Tuesday, January 26, 2016

መልእክት ኀበ ፊልሞና፡፡(3)

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!


ማክሰኞ ጥር 17 ቀን 2008 የምሕረት ዓመት

(መልእክት ወደ ፊልሞና)

‹‹እምጳውሎስ ሙቁሐ ለኢየሱስ ክርስቶስ፡ (ኤፌ. 3፡1)››!

·  ጸሐፊው፡- ሐዋርያው ጳውሎስ ሲሆን፤ መልእክታቱን በአገልግሎት አጠገቡ ሆነው በሚረዱት እርሱ እየተናገረ ያጽፍ እንደ ነበር (ሮሜ 16፡22፤ 1 ቆሮ. 16፡21፤ ገላ. 6፡11፤ ቆላ. 4፡18፤ 2 ተሰ. 3፡17)፤ ነገር ግን ለፊልሞና የተላከውን ይህንን መልእክት በገዛ እጁ እንደ ጻፈው ይነግረናል (ፊል. 19)፡፡
·  የተጻፈበት ጊዜ፡- የፊልሞና መልእክት የቆላስይስ መልእክት በተጻፈና በተላከ ጊዜ በተመሳሳይ ከሮም (ሐዋርያው በእስር ቤት ሳለ) አብሮ የተላከ መልእክት ሲሆን፤ ጊዜውም ከ61 – 63 ዓ/ም ባለው ወቅት እንደ ሆነ ይታሰባል፡፡
· የመልእክቱ ጭብጥ ፡- ሁላችንም ባሮች የነበርን ሲሆን፤ ነገር ግን በክርስቶስ ወንድሞችና እህቶች ነን የሚል ነው፡፡

     ‹‹የተወደደ፤ የሚለው አገላለጽ ሙገሣን አልያም ልዩ መሆንን የሚያሳይ ሳይሆን፤ ጥልቅ የሆነ ፍቅርን ለማሳየት የተነገረ ነው፡፡ . . . አብሮን ለሚሠራ፤ የሚለው ደግሞ ወንጌልን ከማስፋትና ሌሎችን ወደ እምነት ከማምጣት ጋር በተያያዘ ያለውን አገልግሎት በተመለከተ የተነገረ ነው፡፡›› /ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ/

       ሌሎችን መውደድ በሌለበት፤ በትክክል እግዚአብሔርን ማመን አይኖርም፡፡ በክርስትና ውስጥ አብሮ መሥራት ከመዋደድ ባነሰ ነገር ላይ ሊመሠረት አይችልም፡፡ ጌታ ለጴጥሮስ ትልቅ ኃላፊነት ሲሰጠው፤ አስቀድሞ የጠየቀው ‹‹ትወደኛለህን?›› (ዮሐ. 21፡15-17) በማለት ነበር፡፡ ፊልሞና በሌሎች ወንድሞች ልብ ውስጥ የተወደደ መሆኑ ጌታን ከመውደዱ የተነሣ እንደ ሆነ ልንረዳ እንችላለን፡፡

Wednesday, January 6, 2016

‹‹ይህ አሳርፎናል››

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!


ረቡዕ ታኅሣሥ 27 ቀን 2008 የምሕረት ዓመት

          ‹‹ላሜሕም መቶ ሰማንያ ሁለት ዓመት ኖረ፥ ልጅንም ወለደ። ስሙንም፦ እግዚአብሔር በረገማት ምድር ከተግባራችንና ከእጅ ሥራችን ‹‹ይህ ያሳርፈናል›› ሲል ኖኅ ብሎ ጠራው።›› /ዘፍ. 5፡28-29/!

          ‹‹በተረገመች ምድር፡ ረፍታችን!›› በሚል ርእስ የጀመርነው ጽሑፍ ቀጣይ ንባብ ነው፡፡ ላሜሕ ‹‹ይህ ያሳርፈናል›› በማለት ተስፋውን በሚገልጥ መልኩ ከእረፍት ጋር በተያያዘ የልጁን ስም አውጥቷል፡፡ ዳሩ ግን ምድር ከአንተ የተነሣ የተረገመች ትሁን፤ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ፤ እሾህንና አሜከላን ታበቅልብሃለች፤ የምድርንም ቡቃያ ትበላለህ /ዘፍ. 3፡17/ ተብሎ የተረገመውን ላሜሕ (እኛንም ጨምሮ) ከወገቡ ፍሬ፤ ከእጁ ሥራ፤ ጽድቄ ከሚለው ተግባር እረፍትን ሊያገኝ አልቻለም፡፡


         ‹‹ጻድቅ የለም አንድ ስንኳ፤ አስተዋይም የለም፤ እግዚአብሔርንም የሚፈልግ የለም፤ ሁሉ ተሳስተዋል፤ በአንድነትም የማይጠቅሙ ሆነዋል፤ ቸርነት የሚያደርግ የለም፤ አንድ ስንኳ የለም›› /ሮሜ 3፡11-12/ ተብሎ እንደ ተጻፈ፤ ‹‹አንድ ስንኳ›› ቤዛ ለሰው ከሰው መካከል ባለ መኖሩ ‹‹በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአል›› /ዮሐ. 3፡16/፡፡ እንግዲህ የእግዚአብሔር ልጅ ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ ሊሰጥና ኃጢአተኞችን ሊያድን ወደ ዓለም መጥቶአል /ማቴ. 20፡28፤ 1 ጢሞ. 1፡15/፡፡

Monday, January 4, 2016

በተረገመች ምድር፡ ዕረፍታችን!

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!


                                                                           

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

ሰኞ ታኅሣሥ 25 ቀን 2008 የምሕረት ዓመት

          ‹‹ላሜሕም መቶ ሰማንያ ሁለት ዓመት ኖረ፥ ልጅንም ወለደ። ስሙንም፦ እግዚአብሔር በረገማት ምድር ከተግባራችንና ከእጅ ሥራችን ይህ ያሳርፈናል ሲል ኖኅ ብሎ ጠራው።›› /ዘፍ. 5፡28-29/!

         የመጽሐፍ ቅዱሳችን የመጀመሪያ ክፍል የሆነው የዘፍጥረት (የልደት) መጽሐፍ የትውልዶችን ጅማሬ የሚያስረዳን መጽሐፍ ነው፡፡ ስለ ተፈጥሮ ጅማሬ፤ ግሩምና ድንቅ ሆኖ ስለ ተፈጠረው የሰው ልጅ፤ ውድቀት ስላስከተለው ኪሳራ፤ ያንን ተከትሎ ለሰው ስለተሰጠው የመዳን ተስፋ የምናውቅበት ክፍል ነው፡፡ ምእራፍ አምስት ‹‹የአዳም የትውልዱ መጽሐፍ ይህ ነው›› በሚል ርእስ ይጀምራል፡፡

         በምእራፉ ውስጥ

1.     አዳም (5፡1-5)፡- ሰው ማለት ነው፡፡
2.    ሴት (5፡6-8)፡- ምትክ ማለት ነው፡፡
3.    ሄኖስ (5፡9-11)፡- ደካማ ማለት ነው፡፡
4.    ቃይናን (5፡12-14)፡- አሳዛኝ ማለት ነው፡፡
5.    መላልኤል (5፡15-17)፡- በእግዚአብሔር የተባረከ ማለት ነው፡፡
6.    ያሬድ (5፡18-20)፡- ቀጣይ ትውልድ ማለት ነው፡፡
7.    ሄኖክ (5፡21-24)፡- ትምህርት ማለት ነው፡፡
8.    ማቱሳላ (5፡25-27)፡- ሲሞት ይመጣል ማለት ነው፡፡
9.    ላሜሕ (5፡28-31)፡- ኃይለኛ ማለት ነው፡፡
10.  ኖኅ (5፡32)፡- ዕረፍትና ምቾት ማለት ነው፤ (ዝርዝሩ እስከ ዘፍ. 6፡8 ድረስ ይቀጥላል)፡፡

         ከላይ ከተዘረዘሩት ትውልዶች መካከል ኃይለኛና ብርቱ የሚል የስም ትርጉም ያለው ላሜሕ ለልጁ ለኖኅ ያወጣለትን የስም ትርጉም በተነሣንበት ርእስ ለማየት እንሞክራለን፡፡ ስሙንም፦ እግዚአብሔር በረገማት ምድር ከተግባራችንና ከእጅ ሥራችን ‹‹ይህ ያሳርፈናል›› ሲል ኖኅ ብሎ ጠራው፤ ተብሎ ተጽፎልናል፡፡ በላሜሕ ልብ ውስጥ ያለውን ታላቅ ምኞት አስተውላችሁ ከሆነ በአጭር ቃል ‹‹ዕረፍት›› መሆኑን ትደርሱበታላችሁ፡፡