Wednesday, April 17, 2013

የአያቴ ምች መድኃኒት



                                      እሮብ ሚያዝያ 9/2005 የምሕረት ዓመት

          ለዛሬ ለምንነጋገርበት ነገር መነሻ አሳብ የሆነችኝ አያቴ ናት፡፡ መቼም ስለ አያት ሲነሣ ብዙ ነገር በአእምሮአችሁ ላይ ድቅን እንደሚል እገምታለሁ፡፡ በተለይም በአያት ያደጉ ልጆች በብዙ እንክብካቤና ስስት ስለሚያድጉ የእናትን ፍቅር በሚተካከል ደረጃ ፍቅርን ተመግበዋል ተብሎ ይታሰባል፡፡ እንዲያውም ሞልቀቅ የሚሉ ሰዎችን በአያት እጅ እንዳደጉ መገመት የተለመደ ነው፡፡ እንደ የልጅ ልጅ ስናስብ አያት ብዙ ነገር ነው/ናት፡፡ ሚስት ከባሏ ጋር ብትጣላ ለልጆችዋ የአደጋ ጊዜ መሰብሰቢያና የአባወራው ማስፈራሪያ አያት ናት/ነው፡፡ አባት ሚስቱ ብትጎረምስበት፣ ልጆቹን አስታቅፋው እንደ ልቧ ብትሄድ አልያም በሞት ብትለየው ቅድሚያ መፍትሔው አያቱ ናት፡፡ ከዚህ የተነሣ ብዙ ጊዜ ወላጆች ቢሞቱ ልጅ የማሳደግ ግዴታው በሕይወት ባሉ አያቶች ላይ ሲወድቅ ማስተዋል ብርቅ አይደለም፡፡ አንዳንድ ትዳሮችን ስንመለከት ደግሞ በአያት ቁጥጥር ስር የሚተዳደሩ ናቸው፡፡ አጣምረውም አለያይተውም ሊያኖሩ የሚችሉበት አቅም አንዳንድ አያቶች ውስጥ እንመለከታለን፡፡ ጠልተው ሊያስጠሉ፤ ወድደው ሊያስወድዱ፣ ተናግረው ሊታመኑ ይችላሉ፡፡

          ስለ አያት ለምን አነሣሁ መሰላችሁ? የእኔ አያት እንደ ብዙ አያቶች ሁሉ ኃይለኛና አይበገሬነቷ ትዝታ ጭሮብኝ ነው፡፡ በምንድነው አይበገሬነቷ? ብላችሁ ብትጠይቁኝ አያቴ በታመመች ቁጥር የሕክምና ባለ ሙያ ጋር እንድትሔድ በቤትም በጎረቤትም ተለምና በጄ አለማለቷ ነው፡፡ እንኳን በታወቀውና በግልጹ ቀርቶ በተሰወረውም ሕመሟ ከሐኪም ዘንድ መፍትሔ አትፈልግም፡፡ እንደ ምንም አስገድደን ለመውሰድ በምናደርገው ሙከራ እንኳ ገና ክፉና ደጉን እንዳለየ ሕፃን የምታሰማው ጩኸት ልብም እግርም ይይዛል፡፡ ታዲያ ምን እንዲሻል ብንጠይቃት ጓሮ ለብዙ ዘመን ስትንከባከበው፣ ውኃ ስታጠጣው፣ ፍግ ስትመግበው የኖረ፤ እርሷም ልክ እንደ ወላጆችዋ በቅብብሎሽ ከእሷ ዘንድ በደረሰው ቦታ ላይ የጸደቀ ቅልብ (ይጠብቃል) ምች መድኃኒት ቆርጣችሁ አምጡልኝ ትላለች፡፡ ለእሷ በሽታ ከዚህ የበለጠ መፍትሔ የለም፡፡ ምክንያቱም እሷና ምች መድኃኒቷ አብረው ዘመን የተሻገሩ፣ ከየትኛውም መድኃኒት በበለጠ የተላመዱ እንዲሁም በቅርብ ዘወር ብላ የሚገናኙ ናቸው፡፡ ስትናገር፡-“ከዛሬ ሐኪምና መድኃኒት እኔ ጓሮ ያለችው ምች መድኃኒት ትበልጣለች” ትላለች፡፡ ስለዚህ እምቢታዋ ልክ እንዳላይደለ ቢገባንም አያት ስለሚከበር፣ ስለሚፈራ፣ መብት ስለማይጣስ ያለችውን አርሰንና አሽተን እናጠጣታለን፡፡

          አንዳንዴ መለስ ሌላ ጊዜ ደግሞ ቀለስ እያለች በገዛ እጇ ተንጣ ኖራለች (የዛሬን አያድርገውና)፡፡ ስለ ሕክምና ጥቅም፣ ለችግሯ ስለሚሆን መፍትሔ ያለ ማቋረጥ እንነግራታለን፡፡ ዳሩ ግን የአያቴ ምች መድኃኒት የሞት መድኃኒት ያክል ነበር፡፡ እዚያ ሔጄ አንዴ ኪኒን ሌላ ጊዜ መርፌ ከምቀለብ የማይዋጥም የማይወጋም “የሚጠጣ ምች መድኃኒቴ ፍቱን ነው” እያለች ታስቀናለች፡፡ አያቴ በተረቷና በወጓ ሁሉ ምች መድኃኒቷ ትነሣለች፡፡ የእሷን ምች መድኃኒት የሚያጥላላ አልያም የሚያራክስ ውጉዝ ከመ አርዮስ ይባላል፡፡ እንግዲህ አያቴና ምች መድኃኒቷ ግብአተ መቃብራቸው የተፈፀመው እንዲህ ባለ ፍቅር ውስጥ እያሉ ነው፡፡ ዛሬ ሰዎች አያትህ ምን ሆና ነው የሞተችው ሲሉኝ ምች መድኃኒቷ አታሏት እላቸዋለሁ፡፡ በእርግጥም በእርሷ የሆነው ይኼው ነው፡፡ ሰው እንዴት ሰው በተከለው ይታለላል?    
  

Wednesday, April 10, 2013

ሰቆቃወ ፍቅር



እሮብ ሚያዝያ 2/2005 የምሕረት ዓመት

    የሠላሳ ሁለት ዓመት እድሜ ያላት ሲሴሊያ ከባለቤቷ አዳም ጋር በፍቅር ያሳለፈችውን ጊዜ በቀላሉ ልትረሳው፣ በሰዎች የማጽናኛ ቃል ልታልፈው፣ እንደ አሮጌ ኑሮ ቆጥራው አዲስ ምዕራፍ ልትጀምር አቅም አልነበራትም፡፡ የሞተው ባለቤትዋ ስርዓተ ቀብሩ እንዳበቃ ከመቃብር አውጥታ በአልጋዋ ላይ በማስተኛት ለሁለት ዓመታት ያህል ቀን አብራው በመዋል፣ ሌሊቱን አብራው በማደር አሳልፋለች፡፡ የባሏ እስትንፋስ የተቋረጠ ቢሆንም እርሷ ለእርሱ የነበራት ፍቅር ሕያውነት ግን ቀጥሏል፡፡

    ስለ እርሱ ስትናገርም “አዳምን ምን ጊዜም ቢሆን አልረሳውም፡፡ በአካል ቢሞትም ልቤ ላይ ግን ሕያው ነው፡፡ እርሱ በጣም አስደናቂ ሰው ነበር፡፡ አጽሙን ከእኔ ጋር በማኖሬ ተጽናንቻለሁ፡፡ ፍቅሬንም ተወጥቻለሁ፡፡” በማለት ነበር፡፡ በመጨረሻ ግን የባለቤቷን አጽም ወደ መቃብሩ በመመለስ ሄንሪ የተባለ ሰው አግብታለች (ትንግርት መጽሔት፣ ግንቦት/ሰኔ 1985፣ ገጽ 5)፡፡

    አንዳንድ ሰዎች ፍቅር ልክ እንደ እቅፍ አበባ ለሌላው የሚሰጥ ነገር እንደ ሆነ ሲያስቡ ሌሎች ደግሞ በላይህ ላይ የተጣለ የማይረባ ግን ደግሞ የጠነከረ ኃይል ነው በማለት ይስማማሉ፡፡ ፍቅር ግን ልንሰጠው የምንችለው ማንኛውም ነገር አይደለም፡፡ ፍቅር ራሱ ሌሎች ነገሮችን እንድንሰጥ የሚያስችለን ከፍተኛ ግፊት ነው፡፡ ጥንካሬን፣ ኃይልን፣ ነፃነትንና ሰላምን ለሌሎች እንድንሰጥ የሚረዳን ጉልበት ፍቅር ነው፡፡

    ከዚህ አሳብ በመነሣት ፍቅር ውጤት ሳይሆን መንስዔ፣ ወራጅ ሳይሆን ምንጭ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ስለዚህ ከፍቅር የተነሣ የማንሰጥ ከሆነ፣ ከፍቅር የተነሣ ይቅር የማንል ከሆነ፣ ከፍቅር የተነሣ የማንራራ ከሆነ፣ ከፍቅር የተነሣ ለእውነት የማንኖር ከሆነ በእኛ ያለው የፍቅር ኃይል ተዳክሟል አልያም ሞቷል ማለት ነው፡፡ በሕይወት ውስጥ እጅግ የከበረውና ቀዳሚው ነገር ሌላውን ማፍቀር ነው፡፡ በማስከተልም በሕይወት ውስጥ እጅግ የከበረው ነገር በሌላው መፈቀር ነው፡፡ በመጨረሻ እጅግ የከበረው ነገር ከላይ የተመለከትናቸው ሁለቱ በእኩል ጊዜ መሆን ሲችሉ ማለትም ባፈቀሩት ሰው ሲፈቀሩ ነው፡፡

      የሰው ፍቅር ልዩ ልዩ ቢሆንም የእግዚአብሔር ፍቅር አንድ መሆኑ ዘመን የማይሽረው መጽናኛችን ነው፡፡ እግዚአብሔር እኛን እንዴት እንደወደደን መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር “እንዲሁም ዓለም አንተ እንደላከኝ በወደድከኝም መጠን እነርሱን እንደወደድካቸው ያውቃሉ” (ዮሐ. 17÷23) ይላል፡፡ እግዚአብሔር እኛን የወደደን ፃድቅ፣ የዋህና ትሁት የሆነውን እስከ መስቀል ሞትም የታዘዘውን አንድ ልጁን በወደደበት ፍቅር ነው፡፡ ለዚህም ነው እግዚአብሔር ሲወድ የሰውን ማንነት ታሳቢ አድርጎ አይደለም የምንለው፡፡ መልክና ቁመና፣ ሀብትና ሥነ ምግባርን ግምት ውስጥ በማስገባት አልያም ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጥ ሰውን መውደድ የሰው ፍቅር እንጂ የእግዚአብሔር አይደለም፡፡

      ፍቅር የሰውን ልማድ ይሻገራል፡፡ ጥሙን ሳያረካ፣ ርሀቡን ሳያጠግብ፣ መሻቱን ሳይሞላ አይዝልም፡፡ ከንቱ በሆነው በዚህ ዓለም መለፍለፍ ውስጥ ያለው የማይሰለች አጓጊ ወሬ ፍቅር ነው፡፡ ደመ ነፍስ በሆኑ እንስሳት ውስጥ እንኳ ይህ ኃይል መታየቱና መሥራቱ ምንኛ ድንቅ ነው! አብዛኛውን ጊዜ መልካም በምንላቸው ነገሮች ውስጥ ምቾትን ብቻ እናስተውላለን፡፡ ሰው እግዚአብሔርን ተከትሎ መራብ መቸገር፤ ማዘን መከፋት የለበትም የሚለው ሙግት ምንጩ ይኸው አመለካከት ነው፡፡ በዓለም ሳለን መከራ እንዳለብን ግን እናውቃለን (ዮሐ. 16÷33)፡፡ አፍቅረን ካፈቀርነው ጋር፣ ደክመን ከደከምንለት ነገር ጋር፣ ዋጋ ከፍለን ከለፋንለት ነገር ጋር ላንኖር ወይም የእኛ ላይሆን ይችላል፡፡ ሰው ባይነጥቀን እንኳ ሞት ተናጥቆን ይሆናል፡፡ ምድር በብዙ ፍትሐዊ ባልሆኑ ነገሮች የተሞላች ናት፡፡ ከዚህም የተነሣ ዓለም በብዙ ሙሾና ለቅሶ፤ ሰቆቃና እንግልት እረስርሳለች፡፡