Tuesday, January 6, 2015

አያፍርባችሁም!



በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

ማክሰኞ ታኅሳስ 28 ቀን 2007 የምሕረት ዓመት

      ዓለማችን በብዙ የሚያሸማቅቁና የሚያሳፍሩ ታሪኮች የተሞላች ናት፡፡ ሰዎች በሚያፍሩባቸውና በሚታፈርበት ማንነታቸው መካከል ይኖራሉ፡፡ መቀባበል በሥጋ ለባሽ ዘንድ ቀላል ዋጋን የሚያስከፍል አይደለም፡፡ ሰዎች ሌሎች መሰል ወገኖቻቸው ለእነርሱና ለተግባራቸው አዎንታዊነትን እንዲያሳዩ እጅግ ዋጋን ይከፍላሉ፡፡

      በሰው ፊት ላለማፈር ወይም መታፈሪያ ላለመሆን አጊጠውና ደምቀው፤ አጥንተውና ደክመው ብዙዎች በአደባባይ ይቆማሉ፡፡ ብዙ ጓዳዎች የአገር ያህል ተቆጥረው ሰዎች ለሕዝብ እንደሚሆኑት ያህል ተጨንቀው በቤታቸው ይሆናሉ፡፡ በዚህ ሁሉ ግን ሰው ተቀባብቶ በጭንብል፤ ሸነጋግሎ በወሬ የማያልፈው ውስጣዊ መራቆት፤ የሕሊና ሃፍረት ይሰማዋል፡፡

      በሰው ታሪክ እፍረት የጀመረው በመጀመሪያው ሰው መኖሪያ ቤት ቅጥር ውስጥ ነው /ዘፍ. 3፡8/፡፡ አንድ አካል የነበሩት ባልና ሚስት እንደ ነበሩ ቀርቶ፤ ሁለት ሆኖ ለመቆም እንኳን አቅም አጡ፡፡ በደል ጉልበት ያሳጣል፡፡ ነውር አያስተያይም፡፡ ሐዋርያው ‹‹ስለዚህ እኔ ደግሞ በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ሁልጊዜ ነውር የሌለባት ሕሊና ትኖረኝ ዘንድ እተጋለሁ።›› /ሐዋ. 24፡16/ እንዳለ፤ በእግዚአብሔር ፊት ብቻ ሳይሆን ሰው በሰው ፊት ለመቆምም ንጽሕና ትልቅ አቅም ነው፡፡