Tuesday, October 22, 2013

የእግዚአብሔርን አሳብ ማገልገል


                             ማክሰኞ ጥቅምት 12/2006 የምሕረት ዓመት

‹‹ . . . ዳዊትም በራሱ ዘመን የእግዚአብሔርን አሳብ ካገለገለ በኋላ አንቀላፋ፣ ከአባቶቹም ጋር ተጨምሮ መበስበስን አየ፤ ይህ እግዚአብሔር ያሥነሣው ግን መበስበስን አላየም›› (የሐዋ. 13፥36-39)

       ወዳጆች ሆይ ከሁሉ አስቀድሞ የጌታችንና የአምላካችን የመደኃኒታችንም የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ፡፡ በዚህ የጽሑፍ አገልግሎት የእግዚአብሔርን አሳብ ማገልገል ማለት ምን እንደ ሆነ የእግዚአብሔርን ቃል መሠረት በማድረግ እንካፈላለን፡፡ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ጸሐፊ በዚህ ክፍል ላይ ሁለት አገልጋዮችን በንጽጽር ያሳየናል፡፡ ይኸውም ነቢዩ ዳዊትንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ነው፡፡ ስለ ዳዊት የእግዚአብሔርን አሳብ አገልግሎ መበስበስን እንዳየ ሲፃፍ፤ ስለ ክርስቶስ ደግሞ የእግዚአብሔርን አሳብ አገልግሎ መበስበስን እንዳላየ ያስረዳናል፡፡ በዚህ ክፍል የእግዚአብሔርን አሳብ ማገልገል ምን እንደ ሆነ እንመልከት፡፡ ከዚያ በፊት ግን ጥቂት ጥያቄዎችን ለመንደርደሪያ እናንሣ፡፡

አገልግሎት ምንድነው?
የእግዚአብሔር አሳብስ ምን ማለት ነው?
የሚያገለግለው ማን ነው?
ሁሉ ሰው አገልጋይ ነውን?

·                     አገልግሎት ብዙዎች እንደሚያስቡት የሆነ ሃይማኖታዊ ሙያ አልያም የሥራ ድርሻ አይደለም፡፡ አንዳንዶች እንደሚያስቡት ደግሞ ይህንን ያህል ዓመት ተምሬ፣ በዚህን ያህል ውጤት ያገኘሁት  ማዕረግ አልያም ልምምድ አይደለም፡፡  አገልግሎት ከሰው ቃልና ልምምድ የምንወርሰው እውቀትም አይደለም፡፡

          አገልግሎት የእግዚአብሔር የልቡ አሳብና ምክር ነው፡፡ እርሱን ማገልገል ማለትም የእርሱን አሳብ ጠንቅቆ ማወቅና መተግበር ነው፡፡ የእግዚአብሔር አሳብ ማለት የእርሱ ሕይወት፣ የዘላለም እቅድና የልቡ ምክር ማለት ነው፡፡ ይህ ክፍል በደንብ እንዲብራራልን አስቀድሞ ዳዊት የእግዚአብሔርን አሳብ ያገለገለው እንዴት ነው? የሚለውን ለማየት እንሞክር፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን ስንመረምር ዳዊት የእግዚአብሔርን አሳብ አገለገለ የተባለለት በእስራኤል ላይ በመንገሱ፣ ጥሩ የጦር መሪ በመሆኑ፣ ጎልያድን በማሸነፉ አልያም በሌላ ጀብዱ አይደለም፡፡ በዚህ መንገድ ፍለጋችንን ብናደርግ የእግዚአብሔርን አሳብ ማግኘት ከቶ አይሆንልንም፡፡ ስለዚህ ዳዊት የእግዚአብሔርን አሳብ አገለገለ የተባለለት የእግዚአብሔር የልቡ ምክር ምን እንደ ሆነ መረዳቱ ነው፡፡ ከዚህ የተነሣ እንደ ልቤ ተብሏል፡፡

         ዳዊት ካስተዋለው የእግዚአብሔር የልብ አሳብ መካከል አንዱ “ቤት” ነበር፡፡ ዳዊት “እኔ ባማረ ቤት ሆኜ፤ እርሱ ግን በጨለማ ይኖራል” ብሎ የተናገረው ስንፍና ቢሆንም ለእግዚእብሔር ቤትን ለመሥራት ግን ተነሥቷል፡፡ ዛሬም የእግዚአብሔር የልቡ አሳብ ቤት ነው፡፡ እግዚአብሔር ቤትን ይፈልጋል፡፡ ቤት እንዲሠራ በዚያም ለዘላለም መኖር ይፈልጋል፡፡ አሳዛኙ ነገር ግን ዳዊት የእግዚአብሔር የልቡ አሳብ ቤት መሆኑን መረዳቱ እንጂ የትኛውን ቤት እንደ ሆነ አልተረዳም ነበር፡፡ ዳሩ ግን አገለገለ የተባለለት ተግባሩን በመሳቱ ሳይሆን አሳቡ ምን እንደ ነበር በመረዳቱ ነው፡፡ ዳዊት የገባው ያ ቤት ሕያው ቤት እንደ ሆነ ሳይሆን ከእንጨት የሚሠራ ቤት እንደ ሆነ ነው፡፡ ይህን አለመረዳቱ ደግሞ ሕያው ቤት እንዲያፈርስ አድርጎታል፡፡ ለመሆኑ እያልኩ ያለሁትን እየተረዳችሁት ነውን?

         ልብ አድርጉ! ዳዊት እግዚአብሔር ቤት እንደሚያስፈልገው ገብቶታል፡፡ ስለዚህም ቤት ለመሥራት እንጨት እየሰበሰበ ነው፤ በጎን ግን የሕያው እግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ በኃጢአት ምክንያት እያፈረሰ ነው፡፡ ዳሩ ግን እግዚአብሔር ይሻው የነበረው ቤት ሰውን እንጂ የእንጨት ቤትን አልነበረም፡፡ ለእግዚአብሔር ቤትን ለመሥራት በብርቱ ይቀና የነበረው ዳዊት ለእግዚአብሔር ቤት ሆኖ መገኘት አልቻለም፡፡ አካሉን በዝሙት፣ ልቡን በአመጽ፣ ሥልጣኑንም ለግፍ ተጠቅሞበት ነበር፡፡ ዛሬም በዚያው ኃይልና መንፈስ ብዙ ሰዎች ይንቀሳቀሳሉ፡፡ መሮጥ፣ መድከም፣ ማግኘት፣ መሰብሰብ ግን ደግሞ በብዙ መበተን . . . አገልግሎት ግን እንዲህ ያለ አይደለም፡፡

         እግዚአብሔርን የማገልገል ምስጢር የእግዚአብሔርን ትኩረት ፈልጎ የማግኘት ጉዳይ ነው፡፡ የእግዚአብሔርን አሳብ ማገልገል የራሱ የመለኮትን ሕይወትና ማንነት በኑሮ የመግለጥ ሂደት ነው፡፡ የእግዚአብሔርን አሳብ ማገልገል የእግዚአብሔርን መልክ ማሳየት ነው፡፡ እርሱ እግዚአብሔርን በእቅፉ ያለ አንድ ልጁ እንደተረከው የመተረክና የማብራራት መታመን ነው፡፡ የእግዚአብሔር አሳብ አደራረጉ፣ አላማውና አብይ ጉዳዩ ነው፡፡ ከዚህ የተነሣ እግዚአብሔርን ማገልገል ሞያ ሳይሆን ሕይወት፣ እውቀት ሳይሆን የምናሳየው የእግዚአብሔር መልክ እንደ ሆነ እንገነዘባለን፡፡

         አገልግሎት የስነ ልቦና ማንቂያ ደወል ሳይሆን የልጅነት ሥልጣን ነው፡፡ ልጅነት ደግሞ ከእግዚአብሔር ሕይወት የሚገኝ ሰብእና እንጂ በልምምድ የምንወርሰው የሰው ጥበብ አይደለም፡፡ ልክ አንድ ልጅ ከወላጆቹ በመወለድ ብቻ መልክና ጠባያቸውን እንደሚጋራ እንዲሁ ነው፡፡ ማንኛውም ሰው እግዚአብሔርን ወደ ማገልገል ከመሄዱ አልያም ለማገልገል ከመነሣቱ በፊት እግዚአብሔር አሳቡ፣ ትኩረቱ፣ ለሰው ልጆች ያለው ዘላለማዊ አጀንዳ . . . ምን እንደ ሆነ በብርቱ መጠየቅ አለበት፡፡ እንደዚሁ መንፈስ ቅዱስን አሳብ በመንፈስ የመተርጎም፣ ሰዎች ወደ መረዳት ባለጠግነት እንዲደርሱ የማስቻል፣ የተረዱትን ያለ ጭንቀት በደስታ እንዲኖሩበት የማድረግ ተግባር ነው፡፡

         በአገልግሎት ውስጥ መመዘን ያለበት አንድ ሰው የሚናገራቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት ብዛት አልያም በዚህ ረገድ ያለው ብቃት አይደለም፡፡ እንደዚህ ከሆነ በንግግራቸው ብርታት ዓለም ላይ አንቱታን የሚቀበሉ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ሁሉን በሚችል አምላክ ፊት ግን እንደዚህ አይደለም፡፡ እግዚአብሔርን ማገልገል የልቡን አሳብና ምክር መረዳት ከሆነ የእርሱ ልጅ መሆን ግድ ነው፡፡ ልጅነት ከያዛቸው ሥልጣናት አንዱ ምስጢርን ማወቅ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ልጆች ስንሆን በእርግጥም የአባትን የልብ ምክርና አሳብ የማወቅ መብት አለን፡፡ ክርስቶስ አንድ ስንኳ ያየው የለም የተባለለትን እግዚአብሔር እንደተረከልን የተነገረን “በእቅፉ ያለ” ተብሎ ነው፡፡ ይህም ልጅነትን ያሳያል፡፡ የልጅ ስፍራው የአባት እቅፍ ነው፡፡ አገልጋይ የአባትን እቅፍ የተለማመደ ሰውንም ሁሉ ወደዚያ ለማድረስ የበረታ ናፍቅት ሊኖረው ይገባል፡፡

         ተወዳጆች ሆይ እግዚአብሔርን የምናገለግለው በልጅነት ነው፡፡ እርሱን የሚያገለግሉ የሚሰጡትም ከራሱ ከእግዚአብሔር ነው፡፡ በዮሐ. 1፥18 መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው (የሚያውቀው) አንድ ስንኳ የለም፡፡ በእቅፉ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው ተብሎ እንደተፃፈ እግዚአብሔርን ያለ ልጅነት መተረክ፣ መግለጥና አሳቡ ይህ ነው ብሎ መናገር አይቻልም፡፡ አገልግሎት የማይታየውን የእግዚአብሔር መልክ መግለጥ ነው፡፡ እርሱን በልጅነት መንፈስ ተረድቶ እንደ ክርስቶስ መተረክ . . . ይህንን ደግሞ ለማድረግ፡-
1.     አድራሻችንን እቅፉ ውስጥ ማድረግ፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር የዘላለም ሕብረት ማድረግ፣ በእርሱ መገኘት፣ የእርሱን መሻት ከቅዱስ መንፈሱ መገንዘብና እርሱ እንደ ሆነው መግለጥ፡፡

2.    ልጅነትን ማወጅ፡፡ ልጅ በአባቱ ስም የሚጠራው ቤት ውስጥ ብቻ አይደለም፡፡ አደባባይም ላይ መጠሪያው ያው አባቱ ነው፡፡ የውስጥና የውጭ መስመር እንጂ አባት የለም፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድ ያለን ትልቁ ስፍራ ልጅነት ነው፡፡ እንደ ልጅ መናገርና እንደ ልጅ የመኖርን መብት ልንጠቀምበት ይገባል፡፡
3.    የምንተርከው ነገር በልኩ የምናሳየው ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ትረካዎችን ሰምታችሁ ከሆነ እያንዳንዷ እንቅስቃሴና ተግባር ሳትታለፍ ለሰዎች ትደመጣለች፡፡ እግዚአብሔርን የመተረክ ሂደት ይህ ያንሳል ብለን የምንጨምርበት፣ ያ በዝቷል ብለን ደግሞ የምንቀንስበት ምንም ነገር የለም፡፡ እርሱ እንደ ሆነው እንዲሁ እኛም እንገልጠዋለን፡፡ ይህም እኔ እኔ ነኝ ያለውን እግዚአብሔር አንተ ግን አንተ ነህ ማለት ነው፡፡ ጸጋ ይብዛላችሁ!        
          
ማጠናከሪያ ጥቅሶች፡-
ኢሳ. 40፥9-11
ማቴ. 12፥35-42
ሮሜ. 1፥6
ዮሐ. 1፥18
ኤር. 23፥22


No comments:

Post a Comment