Friday, January 13, 2012

ውበት ሲብራራ


ውብ እጆች፡- ላዘኑት ደማቅ የደስታ ክርን በሕይወተታቸው የሚሠሩ በረከቶች ናቸው።
ውብ እግሮች፡- ከጸሐይ መውጫ እስከ ጸሐይ መግቢያ ድረስ ለይቅርታ መልዕክት የሚሮጡ መዳረሻዎች      ናቸው።
ውብ ቅርጾች፡- የተዋረደውን ቦታ ረጋ ካለ አገልግሎት ጋር ሞገስ የሚሰጡ ትሁታን ናቸው።
ውብ ፊቶች፡- መለኮታዊ በሆነ ፍጹም ፍቅር የሚያንጸባርቁ ገጾች ናቸው።
ውብ ከናፍሮች፡- ያዘኑትን የሚያጽናኑ፣ የደከሙትን የሚደግፉ፣ የወደቁትን የሚያነሱ የእውነት ዙፋን ናቸው።
ውብ ዓይኖች፡- እንደ በረዶ በነጣ መንፈስ በጨለማው ላይ የሚያበሩ ከዋክብት ናቸው።
ውብ ነፍሳት፡- በተገኙበት ቦታ ሁሉ የእግዚአብሔርን መፍትሔ የሚያሳዩ ታማኝ ሎሌዎች ናቸው።
ውብ ነዋሪዎች፡- ለሌሎች ኑሮ የሌሎችን ድካም የሚሸከሙ ቅን ትከሻዎች ናቸው።
የእውነተኛ ሰብእና ሕያው ድምቀት፤ አማላይ ውበት ያለው በዚህ ውስጥ ነው፡፡ ለእኛም ሆነ ለሌሎች ሕይወት ትርጉም የሚኖራት መኖርም በናፍቆት የሚቃኘው በዚህ ከተገኘን ብቻ ነው!

Wednesday, January 11, 2012

መቃብር አይሞቅም



  የእግዚአብሔር ፍትሃዊነት በኑሮ ከምናልፍባቸው  ፈተናዎች ጋር ያለው ተዛምዶ አልገባ  ሲለን ከምንናገራቸው ብሶት ወለድ አባባሎች አንዱ “ኑሮ ካሉት መቃብር ይሞቃል” የሚል ነው:: ከዚህ እድሜ ጠገብ ብሂል በ'እኛ' ውስጥ የምናስተውለው ልዩ ልዩ  ቢሆንም በ'እኔ' ውስጥ ብቻ  ሆኜ ስረዳው ግን በመኖር ውስጥ ካለው ቅዝቃዜ በመሞት ውስጥ ሊኖር የሚችለውን ሙቀት ያስበለጠ  ይመስለኛል:: ምንም እንኳን በድንን ሙቀት ሳይሆን ቅዝቃዜ ቢገልፀውም የሰው ምሬት ግን ይህንን በመሻል እና በመሞቅ ደረጃ አስቀምጦታል::
   የመስጴጦሚያ ጥንታዊያን ህዝቦች የአንድን ሰው መጨረሻ አሊያም ተስፋ ቢስ እጣ ፈንታ ለመግለፅ ይጠቀሙበት የነበረው አገላለፅ “ትቢያ ውስጥ መጋደም”  የሚል ነበር:: ይህም ህይወት እንዳከተመች ለሚሰማቸው ሁሉ ከመሬት በታች የቀረላቸው እረፍት ነው::
   ፃድቁም ኢዮብ የመከራው እንቆቅልሽ፣ እግዚአብሔርም በእርሱ መፈተን ላይ ያለው ዓላማ አልረዳ ሲለው “አሁን በምድር ውስጥ እተኛለሁ ማለዳ ትፈልገኛለህ አታገኘኝም” (ኢዮ 7፥21) በማለት በምሬት ተናግሯል:: እንዲህ ያሉ አነጋገሮች ሕይወት ብርቱ ሰልፍ በሆነባት ቁሳዊ ዓለም ውስጥ አዲስ ነገር አይደሉም:: ሰዎች በመንፈሳቸው ጭንቀት፣ በነፍሳቸው ምሬት፣ በቀን ሁከት በሌሊት ቅዠት ውስጥ ሲያልፉ፤ ዓይን የመክደኛ ምራቅ የመዋጫን ያህል እረፍት ከልባቸው መዝገብ ሲርቅ ከመከራ ወደላቀ መከራ መገላበጥ የግዴታ  ትጋት ሲሆንባቸው ከዚህም በላይ ሲናገሩ አልፎም ተርፎ ሲያደርጉ እናያለን:: ሕይወት ግን አንድ ጎን ብቻ አይደለችም። መደሰት እንዳለ ሁሉ ማዘን፣ የምስራች እንዳለ ሁሉ መርዶ መስማት ዓለሙ የተዋቀረበት ሀቅ ነው፡፡
   ለማግኘት በምናደርገው ጥረት ውስጥ የማጣት ሥጋት፣ ዕረፍትን በመናፈቅ ውስጥ የሕመም ፍርሃት፣ ክብርን በመሻት ውስጥ የውድቀት ሥጋት፣ ሕይወትን በማፍቀር ውስጥ የሞት ፍርሃት፣ ድልን በመጠበቅ ውስጥ የሽንፈት ውጥረት በብርቱ ይታገለናል:: ንቁ አእምሮ ያለው ሰው በራስ የመርካትም ሆነ ተስፋ የመቁረጥ ሁኔታ አይታይበትም:: የዘመኑን መርዶ አዘል ዜናዎች ቢሰማም ለመኖር ከሚያሳየው ጉጉና ጥረት አይቦዝንም:: የሕይወትን አስቸጋሪ ገጽታዎች ቢጋፈጥም “አበቃልኝ” አይልም:: የቱንም ያህል ፈተና ቢጋፈጥ የትቢያ ውስጥ ሙቀትን አይመኝም:: ይልቁንም የወደፊት ተስፋው በእግዚአብሔር አስተማማኝ እጆች ውስጥ ፍጻሜ እንዳለው ስለሚያውቅ እያንዳንዱን ዕለት በብልሃት በጭምትነትና በመታዘዝ ያሳልፋል:: አመለካከት የሕይወትን ስኬትና ውጤት ይወስናልና አስተሳሰባችን የቀና ከሆነ ስኬታማነታችንም የተረጋገጠ ነው:: ማናኛችንም ብንሆን መታወክ የሌለበት ከፈተናና ከውጣ ውረድ የጸዳ መሻታችን ሁሉ የተሟላበት ኑሮ ቢኖረን እንፈልጋለን:: ዳሩ ግን ሕይወት ሙሉ ጣዕም የሚኖራት ሁለቱንም ጫፍ (ማግኘትና ማጣት) በመንካት መሐሉ ላይ ስንኖራት ነው::
   ማኅበራዊ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት በምቾት ውስጥ አልፈው ለስኬት ከበቁት ይልቅ በፈተና ውስጥ እንደ ወርቅ ነጥረው በድል ያብረቀረቁ ታታሪ ሰዎች አብላጫውን ቁጥር ይወስዳሉ:: ለምናምን ለእኛ ከሕያው እግዚአብሔር እቅፍ ባለፈ  የሚሞቅ ቦታ የለም:: ያም በሚያስፈልገን ሁሉ በእምነት የምንቀርብበት የጸጋ ዙፋን  ነው:: የእግዚአብሔር ልጅ ከመቃብር ኑሮ  የታደገን እስከ መስቀል ሞት ታዝዞ  ነው:: ስለዚህ እግዚአብሔር ያለው ሰው ኑሮ  የሸክሞቹ ስብስብ፣ ሕይወት የእንቆቅልሾች አደባባይ ብቻ እንደሆነ አያስብም:: ፈረንሳውያን “ክፉን አላይም ብለህ ዐይንህን አትጨፍን ደግ ሲያልፍ ያመልጥሃልና” ይላሉ:: ኑሮን የሚያጣፍጠው ሁሉን  በልኩና በሚዛናዊነት ማስተዋል ነው:: ተወዳጆች  ሆይ መቃብር አይሞቅም!! 
                                                  ይቀጥላል  

Sunday, January 1, 2012

የተወደደ መስዋዕት (ካለፈው የቀጠለ)


     ምስጋና ጣፋጭ ከሆነ መዓዛ፣ ቅን ከሆነ አስተሳሰብ በቀር ምንም ከማያውቅ የሰው ነፍስና መንፈስ የወጣ ውብ አበባ ነው። ልክ አዲስ የተወለደ ሕጻን በፈገግታው ሙሉ ቤቱን ደስ የሚልና አስደሳች እንደሚያደርገው ሁሉ አመስጋኝ ልብ ያለውም ሰው ሙሉ ዓለምን ደስተኛ ያደርጋታል፡፡ የምስጋና ቃል ጥቂት ቢመዝንም ትርጉሙ ብዙ ነው። ለሰጪው የነፍስ ደስታን ሲሰጥ እንዲሁ ተቀባዩ ከእኛ ጋር የሚኖረውን ወዳጅነትም ማለዳ ማለዳ አዲስ ያደርገዋል፡፡ ስለዚህም የምንወደው  ጠባያችን ምስጋና እንዲሆን ፈቅደን መምረጥ ይኖርብናል፡፡ ልብ በሉ! አመስጋኝ ሰው በእሾህ መሐል እንዳለች ውብ ጽጌረዳ ዘመኑን ሁሉ ማራኪ እንደሆነ ይጨርሳል፡፡
     ማንም ሰው ለደስታና ለፍጹምነት ያለውን አጭሩንና እርግጠኛውን መንገድ ሊነግረን ከወደደ ስለሆነልንና ስለሆነብን ማንኛውም ነገር ጌታ እግዚአብሔርን የምናመሰግንበትን መርህ እንድናዘጋጅ ሊነግረን ይገባል፡፡ የትኛውም የከፋ ነገር ቢከሰት እንኳን አመስጋኝነት ወደ በረከት ሊለውጠው አቅም አለው፡፡ ለራሳችንም ልንሠራ ከምንችለው በላይ ተአምር ሲሠራ ማየት እንችላለን፡፡ አመሰግናለሁ ለማለት ምንአልባትም በጊዜው አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ፍሬው ጣፋጭ መከሩም ብዙ ነው፡፡ በዓለም ላይ ትልቁ ምላሽ አመሰግናለሁ የሚለው ነውና!
     ስለ ማመስገን ስናስብ ሁለት ነገሮችን እናስታውሳለን፡፡ የመጀመሪያው ስለተቀበልነው ነገር የሚሰማን ዓይነት ምስጋና ሲሆን ይህም ድንገተኛ ነው፡፡ ሌላኛው ደግሞ ስለሰጠነው ነገር የሚሰማን ምስጋና ሲሆን ይህም ትልቁ ነው፡፡ ለአብዛኞቻችን የመጀመሪያው የለመድነው ዓይነት ሲሆን ከስጦታ ጋር በተያያዘ የሚሰማን ደስታና የጋለ ስሜት ነው፡፡ እንግዳ የሚሆነውና ጥንካሬን የሚጠይቀው የምስጋና ዓይነት ግን ሁለተኛው ነው፡፡ ሁላችንም ልንስማማበት እንደምንችለው ይህ ይበልጥ አስደናቂ ነው። በሌሎች ሕይወት ጨለማ ላይ ጥቂት ብርሃን የማብራት ድካማቸውን የመጋራት ከዕንባቸው ጋር የማንባት አጋጣሚውን ስናገኝ ምን ያህል ሰላም ይሰማናል? ምን ያህልስ እንደሰታለን? እንደ እውነቱ ከሆነ መልካም ፈቃዳችንን እና የልግስና ስሜታችንን ለመግለጥ እድሉ ስለገጠመን ጥቂት የሆነ ግን ደግሞ ታላቅ እርካታ ይሰማናል፡፡
    ስለዚህ ምስጋናችንን የተቸርነውን ጥቂት ካላቸው ጋር ፈቅዶ በመጋራት ልናሳይ ያስፈልገናል፡፡ ትክክለኛ ምስጋና የእውነተኛ ወዳጅነት ልዩ ምልክት ነው፡፡ ይበልጥ ማመስገን ደግሞ ይበልጥ ባለጸጋ መሆን ነው፡፡ ነገሮች ጥሩ ባልሆነ መልኩ እየሄዱብን ሳለ የምናሳየው የምስጋና ጠባይ ሁኔታዎች ከዝንባሌያችን ጋር በተስማሙበት ጊዜ ከምናቀርበው ምስጋና ይልቅ ዋጋው እጅግ ከፍ ያለ ነው፡፡ ብዙ በተደረገልን ቅጽበት ትንሽ ማመስገን ቀላል ሲሆን ምንም ባልተደረገልን ሰዓት ጥቂት ማመስገን ግን ይከብደናል፡፡ ለጥቂቱ ካላመሰገንን ለብዙውም አናመሰግንምና በማመስገን ደካማ ከሆን ደግሞ በሁሉም ጠባያችን ደካማ እንሆናለንና በሁሉ ማመስገንን አሁኑኑ እንጀምር!
     ሰውን ካፈቀርክ ፍቅርህ ሊታይ ይገባል፡፡ ስለ ሰው ሀዘን ከተሰማህ ርኅራሄህ ሊገለጥ ይገባል፡፡ ጥቂት ውለታን ብትፈልግ ትህትናህ ሊብራራ ይገባል፡፡ በነገር ሁሉ አስተዋይ ከሆንክ ደግሞ ምስጋናህ ሊታይ ይገባል፡፡
    ተወዳጆች ሆይ! አመስጋኝነታችን እየደመቀ በመጣ ቁጥር ይበልጥ ለመቀበል ዋጋ ያለን እንሆናለን፡፡ ከሁሉም የሚበልጠው ውብ ጠባያችንም ባለን የምስጋና መጠንና ብርታት ታይቶ የሚፈተን ነው፡፡ ስለዚህ ለሚቀጥፉት እንኳን መዓዛን እንደሚሰጠው ግሩም ሐረግ አመስጋኝ ሁን!