ያልሆነ ማጠፊያው ሲያጥረን ከእንግዲህስ የመጣው ይምጣ በሚል የምንወድቅበት የቢቸግር ምርጫ እንደሆነ ሊያሳዩ የሚያስችሉ መከራከሪያ አሳቦችን በመደርደር የውይይቱን ድንበር፣ ወሰን ማስፋት ይቻል ይመስለኛል፡፡ እናም በዚሁ መንፈስ ጥቂት ነገሮችን ለማለት ወደድሁ፡፡
        መቼም እኛ ኢትዮጵያውያን የተረት ድኃ አይደለንምና ከተነሳው ታሪክ ጋር አብሮ ሊሄድ የሚችል ሌላ ተረት ልጥቀስ ግን በሀገራችን እንደ ጅብ በተረትና በብሂል የተንበሸበሸ ሌላ የዱር አውሬ ይኖር ይሆን እንዴ አንባቢዎቼ፣ እናም ተረታችን አሁንም ከጅቦች ሰፈር የወጣ ወይም የራቀ አይደለም፤ ተረቱ እነሆ፡- ‹‹ጅብ ከሚበላኝ ጅብ በልቼ ልቀደስ፡፡››  ይህ እንግዲህ በጅብ ከመበላትና ጅብን ከመብላት የትኛው ነው የተሻለው አማራጭ በሚል ተጠየቅ የቀረበ ተረት መሆኑን አንባቢ ልብ ይላል፡፡ በመሠረቱ የተረቱ አብይ አሳብ መቼም በቁሜ እያለሁ ጅብ ከሚበላኝ ምንም ጸያፍና የረከሰ ፍጡር ቢሆንም ጅቡን በልቼ ብቀደስ አሊያም የሚወሰንብኝን ቀኖናዬን ብቀበል ሳይሻላል አይቀርም የሚል ስሜት ያለው ነው የሚመስለው፡፡
        ያው የዚህ ውሳኔ መነሻ ደግሞ በእውቀቱ ስዩም የተባሉ ጸሐፊ በአንድ ወቅት ስለ ራብ ባተቱበት መጣጥፋቸው እንደጠቀሱት፡- ‹‹ከሙሴ ሕግ ይልቅ የጨጓራ ሕግ ያይላልና›› ራቤን በማስታገስ ነፍሴን ላቆያት፣ ሕይወትም ትቀጥልና ከዛ በኋላ በጅብ የተነከሰን በግ መብላት ትክክል ነው ወይስ አይደለም፣ ያረክሳል ወይስ አያረክስም… ወደሚለው ክርክር ለማምራት እንችላለን የሚል ይመስለኛል፤ የዚህ ክርክር ጫፍ ደግሞ ከተቸገርን፣ አማራጭ ከሌለንማ እንኳን በጅብ የተነከሰችው በጊቱ ቀርታ ጅቡስ ሌላው ሌላውስ ይበላል እንጂ በክፉ ቀንማ ነፍስን ለማቆየት ክቡር የሆነ የሰው ልጅስ ተበልቶ የለ እንዴ ወደሚለው የሚጎረብጥ አማራጭ ሐቅ የሚያደርሰን ይመስለኛል፡፡
         መቼም በአዲስ ኪዳን ዘመን ውስጥ ሆነን ‹‹በይበላልና በአይበላም›› ‹‹በያረክሳልና በአያረክስም›› ኦሪት ሕግ እንደ አንዳንዶች ወገኖቻችን ጉንጭ አልፋ ክርክር ውስጥ ለመዶል የሚሻ ሰው ካለ የነገራችን ጭብጥ ‹‹ከይበላልና አይበላም›› ‹‹ከያረክሳልና ከአያረክስም›› እሳቤ በእጅጉ እልፍ ስለሚል አልተገናኝተንም ከማለት ውጭ የምኖረው አይኖረኝምና አሳብ ሳላንዛዛ በዚሁ ወደተነሳሁበት ቁምነገር ማጠናከሪያ አሳቦች አብረን በአንድነት እናዝግም፡፡
        መቼም ሰው በሕይወት ትግል፣ ሰልፍና ግብግብ ውስጥ ከሚገጥሙት ውጣ ውረዶችና አጣብቂኝ ለመውጣትና ለማምለጥ የተሻለውን አማራጭ መጠቀሙ ሐቅ ነው፤ ግን በራሱ ያ አማራጭ ፍጹም ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም ባይ ነኝ ምክንያቱም እውነታውን ስንመረምር ያን አማራጭ እንደ አማራጭ አድርገን የወሰድነው ቢያንስ ይሻላል በሚል ማነጻጸሪያ ስለሆነ ነው የሚለው እሳቤ ደግሞ የውይይታችን ማሾሪያና ማጠንጠኛ ዋና እሳቤ ይሆናል ማለት ነው፡፡ በሀገራችን የቆየ እንዲህ የሚል ብሂል አለ፡- ‹‹ከማያውቁት መልአክ የሚያውቁት … ምንትስ ያሻላል፡፡›› በተረቶቻችን ውስጥ ለዘመናት በማኅበረሰባችን ውስጥ የቆየውን የሕይወት ፍልስፍና፣ የኑሮ ዘይቤ የሚገልጹ፣ ታሪካችን፣ ባሕላችን፣ ማንነታችንና ማኅበረሳበዊ አስተሳሰባችን የቆመበትን መደላድል የሚያሳዩ እውነታዎች የታጨቁበት ለመሆኑ ምስክር መቁጠር የሚያሻን አይመስለኝም፡፡ እናም ተረት ማብዛቴ ለዚያ ነው እንጂ አንባቢያንን ለማታከት አይደለም፡፡
       እናም ከላይ የጠቀስነው ተረትም ሊገልጽልን የፈለገው እሳቤ አረረም መረረም፣ ከፋም ለማም፣ ተመቸንም አልተመቸንም… እየተቋሰልንም ቢሆን እየተዳማን ከለመዱት ጋር መኖር ይሻላል እንጂ ምን ሲደረግ አዲስ አስተሳሰብ፣ አዲስ ሥልጣኔ፣ አዲስ የኑሮ ዘይቤ/ፍልስፍና… እሹሩሩ የምንልበት ጫንቃ ሊኖረን ይችላል በሚል ግትር አቋም ላይ የተደላደለ እሳቤን የሚያንጸባርቅ ይመስላል የተረቱ ጭብጥ እናም በታሪካችን ውስጥ አዲስ አስተሳሰብን፣ አዲስ የኑሮ ስልትን፣ አዲስ የስልጣኔ ጎዳናን አማራጭ ለማስተዋወቅ የሞከሩ ሁሉ ከመወገዝና ከመረገም ጦስ እንዳላመለጡ የቅርብ ጊዜ ታሪካችንም ምስክር ነው፡፡
        በዚህ ረገድ መቼም እንደ እምዬ ምኒሊክ ክፉኛ የተቸገረ ንጉሥ ኖሮን የሚያውቅ አይመስለኝም፡፡ ለአብነት ያህል አፄ ምኒልክን በስልክ መነጋገር ያዩ የዘመኑ መኳንትና ካህናት ጃንሆይ ከእርኩስ መንፈስ ጋር እየተነጋገሩ ነው በማለት ክፉኛ እንዳሟቸው፣ እንዳብጠለጠሏቸውና በቤታቸው ስልክ የገባ አንድ መኳንትም ስልኩን ጠበል አስረጭተው በላዩ ላይ እሳት መልቀቃቸውን ታሪካችን ይነግረናል፡፡
       ከተነሳንበት ርእስ ብዙም እንዳንርቅ ስለ አማራጭ ሲነሳ ብዙዎቻችን በሕይወታችን ያልሞከርነውን አማራጭ ከማሰብና አዲስ ነገረን ከመቀበል ይልቅ ከለመድነው ነገር ጋር ተስማምተን እየመረረንም ቢሆን እየተሳቀቅን መኖርን መምረጥ ምንፈልግ ይመስለኛል፡፡ ያልተሞከረና አዲስ ነገርን አማራጭ አድርጎ ለመቀበል የሚተናነቀን እንደሆንን ራሳችንን ብንፈትሽ መልሰን ራሳችንን ሳንታዘበው እንቀራለን ብዬ እገምታለሁ፡፡ ስለዚህም እየመረረንም ሆነ እያለቀሰንና እየተራገምንም ቢሆን ‹‹ከማናውቀው መልአክ ከምናውቀውና ከሚያውቀን እንትና ጋር መኖር…›› የተሻለ አማራጭ መስሎ ስለሚሰማን ያልተሞከሩ አዳዲስ አማራጮችን ለመውሰድ ገና ስናስበው የጥርጣሬ መንፈስ የሚወረን ይመስለኛል፤ ይህ ደግሞ ምክንያት የለሽ ፍርሃት የሚወልደው ተልካሻ አስተሳሰብ ከመሆን ባለፈ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል፡፡
        በሌላ በኩል ደግሞ መራጭ ወይም አማራጭን ፈላጊ ሰው ማለት ይላሉ አንዳንድ ሰዎች ‹‹ከብዙ መጥፎዎች መካከል የተሻለውን መጥፎ የሚመርጥ ነው፡፡›› በእርግጥ ከብዙ መጥፎዎች መካከል የተሻለውን መምረጥም በራሱ ብልህነት ቢሆንም ፍጹምና ሁሌም ግን ትክክልና ውጤታማ ይሆናል ብዬ ግን አላስብም፡፡ በይበልጥ ይህ እውነታ የሚጎላው በመንፈሳዊ ሕይወታችን ወይም ኑሮአችን ውስጥ ስለ ምርጫዎቻችን ስናስብ ከላይ በጠየቅነው ጥያቄ ውስጥ ያለው እውነታ ፍንትው ብሎ ይታየናል፡፡
        እናም በእኛ ዘንድ የተሻለ አማራጭ ነው የምንለው የትኛው ነው… ለአላፊና ለጠፊ ደስታ ስንል ከኃጢአት ጋር ተስማምቶና ተመቻችቶ መኖር ወይስ እንደ ሎጥ ነፍሳችን እያስጨነቀንም ቢሆን የጽድቅን ሕይወት መምረጥ፣ ለጊዜያዊ ጥቅም ሲባል ሀገርንና ወገንን በሚጎዳ ስራ ውስጥ መዘፈቅ ወይስ ከእውነት ጋር በመቆም በሐቅ መኖር፣ ከአንድ ሰው ጋር በቅዱስ ትዳር መወሰን ወይስ ከዚያችም ከዚህችም ጋር ለምን ይቅርብኝ በሚል ዕድሜን መፍጀት፣ እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት ወይስ ሰውን የትኛው ነው የተሻለውና የሚበልጠው አማራጭ፣ የመስቀሉ የእውነትና የሕይወት መንገድ ነው ወይስ ሰፊውና ብዙዎች የሚመርጡትና የሚጓዙበት የሞት ጎዳና . . .፡፡
        እንደ ንጉሥ ዳዊት ‹‹ለእኔ ግን ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ይሻለኛል፡፡›› የሚል ውሳኔ የተሻለ ብቻ ሳይሆን ከሁሉም ወደሚበልጥ አማራጭ መጠጋት ግን በብዙ እንድናተርፍ ይረዳናልና የዕድሜያችን ጀንበር ሳያዘቀዝቅ የተሻለውን ብቻ ሳይሆን ከሁሉ የሚበልጠውን አማራጭ የሙጥኝ ማለቱ ብልህነት ብቻ ሳይሆን በእጅጉ የሚጠቅመንም ነው፡፡ በጹሑፌ ማጠቃለያ ለራሴና ይህን ጽሑፍ ለሚያነቡ ለአንባቢዎቼ ሁሉ ግን አንድ ጥያቄ በመጠይቅ ጹሑፌን ልቋጭ፡- የእኔና የእናንተ ወይም የእኛ የመጀመሪያችንም ሆነ የመጨረሻች አማራጫችን ወይም ምርጫችን ምንና ማን ይሆን . . .??? ቤተ ፍቅር ስለ መጀመሪያውና ስለ መጨረሻው ደግሞም ከሁሉም ስለሚበልጠው አማራጭ ወይም ምርጫ የምትለን ነገር ይኖራት ይሆን… በተስፋ እንጠብቃለን… የእኔን አበቃሁ!!!
                                                           ሰላም! ሻሎም!
                                                             በፍቅር ለይኩን ነኝ፡፡
5. የእኔ እይታ ከፍርድ ጋር በሚያያዝበት መንገድ ነው፡፡ ለቆሎ ተማሪው ምላሽ የሰጡትን መምህር ጌታ ያብዛልን ባይ ነኝ፡፡ ፍርድን ሁሉን ለሚችል እግዚአብሔር መስጠት ካልሆነ ደግሞ ቅን ፈራጅ መሆን የእውነት ዳኛ የሆነውን ጌታ የምንመስልበት አንዱና ዋናው ሂደት ይመስለኛል፡፡ ክርስቶስ ራሱ አምላክ ሆና ሳለ ነገር ግን በማንም ሊፈርድ እንዳልመጣ ተናግሮአል፡፡ እኛማ ታዲያ እንዴታ!
      አገራችን ፍርድ አዛቢዎች እንደ ሊባኖስ ዝግባ ከፍ ከፍ ያሉባት ናት፡፡ ከዚህም የተነሣ እየተቀባበሉ ማልቀስ የአብዛኛዎቻችን ሆቢ ነው፡፡ ፍርድ ከፍተኛ ማመዛዘንን ይጠይቃል፡፡ ከባሕል፣ ከሥርዓት፣ ከልማድና ከእኔነት (ወገናዊነት) በላይ ለእውነት ማድላትን፣ ለፍትሕ መሞገትን ይጠይቃል፡፡ ከተማሪው የሱታ ለእኛ የሚሆን ጥቂት ነገር ላካፍላችሁ፡፡ መምህሩ፡-

ሀ. እንደሰሙ አይፈርዱም
        አንዳንድ ቃላት ሲጠብቁና ሲላሉ ሁለት ዓይነት ትርጉም ይሰጣሉ፡፡ ታዲያ አንዳንዴ የሚጠብቀውን አላልተን፣ የሚላላውን አጥብቀን ለመግባባት የተናገርነው የሚያጣላን አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡ አንዳንድ ሰው ሲሰማ ንግግሩን አልፎ አሳቡን ለማግኘት ይጥራል፡፡ ሌላው ደግሞ ከአፍ ይውጣ እንጂ ለማድነቅም ሆነ ለመኮነን ይህ ብቻውን በቂ ምክንያቱ ነው፡፡ እነዚያ ጊዜ ስለሚወስዱ እርጋታቸውን ያስተምሩናል፤ እነዚህ ደግሞ ስለሚቸኩሉ ስሜታዊነት እናይባቸዋለን፡፡ ብዙ ወዳጅነት እንደ ሰሙ በሚፈርዱ፣ እንዳዩ በሚወስኑ ሰዎች ምክንያት እንዳልነበር ሆኖአል፡፡ እርጋታ በውሳኔያችን እንዳንፀፀት ይረዳናል፡፡
    
ለ. በፍቅር ደግፈው ይሰማሉ
        አስደናቂው ነገር ደግሞ ይህ ነው፡፡ አንዳንድ ትሁታን ሰዎች እየረዳችሁ ስሙኝ ይላሉ፡፡ እኔን እንደገባኝ ከሆነ ደግሞ እግዚአብሔር እኛንም የሚሰማን እየረዳ ነው፡፡ ያጠመምነውን በሚያቀና ጆሮ፣ መኮላተፋችንን በሚያጠራ ልብ እያዳመጠ፡፡ የምንሰማበት ሁኔታ በምንሰማው ነገር ላይ ተጽእኖው ከፍ ያለ ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንድ የሕግ አዋቂ ወደ ክርስቶስ መጥቶ “የዘላለም ሕይወትን እንድወርስ ምን ላድርግ” አለው፡፡ ጌታም ለጥያቄው ምላሽ ከሰጠው በኋላ ሌላ ጥያቄ ጨመረ፡፡ መጽሐፉ እንደሚል ሕግ አዋቂው ጥያቄውን ያቀረበው ሊፈትነው ፈልጎ ስለነበር በመልሱ ሊረካ አልቻለም፡፡ (ሉቃ. 10÷25) አሰማማችን ለእውነት ቅርብ አልያም ሩቅ ሊያደርገን አቅም አለው፡፡ 
        ከመምህሩ የምንማረው ሁለተኛው ነገር በፍቅር መስማትን ነው፡፡ በተለይ ሰዎች ድካማቸውን ሲያካፍሉን በልባዊ ፍቅር ልንሰማቸው ያስፈልገናል፡፡ የሰዎችን ድካም የምናግዝበት የመጀመሪያው ነገር በፍቅር ማዳመጥ ነው፡፡ ትኩረት መስጠት፣ ዓይን ዓይንን እያዩ ማዳመጥ፣ ፊት ለፊት ሆኖ የፈካ ፊት ማሳየት በፍቅር የመስማት ሂደቶች ናቸው፡፡ አገልጋዮች ተገልጋዮቻቸውን በፍቅር ደግፈው ማዳመጥ አለባቸው፡፡ ባል የሚስቱን ድካም በፍቅር ደግፎ ማዳመጥ አለበት፡፡ ግንኙነታችንን የሚያራዝመው፣ ከአጉል ፍርድ የምንጠበቀው በፍቅር ደግፎ በመስማት ነው፡፡

ሐ. ለሕሊና ይፈርዳሉ
        ሰዎች ስሜታቸውን፣ አካባቢያቸውን፣ ጥቅማቸውን፣ ወገናቸውን፣ ልማዳቸውን በመታዘዝ ለእነዚህ ይፈርዳሉ፡፡ መምህሩ ከተማሪው በላይ በዚያ አስተሳሰብና ልማድ ውስጥ አልፈዋል፡፡ ነገር ግን ልማድ ላወረሳቸው ሳይሆን ሕሊና ለሚላቸው ታዘዋል፡፡ ሰው በሰው፣ ልማድ በሌላ ልማድ፣ ጥቅምም በሚበልጥ ጥቅም ይተካል ሕሊና ግን በምን ይደለላል? መምህሩ የፈረዱት ለልማድና ለተማሪው ሳይሆን ለሕሊናቸው ነው፡፡ እኔም የታየኝን እንዲህ አስፍሬዋለሁ፡፡ ለእውነት ፍረዱ!
                                                                  ስም አልተጠቀሰም

ይቀጥላል

Tuesday, June 5, 2012

ጅቡም ይበላል (ክፍል ሁለት)


    በተነሣንበት ርእሰ ጉዳይ ላይ ያላችሁን አስተያየትና የግል አመለካከታችሁን እንድታካፍሉን በጠየቅነው መሠረት ከተላኩልን መካከል መርጠን ከዚህ በታች እናስነብባለን፡፡ ሁሉንም ማካተት ባለመቻላችን ቅር እንደማትሰኙ በመተማመን ይህንን ማድረግ ባለመቻላችን ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡

1. በመጀመሪያ ለውይይት የጋበዛችሁበትን ርእሰ ጉዳይ እንደወደድኩት መግለጽ እፈልጋለሁ፡፡ እኔ ርዕሱን ከቤተክርስቲያን (ኢ.ኦ.ተ.ቤ/ን) ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ቃኝቼ ለመመልከት ሞክሬያለሁ፡፡ በቤተ እምነታችን ውስጥ ስር የሰደደና እድሜ ጠገብ ችግር እንዳለ የማይካድ መሆኑ እንዳለ ሆኖ ነገር ግን ችግሩን ለመቅረፍ እውነተኛ ትጋትና ልብ የሚደርስ መፍትሔ አለመታየቱ ከምናወራው ችግር በላይ አሳሳቢ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ የትኛውም ቦታ ችግር፣ አለመግባባት፣ መንገድ መሳት መኖሩ እሙን ነው፡፡ ግን ችግሩን ወደነው ደግሞም ተስማምተን መዝለቅ ከቻል ይህ ድንዛዜና አዚም ነው፡፡

        በመንፈስ ቅዱስ እንደተሸሙ በሚነግሩን ዳሩ ግን የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ በማናይባቸው አባቶች ዘንድ እንዲመጣ የምንመኘው አስተዳደራዊ ለውጥ የአሁኑ ይባስ ወደሚያሰኝ ደረጃ መጥቶአል፡፡ ለዚህም ደግሞ እንደ ማባባሻ ሆኖ የታየኝ ሕጉን (ቃለ ዐዋዲ) የራሳቸው ጥቅም ማስከበሪያ፣ እውነት ገፍቶ ሲመጣ ደግሞ ማሸሻ አጥር አድርገው መጠቀማቸው እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ማንኛውም ሕግ የሚወጣው ለራስ አሳብ የሁል ጊዜ ይሁንታ ማግኛ ለመሆን ሳይሆን ሰዎች መብትና ግዴታቸውን ጠንቅቀው በማወቅ ተግባራቸውን ፍትሐዊ በሆነ መንገድ መከወን እንዲችሉ ለማስቻል ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ከሆነ ግን ሕጉን (መተዳደሪያ) ያለ አግባብ ተርጉመውታል አልያም ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ አይነት ሆኖአል ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ በሕሊናም በፈጣሪም ፊት በወንጀለኝነት የሚያቆም ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን እያየን ያለነውም ከዚህ ቢብስ እንጂ የተሻለ አይደለም፡፡  

      ጅቡም ይበላል የሚለው አሳብ የሚነሣው እዚህ ላይ ነው፡፡ የምናየውና የምንሰማው ብልሽት እንዲስተካከል የተገኘውን ሁሉ አማራጭ ተጠቅመናል ብዬ በግል አምናለሁ፡፡ ብዙ ሰዎች ለዚህ ብርቱ ዋጋ ከፍለዋል፡፡ ዛሬም ግን ቤ/ን የአሕዛብ መዘባበቻ፣ የጠቃዋሚዎች መሳለቂያ ከመሆን አልወጣችም፡፡ ታዲያ ይህን ጊዜ ጅቡም ይበላል እንዳላችሁት እኛ አንነካ እንጂ ሌላው ድፍት ይበል ብለው በእግዚአብሔር መንጋ ላይ የሚያንኮራፉትን ልንቃወም የተገለጠና ማስረጃ ጠገብ የሆነ ጉዳይ ያለባቸውን ደግሞ እንዲሻሩ መታገል ይኖርብናል እላለሁ፡፡ እረኛ ጉበኛ ነው! ሕዝቡ ሲተኛ ነቅቶ የሚፀልይ፣ ሊመጣ ያለውንም በመንፈስ ቀድሞ የሚያስተውል ነው፡፡ ዛሬ ግን እኛ ስንጸልይ እነርሱ እያንኮራፉ ነው፡፡ እንኳን ሊሆን ያለውን ሊነግሩን ቀርቶ የሆነውን ያለፉ አባቶች እውነተኛ የኑሮ ፍሬ በተግባር እየካዱት ነው፡፡ ክብራቸው እንደተነካ ሲሰማቸው ግን እንደ ሳማ ቅጠል የሚለበልቡ ናቸው፡፡ እናማ ምእመናን ለመፍትሐየ የሚቀርበውን አማራጭ ሁሉ ከዘጉት ጅቡም ይበላል ማለት ያለብን አይመስላችሁም? እግዚአብሔር ያስበን፡፡                                     
                                                                      ሐብተ ማርያም ክፍሌ

2. ከዚህም በላይ በትጋት መፃፍ እንዳለባችሁ ይሰማኛል፡፡ አስተያየት ለመስጠት ያህል ያነሣችሁት ርእሰ ጉዳይ ሰፊና በብዙ ሊያነጋግር የሚችል ሆኖ ሳለ ሃይማኖታዊ ነገር ላይ ሚዛኑ ያጋደል ነው፡፡ ይህ ደግሞ አንባቢዎች በተለያየ እድሜና የእውቀት ደረጃ ላይ ያሉ እንደመሆናቸው አሳባቸውን ከፈለጉት አንግልና በፈለጉት መልኩ እንዳይገልጹ ጫና የሚያሳድር ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ ጽሑፉ ቦይ ባይቀድና የራሱን መስመር ባያበጅ እንዲሁም ሰዎችን ከራሳቸው እይታ አንፃር እንዲመለከቱ አርነት ቢሰጥ መልካም ነው እላለሁ፡፡
                                                                            አቤ

3. ርእሱን ከኢኮኖሚና ከፖለቲካ አንፃር ብንመለከተው ልባችንን የሚኮረኩርና ጩኽታችንን የሚጮኽልን እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ብሎጋችሁን ሳነብ የመጀመሪያዬ እንደመሆኑ አመለካከቴን ለመግለጽ የሚጋብዝ ርእስ በማግኘቴ ተደስቻለሁ፡፡ ልጅ ሳለሁ “የሚበላው ያጣ ሕዝብ አንድ ቀን መሪውን መብላቱ አይቀርም” የሚል አባባል ሰምቻለሁ፡፡ እውነታውን እየተረዳሁት የመጣሁት ግን ርሀብ ምን እንደሆነ በደንብ ስማር ነው፡፡ ስለ ምግብ ብቻ እያወራሁአችሁ እንዳልሆነ እንደምትረዱልኝ ተማምኜባችሁአለሁ፡፡ ፍትሕ፣ ነፃነት፣ ሰላም፣ እኩልነት እነዚህ ሁሉ በምንም የማንደልላቸው ርሀቦች ናቸው፡፡ የእነዚህን መጓደል እንጀራ አይተካውም፡፡
ይቀጥላል


Friday, June 1, 2012

ጅቡም ይበላል


            
         በአገራችን የገጠሩ ክፍል በጅብ የተነከሰ የቤት እንስሳ እንደ ርኩስ ስለሚቆጠር አይበላም፡፡ ታዲያ አንድ የቆሎ ተማሪ ጅብ የነከሰው በግ በልቶ ስለነበር ወደ መምህሩ ዘንድ በመሄድ “የኔታ ጅብ የነከሰው በግ ይበላል ወይስ አይበላም?” በማለት ጠየቃቸው፡፡ መምህሩም የአይን ጥቅሻ ያህል አሰብ አድርገው “አካባቢው ላይ ሌላ የምግብ አማራጭ አለ ወይስ የለም?” በማለት ለጥያቄው ጥያቄ መለሱለት፡፡ ተሜም “በፍጹም አማራጭ አልነበረም” ሲል መለሰላቸው፡፡ አስተዋዩ መምህር “እንግዲያማ እንኳን በጉ ጅቡም ይበላል” አሉት፡፡
         ድህነት አማራጭ ማጣት ነው፡፡ የከፋ ቅጣት ትኩረት መነፈግ ነው፡፡ ትልቁ ሞት ተስፋ መቁረጥ ነው፡፡ የሠራችሁትን የሚበላ፣ የወለዳችሁትን የሚስም፣ ጣፋጭ ቃላችሁን የሚሰማ፣ ቀርባችሁ የሚሸሽ፣ ፈልጋችሁ የሚሸሸግ፣ ምራችሁ የሚበቀል፣ ወዳችሁ የሚገፋ ሲበረክት ውሳኔያችሁ የጨነቀው እርጉዝ ያገባል ስትወልድበት ግራ ይጋባል አይነት መሆኑ በኑሮአችን ውስጥ የሚስተዋል ሐቅ ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ልጆቻቸውን ቀቅለው ስለ በሉ እናቶች፣ ለአገልጋዮች ብቻ የተፈቀደውን መሥዋዕት ስለበላ ነቢይ ዳዊት እናነባለን፡፡
         አማራጭ ማጣት የጠሉትን ያስቀላውጣል፣ የተጸየፉትን ያስታቅፋል፣ ሰው መሐል ብቸኛ ያደርጋል፣ ሕሊናን ተጋፍቶ ድንበር ያስጥሳል፡፡ በየሆስፒታሉ ሐኪሙን እባክህ አድነኝ! ትምህርቴን ልጨርስ፣ እናትና አባቴን ልጡር፣ እንደ ሰው ወግ ማዕረግ ልይ፣ ልጆቼን ላሳድግ እያሉ የሚሞቱ ወገኖቻችን ያለ መሞት አማራጭ ቢኖራቸው ኖሮ ሞትን ፊት ለፊት ባልጨለጡት ነበር፡፡ ዳሩ ግን ምን ያደርጋል? ሐኪሙ አይኑ ፈጦ ሟች በድን ይሆናል፡፡ ቀጣዩ ቀብር ብቻ ነው!!
         አንዳንድ ጊዜ በኪሳችሁ ብዙ ብር ይዛችሁ ምን እንደምትበሉ፣ ምን እንደምትገዙ ግራ ገብቶአችሁ አያውቅም? ለካ የምንፈልገውን ለማግኘት የመግዛት አቅማችን ብቻውን በቂ አይደለም? ደጃችን ድረስ የምንፈልገው ነገር ሲመጣ ይህንን ለሚያደርጉ ሰዎችስ አክብሮታችን ምን ያህል ነው? በእርግጥ አንድ እውነት አለ፡፡ ሰው ላልደከመበትና ዋጋ ላላስከፈለው ነገር ያለው ምልከታ የወረደ ነው፡፡ ይህ ሊሆን ግን አግባብ አይደለም!
        በሰው ላይ ከመፍረዳችን በፊት ልክ ከላይ እንደተመለከትነው የተግባር መምህር አውጥተን አውርደን፣ ዙሪያ ገባውን ፈትሸን ነገሩን ለመመርመር የምንጥር ስንቶቻችን ነን? ወይንስ አይናችሁ እንዳየች፤ ጆሮአችሁ እንደሰማች ትፈርዳላችሁ?               
         ውድ አንባቢዎች በዚህ ርዕስና አሳብ ዙሪያ በሰፊው ብንወያይበት እንዲሁም ለእናንተ የታያችሁን ብታካፍሉን መልካም ነውና በፍቅር እንጋብዛችሁአለን፡፡ በአድራሻችን betefikir@gmail.com ብላችሁ ላኩልን፡፡
ይቀጥላል