Friday, December 23, 2011

ከዚህም ጹም


ከቁጣና ከጥላቻ ጹም ለባልንጀሮችህ የበዛ ፍቅርን ስጥ፡፡
ከመለያየት ጹም ቢቻልህስ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑር፡፡
በሌሎች ላይ ከመፍረድ ጹም ማንንም ሰው ከመዳኘትህ በፊት እግዚአብሔር ጥፋቶቻችንን እንዴት እንደሚመለከት አስተውል፡፡  
ለራስ ከሚሰጥ አነስተኛ ግምት፣ ከጨለምተኝነትና አሉታዊ ከሆነ አስተሳሰብ ጹም ስለ ሕይወት በሚኖርህ አመለካከት ሁሉ ሚዛናዊ ሁን፡፡  
ተስፋ ከመቁረጥ ጹም ይህ የቁም ሞት ነውና በምታደርገው ነገር ሁሉ ተስፋ ይኑርህ፡፡
ከማጉረምረም ከፍርሃትና ከጭንቀት ጹም ጌታ ለሙሉ ሕይወታችን ያስባልና እምነትህን በእርሱ ላይ ጣል፡፡
ከስንፍና ጹም በሚያስፈልግህ ሁሉ በጸሎትና በምልጃ የእግዚአብሔርን እርዳታ ጠይቅ፡፡
ሕይወትን ካከበዱብህ ችግሮች፣ ወድቆም ከመቅረት ጹም የደስታዎችህን ጊዜያት ሁሉ ልትደሰትባቸዉ ጣር፡፡
ከምሬት ጹም የደስታዎችህን ጊዜያት ሁሉ ልትደሰትባቸው ጣር፡፡
አብዝቶ ለራስ ከመጨነቅ ጹም ራስህን ምን ጊዜም በጌታ እግር ሥር አድርግ፡፡
ከማንኛውም ዓይነት ቅሬታ አልያም ቂም ጹም የበደሉህን ሁሉ ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ይቅር በል፡፡ 
ከአሉባልታና ፌዝ ከተቀላቀለበት ወሬ ጹም እውነተኛ በሆኑና በደስታ ለዛ በተሞሉ ቁም ነገሮች ውስጥ ተሳተፍ፡፡
ከአባካኝነትና ከአጥፊነት ጹም መውጣትና መግባትህ በመጠን ይሁን፡፡ 
ለዓለም አብዝቶ ከመጨነቅ ጹም ተጨማሪ ጊዜ ለአምላክህ ለመስጠት ትጋ፡፡ 
ከክፉ ልማዶችህ ጹም አንተ የተፈጠርከው በእግዚአብሔር አምሳል ነው፡፡
    ልብ በሉ! ዛሬ ምድራችን የምትጨነቀው ከመብል ተከልክለው ነገር ግን ከእነዚህ የክፋት አውራዎች መፆም ባልቻሉ ወገኖች ነው፡፡ ለሚበልጠው ያትጋን!

Thursday, December 22, 2011

ሕይወትን በፍቅር


የፍቅርን ትክክለኛ ትርጉም ተማር፡፡ በሕይወትህ ውስጥም ዋናው ነገር ይህ ይሁን፡፡ እግዚአብሔርን አፍቅር፣ ራስህን ውደድ ሌሎችንም እንዲሁ፡፡ ይህንንም ግልጽ ባልሆነ መንገድ አታድርገው፡፡ ትህትና ይኑርህ፡፡ ከእያንዳንዱ ሕይወት ካለው ነገር የምትማረው የሆነ ነገር አለ፡፡ በሌሎች ሰዎች ደስተኛ ሁን፡፡ የሌሎችንም ሰሜት ተረዳ፡፡
ከሞከርክ ሁሉንም ሰው መውደድ ትችላለህ፡፡ ከምስጋና ጋር ቸር፣ ከትችት ጋር ጥንቁቅ፣ አገልግሎት ለመስጠትም የነቃህ ሁን፡፡ ብዙውን ድርሻ የሚወስደው እኛ ለሌሎች የምናደርገው ነው፡፡ ስለዚህ እንክብካቤህን ለሚሹ ከምትችለው ያነሰ አታድርግ፡፡ እውነተኛ ፍቅር ምድር ላይ ያለውን ሁሉ ቋንቋ ይናገራልና፡፡
ብርሃን ወረቀት ላይ በብርሃን እጅ የተጻፈ የብርሃን ቃል፣ ሥፍራን፣ ርቀትንና ጊዜን የሚደመስስ ኃይል ፍቅር ነው፡፡ ስለዚህ ትመሰገን ዘንድ አመስግን፣ ፍቅርን ትቀበል ዘንድ ፍቅርህን ስጥ፣ መልካም ስም የሚገዛው በፍቅር ነውና!
ፍቅር በሚያስደምምና ባልተለመደ መንገድ ይሠራል፡፡ በሕይወትም ውስጥ ፍቅር ሊለውጠው የማይችለው ምንም ነገር የለም፡፡ በጣም የተለመደውን ቦታ እንኳን ሳይቀር ወደ ተዋበ፣ ወደ አሸበረቀና ግርማን ወደ ተላበሰ መንደር ይቀይረዋል፡፡

ፍቅር፡-
1.     ራስ ወዳድ ብቻ አይደለም፡- ይረዳል፣ ይራራልም፡፡ ሁሉን በስሜት ሳይሆን በልቡ ያያል፡፡
2.    እያንዳንዱ ሰው የሚፈልገው ምላሽ ነው ፡- ከጨቅላው ጀምሮ እስከ ትልቁ፣ እንስሳትን ጨምሮ የሁሉም ሕይወት የሚናገረው ቋንቋ ነው፡፡
3.    የሚገዛ አይደለም፡- የዋጋ ተመን የሌለው ነጻ ነው፡፡ ልክ እንደ ንጹሕ ተአምር የሕይወት ጣፋጭ ምስጢር ነው፡፡ ስለዚህ ፍቅርን እንደ ትልቅ ሀብት ቁጠረው፡፡ በጥልቀትና በፍጹም ልብ ውደድ፡፡ ይህንንም በደስታ አድርገው፡፡ ምናልባት በሂደቱ ውስጥ ትጐዳ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ሕይወትን ሙሉ ለሙሉ ለመኖር ብቸኛው መንገድ ነው፡፡ ምን ጊዜም ቢሆን ታላቅ ፍቅርና ታላቅ ስኬት ትልልቅ ፈተናዎች አሉበት፡፡ ስለዚህ ያለ ማቋረጥ ፍቅርን ለግስ፡፡ ወደ ሌሎች ያፈሰስከው ፍቅር መልሶ ወደ አንተ መፍሰሱ አይቀሬ ነው፡፡ ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበዛ በረከት ስለሆነ በዚህ ውስጥ በመኖር ልዩ ደስታን ማግኘት እንችላለን፡፡
የማያስተውል ዓይን ብቻ በሰው ውስጥ የሉትን መልካምነቶች ማየት አይችልም እንጂ ፍቅር እውር አይደለም፡፡ እውነተኛ ፍቅርና ርኅራኄ ሁልጊዜም ደስታዎቹን ያጠራል፡፡ በትክክል ለማየት ይረዳል፣ ይፈውሳል፡፡ ክፉ ስሜት እንዲደበዝዝ፣ መልካሙ መንፈስ ደግሞ እንዲነቃ ያስችላል፡፡ በሰው ውስጥ ያለውን መጥፎውን ሳይሆን መልካሙን ነገር ያፋጥናል፡፡ ከብርሃን ይልቅ የሚያድስ፣ ከአበቦች ይልቅ መዓዛ ያለው፣ ከብዙ ዜማዎችም ይልቅ ጥዑም ነው፡፡
አስታውስ! ሕይወት የምትለካው ሌሎችን ሰዎች በመሰጥንባቸው ጊዜያቶች ሳይሆን እኛ በሕይወት በተመሰጥንባቸው ቅጽበቶች ነው፡፡ ሰው ሃይማኖቱን ሲወድ በሃይማኖቱ ሥር ያሉትን ያፈቅራል፡፡ ሰው እግዚአብሔርን ሲያፈቅር ግን የሰውን ዘር ሁሉ ይወዳል ፍቅር ኃይለኛ ልብን የማስታገስ፣ እንደ ድንጋይ የሆነውን ነገር የማለስለስ፣ ቋጠሮንም የመፍታት ለዛ አለው፡፡

የወዳጅ ሰንሰለት (ካለፈው የቀጠለ)


     ማስተዋል የጎደለው ሰው ተናግሮት የነበረው ላይ ሲያተኩር፤ አስተዋይ ሰው ግን በሚናገረ ነገር ላይ ያነጣጥራል፡፡ ሰፊ አስተሳሰብ ያለው ሰው ደግሞ ይቅርታው ላይ ያተኩራል፡፡ መሠረታዊውን ሕግ አስታውስ የወዳጅነት ስሜት ከአንተ ወደ ሌሎች እስካልሄደ ድረስ ወደ አንተ ሊመጣ አይችልም፡፡ በአንተ በኩል ያለን ስህተት ለማስተካከል አሳዛኙን ሁኔታ የፈጠሩትን ምክንያቶች መርምር፡፡ ይህም መንገድ ወደፊት ሊከሰቱ የሚችሉ ተመሳሳይ ግጭቶችን ለመቀነስ ይረዳሃል፡፡ ቢያንስ በቀን አንድ ጊዜ ልብና አእምሮህን ከፍርሃት፣ ከጥላቻ፣ ከጸጸት፣ ከቅሬታና ከጥፋተኝነት ስሜቶች ነፃ አድርገው፡፡ አሉታዊ አመለካከቶች እንደገና እየተነሡ እንዳይረብሹህ ጤናማና አዎንታዊ በሆኑ አስተሳሰቦች ሕይወትህን ሙላ፡፡
 ይቅር ባይነት፡-

ወዳጅነትን የሚያጸና ነው፡፡
ብዙ ጊዜም የክብር ዕዳ ነው፡፡
መቼም ቢሆን ግን የደካማነት ምልክት አይደለም፡፡
የጥላቻ ማርከሻ ነው፡፡
ከክብር በስተቀር ሌላ ምንም አያስከፍልም፡፡
ምን ጊዜም ከሚጎዳው ይልቅ የሚያተርፈው ይበልጣል፡፡
በእያንዳንዱ ቤትና ሕይወት ሊኖር የሚገባው ቀዳሚ ተግባር ነው፡፡

ሁሉንም ነገር መልካምነትን በተላበሰ መንፈስ በጨዋ ለዛ አድርገው፡፡ ምንም እንኳን መብቶችህን ብትገድባቸውም ይቅርታ ማድረግ የምንለው ግን በመልካምነት ሰዎችን ለመንከባከብ ፈቃደኛ መሆንንም ጭምር ነው፡፡
ሰዎችን ይቅር ስንል ሥራቸውን እያበረታታን አልያም የሠሩትን ነገር ሁሉ ትክክል ነው እያልን አይደለም፡፡ ነገር ግን ለአብሮነታችን ዋጋ፣  ለይቅርታ ተቀባዩ እድል፤  ለራሳችንም ፍፁም ደስታን እየሰጠን ነው፡፡ ስለዚህ በሕይወት ውስጥ ካለው ተጽእኖ የተነሣ ይቅር ባይነት የበለጠ ቅድሚያ የሚሰጠው ነገር ነው፡፡ አንተም አሁኑኑ ይቅር በልና አሁኑኑ ውጤቱን ከሥራው ታያለህ! ነገ የእኛ አይደለም፡፡ ትላንትም እንዲሁ፡፡ የዛሬ በረከቶች ወይም ስጦታዎች ብቻ በቁጥጥራችን ሥር ናቸው፡፡ የአሁኗን ቅጽበት በሚገባ መኖር ሕይወትን አጣጥሞ የመኖር ምሥጢር ነው፡፡ ትላንት የዛሬ ትውስታ ሲሆን  ነገ ደግሞ የዛሬ ሕልም ነው፡፡ ዛሬን በይቅርታ ኑር፡፡ አስቸጋሪው ነገር ይቅር ለማለት ምክንያት እያለን ይቅር ማለቱ ሳይሆን ያለምንም ምክንያት ይቅርታ ማድረጉ ላይ ነው፡፡ የይቅርባይነት ትልቁ ዋጋ ያለውም እዚህ ላይ ነው፡፡ 
ሌሎች ሲያወግዙ ይቅር ማለት
በሚነፍጉበት ጊዜ መስጠት
በሚያማርሩበት ጊዜ መደሰት
ሲያልሙ መሥራት
ሲያቆሙ መጽናት
በተጠራጠሩበት ጊዜ ማመን
ሲነቅፉ ማመስገን
በሚያፈርሱበት ጊዜ ማነጽ
ሲያመነቱ ኃላፊነትን መውሰድ
በሚፈልጉበት ጊዜ ማገልገል፡፡ 
በእርግጥ ይከብዳል ግን ደግሞ ዋጋው እጅግ የበዛ ነው፡፡ የባልንጀራችንን ጥቃቅን ስህተት ይቅር ማለት ካልቻልን እንዴት በጓደኛችን ታላላቅ የሆኑ መልካም ነገሮች መደሰት እንችላለን።

Wednesday, December 21, 2011

ዝም ስል


በገናውን ብደረድር ጸናጽሉን  ብጸነጽል
ከበሮ ብመታ እንቢልታ ብነፋ
ክራርና ዋሽንት የአታሞ ቅኝት
በመዝሙር ብርቱ ቃል ብዘል እንደንቦሳ
አይገልጠውም ውስጤን ሳስብ ውለታህን  
እጄን ከልቤ ጋር
በእልልታ ሕብር በጭብጨባ ዜማ ለአንተ ከማሰማ
እንደ  ሃና ቅድስት እንደ ሰራፕታዋ የጸሎት መበለት
እንደ ዕንባቆም ነቢይ በዝምታ መኃልይ
ሳስበው እረካለሁ ዝም ስል ጌታዬ በሥራህ አርፋለሁ፡፡ 
        (አቤኔዘር)

Saturday, December 17, 2011

የወዳጅ ሰንሰለት


እጅግ የሚያስፈልገን ነገር መረጃ ቢሆን ኖሮ እግዚአብሔር የግንኙነት ባለሙያ በላከልን ነበር፡፡
እጅግ የሚያስፈልገን ነገር ሙያዊ ሥልጣኔ ቢሆን ኖሮ እግዚአብሔር ሳይንቲስት በላከልን ነበር፡፡
እጅግ የሚያስፈልገን ነገር ፌሽታ ቢሆን ኖሮ እግዚአብሔር አዝናኝ በላከልን ነበር፡፡
እጅግ የሚያስፈልገን ነገር ገንዘብ ቢሆን ኖሮ እግዚአብሔር የምጣኔ ሀብት ሊቅ በላከልን ነበር፡፡
ነገር ግን እጅግ የሚያስፈልገን ነገር ይቅርታ ነበር ጌታ እግዚአብሔር አዳኙን ላከልን፡፡ አሜን!
ሰፊ በሆነው የሰው ልጆች ግንኙነት ውስጥ የቆሰለው ቁስሉ የሚሽርበት ያደፈው የሚነጻበት፣ የወደቀው የሚነሳበት፣ የተሰበረው የሚጠገንበት ቀዳሚ ተግባር ይቅርታ ነው፡፡ ስለ ይቅርታ ጥርት ያለ አስተሳሰብ ሊኖረን ይገባል፡፡ በእርግጥም ከስሜት ነፃ መሆን የማይቻል ቢሆንም እንኳን ይቅርታ ምርጫ መሆኑን ግን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ ምንም እንኳን አሁንም ጉዳቱ በውስጥህ ቢሆንም ይቅር ልትል ግን ትችላለህ፡፡
ይቅር ለማለት ለመደሰትና የመጀመሪያውን ደረጃ ለመሄድ አንተ የመጀመሪያው ሁን፡፡ በሰብአዊ ወንድምህ ወይም እህትህ ፊት ደስታ ሲፈካ ታያለህ፡፡ በዚህም የሕይወት አስዋቢ፤  የደስታ ምንጭ፤ ተአምር አድራጊ መሆን ይቻላል፡፡ ሁል ጊዜም ሰዎች ወደ እኛ እንዲመጡ ሳንጠብቅ ቀዳሚ መሆናችን የደስታ እጅግ ማራኪ ገጽታ ውስጥ እንድንቆይ ያደርገናል፡፡
ባልንጀሮቻችንን መውደድ ከቻልን በዚያኑ ልክ ደግሞ የወቀሳ መዓት ልናወርድባቸው፤ ተስፋን በእነርሱ ላይ የቆረጠ ፊት ልናሳያቸው አይቻለንም፡፡ ሁሉም ሰው ያው ሰው ነውና፡፡ ብዙ ጊዜ ራሳቸውን ፍፁም አድርገው የሚመለከቱ ሰዎች አይወደዱም፡፡ ራስን ማጽደቅ በእርግጥም አያስኬድም፡፡ ስህተት እንዳለብን ማመን አለመቻል ደግሞ በራሱ ስህተት ነው፡፡ ለጥፋቱ ይቅርታ ለማድረግ ፍላጎት አለማሳየት  ደግሞ ትልቅ ስህተት ነው፡፡
ሰዎችን ለመዳኘት የሚፈጥኑ ሰዎች የአእምሯቸውን ሚዛን ያወሳስቡታል፡፡ በሌላው ሰው ላይ በደንብ አድርገው ለመፍረድ ጥሩ ምክንያት ይኖራቸው ይሆናል፡፡ ነገር ግን እንዲህ በማድረጋቸው ራሳቸውን ለጥላቻ መንፈስ ክፍት ያደርጋሉ፡፡ ይቅር መባባልና መወዳጀት በእርጋታና በትጋት ከተደረጉ የሰውን ልጅ ልቡና የሚጠርቡና የሚቀርፁ የፍቅር መዳፎች ናቸው፡፡ ምንም እንኳን ጥረትን ቢጠይቅም ይቅር ማለት እንዳለብን ልንወስን ግን ይገባል፡፡ ስለዚህ የቱንም ያህል ከባድ ቢሆንም  እንኳን አድረገው፡፡ በዚያም ጊዜ የተሰማህ ቅሬታ ጥሎህ ሲሄድ ይታወቅሃል በምትኩም የነፍስህን አደባባይ ሰላም ሲከባት ይሰማሃል፡፡
ይቅር ባይነት ስሜትህን ሳይሆን ውሳኔህን ይጠይቃል፡፡ የፈቃደኝነትም ተግባር ነው፡፡ ስለዚህ ምክንያት አትጠብቅ፡፡ አንዴ ይቅር ለማለት ከቆረጥክ እንዲህ ቢሆን ኖሮእና ነገር ግንየሚሉትን ቃላት አታንሣቸው፡፡ ስለ ተቃረነህ ሰውም ስትናገር ትህትናን በተላበሰ መንገድ ይሁን፡፡ ነገር ግን ሁሉን ለመልካም አድርገው!      “አውቄ በድፍረት፤ ያለ ዕውቀት ስቼ በስህተት የበደልኳችሁ ከልቤ ይቅርታ”
(ይቀጥላል)