Tuesday, October 14, 2014

ቱንቢ (plumbline)



ጥቅምት 4 ቀን 2007 የምሕረት ዓመት

‹‹እንዲህም አሳየኝ እነሆም፥ ጌታ ቱንቢውን ይዞ በቱንቢ በተሠራ ቅጥር ላይ ቆሞ ነበር››
/አሞ 7÷7/

        በአዲስ ኪዳን መጻሕፍት የታሪክ ክፍል በሆነው የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ከምንማራቸው መንፈሳዊ ትምህርቶች መካከል ትጋት አንዱ ነው፡፡ ክርስቲያኖች በእግዚአብሔር ፊት የሚተጉበትን ነገር መመርመርና መመዘን አለባቸው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ስለሆነ አይመረመርም፡፡ የሰው ፍለጋና ጥረትም አያገኘውም፡፡ ዳሩ ግን ሥጋ ለባሽ ሁሉ ሕያውና ጻድቅ በሆነው በእርሱ በእግዚአብሔር ፊት ቃልና ኑሮው ይመዘናል፡፡ በእውነት ላይ የተመሰረተው ‹‹ይበል›› ተብሎ ይሁንታን ሲያገኝ፤ እንደ ዘላለም ምክሩና እንደ ጌታ ልብ ያልሆነው ሁሉ ግን ሁሉን እንደ ፈቃዱ በሚያደርግ ሉዓላዊ አምላክ ዙፋን ፊት በጽድቅ ይዳኛል፡፡

        እግዚአብሔር እውነቱን የሚለካ ሌላ እውነት የሌለ እውነተኛ፤ ጽድቁን የሚመዝን ሌላ ሚዛን የሌለ ጻድቅ፤ ቅድስናውን የሚተያይ ሌላ ቅድስና የሌለ ቅዱስ አምላክ ነው፡፡ ሁሉ በእርሱ ተፈጥሮአልና፤ ከሆነውም ሁሉ ያለ እርሱ የሆነ አንድ ስንኳ የለምና ሁሉን የሚመዝን እርሱ ነው፡፡ እውነተኛ አምላክ የሆነ እርሱ ብቻ /ዮሐ 17፣3/ የቃልና የኑሮአችን ቱንቢ በእጁ አለ፡፡ እርሱ እውነተኛ አምላክ ነው፡፡ ሁሉ በእርሱ ይመዘናል፡፡ ‹‹እግዚአብሔር የመረጣቸውን ማን ይከሳቸዋል? የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው፥ የሚኰንንስ ማን ነው?›› /ሮሜ 8፥33/ ተብሎ እንደ ተፃፈ፤ እግዚአብሔር ነገሮቻችንን ሊመዝን፤ ሊያጸድቅና ሊኮንን እውነተኛ ዳኛ ነው /መዝ 7÷11/፡፡

       በእግዚአብሔር ዘንድ ነን ያልነው ሳይሆን፤ ናችሁ ያለን ብቻ ሚዛን ይደፋል፡፡ ብዙ ሰዎች ከሰው ሚዛን ባልዘለለ ኑሮ ውስጥ ላይ ታች ይላሉ፡፡ ‹‹እኛን በሚቆጣጠር በእርሱ ዓይኖቹ ፊት ሁሉ ነገር የተራቆተና የተገለጠ ነው እንጂ፥ በእርሱ ፊት የተሰወረ ፍጥረት የለም።›› /ዕብ 4፣13/ እንደ ተባለ፤ ሁሉን የሚመረምር፤ ከሚታየው አልፎ የማይታየውን፤ ከሚሰማው አልፎ የማይሰማውን፤ ከተጨበጠው ባለፈ የተሰወረውን የሚያስተውል ጌታ አለን፡፡ እርሱ አባታችን እግዚአብሔር እኛን እንደሚቆጣጠርና ‹‹ቅጥሮችሽም ሁልጊዜ በፊቴ አሉ›› /ኢሳ 49÷16/ ተብሎ እንደተፃፈ፤ የኑሮ ቅጥራችን በዓይኖቹ ፊት ግልጥ የሆነ መሆኑን ልብ ማለት መንገድ ከመሳት፤ ከክርስትናው እውነት ከማነስ ይታደጋል፡፡   

       በሐዋርያት ሥራ (1፣14) እና (2፣5) ላይ የምናስተውለው፤ በንባብ ደረጃ አንድ አይነት፤ በአሳብ ደረጃ ሁለት አይነት ‹‹ትጋት›› አለ፡፡ ‹‹እነዚህ ሁሉ ከሴቶችና ከኢየሱስ እናት ከማርያም ከወንድሞቹም ጋር በአንድ ልብ ሆነው ለጸሎት ይተጉ ነበር።›› /1፣14/፤ ‹‹ከሰማይም በታች ካሉ ሕዝብ ሁሉ በጸሎት የተጉ አይሁድ በኢየሩሳሌም ይኖሩ ነበር›› /2፣5/፡፡ ትጋት በተደጋጋሚ አንድ ነገር ላይ የምንታይበት ወጥ ሂደት ነው፡፡ ወደ ፈተና እንዳንገባ ተግተን መጸለይ እንዳለብን /ማቴ 26÷41/ ታዘናል፡፡ በሚያስፈልገን ጊዜ የእግዚአብሔርን እርዳታ እንድናገኝ ወደ እርሱ መቅረብ ያለብንም ዛሬ ነው፡፡ የጭንቅ ቀን ሳይመጣ፤ ደስ የማያሰኙ ጊዜያት ሳይደርሱ /መክ 12÷1/ በእግዚአብሔር ፊት መትጋት ያስፈልገናል፡፡ በብዙ ነገሮቻችን ላይ ጉብዝናው /በአካል፤ በእውቀት፤ በሀብት፤ በወዳጅ፤ በዝና . . . / ሳለ መንፈሳዊ ኅብረትን ከእግዚአብሔር ጋር ማጠናከር ይገባል፡፡

        እግዚአብሔርን በጭላጩ አልያም በእላቂው ለመገናኘት ለቀጠሩ፤ ጉብዝናቸው በሚያልፈው ከንቱ የተተበተበ ብዙ ሰዎችን በዙሪያችን እናያለን፡፡ እንዲህ ካለው ድካማቸው ፍሬውን ስናየው ግን መራራ ነው፡፡ እግዚአብሔር የትጋቶቻችን የበላይ ተመልካች ነው፡፡ በእርሱ ፊት በሚኖረን መንፈሳዊ ትጋት ውስጥ ያለውን እውነት/ ውሸት፤ መልካም/ ክፉ፤ ጽድቅ/ አመፃ፤ ብርሃን/ ጨለማ ‹‹ዓይኖቹም እንደ እሳት ነበልባል›› /ራዕ 1÷14/ የሆኑት ጌታ ይለያል፡፡ አሳላፊው ሰው አይደለምና ግርግር ሌባውን አይረዳውም፡፡ የእርሱ ዓይኖች እንደ እሳት ነበልባል ናቸው፡፡ ሁሉን በልኩ ይመረምራል፡፡ የሚሰወረው አንዳች የለም፡፡

       በመቶ ሃያው የመጀመሪያ ክርስቲያኖችና ሃይማኖተኛ በሆኑት አይሁድ መካከል ስለ ነበረው መንፈሳዊ ልዩነት ሁለቱ ምዕራፎች ግልጽ ያደርጉልናል፡፡ በደቀ መዛሙርቱ መካከል የነበረውን ትጋት መሠረታዊ ነገር ስንመለከት፤ የእግዚአብሔር ልጅ ከሙታን መካከል ተለይቶ መነሣቱንና ወደ አባቱ ማረጉን ተከትሎ የተሰጣቸውን የተስፋ ቃል /መንፈስ ቅዱስ/ በመጠባበቅ፤ አይሁድ በሰቀሉት እግዚአብሔር ግን የሞትን ጣር አጥፍቶ ባስነሣው በናዝሬቱ በኢየሱስ ስም የተሰበሰቡ ናቸው፡፡ ‹‹ከሰማይ በታች›› ተብሎ በተገለጸልን መሰረት ደግሞ፤ የአይሁድ የተለመደ በዓል /ዘሌዋ 23÷15፣16/ ለመከወን ከአስራ አምስት አገሮች የመጡ ሰዎችን ጨምሮ በኢየሩሳሌም የአምልኮ ስፍራ እንደ ኦሪቱ ሥርዓት የሚፈጸመውን አምልኮ ለመፈጸም የተሰበሰቡ ሕዝቦች ናቸው፡፡

      ሐዋርያቱን በተመለከተ በግለሰብ ቤት ውስጥ የአይሁድን ክፋት እየፈሩ ከሰማይ መልስን የሚጠባበቁ፤ ያላቸውን ትተው ክርስቶስን ‹‹አለን›› /ሐዋ 3÷6/ ያሉ፤ በኋላ እንደምናነበው ‹‹የገሊላ ሰዎች›› አይደሉምን ተብለው የተናቁ ናቸው፡፡ ከተለያየ የዓለም ክፍል የተሰበሰበውን አይሁድና ወደ ይሁዲነት የገባ ወገን ስንመለከት ደግሞ ፍጹም ተቃራኒ በሆነ ሁኔታ የእግዚአብሔርን ልጅ ሰቅለው በሞቱ ላይ የተሰበሰቡ፤ ባለ ጠጎችና አንቱታን የተላበሱ እና በብዙ የአምልኮ ሥርዓት፤ በመሥዋዕቶችና በካህናት እንዲሁም ይህንን ሥርዓት ደኅንነቱን ለመጠበቅ በቆሙ ዘቦች የተከበቡ ናቸው፡፡ ኃይሉን ሰቅለው በመልኩ የደመቁ፤ በሰው ፊት ከብረው በሰማይ የተናቁ፤ ለጊዜው ኖረው ከዘላለሙ የቀሩ ናቸው፡፡ ግን በጸሎት ሁሉን ወደሚችል አምላክ ይተጉ ነበር፡፡

       በዙሪያችን ያለው ክርስትና ካላስተዋላቸው ብርቱ ነገሮች አንዱ መንፈሳዊ ትጋት ሁሉ ጤናማ አለመሆኑን ነው፡፡ ስለ ትጋት ሳስብ ከማስታውሳቸው ጥቅሶች መካከል መክብብ 2÷26 እንዲህ ይላል፡- ‹‹እርሱም ደስ ለሚያሰኘው ሰው ጥበብንና እውቀትን ደስታንም ይሰጠዋል ለኃጢአተኛ ግን እግዚአብሔርን ደስ ለሚያሰኘው ሰው ይሰጥ ዘንድ እንዲሰበስብና እንዲያከማች ጥረትን ይሰጠዋል።››፡፡ ጥረት ሁሉ ጤናማ አይደለም፡፡ ምቾት ሁሉ ዕረፍትን አያስገኝም፡፡ የሰበሰቡት የበተናቸው፤ የጨበጡት ያቃታቸው፤ የደረሱበት ያላረካቸው ብዙ ናቸው፡፡ እግዚአብሔር አለንጋውን ምቾት አድርጎባቸው ተግሣጹን ያላስተዋሉ ይስተዋላሉ፡፡ የምትተጉ እናንተ ወዳጆቼ ልብ በሉ፡፡ እያደረጋችሁ ያላችሁት ምንድነው? በዚህ ድርጊት ላይ እግዚአብሔር ያለው ትክክለኛ አሳብ ምን ይመስላል? በመንፈሳዊ ሚዛን ፋይዳው ምንድነው? የመሳሰሉ ጥያቄዎችን ለራስ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡

       እኛን ከሚሰማን በላይ ከእግዚአብሔር የምንሰማው እጅግ ማትረፊያ ነው፡፡ የቱንም ያህል ዘመን ብናስቆጥር፤ የደከምንበት ቢደረጅ፤ እውነት ነው ካልነው ጋር ብናረጅ ‹‹የመለኮት ቱንቢ›› በእኛ ቱንቢ በተሠራ ቅጥር ላይ ይቆማል፡፡ ያን ጊዜ ድካማችን ሳይሆን እውነቱ ይገዛል፡፡ ነን ያልነው ሳይሆን የሆነው ሚዛን ይደፋል፡፡ ጉዳዩ እንደ ምድራዊ አናፂ ከጭቃና ከሲሚንቶ ጋር የተያያዘ አልያም ከድንጋይና ከጡብ ጋር የተገናኘ አይደለም፡፡ በእግዚአብሔር ፊት ያለንን መንፈሳዊ ሁኔታ በአጠቃላይ የሚዳስስ ነው፡፡

       ወደምናብራራው ሁለት አይነት ትጋት ስንመለስ ‹‹ልክ ነው›› በመለኮት ጉባኤ መወሰን እንዳለበት፤ ራይትና ኤክስ ከልዑሉ ዙፋን መምጣት እንደሚገባው እናስተውላለን፡፡ ብዙ ያልጠሩና ያለዩ ነገሮች ሲኖሩን መዋከብን ማስወገድ ይገባናል፡፡ ቆም ብለን ጉዳዩን ማመዛዘን፤ በእኛ ዓይኖች ፊት አልያም በሰዎች አስተያየት ውስጥ ያለውን ነገር ሳይሆን እውነት ለሆነው ነገር መጨከን ያስፈልገናል፡፡ ሰዎች መለኮት ከሆነው አምላክ ይልቅ ሥጋና ደም በልጦባቸው፤ የሆነ ሳይሆን የመሰለ አስምጦአቸው አስተውያለሁ፡፡ እግዚአብሔር በሰው ቱንቢ ሲታይና ሲፈተሽ ልክ እንደ ሆነ በሚታሰበው በየትኛውም የሥጋ ለባሽ ትጋት ላይ የራሱን ቱንቢ ይዞ በቅጥሩ ላይ ይቆማል፡፡ እውነት ላልሆነች ለዚያች ከተማ መፍረስ ይሆናል፡፡ ቅጥሯም ይመነጠራል፡፡ በሩቅ አይተው ውበቷን ያደነቁ፤ ተግባሯን ያጸደቁ፤ ክብሯን ያረቀቁ እፍረት ይወርሳቸዋል፡፡

       እግዚአብሔር በድምፅ ብልጫ አልያም በሰው አስተያየት አይሠራም፡፡ ጽድቁ ሁሉን ይመዝናል፡፡ እንዲህ ቢሆን ኖሮ እግዚአብሔር ከጥቂቶቹ ጋር ባልሆነ ነበር፡፡ ‹‹ሰው ሁሉ ውሸተኛ ከሆነ እግዚአብሔር እውነተኛ ይሁን›› /ሮሜ 3÷4/ ተብሎ እንደ ተፃፈ፤ እርሱ ከእውነቱ ጋር ለዘላለም ይኖራል፡፡ በሕይወት የተጓዝንባቸው እረጅም እርቀቶች፤ እልህ አስጨራሽ ትጋቶች፤ እንኳን በሥጋ በመንፈስ ኑሮ ቢሆን የእግዚአብሔር ቱንቢ እውነት ያልሆነውን ያፈርሳል፡፡ ሥጋና ደም ሒሳብ ሊተሳሰብ፤ ትርፍና ኪሳራ ሊያሰላ ይችል ይሆናል፡፡ ከሀቁ ግን የሚበልጥ ምንም የለም፡፡ የመለኮት ጽድቅ በሰው ጽድቅ ላይ ይገዛል፡፡

        በሰማይና በምድር ፊት ሁለቱ ትጋቶች ተዳኙ፡፡ የመቶ ሃያውና ከሰማይ በታች የተሰበሰቡት ሕዝቦች በመለኮት ዓይን ፊት ታዩ፡፡ የእግዚአብሔር ቱንቢ በላያቸው ሆነ፡፡ መንፈስ ቅዱስ በወረደ ጊዜ ‹‹በልጁ ሞትና ትንሣኤ›› የተሰበሰበውን ጉባኤ አድራሻ አድርጎ ሲመጣ፤ ከዚህ መሰባሰብ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘውን ኅብረት ግን እውቅና ነፈገው፡፡ የደቀ መዛሙርቱ ትጋት ላይ የሆነው ነገር በሌሎቹ ትጋት ውስጥ እንዳይታይ ልዩነቱን የፈጠረው ምንድነው? ስንል ‹‹ክርስቶስ ኢየሱስን›› እናገኛለን፡፡ ብዙዎች እርሱ የአንድነት ርዕስ እንደ ሆነ ብቻ ያስባሉ፤ ዳሩ ግን እርሱ የመለየታችንም ርዕስ ነው፡፡ ክርስቶስ ለዘላለም ከማይረባን፤ እንደ ጽድቁ ካልሆነ ነገር ይለየናል፡፡ ይህ ደግሞ ሰውንም ይጨምራል፡፡ ስለ ተቀበልነው ብቻ ሳይሆን ስለተከለከልነው፤ ወደ ሕይወታችን ስለመጡ ሰዎች ብቻ ሳይሆን ስለተወሰዱም የምናመሰግነው ከዚህ የተነሣ ነው፡፡ ያቀረበልን እግዚአብሔር ሲያርቅም፤ ያቀረበን እግዚአብሔር ሲያርቀንም ልክ ነው፡፡ ስሙ ብሩክ ይሁን፡፡

        እግዚአብሔር ከሰማይ በመንፈሱ ‹‹በዚህ መካከል ነው ያለሁት›› አለ፡፡ ምንም እንኳን ሁለቱም ወደ እግዚአብሔር በእግዚአብሔር ስም ቢተጉም፤ ልብና ኩላሊትን የሚመረምረው፤ ሁሉ በፊቱ የተራቆተለት አምላክ ግን እንደ ልቡና የዘላለም ምክሩ የሆነውን ለየ፡፡ ‹‹ጌታ ለእርሱ የሆኑትን ያውቃል›› /2 ጢሞ 2÷19/ ተብሎ እንደ ተፃፈ፤ የትኛውም ስፍራና ሁኔታ ውስጥ ቢሆኑ፤ ጌታ በእውነትና በመንፈስ ከእርሱ ጋር ኅብረት የሚያደርጉትን የአፍ ሳይሆን የልብ አማኞች ያውቃል፡፡ ከሰው እውቅና በላይ እጅግ አብዝቶ የሚበልጥ መታወቅ ከላይ ነው፡፡ ‹‹እንዲህም አሳየኝ እነሆም፥ ጌታ ቱንቢውን ይዞ በቱንቢ በተሠራ ቅጥር ላይ ቆሞ ነበር››፤ በእኛ ቱንቢ የሆነው ሳይሆን የጌታ ቱንቢ ጉዳዮቻችንን ሊያጸድቅና ሊኮንን ከበቂ በላይ ነው!!
                                     ‹‹ . . . ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ፤›› /ቆላ. 4፡3/!

7 comments:

  1. Tunbee: betam yigermal bezih melku menfesawinetn aychew alawikim neber. Tebareku

    ReplyDelete
  2. በእንግሊዝኛ Measurement Line ይባላል፡፡ ክርስትናም በእግዚአብሔር ፍትህ መዳኘት አለበት፡፡ እኛም ስንኖር የቃሉ እውነት ስላለን ከእውነት ጋር ወግነን እያሰመርን መኖር አለብን፡፡ ግሩም ቃል!

    ReplyDelete
  3. Ewnet yashagiral. egna yalinew sayihon ersu yalew ybelital

    ReplyDelete
  4. Yegizew kali new. E/r behagerachinm hone bebetkiristiyan tunbiewn yansa. bewinet meshigew letiliku yemeeserutinm yigiletachew.

    ReplyDelete
  5. O! my God. bless u

    ReplyDelete
  6. Geta tunbewin yansa. Betekiristiyan yih yasfeligatal. Wedajochee zemenu bebizu yeminastewilibet new. BEYESUS SIM NIKUUUUUUUUU

    ReplyDelete