Friday, October 17, 2014

አብርሃም እንዲህ አላደረገም


ጥቅምት 7 ቀን 2007 የምሕረት ዓመት

‹‹አብርሃም እንዲህ አላደረገም›› /ዮሐ 8÷40/!

       የተሻለ ሰምቶ የተሻለ መናገር፤ የበለጠ አይቶ የበለጠ መሥራት በሰው ልጆች ሕይወት ውስጥ የማይቋረጥ ቅብብሎሽ ነው፡፡ ይህንንም አበው ‹‹ትውፊት›› ወይም ጤናማ መወራረስ ይሉታል፡፡ ያለንን መቀባበል መልካም ነው፡፡ የምንቀበለው ሁሉ ግን መልካም ሊሆን አይችልም፡፡ ከእግዚአብሔር የተቀበልነውን ሕሊና ሥራ ላይ ከምናውልበት መንገድ አንዱ መምረጥ ስለሆነ፤ እንደ ባለ አእምሮ አስተውለን ልንመርጥ  ያስፈልገናል፡፡ የሚረባንን ከማይረባን መለየት የምንችልበት መንሽ ደግሞ ቅዱስ ቃሉ ነው፡፡

       መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹አባትህን ጠይቅ ይነግርህማል›› /ዘዳ 32÷7/ የሚል መጽሐፍ ብቻ አይደለም፡፡ ለአንዳንድ ልብ የመጽሐፉ ሙሉ ጭብጥ ከዚህ አይዘልም፡፡ ነገር ግን ‹‹ማስተዋል ይጋርድሃል›› /ምሳ 2÷11/ ተብሎ እንደ ተፃፈ፤ የቃሉን ሙሉ ገጽታ መመልከት ያስፈልጋል፡፡ በኑሮአችንም እንዲሁ ነው፡፡ ማስተዋል ከከንቱ ኑሮ፤ ውልና ማለቂያ ከሌለው ጥረት፤ ከስህተት ጎዳና ይጠብቃል፡፡ ምድሪቱ ላይ እኛን አድራሻ አድርጎ ከሚመጣ ከየትኛውም ክፉ ትግል፤ ከቅርብም ከሩቅም ባላንጣ መጋረድ በቃሉ ነው፡፡ ጌታ በሊቀ ካህናትነት ጸሎቱ ‹‹በእውነትህ ቀድሳቸው፤ ቃልህ እውነት ነው።›› /ዮሐ 17÷17/ እንዳለ፤ ከየትኛውም ጠላትነት የምንጠበቅበት አጥር ቅዱስ ቃሉ ነው፡፡ በዚህም ውስጥ የምናስተውለው ትልቁ ነገር ቅዱሱን እግዚአብሔር ነው፡፡

       ካለፉት በሕይወት ኖሮ መማር እጅግ ጤናማ ነው፡፡ ሌሎች ቀድመውን ካዩት መማር እየቻልን ‹‹እስክናይ›› ብለን ግትር አንሆንም፡፡ ነገር ግን የቀደሙን ያዩት ሁሉ ልክ፤ የሠሩት ሁሉ እጅግ በጣም ጥሩ እንደ ሆነ ማሰብ ደግሞ ጤናማ አይደለም፡፡ ኑሮአችን ከዘላለም እስከ ዘላለም ያው /መዝ 89÷2/ በሆነው እግዚአብሔር ይመዘናል፡፡ በተሰጠን የእውነት ቃል /ኤፌ 1÷13/ ሁሉም ይፈተሻል፡፡ ሐዋርያው ጴጥሮስ ‹‹ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከከንቱ ኑሮአችሁ በሚያልፍ ነገር›› /1 ጴጥ 1÷19/ ሲል፤ ውርስ ሁሉ ጤናማ አለመሆኑን ያስገነዝበናል፡፡ ከሙግቶቻችን አልፈን ማየት ካልቻልን ለእኛ መዳን እንዴት ጭንቅ ነው?

        የእግዚአብሔር ልጅ ከዳዊት ዘር ከድንግል ማርያም በሥጋ ተወልዶ በተገለጠበት ጊዜ፤ ክርስቶስን ሰቅሎ የገደለው በጊዜው የነበረው ትውልድ ብቻ አልነበረም፡፡ ውርሳቸውም ጭምር እንጂ፡፡ አዎ! ውርስ ሁሉ ጤና አይደለም፡፡ መቃብር ወርደው እንኳ የቆሙትን የሚያጋድሉ፤ ቆመው ሳሉ ሞተው የኖሩ ብዙ ሰዎች ናቸው፡፡ ሐዋርያው ‹‹ከከንቱ ኑሮአችሁ›› እንጂ ከከንቱ ኑሮአቸው አላለም፤ ውርሱ ቃል ሳይሆን ኑሮ ጭምር ነው፡፡

        ተወዳጆች ሆይ፤ ኑሮ ሁሉ መልካም አይደለም፡፡ የኖረም ሁሉ ሕያው አይደለም፡፡ ቁም ነገሩ ኖረ ሳይሆን እንዴት ኖረ፤ ኖረች ሳይሆን እንዴት ኖረች ነው፡፡ መኖርማ ጋራ ሸንተረሩ፤ ባህር ውቅያኖሱ፤ ዛፍ ቅጠሉ፤ እንስሳ አራዊቱም ይኖራል፡፡ ሰው ቆሞ ከሞተ፤ ሞቶ ይኖራል ማለት ነው፡፡ ታዲያ የሠራን እግዚአብሔር እንዳሰበልን አይነት ኑሮ እየኖርን ነው ወይ? ዛሬ የቸገረው ማንም የሚኖረውን ኑሮ መኖር አይደለም፡፡ ለብዙዎች ጭንቁ እንደ እግዚአብሔር የልቡ ፈቃድና የዘላለም አሳቡ መመላለስ ነው፡፡

       ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹አለማመን››፤ ‹‹ኃጢአት›› እንደ ሆነ በተናገረበት ክፍል፤ አይሁድ አብርሃም አባታቸው እንደ ሆነ አጠንክረው ነገሩት፡፡ እርሱም ‹‹እኔ በአባቴ ዘንድ ያየሁትን እናገራለሁ፤ እናንተም ደግሞ በአባታችሁ ዘንድ ያያችሁትን ታደርጋላችሁ።›› /ዮሐ 8÷38/ ሲላቸው እናነባለን፡፡ አብርሃም ሳይወለድ ላለው ጌታ /ዮሐ 8÷58/፤ አይሁድ ስለ አብርሃም አባትነት ይነግሩታል፡፡ እርሱ ግን ስለ ትክክለኛ አባታቸው አስረግጦ ነገራቸው ‹‹እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ፤ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ።›› /ዮሐ 8÷44/፡፡ ጌታ እንዲህ ለመሆናቸው አስረጅ ያደረገው ተግባራቸውን ሲሆን፤ ይህንንም አብርሃም እንዲህ አላደረገም በማለት አስረዳቸው፡፡

       በእርግጥም አይሁድ ያደረጉትን አብርሃም በዘመኑ አላደረገውም፡፡ ግን በእርሱ ይመኩበት ነበር፡፡ አብርሃም እንዳመነና እንደ ጸደቀ /ዘፍ 15÷6/፤ እምነቱ ጽድቅ ሆኖ እንደ ተቆጠረት በኦሪት መጽሐፋቸው በግልጥ ተቀምጦ ሳለ፤ አይሁድ አለማመን ጠንቅ ሆነባቸው፡፡ መርጦ መታዘዝ፤ ቃሉን መጠምዘዝ /Confirmation biased/ ብዙ ጊዜ የማናስተውለው ድካማችን ነው፡፡ በቃሉ ውስጥ ወደ ምናስተውለው ውሳኔ ከመጠቅለል ይልቅ በእኛ ውስጥ ላለው ውሳኔ ቃሉን እንደሚስማማን አድርገን መሸነፍ ይቀናናል፡፡

       ተወዳጆች ሆይ፤ በዙሪያችን እየሆነ ያለው ከዚህ ሀቅ የራቀ ነውን? ኑሮ እንደ አባቶቻችን ነውን? ብዙዎች የወረወሩትን ድንጋይ የወረወሩ፤ ካፋቸው የወጣውን ነውር የተናገሩ፤ ካላመኑ ይልቅ በከፋ ልብ የኖሩ ናቸውን? ለአይሁድ ልክ የሆነውን የተናገረ ጌታ፤ ለእኛስ ቢመልስ ምን ይመልሳል? በእምነት አባቶች የምንላቸው፤ ለእውነት እንደ ተሰደዱ ከምንሰማበት ከዚያው ወሬ መካከል እውነትን የሚያሳድዱ፤ ስለ ቀደሙት፤ በጽድቅ ኖረው እንዳለፉ በሚዘከርበት በዚያው አደባባይ ጽድቅ ሲረገጥ /ኢሳ 59÷14/፤ በክርስቶስ አምነው እንደ ሞቱ ብዙ ከሚባልበት ከዚያው መሰብሰብ መካከል በወንጌል ላይ ሽለላ፤ በእውነተኞች ሬሳ ላይ እንኳን የሚፎከርበትን ሁኔታ፤ ጌታ ‹‹አብርሃም እንዲህ አላደረገም›› አይለውምን?     
  
       በማይታዘዙት ልጆች ላይ አሁን የሚሠራው መንፈስ አለቃ /ኤፌ 2÷2/ ዲያብሎስ አባት የሆነላቸው ካልሆኑ በቀር ‹‹ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን የማይወድ ቢኖር የተረገመ ይሁን። ጌታችን ሆይ፥ ና›› /1 ቆሮ 16÷22/ እየተባለ፤ ተግባራዊ በሆነ ሁኔታ ለዚህ ጌታና ለባሪያዎቹ ፍፁም ጥላቻን ማሳየት በደል ነው፡፡ አይሁድ ‹‹ነን›› የሚሉትና እግዚአብሔር ‹‹ናችሁ›› የሚላቸው ፍጹም ለየቅል ነበር፡፡

       እነርሱ የዲያብሎስ ልጆች፤ የጽድቅም ሁሉ ጠላት ሆነው ሳለ እግዚአብሔርን የሚያመልኩ ይመስሉ ነበር፡፡ እየተጉ የሰለጠነባቸውን አያስተውሉትም ነበር፡፡ ዛሬም በዚህች መንገድ ለሚሠሩባት ወዮታ አለባቸው፡፡ የዲያብሎስን ሥራ እንዲያፈርስ /1 ዮሐ 3÷9/ የተገለጠው የእግዚአብሔር ልጅ ክፋትን ሲበቀል፤ ቁልሉን ሲንደው አብራችሁ እንዳትገኙ ፊታችሁን ወደ እውነት ዘወር አድርጉ፡፡ ጌታ ቸር ነውና ምሕረቱም ለዘላለም ናትና፤ ቸል አትበሉ፡፡ እጁ ዛሬም ተዘርግታ አለች፡፡ ‹‹እንግዲህ። በኃጢአታችሁ ትሞታላችሁ አልኋችሁ፤ እኔ እንደሆንሁ ባታምኑ በኃጢአታችሁ ትሞታላችሁና አላቸው።›› /ዮሐ 8÷24/፡፡ ጸጋ ይብዛላችሁ!!  
                                   ‹‹ . . . ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ፤›› /ቆላ. 4፡3/!

4 comments:

  1. Tebareku betikikil endalachihut new.

    ReplyDelete
  2. የፍቅር አምላክ ይባርካችሁ

    ReplyDelete
  3. በጣም ፈጣሪ ይባርክህ

    ReplyDelete