Tuesday, March 26, 2013

ትልቁ ጉድለት



ማክሰኞ መጋቢት 17/2005 የምሕረት ዓመት

“. . . በዚህም ዓለም ተስፋን አጥታችሁ ከእግዚአብሔርም ተለይታችሁ ያለ ክርስቶስ ነበራችሁ፡፡ አሁን ግን እናንተ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁ በክርስቶስ ደም ቀርባችኋል፡፡” (ኤፌ. 2÷12)

        ምድራችን ሰዎች ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላት የሚራወጡባት አደባባይ ናት፡፡ ከትንሽ እስከ ትልቅ ሁሉ ለፍላጎቱ ከእንባ ጀምሮ እስከ ሞት ድረስ ዋጋ ሲከፍልም እንመለከታለን፡፡  በተገኘው አጋጣሚና በቻለው መጠን ሁሉም ሀዘኑን በደስታ፣ ሁከቱን በሰላም፣ ማጣቱን በማግኘት፣ ውርደቱንም በክብር ለመለወጥ ጥረት ያደርጋል፡፡ አቅም እምቢ ቢል እንኳ አሳብ ይፍጨረጨራል፡፡ ሰው ሁሌና ሁሉ እንደማይሞላ መረዳቱ አያሳርፈውም፡፡ እንዲያውም ከፊት ይልቅ ጥማቱ እየጨመረ ይመጣል፡፡ ነገር ግን በዚህ ዓለም የሚኖረንንን ሩጫ መጨረሻው ምን እንደሆነ ስንፈትሸው ከሥጋ ስኬት የዘለለ ሆኖ አናገኘውም፡፡  ብዙ ሰው ከደህና ቤተሰብ አለመወለዱ፣ አድጎ በተሻለ የኑሮ ደረጃ ላይ ራሱን አለማግኘቱ፣ ከባልንጀሮቹ እኩል በሥጋ ነገር አለመለወጡ፣ በዚህ ዓለም ነገሮች የተደላደለ ነገር በሕይወቱ ብዙ ጉድለት መኖሩ የብቻ አሳብ አጀንዳው፤ የሰው ፊት የወሬ ርዕሱ ነው፡፡

        የእግዚአብሔር ቃል  ስለ ሰው ልጆች ትልቅ ጉዳት ሲናገር ግን “ያለ ክርስቶስ ነበራችሁ” ይላል፡፡ ሐዋርያው በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን ክርስቲያን ለሆኑ የኤፌሶን ምእመናን “ነበራችሁ” በማለት የሆነላቸው ነገር ከነበሩበት ኑሮ ምን ያህል የላቀና እንደ አዲስ መፈጠር እንደ ሆነ ያስረዳል፡፡ ሰው ተስፋን ካጣ የመኖር ትልቅ ኃይሉን አጣ ማለት ነው፡፡ ሀብትና ቁሳቁስ፣ ሥልጣንና ክብር ኖሮን ተስፋችን ከሞተ ግን ሕይወት ትቀጥ ዘንድ በቂ አቅም ታጣለች፡፡ ተስፋ ሁለነገራችን የተያያዘበት ሰንሰለት ነው፡፡ ሰው ተስፋው ከተቆረጠ ሕይወት እንድትቀጥል ዕድል የለውም፡፡ በባሰ ነገር ላይ ተቀምጠን የተሻለ የምንጠብቀው ተስፋ ስለምናደርግ ነው፡፡ የሰውን ኃጢአተኝነት ተከትሎ የመጣው ቀላል የማይባል ውድቀት እንዲሁም የእግዚአብሔር ፍርድ ነው፡፡ በሰው ሕይወት ውስጥ የዔደን ገነትን ለቅቆ ከመውጣት ጋር በተያያዘ ብርቱ ተስፋ ነበር፡፡ ያም መዳናችን ነው! ብዙዎች ሳያዩ የተስፋውን ቃል በማመን ከዚህ ምድር አልፈዋል፡፡ እኛ ግን እንዲህ ያለውን መዳን ከዚህ ምድር ጀምሮ እንድናጣጥም ጌታ ረድቶናል፡፡

Wednesday, March 13, 2013

ከዚህም ጹም



ከቁጣና ከጥላቻ ጹም ለባልንጀሮችህ የበዛ ፍቅርን ስጥ፡፡
ከመለያየት ጹም ቢቻልህስ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑር፡፡
በሌሎች ላይ ከመፍረድ ጹም ማንንም ሰው ከመዳኘትህ በፊት እግዚአብሔር ጥፋቶቻችንንእንዴት እንደሚመለከት አስተውል፡፡  
ለራስ ከሚሰጥ አነስተኛ ግምት፣ ከጨለምተኝነትና አሉታዊ ከሆነ አስተሳሰብ ጹም ስለሕይወት በሚኖርህ አመለካከት ሁሉ ሚዛናዊ ሁን፡፡  
ተስፋ ከመቁረጥ ጹም ይህ የቁም ሞት ነውና በምታደርገው ነገር ሁሉ ተስፋ ይኑርህ፡፡
ከማጉረምረም ከፍርሃትና ከጭንቀት ጹም ጌታ ለሙሉ ሕይወታችን ያስባልና እምነትህንበእርሱ ላይ ጣል፡፡
ከስንፍና ጹም በሚያስፈልግህ ሁሉ በጸሎትና በምልጃ የእግዚአብሔርን እርዳታ ጠይቅ፡፡
ሕይወትን ካከበዱብህ ችግሮች፣ ወድቆም ከመቅረት ጹም የደስታዎችህን ጊዜያት ሁሉልትደሰትባቸዉ ጣር፡፡
ከምሬት ጹም የደስታዎችህን ጊዜያት ሁሉ ልትደሰትባቸው ጣር፡፡
አብዝቶ ለራስ ከመጨነቅ ጹም ራስህን ምን ጊዜም በጌታ እግር ሥር አድርግ፡፡
ከማንኛውም ዓይነት ቅሬታ አልያም ቂም ጹም የበደሉህን ሁሉ ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታይቅር በል፡፡ 
ከአሉባልታና ፌዝ ከተቀላቀለበት ወሬ ጹም እውነተኛ በሆኑና በደስታ ለዛ በተሞሉ ቁምነገሮች ውስጥ ተሳተፍ፡፡
ከአባካኝነትና ከአጥፊነት ጹም መውጣትና መግባትህ በመጠን ይሁን፡፡ 
ለዓለም አብዝቶ ከመጨነቅ ጹም ተጨማሪ ጊዜ ለአምላክህ ለመስጠት ትጋ፡፡ 
ከክፉ ልማዶችህ ጹም አንተ የተፈጠርከው በእግዚአብሔር አምሳል ነው፡፡

    ልብ በሉ! ዛሬ ምድራችን የምትጨነቀው ከመብል ተከልክለው ነገር ግን ከእነዚህየክፋት አውራዎች መፆም ባልቻሉ ወገኖች ነው፡፡ ለሚበልጠው ያትጋን!

Tuesday, March 5, 2013

አሜን እንደ አቀበት




ማክሰኞ የካቲት 26/2005 የምሕረት ዓመት

         የሰዓቱ መገስገስ፣ የሰማዩ  መዳመን፣ የንፋሱ ሽውታ፣ የጀንበርዋ ማዘቅዘቅ፣ ልክ እንደ ገደል ማሚቱ ኑሮዬን ያሳበቀብኝ ያህል ተሰማኝ፡፡ ከጥያቄ ወደበለጠ ጥያቄ፣ ከእንባ ወደ ባሰ እንባ፣ ከፈተና ወደ ብርቱ ፈተና መገላበጤን ልቤ ልክ እንደ ሰው እየታዘበው ለዚህ የተፈጠርኩ ያህል ቆጥሬው የአሳብም የእግርም ጉዞዬን በምሬት ኃይል እገፋለሁ፡፡ ትላንትና ዛሬ፤ ቅድምና አሁን ተጨፍልቀው አንድ ሆነውብኛል፡፡

     ሁሉም ነገር ለምሬት ምክንያት የሆነ ያህል ተሰማኝ፡፡ ከሰው ዘንድ ምክርም ልግስናም ጨርሻለሁ፡፡ የባሰ ነግረው ሊያጽናኑኝ፣ ስለተጎዳ አውርተው ሊጠግኑኝ፣ ከኑሮ ተሞክሮአቸው መክረው ሊመልሱኝ ብዙ ጊዜ ሞክረዋል፡፡ ይህ ግን ችግሬን ለማረሳሳት እንደ ማዳፈኛ ያህል ብቻ ነበር እንጂ ዘላቂ እረፍት አልሰጠኝም፡፡ ከሰው ቃል የእግዚአብሔር ቃል፣ ከሥጋ ለባሽ ማጽናናት የመንፈስ ቅዱስ ማጽናናት፣ ከምድራዊ መፍትሔ የመለኮት ምላሽ እንዲሻል ልቤ ግድ ስላለኝ አሳቡ ከሚሰበክበት፣ ምስጋናው ከሚደርስበት፣ ኃጢአተኛ በምሕረት ከሚመለስበት አደባባይ ለድምፁ ቅርብ፣ ለታዳሚው ሩቅ ሆኜ ጥግ ላይ ቁጭ አልኩ፡፡ የመከራዬ እድሜ እንደተደገፍኩት የጥድ ዛፍ ያህል መሰለኝ፡፡ በዕለቱ የነበረው ሰባኪ “እግዚአብሔር አለ” ሲል ቃሉ ጆሮዬ ጋር ደረሰ፡፡ ሕዝቡ ሁሉ ከፍ ባለ ድምፅ “አሜን!” አሉ፡፡
        
       ባለፉት ልምምዶቼ አሜንታ እንደ እኔ የሚቀለው፣ አፉንም ሞልቶ የሚናገረው አልነበረም፡፡ አሁን ግን እሩቅ እንዳለ የማስበውን እግዚአብሔር ቀርቶ የራሴን ሕልውና እንኳን እጠራጠራለሁ፡፡ እነርሱ እንደ መለሱት ልመልስ፣ እንደተስማሙት ልስማማ ውስጤ ታገለኝ፡፡ እናም ተሸነፍኩ፡፡