Tuesday, July 31, 2012

የቃየን መንገድ (ካለፈው የቀጠለ)



1. ቤተ ፍቅር በየጊዜው የምታነሷቸው ርእሶች ጠንካራነትና አመራማሪነት በእጅጉ ይማርከኛል፡፡ በተለይ ከመጽሐፍ ቅዱስ ለመወያያነት የምታቀርቡት ትምህርት ከአሁን በፊት ከነበረኝ እይታና የመረዳት መንገድ በተሻለና በላቀ መንገድ እንዳስተውል ረድቶኛል፡፡ እግዚአብሔር በጥበብና በማስተዋል ጸጋውን ያብዛላችሁ፡፡ እኔ በፊት ስረዳው የቃየልን መንገድ ወንድምን ከመግደል አንፃር ብቻ ነበር፡፡ ለካስ ትውልድንም በመንፈሳዊው መንገድ ከመግደል አንፃር ይታይ ኖሮአል? ደጋግሜ ሳነበው የቃየል መንገድ የራሱ የቃየል ብቻ ችግር ሆኖ አልቀረም፡፡ በሺህ የሚቆጠሩ ዘመናትንም ተሻግሮ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ዘልቆአል፡፡ ችግሩ ከአምልኮ ጋር የተያያዘ መሆኑ ደግሞ ጉዳዩን ይበልጥ ያንረዋል፡፡
        በመጀመሪያ ቃየልና አቤል መካከል ልዩነት የፈጠረው መሥዋዕቱ እንደሆነ አስተውያለው፡፡ በቀጥታ ትዝ ያለኝ ደም ሳይፈስ ስርየት የለም የሚለው ብቸኛ መፍትሔ ነው፡፡ የቃየል መሥዋዕት ግን ደም አልባ በመሆኑ ሥርየት ሊያመጣ አልቻለም፡፡ አቤል እንደዚህ ያለውን መሰረታዊ ትምህርት ከቤተሰቦቹ የተማረ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም አዳምና ሔዋን ከበደሉ በኋላ በእግዚአብሔር ፊት መቆም ስላልቻሉ ቅጠል ሰፉ ይህም የሰው ምስኪን መፍትሔ ከመሆን ባለፈ ያሰቡትን ውጤት ሊያመጣ አልቻለም፡፡ ስለዚህ ያዘነላቸው እግዚአብሔር ቁርበት ሰፍቶ አለበሳቸው፡፡ ቁርበት የእንስሳ ቆዳ እንደመሆኑ በቀጥታ አንድ መሥዋዕት እንደተሰዋ እንድናስብ ይጋብዘናል፡፡ እንግዲህ ቀዳማዊ ቤተሰቦቻችን ከእግዚአብሔር ይህንን ትምህርት ተምረዋል ማለት ነው፡፡
         እኔ እንደተረዳሁት የአቤልን መሥዋዕት አቀራረብ ስመለከተው ከመስማት በሆነ እውቀት የተከናወነ እንጂ በዘፈቀደ የተሠራ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም አቤል መሥዋዕት ያቀረበው ከበጉ በኩራት፣ ከበኩራቱ ስቡን ነው፡፡ ይኼ ደግሞ መንፈሳዊ ትምህርትን መሰረት ባደረገ መንገድ የተፈፀመ እንደሆነ ያስረዳናል፡፡ በተጨማሪም አቤል እንደ እግዚአብሔር ልብ በሆነ መንገድ ለእግዚአብሔር መሥዋዕትን ሲያቀርብ ቃየል ግን እንደ ልቡ በሆነ መንገድ በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት ለማግኘት እንደሞከረ እናያለን፡፡
        ከሁሉም በላይ የተገረምኩት ደግሞ በቃየል ውስጥ እምነት አለመኖሩ በአቤል ውስጥ ደግሞ እምነት የመገኘቱ ነገር ነው፡፡ ዳሩ ግን ሁለቱም መሥዋዕት አቅርበዋል፡፡ አንድ ሰው ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ማቅረቡ ብቻ እምነት አለው ለመባል ብቸኛ ማረጋገጫ ሊሆን አይችልም፡፡ መንፈስ ቅዱስ ግን የሰውን ልብና ኩላሊት ይመረምር ዘንድ አዋቂ ነው፡፡ አቤል ከቃየል ይልቅ የሚበልጥን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር በእምነት አቀረበ (ዕብ. 11÷4) የሚለውን ምስክርነት ስናነብ መበላለጡን ያመጣው መሥዋዕቱ እንደሆነ ደግሞም በእምነት አቀረበ የሚለው ገለፃ ቃየል እምነት እንዳልነበረው ያረጋግጥልናል፡፡
        መሥዋዕትን ስናስብ ትልቁ አገልግሎቱ ምትክነት ነው፡፡ ማለትም ኃጢአተኛው በእርሱና በኃጢአት ደመወዙ ሞት መካከል ሌላ በመሞት ቤዛ የሚሆነው ማቆም አለበት፡፡ በእኛና በእግዚአብሔር መካከል ኃጢአታችን ስለለየች የጠብ ግድግዳ ቆሞ ነበር፡፡ እግዚአብሔር አብ ይህንን የጠብ ግድግዳ ለማፍረስ ደግሞ ማስተሰርያ ማቆም ነበረበት፡፡ ስለዚህም ልጁን ማስተሰሪያ አድርጎ አቆመው (ሮሜ. 3÷25)፡፡
        ሌላው ሳነብ የተረዳሁት አቤል በስጦታውና በስጦታው ላይ በነበረው ሙሉ እምነት በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነትን ሲያገኝ ቃየል ደግሞ በኃጢአቱ ምክንያት ተቀባይነትን አጣ፡፡ ቃየል በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት ያገኝ ዘንድ የተጠቀመበት መንገድ ዛሬም ድረስ ወዮታ አለበት፡፡
       በመጨረሻ ያስተዋልኩት ከመሠዊያው በኋላ በሁለቱ ሕይወት ውስጥ የታየውን ግልጽ ልዩነት ነው፡፡ መሥዋዕት ይዘው እግዚአብሔር ፊት ከመቅረባቸው አስቀድሞ ስለ ሁለቱ ጠባይና የአኗኗር ሁኔታ የተገለፀ ነገር የለም፡፡ ከመሠዊያው በኋላ ግን የሁለቱም መከር አስቀድሞ እንደዘሩት አይነት ሆነ፡፡ በእርግጥ ሁለቱን የሚያመሳስላቸው ባሕርይ አለ፡፡ ይኸውም ከዔደን ገነት ውጪ መወለዳቸው ደግሞም ከመጀመሪያው አዳም በልደት የኃጢአቱ ተካፋይ መሆናቸው ሁለቱንም በእኩል በደለኛ ማንነት ያስይዛቸዋል፡፡ በዚህ መንገድ ከሄድን ሁለቱንም በእግዚአብሔር ፊት የሚያበላልጣቸው ነገር አይኖርም፡፡ ዳሩ ግን መሥዋዕታቸው በወንድማማቾቹ ሕይወት ላይ ይህ ነው የማይባል ልዩነት ፈጥሮአል፡፡ እኔ በፊት ያለ ማስተዋል መጽሐፍ ቅዱስን አነብ በነበረበት ጊዜ በአቤል ውስጥ ጽድቅ ያለ ይመስለኝ ነበር፡፡ ነገር ግን አሁን ኃጢአተኛው አቤል ቅንና ፃድቅ በሆነው እግዚአብሔር ፊት ሞገስን ያስገኘለት ይዞ የቀረበው መሥዋዕት ነው፡፡
      ከመሠዋት በኋላ አቤል ለስደት ቃየል ለማሳደድ፤ አቤል ለሞት ቃየል ደግሞ ለነፍሰ ገዳይነት በቁ፡፡ ቃየል በራሱ ተቀባይነት አለማግኘት ሳይሆን በወንድሙ ሞገስ ማግኘት ቀና፡፡ ቃየል ፊቱ ጠቁሮ ሳለ እግዚአብሔር መልካም ብታደርግ ፊትህ የሚበራ አይደለምን? (ዘፍ. 4÷6) ባለው ጊዜ ዳግመኛ ከስህተቱ የመመለስና የመታረም እድል አግኝቶ ነበር፡፡ ግን በመንገዱ እንደጸና ዘለቀ፡፡ ለክፋትም ትልቅ ምሳሌ ለመሆን አገለገለ፡፡ መጨረሻውም ዓለምን ያስጌጠና ለሥጋው ብቻ በትጋት የኖረ ምስኪን ተቅበዝባዥ ሆኖ አለፈ፡፡ ከመሥዋዕቱ ጋር መታየት ምን ያህል ዋጋ አስከፋይ እንደሆነ የአቤል ኑሮ ያስረዳል፡፡ እኔ በትንሿ አእምሮዬ ይህንን ታክል ታይቶኛል፡፡ እናንተም በሰፋና በተረጋጋ አእምሮ ሆናችሁ ብትመረምሩት  ለእምነት ሰው የሚረባ ትምህርት እንዳለው አስባለሁ፡፡ ይህንን አሳቤን ለንባብ በማቅረብ ለሌሎችም እንደምታካፍሉልኝ በመማፀን ጨረስኩ፡፡
                                                            ዮርዳኖስ ወ/ትንሣኤ

2. በቤተ ክርስቲያን ብዙ ጊዜ ሲሰበክና ትምህርት ሲሰጥበት አስታውሳለሁ፡፡ ነገር ግን የአቤልና የቃየል ጉዳይ ይሁዳ መልእክት ድረስ እንደደረሰ ግን ሳውቅ የመጀመሪያዬ ነው፡፡ ታሪኩን እንድናይ ፍንጭ የሰጣችሁበት መንገድም በጣም ደስ ይላል፡፡ ብዙ ሰው ለመልኩ፣ ለቁመናው፣ ለኑሮው ልዩነት ደፋ ቀና ይላል፡፡ ነገር ግን ዘላለማዊ ልዩነት ስለሚፈጥረው መሥዋዕት ግድ የለውም፡፡ የወንድማማቾቹን ታሪክ ሳነበው የቃየል ትምክህት ያስገርመኛል፡፡ እንደውም እግዚአብሔርን እንደ እግዚአብሔርነቱ የተረዳው አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር ማንና ምን እንደሆነ የተረዳ ሰው “የወንድሜ ጠባቂው ነኝን?” የሚል ስንፍና ሁሉን ለሚችል አምላክ አይመልስም፡፡
         እንደ እኔ አስተያየት ታሪኩን ወቅታዊ ከሆነው ታሪካችን ጋር አገናዝበን ማየቱ ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡ የይሁዳ መልእክት ለክርስቲያኖች እንደ መፃፉ ወዮላቸው የሚለው የፍርድ ቃል በመካከላችን እንደሆነ መረዳት ይገባል፡፡ እኛ የቆምነው በየትኛው መንገድ ነው፡፡ ቃየል ወንድሙን ሲገድል መሥዋዕቱንም እየተቃወመ ነው፡፡ በዚህ ታሪክ ውስጥ ግን አንድ ነገር ተረዳሁ አምልኮ በእግዚአብሔር ፊት ምን ያህል ከባድ ትርጉምና ከፍታ እንዳለው፡፡ እርሱ ባለቤቱ እንዲህ ካለው መንገድ ይጠብቀን፡፡
                                                                ገ/ኢየሱስ ኃይሌ

3. ቤተ ፍቅር በርቱ ጌታ ኃይሉን ይስጣችሁ፡፡ እኔ በስደት አገር የምኖር ክርስቲያን ነኝ፡፡ ጽሑፎቻችሁን በመከታተልም ብዙ አሳልፌአለሁ፡፡ ነገር ግን የምታነሷቸው አሳቦች ትንሽ ጠጠር ይላሉ፡፡ ስለዚህ በተቻለ መጠን ቀለል ማድረግ ብትችሉ፤ በተለይ እንደ እኔ ላሉ በቂ አማራጭ ማብራሪያና ተጠያቂ ሰው ለማያገኙ ወገኖች እጅግ ጥሩ ይመስለኛል፡፡ ምድራችን በቃየል መንገድ ተጨናንቃለች፡፡ የመንገዱም ፍሬ በግልጥ እየታየና ከእለት ወደ እለት ተባባሪዎችን እያከማቸ ነው፡፡ ብልህ ሰው ግን ወድቆ ሳይሆን ቆሞ ይማራል፡፡ወገኖቼ አምልጡ!
                                                                  ሶስና ተወልደ
       

Tuesday, July 24, 2012

የቃየል መንገድ


                 
       ከውድቀት በኋላ የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ጋር ያለው ግንኙነት በመሥዋዕት ላይ የተመሰረተ እንደሆነ በቅዱሳት መጽሐፍት ውስጥ እናስተውላለን፡፡ ሰው በእግዚበብሔር መልክነት እንደምሳሌው የኖረባቸው ጊዜያት እጅግ የተወደዱና የመለኮትን አሳብ መታዘዝ የታየባቸው ቢሆኑም ሰው እንዲህ ያለውን ቅዱስ ሕብረት ጠብቆ የዘለቀው ለአጭር ጊዜ ነው፡፡
       እግዚአብሔር ለሰው የሚያስፈልገውን ሁሉ አስቀድሞ በመፍጠር ሰውን በተጠናቀቀና በተዋበ ዓለም በማስቀመጥ ምን ያህል አሳቢና አፍቃሪ መሆኑን አሳይቶናል፡፡ ዳሩ ግን ሰው ከነበጀቱ እንደ ዔደን ገነት ባለው ያማረ ስፍራ መቀመጡ ደግሞም ሊጠቀም የሚችልበት ብዙ አማራጭ መሐል መመላለሱ ፈጣሪውን ላለመበደል አቅም አልሆነውም፡፡ ስለዚህ ባለመታዘዝ ጠንቅ ኃጢአት በአንድ ሰው አዳም ምክንያት ወደ ዓለም ገባ፡፡ ከዚህ የተነሣ ሰው እግዚአብሔር ፊት የሚቆምበት መንፈሳዊ ድፍረትና ተቀባይነት አጣ፡፡
       አዳም ከበደለ በኋላ በመልኩ እንደ ምሳሌው ልጅ በመውለዱ ኃጢአተኝነት ለሰው ሁሉ ደረሰ (ዘፍ. 5÷1)፡፡ ይህ ክፍል እኔ ባልበደልኩትና በስፋራው ላይ ተገኝቼ ባልበላሁት ከአዳም ኃጢአት ጋር ስለ ምን እደመራለሁ? ለሚለው የአንዳንድ ሰዎች ሙግት ከበቂ በላይ ምላሽ የሚሆን ይመስለኛል፡፡ እግዚአብሔር አዳምን በመልኩ (ጽድቅ፣ ቅድስናና እውቀት) እንደ ምሳሌው (ምድርን መግዛት) እንደፈጠረው ከተረዳን (ዘፍ. 1÷26) ከውድቀት በኋላ ኃጢአተኛው አዳም በመልኩ (ኃጢአተኝነት) እንደ ምሳሌው (ፍርሃት) ልጅ በመውለዱ ኃጢአት በዘር የሚደርስ (orginal sin) ሆኖአል፡፡ 
        አቤልና ቃየልን የምናገኛቸው በዘፍጥረት ምዕራፍ አራት ላይ ሲሆን ርእሳችን የሚገኘው ደግሞ በይሁዳ መልእክት ውስጥ ነው፡፡ በዘፍጥረት መጽሐፍና በይሁዳ መልእክት መካከል የብዙ ዘመናት ልዩነት አለ፡፡ ዳሩ ግን በሁለቱም ዘመናት ውስጥ አንድ መንገድ እንመለከታለን፡፡ ይህም የቃየል መንገድ ነው (ይሁዳ 11)፡፡ የቃየል መንገድ በአዲስ ኪዳኗ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በስህተት አስተማሪዎች ምክንያት ጠላት በስንዴው መካከል ከዘራቸው እንክርዳድ ትምህርቶች አንዱ ነው፡፡ እንደነዚህ ላሉቱ እግዚአብሔር ያለውን መልእክት ሐዋርያው ሲናገር “ወዮላቸው” በማለት ነው፡፡ ይህም የመንገዱን አስከፊነት እንዲሁም የቅጣቱን ክብደት የምንረዳበት እጅግ ግልጥ የሆነ ማሳያ ነው፡፡
        የያዕቆብ ወንድም የይሁዳ መልእክት አንድ ምእራፍ ያለው ቢሆንም በውስጡ የያዘው ትምህርት ግን በጣም ሰፊ ነው፡፡ ሾልከው ስለ ገቡ የስህተት ትምህርቶች፣ የአምላካችንን ጸጋ በሴሰኝነት ስለሚለውጡ ሴሰኛች፣ ንጉሣችንንና ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ስለሚክዱ ዓመፀኛች፣ ሥጋቸውን ስለሚያረክሱ ግድየለሾች፣ ጌትነትን ስለሚጥሉ ትዕቢተኞች፣ ሥልጣን ያላቸውን ስለሚሳደቡ ሰነፎች እንዲሁም ውኃ ስለሌለባቸው ደመናዎች (የስህተት አስተማሪዎች) በመልእክቱ ውስጥ ከተጠቀሱት አሳቦች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ መልእክቱን በማስተዋል ሆነን በመንፈስ ቅዱስ አጋዥነት ብናጠናው ልባችንን  የሚሞላና ለነፍሳችን የሚረባ ብዙ ትምህርት እንዳለው አምናለሁ፡፡
        “ከብዙ ቀን በኋላም ቃየል ከምድር ፍሬ ለእግዚአብሔር መሥዋዕትን አቀረበ፡፡ አቤልም ደግሞ ከበጎቹ በኩራትና ከስቡ አቀረበ፡፡ እግዚአብሔርም ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ ወደ ቃየልና ወደ መሥዋዕቱ ግን አልተመለከተም (ዘፍ. 4÷4)” የመጀመሪያዎቹ ቤተሰቦቻችን የመጀመሪያ ልጆች ታሪክ ነው፡፡ ዛሬ የምናያቸው ብዙ ብልሽቶች ጽንሰትና ውልደት የሚጀምረው ከላይ ባለበብነው ክፍል ላይ ነው፡፡ በእድሜያችን የምንሠራው በጎም ሆነ ክፉ ተግባር በወደፊቱ ትውልድ ላይ የሚኖረው መልካምም ሆነ መጥፎ ተጽእኖ ግልጽና ብዙ ነው፡፡
        ወንድማማቾቹ በመሠዊያው ፊት መሥዋዕታቸውን ይዘው ሲቀርቡ እነርሱ ብቻ አይደሉም የተለያዩት ከእነርሱ በኋላ የተነሣውም ትውልድ መሠዊያው ፊት ሲደርስ እየተለያየ ነው የኖረው፡፡ ስለመለያየት ስናወራ እነሆ የዓለምን ሁሉ ኃጢአት የሚያስተሰርይ የእግዚአብሔር በግ ቀራንዮ መስቀል ላይ በተሰቀለ ጊዜ በቀኝና በግራ የተሰቀሉትን ሁለት ወንበዴዎች እናስታውሳቸዋለን፡፡ በመስረቅ ብቻ ሳይሆን በመግደልም ሕብረት አድርገው የኖሩ፤ ፍቅራቸው በክፉ ባልንጀርነት ላይ የተመሰረተ ዓመፀኞች ነበሩ፡፡ ዳሩ ግን ራሱን የዘላለም መሥዋዕት አድርጎ ባቀረበው፣ ስለ ሁሉ በሞተው በአንዱ በክርስቶስ ደግሞም ለዘላለም ሞታችን ማርከሻ የዘላለም ሕይወት በሆነው ጌታ መስማማት አልቻሉም፡፡ አንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ያለውን ጠንካራ እምነት ሲመሰክር ሌላው ደግሞ እኔነቱንና ትምክህቱን አሳየ፡፡ ይህም ለሁለቱ ባልንጀሮች የአንድና የሁለት ቀን ሳይሆን የዘላለም ልዩነት ሆነ፡፡
      ከላይ ባነሣነው ርእስ ዙሪያ ማለትም ስለ ቃየልና አቤል አብዛኞቻችን ደጋግመን ስለሰማነው በቂ እይታ እንዳለን የምናስብ እንደመሆኑ አንባቢዎች ይህ ታሪክ በይሁዳ መልእክት ላይ ከተጠቀሰበት ምክንያት አንፃር ያላችሁን አስተያየት ብትሰጡበት የተሻለ በመሆኑ በትህትና እንጋብዛለን፡፡
                                                
                                                        - ይቀጥላል -
        

Friday, July 20, 2012

የአዳኝ ባልንጀራ



(ውዴ ይህ ነው÷ ባልንጀራዬም ይህ ነው)
መኃ. 5÷16
         አንድ ሕግ አዋቂ ወደ ኢየሱስ መጥቶ መምህር ሆይ የዘላለምን ሕይወት እንድወርስ ምን ላድርግ? አለው፡፡ (ሉቃ. 10÷25) ጌታም ሕግ አዋቂው በሕይወት ይኖር ዘንድ የሚችልበትን ትምህርትና ሊተገብረው የሚገባውን ነገረው፡፡ ዳሩ ግን ሕግ አዋቂው የመጣበት አላማ ጌታን መፈተን እንጂ የሚረባውን አስተውሎ መመለስ ባለመሆኑ ሌላ ተጨማሪ ጥያቄ ጠየቀው፡፡ ሁሉን በሚችል አምላክ ፊት በፈታኝ ልብ መቆም ምን ያህል አስፈሪ ነው? እርሱ ሁሉን ይመረምራል በማንም ግን አይመረመርም፡፡ እርሱ ሁሉን ይፈትናል በማንም ግን አይፈተንም፡፡
        አንዳንድ ጊዜ የእግዚአብሔር ቃል ለመስማት ስንሰበሰብ እንዲህ ያለውን ልብ ይዘን እንቀርባለን፡፡  ከዚህም የተነሣ ለነፍሳችን ሊቀርላት የሚገባውን ከማር ወለላ ይልቅ ለጉሮሮ ጣፋጭ የሆነው ትምህርት ሬት ሆኖብን፤ ለአገልጋዩም ፈተና ሆነን የምንመለስበት ጊዜ ጥቂት አይደለም፡፡ ከእባብ ልባምነትን እንድንማር የታዘዝን ሰዎች ከሰው ጥቂት መልካም ነገር መማር ያንንም በዚያው በተነገረበት መንፈስ መረዳት ካልቻልን የእባብን ያህል እንኳን ልባምነት የለንም ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር የሚለን ቅን ተናገሩ ብቻ ሳይሆን በቅንነትም ስሙ ነው፡፡ በጎ እየተናገርን በበጎ ካልሰማን፤ በፍቅር እየሰማን መልካሙን ካልተናገርን ሁለቱም በአንድ ጆሮ ሰምቶ በሌላው እንደማፍሰስ ነው፡፡
        ሕግ አዋቂው ይህንን ከሚያህል እውቀቱ ማስተዋልን አለማትረፉ ምንኛ ያሳዝናል? በእርግጥ እውነተኛ ማስተዋል የጥበብና የእውቀት ባለቤት ከሆነው ከእግዚአብሔር ካልተገኘ በቀር እውቀት ሁሉ እንጀራ እንጂ ሕይወት አይሆንም፡፡ በሌላ ስፍራም ከፈሪሳውያን ወገን የአይሁድ አለቃ የሆነውን ኒቆዲሞስ ጌታ “አንተ የእስራኤል መምህር ስትሆን ይህን አታውቅምን? (ዮሐ. 3÷10)” ብሎታል፡፡ ኒቆዲሞስ ሕግ አዋቂና ሳንሄድሪን የሚባለው የአይሁድ ሸንጎ አባል ነው፡፡ ነገር ግን ጥልቅ የሆነውን የጌታ አሳብ መረዳት አልተቻለውም፡፡ በየትኛውም የሰው ሁኔታ ውስጥ ጌታ ትሁት ነው፡፡ ሕግ አዋቂው ለመፈተን ቢመጣም ጌታ አዋርዶ አልሸኘውም፡፡ ይልቁንም እንዲህ ላለው ልቡ ርኅራኄ በማሳየት፣ ራሱን ያጸድቅ ዘንድ “ባልንጀራዬስ ማን ነው?” በማለት ላቀረበው ጥያቄም ተጨማሪ ምሳሌ በመስጠት አሰናበተው፡፡ ማን ምን እያሰበ እንደሆነ እያወቀ የሚታገስ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡
           መልካሙን አመል የሚያጠፋ ክፉ ባልንጀራ በበዛበት ዘመን ባልንጀራዬ ማን ነው? የሚለው ጥያቄ አስፈላጊ ነው፡፡ አብዛኛው ጥፋት የሚፈጸመው በባልንጀራ ምክር ነው፡፡ ነቢዩ ዳዊት “ምስጉን ነው በክፉዎች ምክር ያልሄደ” (መዝ. 1÷1) ይላል፡፡ በክፉ ባልንጀራ ምክንያት ብዙ ጎጆ ፈርሶአል፡፡ ጓደኞች ተቆራርጠዋል፡፡ የቆሙ ሰዎች ወድቀዋል፡፡ ለክፉዎች ምክር አለመሸነፍ ብፅና ነው፡፡ ስለ ምክር ከተነሣ የኢዮብን ሚስት እናስባታለን፡፡ እግዚአብሔርን ስደብና ሙት ስለ ምን ፍጹምነትህን ትጠብቃለህ በማለት መከረችው፡፡ (ኢዮ. 2÷9) የሴቲት ምክር ምን ያህል አስገራሚ ነው? ምክር የእርሷ ሲሆን ሞቱ ግን የእርሱ ነው፡፡
           ሱሰኝነትን ለባልንጀራቸው ያስተማሩ ሰዎች ትምህርቱ የሚያመጣው ኪሳራ ላይ የሉም፡፡ ስካርና ዝሙትን ያስተማሩ ሰዎችም ውጤቱ የሚያመጣው ስብራትና በሽታ ላይ የሉም፡፡ ተንኮልን፣ ክፋትን አቀብሎ ሸሽ አይነት ሰዎች ናቸው፡፡ የምንቸራውን ይሰጡናል አብረውን ሊያጭዱ ግን አይኖሩም፡፡   ኢዮብ ለገዛ ሚስቱ ክፉ ምክር የሰጠው ምላሽ የእርሱን ጥንካሬ ያሰየ፣ የመካሪዋን ፍላጎት ያሳፈረ፣ ጌታ እግዚአብሔርን ደግሞ ያከበረ ነበር፡፡ የምንመከረውንም የምንመክረውንም የምናስተውልበትን ጸጋ መንፈስ ቅዱስ ያድለን፡፡ እውነተኛ ባልንጀራ ትርጉሙ ከወንድምም ይበልጣል፡፡
        ጌታ ሕግ አዋቂው ራሱን ለማጽደቅ ብሎ ያቀረበውን ጥያቄ ለተሻለ ትምህርት ተጠቀመበት፡፡ ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ስለ ወረደ በዚያም ወንበዴዎች አግኝተው ስለ ደበደቡት በሞትና በሕይወት መካከልም ሲሆን ትተውት ስለሄዱ አንድ ሰው ተረከለት፡፡ በዚያም መንገድ አንድ ካህን ሲያልፍ ምንም ሳይረዳው ገለል ብሎ አለፈ፤ ደግሞ አንድ ሌዋዊ በዚያ ሲያልፍ እንደ ካህኑ ሁሉ ምንም ሳይረዳው ትቶት ሄደ፡፡ አንድ ሳምራዊ ግን ሲሄድ ወደ እርሱ መጣ አይቶትም አዘነለት፡፡ ቀርቦም ዘይትና የወይን ጠጅ በቁስሎቹ ላይ አፍስሶ አሰራቸው እስኪድንም ድረስ የሚያስፈልገውን ሁሉ ዋጋ ከፈለ፡፡ (ሉቃ. 10÷33)
        ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌውን ከጨረሰ በኋላ ለሕግ አዋቂው “ከእነዚህ ከሦስቱ በወንበዴ እጅ ለወደቀው ሰው ባልንጀራ የሆነው የትኛው ነው?” በማለት ጥያቄ አቀረበለት፡፡ እናንተስ የትኛው ይመስላችኋል? በዚህ ምሳሌ ውስጥ ለመጽናናት የሚሆን ትምህርት እናገኛለን፡፡ በወንበዴ እጅ ለወደቀው ምስኪን በዚያ መንገድ ካህኑና ሌዋዊው ብቻ የሚያልፉ ቢሆን ኖሮ ምን ተስፋ ነበረው? ወድቆ ከመረሳት፣ ሞቶ ከመቀበር ከዚህ የተሻለ የሚቀርለት ተስፋስ ምን ይሆን ነበር? እንደ ኢያሪኮ ባለው ስፋራ ከንፈር ከመምጠጥ ያለፈ እርዳታ ማግኘት ቀላል አይሆንም፡፡
         ከተማይቱ በዓለም ላይ ከሚገኙ ከተሞች ሁሉ ዝቅተኛ እንደመሆንዋ ለወንበዴዎች ዓመጽ ምቹ ማስፈጸሚያ በመሆን አገልግላለች፡፡ ካህኑና ሌዋዊው በወንበዴዎች ተደብድቦ መንገድ ላይ የወደቀውን ሰው ያልረዱት መርዳታቸው ዋጋ እንደሚያስከፍላቸው አስበው ሳይሆን አይቀርም፡፡ ምሳሌውን አማናዊ ስናደርገው ደግሞ ዋጋ ለመክፈልና የወደቀውን ሰው ለማዳን የሚያስችል አቅም በእነርሱ ውስጥ አለመኖሩ ነው፡፡ ደጉ ሳምራዊ ግን ይህንን ምስኪን አይቶ አልፎ ይሄድ ዘንድ በእርሱ ያለው ፍቅር አይችልም፡፡ የወደቀውን ሰው ሳይጸየፍ ይታቀፍ ዘንድ የሚችል የደጉ ሳምራዊ እጅ ብቻ ነው፡፡ የጨረቃ ከተማ ላይ ለወደቀው ፀሐይ ካልወጣች በቀር መፍትሄ የለም፡፡ ጨረቃ ጨለማውን ተባብራ ታድራለች፡፡ ፀሐይ ግን ጽልመትን ገፋ በሚያስደንቅ ብርሃን ትቆማለች፡፡
         በበደሉና በኃጢአቱ ሙት ለሆነው፣ የልቡን ፈቃድና የሥጋውን ምኞት በመፈፀም ለሚረካው፣ ከፍጥረቱም የቁጣ ልጅ ለሆነው ሰው፣ በወንበዴው ዲያቢሎስ በክፉው እጅ ለወደቀው ሰው ተራ ባልንጀራ ሳይሆን አዳኝ (ታዳጊ) ባልንጀራ ያስፈልገው ነበር፡፡ በቁስሉ ላይ ዘይት የሚያፈስ፣ የሚሰማ ብቻ ሳይሆን እንደ ችግረኛው የሚሰማው፣ ዲናሩን አውጥቶ መድኃኒት የሚሆን የሚታደግ፣ የሚምር፣ የሚወድ፣ የሚሸከም ወዳጅ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው!!

የአዳኝ ባልንጀራ ከወዴት ይገኛል
ክርስቶስ ላመኑት ከሁሉም ይለያል
ሌዊና ካህኑ ረግጠው ላለፉት
ኢየሱስ ይራራል ሳምራዊ ነው ያሉት፡፡

የአንደበትን ሳይሆን የልብ የሚሰማ
ኃጢአተኛን ወድዶ አብሮ የሚታማ
የጠፋውን ሊያድን ሕይወቱን የሰጠ
ኢየሱስ ብቻ ነው ታሪክ የለወጠ

          አሳቡ እንደሚገባ ያልተብራራው ለአንባቢው ፍንጭ የማሳየትና በተሻለ አገላብጦ ለማየት እንዲረዳ ሲባል ነው፡፡ በመሆኑም ከመነሻው ጀምሮ ያለውን በማመዛዘን ማጥናት ይቻላል፡፡ ማስተዋል ይብዛልን፡፡

Tuesday, July 17, 2012

በመልካም መበደል (ካለፈው የቀጠለ)


        
ባለፈው ጽሑፋችን በመልካምነት ስለመበደል በመጠኑ ለመነጋገር የሞከርን ሲሆን በዚህ ክፍልም ያነሣነውን ርእስ በተሻለ በማብራራትና የሚረባንን አሳብ በማንሸራሸር መጣጥፋችንን እናጠናቅቃለን፡፡
       አንድ አባት “በዚህ ዘመን መልካምነት መልክ ሆኖአል” በማለት የተናገሩትን አስታውሰዋለሁ፡፡ ምን ማለት ፈልገው ይሆን? ብዬ ስጠይቅ በቀጥታ አእምሮዬ ውስጥ የመጣው የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ እርሱም “የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል (2 ጢሞ. 3÷5)” የሚል ነው፡፡ ይህ የተፃፈው በጊዜው ለቅዱስ ጳውሎስ የመንፈስ ልጁ ለሚሆን ለጢሞቴዎስ ነው፡፡ ነገር ግን ከመንፈስ ቅዱስ የመጣ መመሪያ እንደመሆኑ እኛም ራሳችንን እንፈትሽበት ደግሞም ተግባራዊ እናደርገው ዘንድ የተገባ ቃል ነው፡፡
       የአምልኮት መልክ አላቸው የሚለው አገላለጽ ላላመኑት የተነገረ አይደለም፡፡ ይልቁንም በቂ እምነት አለን ብለው ለሚመፃደቁት፣ ክርስቶስ እንዳላቸው ለሚለፍፉት፣ በእግዚአብሔር ስም በእናመልካለን ምክንያት ለሚሰበሰቡት ነው፡፡ ይህንን ማሰብ ምንኛ ልብን የሚያዝል ነገር ነው? ብዙ ጊዜ የክርስትናውን ማኅበረሰብ ስንመለከት አብዛኛው ክርስቲያን ስለመሆኑ የሚጨነቅ ሳይሆን በመባሉ የረካ ብቻ ነው፡፡
       ጌታ በአንድ ስፍራ ላይ ለደቀ መዛሙርቱ ሲናገር ጽድቃችሁ (መልካምነት) ከፈሪሳውያን ጽድቅ ካልበለጠ መንግስተ ሰማያት መግባት አትችሉም (ማቴ. 5÷20) ብሏል፡፡ ፈሪሳውያን ትልቁ ትምክህታቸው የአብርሃም ልጅ መሆናቸው ነበር፡፡ የአብርሃም ልጅ መሆን መልካም ነገር ነው፡፡ ዳሩ ግን የአብርሃም ልጅነታቸውን የአብርሃምን ተግባር ለመፈፀም ሳይሆን ለማፍረስ ተጠቀሙበት፡፡ በመልካሙ በደሉበት! ጌታ ግን ያለተግባር መመሳሰል የዘር ፉከራው ፋይዳ እንደሌለው በተግሣጽ ተናገራቸው፡፡ በእርግጥም በዓመጽ እየኖሩ በሰው ጽድቅ ተንጠላጥሎ ለመጽደቅ መሞከር የከፋ አመጽ ነው፡፡ ለዚህ ነው ከላይ አባባላቸውን የተዋስነው አባት ስለ መልከኛው መልካምነት የነገሩን፡፡
       በክርስትናው ውስጥ እየታየ ያለው ውድቀት ኃይሉን መካድ ነው፡፡ ክፉው መልካምን ለብሶ ከተንቀሳቀሰ በቀጥታ መልካምነት ኃይሉ ተክዶአል ማለት ነው፡፡ ስሙ አለ ግን ሞቶአል! ባለፈው ክፍል ላይ የመጀመሪያውን በመልካም የመበደል ትርጉም አይተናል፡፡ በዚህ ክፍል ደግሞ ሁለተኛውን አይነት ማለትም ከትዕቢት የመነጨውን በመልካም የመበደል ሁኔታ እንመለከታለን፡፡
       በወንጌላዊው ሉቃስ መጽሐፍ ውስጥ መንፈስ ቅዱስ ከሚያስነብበን አስደናቂ ድርጊት መካከል ፈሪሳዊውና ቀራጩ በእግዚአብሔር ፊት ያቀረቡት ጸሎት ልንነጋገርበት ላሰብነው ለዚህ ርእሰ ጉዳይ ግልጥ የሆነ ትስስር ያለው ነው፡፡ (ሉቃ. 18÷9-14) ኢየሱስ ክርስቶስ ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ ሊሰጥ የመጣበትን ዓላማ ለማሰናከል ሰይጣን አብዝቶ ከተጠቀመባቸው መካከል ፈሪሳውያን በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡ ጌታም አለማመናቸውንና ራሳቸውን ማጽደቃቸውን በብርቱ ሲቃወመው እንመለከታለን፡፡        
       ለሁላችንም ግልጽ እንደሚሆነው ፈሪሳውያን ጌታን ከጠሉበት ጥልቅ ምክንያት አንዱ ለዘመናት ተሸፍኖ በኖረው ኃጢአታቸው መካከል ፍጹም ንፁሕ የሆነው ጌታ ሲገኝ ከበሬታን በሚሰጣቸው ሕዝብ መካከል ነውራቸው መጋለጡ ነው፡፡ ፀሐይ እንዳረፈችበት ቆሻሻ ብርሃን የሆነው ክርስቶስ ጽድቃችን ብለው በሚመኩበት ተግባራቸው ፊት ሲቆም የተመኩበት መልካምነት እንደ መርገም ጨርቅ ሆኖ ታየ፡፡ ስለዚህም ካፈርኩ አይመልሰኝ አይነት ዘመቻ በጌታ ላይ ዘመቱ፡፡
       ጌታ ፈሪሳውያንን ለእግዚአብሔር ዕዳቸውን ለመክፈል እንዳልቻሉ ድሆች (ሉቃ. 7÷40)፣ የተሻለ መቀመጫ ለማግኘት እንደሚጣሉ እንግዶች (ሉቃ. 14÷7) በታዛዥነታቸው እየተመኩ ለሌሎች ጉድለት ግድ እንደሌላቸው ልጆች (ሉቃ. 15÷25) አድርጎ ገልጾአቸዋል፡፡ ፈሪሳዊው በሳምንት ሁለት ጊዜ እንደሚፆም ደግሞም አስራት እንደሚያወጣ ከዚህ ሁሉ በላይ እንደ ቀራጩ ባለመሆኑ እንደሚያመሰግነው አይኖቹን አንስቶ ለእግዚአብሔር አስረዳ፡፡ (ማቴ. 23÷23) ቀራጩ ግን ድካሙን በበቂ ሁኔታ የተረዳ ስለነበር ደረቱን እየደቃ የእግዚአብሔርን ምሕረት ይጠይቅ ነበር፡፡
       ጌታ ቀራጮችን ቤተ ክርስቲያንን እንዳልሰማ አረመኔ ገልጾአቸዋል፡፡ (ማቴ. 18÷17) በሌላ ስፍራ ግን በኋላ ማቴዎስ የተባለውን ሌዊ ከቀራጭነት ተነሥቶ እንዲከተለው እንደጠየቀው ተጠቅሷል (ሉቃ. 5÷27)፡፡ በጸሎት ጌታ ፊት የቆመው ቀራጭ መልካሙን ጸሎት በመልካም ሲጠቀምበት፤ ፈሪሳዊው ግን እንዲህ ባለው በጎ ነገር ይበድልበት ነበር፡፡ ቀራጩ ስለ ራሱ ኃጢአት ግዝፈት ሲያስተውል ፈሪሳዊው ግን ስለ ራሱ ልብ በቂ ዕውቀት አልነበረውም፡፡ ብዙ ሰዎች ስለ ሰዎች መውጣትና መግባት በቂ መረጃ ሲኖራቸው ስለ ራሳቸው ብርታትና ድካም ግን አያውቁም፡፡ ካስተዋልን ሰውን ለመክሰስና ለመውቀስ ፈሪሳዊው በጸሎት ስፍራ ላይ ምን ይሠራል? ምክንያቱም ስፍራውን ያለ አላማው እየተጠቀመበት ነው፡፡ ዛሬም እየተመለከትን ያለነው ይህንኑ ነው፡፡
       ቤተ ክርስቲያን የእርቅ ቦታ ሆና ሳለ የእግዚአብሔር አደባባዮች መሰዳደቢያ ሲከፋም ድንጋይ መወራወሪያ ሆነዋል፡፡ ሲጀመር ድንጋይ ለመወርወር፣ ለመሳደብ፣ ለመደባደብ መፆምና መጸለይ አያስፈልግም፡፡ የሚያስፈልገው ጥሩ ዱርዬ መሆን ነው፡፡ ለባልንጀራ ጉድጓድ ለመቆፈርም አስቀዳሽ አወዳሽ መሆን አይጠይቅም፡፡ ይህንን ጡንቻ ለማፈርጠም የሚጠይቀው የክፋትን ብረት መግፋት ብቻ ነው፡፡ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል ያህል በልባቸው አሳብ ሲመሩ ማየት ምንኛ አሳፋሪ ነው፡፡ እኛ መንፈሳዊ ስድብ፣ አድማ፣ ድብድብ፣ አመጽ አለን፡፡ ነገር ግን ይህንን ከየት አመጣነው? ከማንስ ተማርነው? በመልካሙ መበደል ይሏችኋል ይህ ነው፡፡ እንዲህ ያለው ደግሞ ሳናውቅ በስህተት አይነት የሚሠራ አይደለም፡፡ ሆን ተብሎ እውነትን ረግጦ በእግዚአብሔር አሳብ ላይ የሚፈጸም አመጽ ነው፡፡
       ፈሪሳዊው በትእቢቱ ሲኮነን ቀራጩ ግን በእምነቱ ሊድን ችሏል፡፡ የፈሪሳዊው ጸሎት ስለ ቀራጩ ለእግዚአብሔር መረጃ እንደማቀበልም ነበር፡፡ ራሳችንን እንደ መንፈሳዊ ፓፓራዚ የምናስብ፣ ለእግዚአብሔር የመረጃ ምንጭ እንደሆን የሚሰማን ካለን በደላችን ጌታን አውቅልሃለው የማለት ያህል ነውና ፈጥነን ንስሐ እንግባ፡፡ በመልካሙ ፆም፣ በመልካሙ ጸሎት፣ በጎ በሆነው መንፈሳዊ ተግባር የምንበድልበት ከሆነ እንግዲህ የእኛ ብልጫ ምኑ ላይ ነው?    

Tuesday, July 10, 2012

በመልካም መበደል



         ከምድራችን ጩኸት አንዱ የመልካም ያለህ የሚለው ነው፡፡ በጎውን ማድረግ ሰው የተፈጠረበት ዓላማ ሆኖ ሳለ ዛሬ አንድ መልካም ማግኘት የአንድ በዓልን ያህል የሚያስቦርቅ ሆኖአል፡፡ በእርግጥም በክፉ በተያዘው ዓለም ክፉዎች አይደንቁንም፡፡ ጥሩ ነገር ከሰዎች ልቦና በተንጠፋጠፈበት፣ ለዓመጽ የተዘረጉ፤ ለመታደግ የታጠፉ እጆች በበረከቱበት፣ ለመርዶ የሚፋጠኑ፤ ለምስራች ሽባ የሆኑ እግሮች በሚስተዋሉበት፣ አደበት ሁሉ ስንፍናን አብዝቶ በሚያወራበት ዓለም መልካምነት ጌጡ የሆነ ሰው ሲገኝ ከዚህም በላይ ያስደስታል፡፡ ልብ ብለነው ከሆነ ግን መልካም መሆን፤ በጎ ማድረግ ብቻ ሳይሆን በዚያ መልካም ላለመበደል፣ በዚያ በጎ ላለመሳት መጠንቀቅም እንደ እግዚአብሔር አሳብ ሊኖሩ ለሚፈልጉና ከሕሊና ውቅሻ ማምለጥ ለሚሹ ሁሉ የተገባ ነው፡፡
        አብዛኛውን ጊዜ በውጪው ዓለም ላይ በሥራ የሚሰማሩ ወገኖቻችን የኑሮአቸውን ያህል የሚኖሩት ለቤተሰብና ለዘመዶቻቸው ጭምር ነው፡፡ አንዳንዴም የራሳቸውን እስኪረሱ ለቤተሰብ የሚኖሩ፣ የሚለፉ ሰዎችን አስተውለናል፡፡ አገር ቤት ያለውን ነገር ስንመለከተው ደግሞ በእህትና ዘመድ ልፋት ሳይማሩ፣ ሳይሠሩ፣ ሳይጥሩ የሰው ወዝ ባመጣው የሚኖሩ ወጣቶችንና ወላጆችን ታዝበናል፡፡ ነገር ግን ረጂዎቹ አስተውለውት ከሆነ በመልካምነት እየበደሉ ነው፡፡ መስጠት ስላለብን እንጂ ብር ስላለን ብቻ አንሰጥም፡፡ መርዳት ስላለብን እንጂ መርዳት ስለቻልን ብቻ አንረዳም፡፡ ምናልባት ይህንን ከመንፈሳዊው ጎን ተመልክታችሁ ልክ ያልሆነ አባባል እንደሆነ ሊሰማችሁ ይችል ይሆናል፡፡ ዳሩ ግን መንፈስ ሁሉን ይመረምራል፡፡ የእግዚአብሔር አሳብም ሞኝነትን አያበረታታም፡፡ ሁሉን ለማነጽ እንድናደርገው ታዘናል፡፡
        የዋህነት የሚለው መንፈሳዊ አሳብ ሞኝነትን ከምንተረጉምበት መንገድ በእጅጉ የራቀ ነው፡፡ በቂ ብር ከተላከልኝ አልማርም አልሠራም ለሚል ሁሉ እያወቁ ማድረግ የዋህ አያስብልም፡፡ የምናደርገው ነገር ሰውየውን የተሻለ እንዲያስብ፣ የበለጠ እንዲያይ፣ ካለፈው በበረታ ሁኔታ እንዲጣጣር ካላደረገው እኛም ይህንን መመዘን ካልቻልን በምናደርገው በጎ ነገር እየበደልንበት ነው፡፡
        በመልካም መበደል ማለት የምናደርገው ጥሩ ነገር በተቀባዩ ላይ እየፈጠረ ያለውን አሉታዊ ተጽእኖ በግልጥ እያወቅን እርምጃ አለመውሰድ ነው፡፡ ከዚህ የሚከፋው ትርጉም ደግሞ ሆን ተብሎ በታቀደና በተቀናበረ እንዲሁም በታሰበበት መንገድ መልካሙን ነገር ለክፋት ማዋል አልያም በበጎ ውስጥ በክፋት መሸመቅ ማለት ነው፡፡ ሁለቱንም አንድ የሚያደርጋቸው ነገር መልካምነታቸው ውስጥ በደል መኖሩ ነው፡፡ በእርግጥ አንጻራዊ በሆነ መንገድ ካልሆነ በቀር ሰው በጎነቱ ውስጥም እድፍ አለ፡፡ እግዚአብሔር የወዳው ቅንነታችንን የሁል ጊዜ ያህል እየቆጠረው ካልሆነ የፈረቃ መልካምነታችን ያውና ሕያው በሆነው ጌታ ፊት መርገም ባስታቀፈን ነበር፡፡
        በመልካም መበደልን ስናስብ በነቢዩ በሕዝቅኤል መጽሐፍ ያለና የነበረ እግዚአብሔር የተናገረውን ብርቱ ቃል እናስታውሳለን፡፡ “የሰው ልጅ ሆይ እነሆ የአይንህን አምሮት በመቅሰፍት እወስድብሃለሁ፤ አንተም ወይ አትበል አታልቅስም፤ እንባህንም አታፍስስ (ሕዝ. 24÷16)” በጋብቻ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በማንኛውም የኑሮ ሁኔታ እግዚአብሔርን ማየት በዋጋ የማይተመን ትርፍ አለው፡፡ ከእግዚአብሔር ውጪ የምናያቸው ነገሮች ሁሉ በራሳቸው ተስፈኛ ስለሆኑ የእኛን እምነት የመሸከም አቅም የላቸውም፡፡ ራሳችን እንኳን በራሳችን ያፈርንበት ጊዜ ትንሽ አይደለም፡፡ እባካችሁ አይናችሁን ከሰው ላይ አንሱ! ለየትኛውም ነገር መስፈርታችን እግዚአብሔርን ማስቀደም አለበት፡፡ ፍቅር እንኳን ቢሆን፤ እግዚአብሔርን መርጦ ጥላቻን ማስተናገድ እጅግ ማትረፊያ ነው፡፡ እኛ በእኔ ጉዳይ ማን ያገባዋል? የወደድኩትን የትኛውንም ያህል ብወድድ ጠያቂ ማነው? ልንል እንችላለን፡፡ ነገር ግን ነቢዩ የገዛ ሚስቱ የአይኑ አምሮት ሆናበት ስለነበር እግዚአብሔር በሞት ከፊቱ አስወገዳት፡፡
       ሰውን ስንጠላ ብቻ ሳይሆን የአይንና የልባችን አምሮት አድርገን ስንወድም እንበድላለን፡፡ ነቢዩ ሚስቱ የጣዖት ያህል እንደሆነችበትና የፍላጎቱ ሙላት እንዳደረጋት ልናስተውል እንችላለን፡፡ ሚስት ማግባት ደግሞም ከእርሷ ጋር በፍቅር መኖር ኃጢአት አይደለም፡፡ እግዚአብሔር መልካም እንደሆነ ካየውና ደስ ከተሰኘበት ትልቅ ነገር አንዱ ጋብቻ ነው፡፡ የትዳር መስራች፣ አክባሪና የበላይ ጠባቂም እርሱ ነው፡፡ ነገር ግን እንዲህ ባለው መልካም ነገር ሕዝቅኤል በአይን አምሮት ተያዘ፡፡ እንግዲህ በደሉ ያለው ጋብቻው ላይ ሳይሆን “የአይን አምሮት” ላይ ነው፡፡ ምን ጊዜም ቢሆን ለሰጪው ሳይሆን ለስጦታው ስንሸነፍለት የሚሆነው እንደዚህ ነው፡፡ እግዚአብሔር የአይናችን አምሮት የሆነውን ሁሉ ይወስዳል፡፡ በመልካሙም መበደል ያስቀጣል፡፡
       ሀብትም፣ ንብረትም፣ ሰውም ጭምር ከእግዚአብሔር ጋር በአማራጭነት ሊቆም አልያም ስፍራውን ሊወስድ ከቶ አይችልም፡፡ እነዚህ ነገሮች በራሳቸው መጥፎ አይደሉም፡፡ ጌታን በገንዘባቸው፣ በሥልጣናቸው፣ በእውቀታቸው፣ በጉብዝናቸው ላይ ሾመውት ያገለገሉ ብዙ ሰዎችን እናውቃለን፡፡ ነገር ግን እውቀት ያለው የእግዚአብሔርን ያህል አያውቅም፡፡ ብር ያለውም የእግዚአብሔርን ያህል ሀብት አይሆንም፡፡ ሀብት ብልና ዝገት ያጠፋዋል፡፡ እውቀት በእብደት ሞኝነት ይሸፈናል፡፡ ደም ግባትም እንደ ደረቀ ቅጠል ይረግፋል፣ ሥልጣን በሚበልጥ ሥልጣን ይሻራል፡፡ ጉብዝናን ሽምግልና ይከተለዋል፡፡ ጌታ ግን ማለዳ ማለዳ አዲስ እንደሆነ በማይዝል ብርታት ይኖራል፡፡
        ነቢዩ ወይ እንዳይል እንዳያለቅስም ታዟል፡፡ እግዚአብሔር በእውነቱ ልክ ትክክል ነው፡፡ ሲያኖር ብቻ ሳይሆን ሲገልም እውነተኛ ነው፡፡ ምን ያህሎቻችን ባሉን መልካም ነገሮች እየበደልን ነው? ሚስት መልካም ናት የአይናችን አምሮት ከሆነች ግን እንበድልባታለን፡፡ ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታዎች ናቸው የልባችን ሙላት ካደረግናቸው ግን በእግዚአብሔር ስጦታ እንበድላለን፡፡ ከባል ጋር መኖር የተወደደ ነው፡፡ ዳሩ ግን ሁለ ነገራችን እርሱ እንደሆነ የምናስብ ደግሞም ያለ እርሱ መኖር የማንችል ያህል ከተሰማን በመልካሙ እንበድልበታለን፡፡ ተወዳጆች ሆይ በጎ መሆን ለሌላውም ማሰብ ነው፡፡ ሰዎች የአይናችን አምሮት እስኪሆኑ ድረስ ስንወዳቸው እንደ ሕዝቅኤል ሚስት በተለያየ ምክንያት በርቀት ሲከፋም በሞት እንዲወሰዱ ምክንያት እንሆናቸዋለን፡፡ እኛም በዚያው መጠን የሰው አይን አምሮት ለመሆን በጣርን ቁጥር ለእግዚአብሔር ቁጣ እንጠጋለን፡፡
                                                      - ይቀጥላል -

Friday, July 6, 2012

የመንደር ፍም



“የአሮንም ልጆች ናዳብና አብዩድ በየራሳቸው ጥናውን ወስደው እሳት አደረጉበት በላዩም ዕጣን አኖሩበት በእግዚአብሔርም ፊት እርሱ ያላዘዛቸውን ሌላ እሳት አቀረቡ፡፡ እሳትም ከእግዚአብሔር ፊት ወጥቶ በላቸው በእግዚአብሔርም ፊት ሞቱ፡፡ (ዘሌዋ. 10÷1)”
         በዘፍጥረት መጽሐፍ እግዚአብሔር በመልኩ (ጽድቅ፣ ቅድስና፣ እውቀት) እንደ ምሳሌው (ወኪል ገዥነት) የፈጠረውን የሰው ልጅ የታሪክ ጅማሬ (ልደት) እናስተውላለን፡፡ ሰው የመጨረሻው ቀን ፍጥረት እንደመሆኑ ለሰው የሚያስፈልጉት ነገሮች ሁሉ አስቀድመው ተፈጥረዋል፡፡ በዚህም የእግዚአብሔር አሳቢነትና ፍቅር ይስተዋላል፡፡ አንድ የስነ መለኮት አጥኒ “እግዚአብሔር ሰውን አስቀድሞ ፈጥሮት ቢሆን ኖሮ ሌሎቹ ፍጥረታት እስከ ዛሬ አይፈጠሩም ነበር፡፡ ምክንያቱም ሰው አስተያየት ሲሰጥና አሳቡን ሲቀያይር እንቅፋት ይሆናል፡፡” በማለት ሰው መጨረሻ የተፈጠረበትን ምክንያት ተናግረዋል፡፡ እግዚአብሔር ግን በዚህ ሁሉ አዋቂ ነው፡፡ እርሱ የሚያውቀውን መላእክቱና ቅዱሳኑ እንኳን አያውቁም፡፡ እንደ እግዚአብሔር ፍጹም ጽድቅ ያለው ካለ እርሱ እግዚአብሔር ነው፡፡ እንደ እግዚአብሔር ፍጹም ቅድስና ያለው ካለም እርሱ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡
        በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ሰው ከተፈጠረ በኋላ ለተፈጠረበት ዓላማ ሲታዘዝ የምናየው አንድ ምዕራፍ ነው፡፡ በቀጣዩ ምዕራፍ ላይ ሰው ከእግዚአብሔር አሳብ ባለመታዘዝ ጠንቅ ሲለያይና ውድቀትን ሲያስተናግድ እንመለከታለን፡፡ ደግሞም እግዚአብሔር መንግስት ነውና በበደለው ሰው ላይ ቅጣትን ሲያስተላልፍ እናነባለን፡፡ አዳም ከበደል በኋላ በመልኩ እንደ ምሳሌው ልጅን እየወለደ (ዘፍ. 5÷1) በአንድ ሰው ምክንያት በደለኝነት ለሁሉ ደረሰ፡፡ በዘፍጥረት መጽሐፍ እግዚአብሔር አብርሃምን እንደጠራ፣ በልጁ በይስሐቅ አንድያ ልጁን ክርስቶስን እንዳብራራ፣ በያዕቆብ የራሱን ሕዝብ እንደለየና የእስራኤል አምላክ እንደተባለ እናስተውላለን፡፡ ዮሴፍ ወደ ግብጽ ከተሸጠ በኋላ የያዕቆብ ቤት ዕጣ ባርነት ሆነ፡፡ ሕዝቡ ሁሉ በግብጽ ልክ እንደ አንድ ሰው በባርነት የአብራካቸውን ክፋይ ከጡብ ጋር እየረገጡ ተገዙ፡፡ ይህም በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአትን ላደረገው ሕዝብ የኃጢአቱ ደመወዝ ነበር፡፡
       በቀጣይ የምናገኘው መጽሐፍ ኦሪት ዘፀአት ሲሆን ይህም የመውጣት መጽሐፍ ይባላል፡፡ በዘፍጥረት መጽሐፍ ላይ በባርነት ቀንበር ስር እንደወደቀ ያየነው የእስራኤል ሕዝብ ነፃነቱ የታወጀው በዚህ መጽሐት ውስጥ ነው፡፡ የፋሲካውን በግ ደም በመቃንና በጉበናቸው ላይ ቀብተው ግብጽን የለቀቁበትን አስደናቂ መዳን እናስተውላለን፡፡ እግዚአብሔር በጸናችና በተዘረጋች እጅ ሕዝቡን ከጨቋኝ ገዥአቸው አላቆ ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባሕር ጣለ ጉልበቴ ዝማሬዬም እግዚአብሔር ነው! በሚል ምስጋና አፋቸውን በእልልታ ሞላው፡፡
       እግዚአብሔር ሕዝቡን አዳነ ስንል መጀመሪያ የሚፈጠርብን ጥያቄ ከምን? የሚል ነው፡፡ የእስራኤል ሕዝብ በኃጢአታቸው ምክንያት ለኃጢአት ውጤት ባርነት ተዳርገዋል፡፡ ስለዚህም ከዚህ የባርነት ኑሮ የሚያድናቸው ያስፈልግ ነበር፡፡ ይህ በእነርሱ የፍላጎት ጊዜ ውስጥ አልተከናወነም፡፡ የሰው አቅም ሲሟጠጥና የሰው ብቸኛ አዳኝ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደሆነ ሕዝቡ ሲረዳ እግዚአብሔር ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ ራሱን ምክንያት አድርጎ እርሱ በወደደውና በላከው ሙሴ ባርነት ታሪክ ሆነላቸው፡፡
       እስራኤል በበጉ ደም ዳኑ በማለት ስለዳነ ሰው ስናወራ ሌላው የምንጠይቀው ጥያቄ ሊሆን የሚችለው  መዳን ለምን? የሚለው ነው፡፡ የዘሌዋውያን መጽሐፍም የሚመልስልን ይህኑ ጥያቄ ነው፡፡ በተለይ ስለ አምስቱ መሥዋእቶች ማለትም የሚቃጠል፣ የእህል፣ የደኅንነት፣ የኃጢአት እና የበደል መሥዋእት ስናነብ ከግብጽ ባርነት እግዚአብሔር ሕዝቡን ነፃ ያወጣበት ዓላማ እንዲያገለግሉትና እንዲያመልኩት እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ይህ አሳብ ግን እግዚአብሔር ለሕዝቡ ያደረገውን እንደ መደራደሪያነት አቅርቦታል የሚል ትርጉም አይሰጥም፡፡ ምንያቱም በማምለክ ውስጥ ያለው ጥቅምና በረከት ለሰው ነው፡፡ እግዚአብሔር ግን በየትኛውም መንገድ ማለትም በመመለክ ቢሆን ባለመመለክ፣ በመገልገል ቢሆን ባለመገልገል ሁሉ ከእርሱ በእርሱ ለእርሱ ነው፡፡ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ እግዚአብሔር ሊመለክና ሊገለገል እንዴት እንደሚገባው ለሕዝቡ መመሪያን ሲሰጥ እንመለከታለን፡፡
        አብዛኛውን ጊዜ የእግዚአብሔርን ደስታ ከእኛ ደስታ፣ የእግዚአብሔርን ፍላጎት ከእኛ ፍላጎት አንፃር ለመዳኘት ስንሞክር ይስተዋላል፡፡ ነገር ግን ማንኛውም እንቅስቃሴአችን በተለይ አምልኮ ከእግዚአብሔር አሳብና ፈቃድ አንፃር ይመዘናል እንጂ እግዚአብሔርን በእኛ ልምምድ ላይ እንዲደገፍ ማድረግ አንችልም፡፡ ምክንያቱም መንፈስ የሆነውን እግዚአብሔር በመንፈስ ሆነን ካላደመጥነው በቀር አሳቡ ከአሳባችን መንገዱም ከመንገዳችን በእጅጉ የራቀ ነው፡፡
        በነቢዩ በሳሙኤል መጽሐፍ ውስጥ እግዚአብሔር የእስራኤል ንጉሥ ያደረገውን ሳኦልን የናቀበት መንገድ የሰውና የእግዚአብሔር አተያየት ምን ያህል የተራራቀ እንደሆነ ያስረዳናል፡፡ እስራኤል ከግብጽ ወጥተው በምድረ በዳ በሚያደርጉት ጉዞ ብርቱ ተቃዋሚዎቻቸው አማሌቃውያን ነበሩ፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔር ለሕዝቡ ሊበቀልለት ሳኦልን ላከው፤ ፈጽሞም እንዲያጠፋቸው እንዳይምራቸውም በማስጠንቀቂያ ጭምር አዘዘው፡፡ ሳኦል ግን የአማሌቅን ንጉሥ አጋግን ማርኮ፣ ለእግዚአብሔር ሕዝቡ ይሠዉአቸው ዘንድ መልካሞቹን በጎችና በሬዎች ይዞ ተመለሰ፡፡ በሰው ሰውኛው ስናስበው ሳኦል ለእግዚአብሔር የቀና መልከ መልካሙን ያደረገ ይመስላል፡፡ ዳሩ ግን አለመታዘዝ በየትኛውም ያማረና የተዋበ ነገር ውስጥ ቢሸሸግ ሁሉን ከሚችል አምላክ ፍርድ ሊሰወርና ሊሰውር አይችልም፡፡ (1 ሳሙ. 15) እግዚአብሔር ለጨከነበት ብንራራ፤ እግዚአብሔር በራራለት ላይ ደግሞ ብንጨክን ሁለቱም ራስን በእግዚአብሔር ፊት ለማጽደቅ መሞከር ነው፡፡ የሰው ጽድቅ በእግዚአብሔር ፊት ያለው ዋጋ ኢዮብ እንዳለው ራስን የመናቅ ያህል ነው፡፡ (ኢዮ. 42÷5) ስለዚህ እግዚአብሔር በጨከነበት ነገር ላይ መጨከን ለእውነት ምላሽ መስጠት ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር በሚኖረን የትኛውም ግንኙነት “እርሱ እንዳለ” የሚል መሆን አለበት፡፡
          በርእሳችን ላይ ያነሣነው ክፍል የሚነግረንም ይህንን ነው፡፡ የአሮን ልጆች በየራሳቸው ጥናውን ወስደው በእግዚአብሔር ፊት እሳት አደረጉበት በላዩም ላይ እጣን ጨመሩበት፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ያለው ስህተት ምንድነው? የሚለው ጥያቄ የምንነጋገርበት ማእከል ነው፡፡ ናዳብና አብዩድ ያደረጉት የተለመደውን ተግባር ቢሆንም በዚህ ውስጥ ግን የእግዚአብሔርን ቁጣ የሚቀሰቅስ ሌላ ድርጊት እናስተውላለን፡፡ እርሱም እግዚአብሔር ያላዘዘው “ሌላ እሳት” ነው፡፡ ልብ የምንላቸው ብዙ ነገሮች በዚህ ትምህርት ውስጥ እንደተካተቱ ማስተዋል ከእግዚአብሔር ፍርድ ያስመልጣል፡፡ ሌላ ጥና አልያም ሌላ እጣን እንደወሰዱ አልተነገረንም፡፡ ነገር ግን ሌላ እሳት (እንግዳ እሳት) እንዳቀረቡ ተጠቅሷል፡፡ እንግዲህ የአሮን ልጆች የከፋ ኃጢአት ሌላ እሳት እንደሆነ እንረዳለን፡፡
        የዘሌዋውያን መጽሐፍ ከፍጥረቱ የቁጣ ልጅ የሆነው የሰው ልጅ በበደሉና በኃጢአቱ የሞት ባርያ ሆኖ ሳለ እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለ ጠጋ ስለሆነ በእውነትና በመንፈስ ያመልክ ዘንድ በልጁ በክርስቶስ ያዳነውን ክርስቲያ የምናይበትን ትምህርት የሚሰጠን ክፍል እንደመሆኑ ከዚሁ አንፃር ሕይወታችንን መፈተሽ ይጠበቅብናል፡፡
         የአሮን ልጆች እሳት ከእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ መውሰድ እንዳለባቸውና አምልኮም በዚህ መንገድ መሆን እንደሚገባ በግልጥ የተቀመጠላቸው መመሪያ እያለ ከመገናኛው ድንኳን ውጪ የመንደር ፍም ያቀረቡበት ምክንያት ከመገመት የከበደ አይሆንም፡፡ በድፍረትም (ምን ይመጣል) ይሁን በቸልተኝነት (ምን አለበት) ጉዳዩ አለመታዘዝ ነው፡፡ ይህም የእግዚአብሔርን ቤት በሌላ እሳት የማርከስ እንዲሁም ክብሩን የማቃለል ሂደት ነው፡፡ ሰው ከራሱ ካለው ወስዶ እግዚአብሔርን ደስ ሊያሰኘው አይችልም፡፡ ምክንያቱም ስለ በጎ ፈቃዱ መፈለግንም ማድረግንም በእኛ የሚሠራ እግዚአብሔር ነው፡፡ (ፊል. 2÷13) ጌታ እንኳን ስለ እውነት መንፈስ ሲናገር “ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋል” (ዮሐ. 15÷13) ብሏል፡፡ እግዚአብሔርን ደስ የምናሰኘው ከእርሱ በእርሱ ለእርሱ በማድረግ ነው፡፡ ዛሬ በዚህ ጉዳይ ላይ ቸልተኝነትና ዓመጽ ቢታይም እግዚአብሔር ግን በናዳብና አብዩድ ላይ የነበረው አይን ዛሬም በዙሪያችን ነው፡፡ በኃይለኛው በእግዚአብሔር እጅ መውደቅ ምንኛ አስፈሪ ነው?
       በመንደር ፍም እግዚአብሔር ፊት ለመቆምና ደስ ለማሰኘት መትጋት በዘመናችን በእጅጉ የሚስተዋል ሐቅ ነው፡፡ ሰዎች በድፍረት የእግዚአብሔርን አሳብ ሲያጣምሙ፣ መንፈስ ቅዱስን ተክተው መለኮታዊ በሆነው መመሪያ ላይ የሥጋና የደም ምክራቸውን ሲያቆሙ፣ እውነትን ገፍተው ፊደላዊ ለሆነው የሞት አገልግሎት ሲፋጠኑ እየተመለከትን ነው፡፡ ነገር ግን የእግዚአብሔር እሳት በመሠዊያው ላይ ያለውን መሥዋእትና ስብ እንደምትበላ ሁሉ በመሠዊያው ላይ የሚዘብቱትንም ዘባቾች ትበላለች፡፡ እስቲ የመንደር ፍሞችን (እንግዳ እሳት) ወደ ሕሊናችሁ በማምጣ ጥቂት አስቡ፡፡ በቤቱ ላይ ማዘዝ የራስ ሙሉ መብት አይደለምን? ከገዛ ቤቱ በስተውጪ ተጥሎ ማንኳኳ ይገባዋልን? ሀብታም ነኝ ባለ ጠጋ ሆኜአለሁ አንድም ስንኳ አያስፈልገኝም ማለት፤ ጎስቋላና ምስኪንም ድሀም ዕውርም መራቆትንም አለማወቅስ ከፍርድ ያድናልን?
     የአሮጌው ሰው ማንነት ሁለቱም እሳት አይደለምን? ችግሩ ምኑ ላይ ነው? እንዲህና እንደዚያ? በማለት ይጠይቅ ይሆናል፡፡ ዳሩ ግን እግዚአብሔር ካለ ሰው ከአሳቡ ጋር ይታገል ዘንድ አግባብ አይደለም፡፡ አምልኮ በእግዚአብሔር እሳት እንጂ በመንደር ፍም (ስሜት፣ የሰው የበላይነት፣ ተረት፣ እኔነት፣ የሰው ብልሃት፣ ለዚህ ዓለም የሚመች አካሄድ፣ ማስመሰል) ጌታን አያከብርም፡፡ የአክዓብ ሚስት ኤልዛቤል እግዚአብሔር ፍርዱን ነቢይ በሆነው በኢዩ አማካኝነት በገለጠ ጊዜ ውድ በሆነ ጌጣ ጌጥ ራስዋን አስጊጣ ደግሞም ዓይኖቿን ተኳኩላ ጠበቀችው፡፡ (2 ነገ. 9÷30) የቱንም ያህል ብትዋብ ግን ከእግዚአብሔር ቁጣ መዳን አልቻለችም፡፡ ምክንያቱም ጌጧ የዚህ ዓለም፤ ኩሏም የሰው ኩል ነበር፡፡ እግዚአብሔር ዝርግፍ ጌጥ የሆነላቸው (ኤር. 2÷32) በእርሱም ኩል የደመቁ (ራዕ. 3÷18) ሁሉ ከፍርድ አምልጠዋል፡፡ አንተስ?
    ተወዳጆች ሆይ ቤተ ክርስቲያን እየታመሰች ያለችው በመንደር ፍም ነው፡፡ ለእውነት ሳይሆን ለጥቅም ባደሩ፣ ለመንፈስ ቅዱስ ሳይሆን ለልባቸው አሳብ በተሸነፉ፣ ለክብሩ ሳይሆን ለክብራቸው ዘብ በቆሙ ወገኖች ምክንያት የሥጋ አቅም እየገነነ የመለኮት ፈቃድ ደግሞ ወደ ጎን እየተተወ ነው፡፡ ለአንድ እውነተኛ ክርስቲያን ደግሞ ይህንን መለየትና ከዚህ ዓመጽ ራስን መለየት የተገባ ነው፡፡ ልባቸው በእውነት መንፈስ ሳይሆን በመንደር ፍም በተሞላ አስመሳዮች ብዙዎች እየተቃጠሉ ነው፡፡ ቅን ፈራጅ የሆነው ጌታ ግን በዙፋኑ አለ፡፡ ጌታ እግዚአብሔር ሕያው በሆነው በእርሱ ፊት በመንደር ፍም ፊቱ እንዳንቆም ለዘላለም ይጠብቀን፡፡ 

Tuesday, July 3, 2012

ማን ያግባሽ? (ክፍል አራት)



5. ለውይይት ያቀረባችሁት አሳብ የሁሉንም ልብና ጓዳ የሚፈትሽ እንደመሆኑ ያየሁት ተሳትፎ አነስተኛ መሆን በእጅጉን አስገርሞኛል፡፡ የሆነው ሆኖ ሕሊና የተባለች ተሳታፊ ለጠየቀችው ጥያቄ ምላሼን ለማካፈል እሞክራለሁ፡፡ ማንኛውም ሰው እንደ አንድ ቀን ሁለት አይነት የሕይወት ገጽታ አለው፡፡ ማለትም ቀን የምንለው ግማሽ ብርሃን እና ግማሽ ጨለማ እንደሆነ ሁሉ የአንድ ሰው ሙሉ ታሪክም ደካማና ጠንካራ ጎን አለው፡፡ ጨለማውን እያስወገድን ብርሃኑን ብቻ ተቀብለን እንኑር ወደሚል ጽንፈኝነት ከመጣን ደግሞ የሚኖረው ሙሉ ቀን ሳይሆን  ግማሽ ቀን ነው፡፡ እንዲህ ቢሆን ደግሞ በሰው ልጅ ኑሮ ላይ የሚያስከትለው ለውጥ ምን ሊሆን እንደሚችል አስቡ!
         አንድን ሰው ስናስብም ከዚህ የተለየ፤ አልያም የራቀ ሊሆን አይችልም፡፡ ብርቱ ጎን እንዳለ ሁሉ ደካማም ጎን አለ፡፡ ሕይወትን ለመኖርና ሰውን መትጋት እንዲጓጓ የሚያደርገውም ይህ ይመስለኛል፡፡ ማግኘትና ማጣት፣ መክበርና ውርደት፣ ሀዘንና ደስታ ያሉት ሰው ውስጥ ነው፡፡ መልክዓ ምድሩ ሲያለቅስ አልያም ሲስቅ አናየውም፡፡ እንግዲህ የዓለም ገጽታ የሚለካውም ከዚህ አንፃር ነው፡፡ የምንወደው ሰው የቱንም ያህል መልካም ቢሆን የአንድ ቀን እውነት በእርሱ ውስጥ አለ፡፡ ልዩነቱ ያኛው ተፈጥሮአዊ ስለሆነ መቀየር አልያም ማሻሻል አለመቻሉ ሲሆን ይኼኛውን ግን በትምህርት፣ በፍቅር፣ በተግሳጽ፣ በልምድ ባናጠፋው እንኳን በተወሰኑ ጨለማዎቹ ላይ ማሻሻያና ለውጥ ማምጣት እንችላለን፡፡ እውነታው ግን ሁሉም ሰው ጨለማዊና ብርሃናዊ የሕይወት ገጽታ እንዳለው መረዳት ነው፡፡  
           የእህታችን ሕሊና ጥያቄ አንድን ሰው በአዎንታዊ ገጽታው ብቻ የመመልከትና ከእርሱ ጋር ብቻ የመኖር ፍላጎት ችግርን ያሳየናል፡፡ እንደዚህ ያለው ፍላጎት የመጀመሪያ ችግር እውነታን አለመቀበል ነው፡፡ እንዲህ ከሆነ ከራስ ጋር ግጭት፣ የዘወትር ሙግት፣ ከማይለወጠው ጋር ትግል ይመጣል፡፡ እያየለ ሲመጣ ደግሞ እልህ ውስጥ ይገባል “ያልኩት ይሁን” የሚል የማያባራ ጦርነት ያስከትላል፡፡ ጠያቂ ሕሊና እውነቱ ሌላ እንደሆነ ቢገባትም በውስጧ ስር የሰደደው መሻት ግን ይህንን እንድታስተውል እድል የሰጣት አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ በአንድ ሰው ታሪክ ውስጥ ያለውን ሁለት ዓይነት የኑሮ ገጽታ መቀበል ይኖርባታል፡፡
           ከዚሁ ጋር አያይዤ ስለ እግዚአብሔር ፈቃድ ያነሣችውን ጥያቄ ለመመለስ ልሞክር፡፡ እግዚአብሔር ለሚያምኑት እውነተኛ ምሪት አለው፡፡ ሰው ሁሉ የእግዚአብሔርን ምሪት ይረዳዋል ወይ? ለሚለው ግን መልሱ አይረዳውም የሚል ይሆናል፡፡ የእህታችንን ጥያቄ ያመጣውም ይኼው ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ “በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ ሁሉ እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው (ሮሜ. 8÷14” ተብሎ እንደ ተጻፈ ከመንፈስ ቅዱስ የሆነ የማያቋርጥ ምሪት ጌታን ለሚያምኑ ሁሉ አላቸው፡፡ ይህንን  መረዳት የሚቻለው ደግሞ ከቃሉ ጋር የጠበቀ ሕብረት በማድረግ እንዲሁም በጸሎት በመትጋት የምንረዳው ነው፡፡ (የሐዋ. 16÷7) በዚህ ጊዜ የእውነት መንፈስ ምስክርነት በልባችን ይኖረናል፡፡ ነገር ግን መንፈስን ሁሉ በቃሉ በኩል መርምሩ የሚለው መመሪያ ምን ጊዜም ተግባራዊ መሆን ያለበት ጉዳይ ነው፡፡
         በአጠቃላይ በኑሮሽ ጭምር የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመከተል በዋናነት በቃሉ ውስጥ በግልጥ የተቀመጡትን መመሪያዎች አስተውያቸው፡፡ ለምሳሌ በእምነት ከማይመስልሽ ሰው ጋር ጋብቻን መመስረት ተጨማሪ የእግዚአብሔር ምሪት ሳያስፈልግ በግልጥ ተከልክሏል፡፡ በክፉ ባልንጀርነት መጠመድም እንዲሁ፡፡ ሌላው ከሕሊናሽ አንፃር መልካም ምስክርነት የሚያገኘውን እንዲሁም ለወቀሳ የማይሰጥሽን ነገር ልዩ ምሪት ሳትጠብቂ በጸሎት ማድረግ ትቺያለሽ፡፡ በመጨረሻ በእምነት መመላለስን መለማመድ ይኖርብሻል፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔርን ለሚወዱት፣ በስሙም ለሚያምኑት ደግሞም እንደ አሳቡ ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንደሆነ እናውቃለን፡፡ (ሮሜ. 8÷28) የእግዚአብሔርን ምሪት ባትረጂው እንኳን የጸና እምነት ካለሽ ያመንሽው አምላክ ለክፉ እንዳይሰጥሽ የታመነ ነው፡፡ ከዚህ በተረፈ የሚከብድሽ እንዲሁም አቅምሽን የሚፈትን ነገር ሲመጣ ወደ ጸጋው ዙፋን በጸሎት መቅረብና በብርቱ ልመናና ለቅሶ ለጌታ ማስታወቅ ትቺያለሽ፡፡
             ከላይ እውነታውን አለመቀበል እህታችን ላነሣችው ችግር እንዳጋለጣት አልያም አብራው ከችግሩ ጋር እንድትቆይ እንዳደረጋት ተመልክተናል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ እንደ ድክመት የታየኝ ደግሞ ከሰው አቅም በላይ ከሰው መጠበቅ ነው፡፡ ይህ ማለት በአንድ ሰው ውስጥ የሁለት ሰውን ሁኔታ እንደ መፈለግ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ለብዙ ወዳጅነቶች መሻከር አንዱ ምክንያት የአንዱ አቅምና የሌላው ፍላጎት አለመመጣጠን (የአቅርቦትና ፍላጎት አለመመጣጠን) ነው፡፡ ሰውን በሆነው  መቀበል ደግሞ ጤናማነት ነው፡፡ ሕሊና ከሁለት ወንዶች ጋር በነበራት ግንኙነት ወቅት ያገኘችውን በጎ ነገር (እንደ እርሷ አገላለጽ) ከአንድ ሰው ለመፈለግ መሞከሯ ፍትሃዊነት አይመስለኝም፡፡ ባል ሁሉ ወደ ቤቱ ተመልሶ የሚገባው ሚስት ሁሉ ደግ ስለሆነ አይደለም፡፡ ሚስትም እንደዚሁ ቤቴ የምትለው ባል ሁሉ ቅን ስለሆነ አይደለም፡፡ ነገር ግን በአንድ ሰው ውስጥ ያለውን ሁለት ክፍል ስለተቀበሉት ነው፡፡ ልክ እንደ አንድ ቀን!
            በሦስተኛ ደረጃ የታየኝ ድክመት ዛሬን በትላንት አልያም እንደ ትላንት ለመኖር መሞከር ነው፡፡ ይኼ አደገኛ ነገር ነው፡፡ ወጣት የምንለው አንድ ሰው እንደ ትላንትና ሕፃንነቱ መኖር ቢያምረው መጀመሪያ የምንቸገረው በወተት ሒሳብ ይመስለኛል፡፡ በልጆች አስተዳደግ ውስጥ አስተውለን ከሆነ አንዳንድ ልጆች እንቅስቃሴያቸው ከእድሜያቸው በጣም የራቀ ይሆንና የአንዳንዶቹ ደግሞ ሁኔታቸው እድሜያቸው ከሚጠይቀው በጣም የዘገየ ይሆናል፡፡ ሁለቱም ግን አስቸጋሪዎች ናቸው፡፡ በይበልጥ ደግሞ ዛሬ ላይ ሆኖ እንዳለፈው መኖርን ለማስታመም የሚከብድ ይመስለኛል፡፡ እስቲ አስቡት አዳራሽ በሚያህል ቤት ውስጥ እንኖረው የነበረውን ኑሮ አንገት በምታስገባ ቤት ውስጥ ለመኖር ብንሞክር የፍንዳታ ድምጽ የሚሰማ ይመስለኛል፡፡ ለአሳቤ መነሻ የሆነችኝ ሕሊናም ባለፈ ኑሮዋ ውስጥ የነበረውን ነገር በአሁኑ የመፈለግ ዝንባሌ ይታይባታል፡፡
           ሕይወት ልክ እንደ መጽሐፍ በምዕራፍ በምዕራፍ የተከፋፈለች ናት፡፡ ሁሉም ምዕራፍ አንድ ሊሆን ደግሞ አይችልም፡፡ ከሆነም ለመሰልቸት በጣም የቀረብን እንሆናለን፡፡ ስለዚህ አንቺም ከሁለቱ ፍቅረኞችሽ ጋር የነበረሽ ጊዜ ልክ እንደ ሁለት ምዕራፍ የአንድ መጽሐፍ አካል አድርገሽ ውሰጂው እናም ቀጣዩን የሕይወትሽን ምዕራፍ ሳታባክኚ በአግባቡ ኑሪ፡፡ በአንዱ መልካምነት ሁሉንም መልካም ማለት እንደማንችል ሁሉ ጥቂት ጥሩ ባልሆኑ ሰዎች ሁሉም ወንድ በጎነት የለበትም ማለት አንችልም፡፡ ይልቅስ የሳልሽውን መልካምነት ስትጠብቂ የበለጠው መልካም እንዳያመልጥሽ በጽሞና አስቢ፡፡ ከበውቀቱ ስዩም ግጥም ባነበብኩት እንሰነባበት፡፡ ማን ያግባሽ? አስተውላችሁ ግቡ!
አዳም የትላንቱ
የጥንት የጠዋቱ
ሳይለፋ ሳይታክት ተኝቶ ባደረ
ውኃ አጣጭ አቻውን ተጎኑ ተቸረ
ይብላኝ ለአሁኑ አዳም ለታካች ምስኪኑ
ምነው በተኛና በሸሸሁ ተጎኑ
ለምትል ሔዋኑ፡፡

                                                                   የጌታ ደረጀ

6. የመወያያው ርዕስ ዋና አሳብ ሊሆን የሚገባው ቅድሚያ ለሚሰጠው ቅድሚያ ስለመስጠት እንደሆነ ተረድቻለሁ፡፡ እንደዚህ ካሰብነው ደግሞ ከሁሉም በፊት ቀዳሚውን ስፍራ መያዝ ያለበት ፍቅር ነው፡፡ ፍቅርን ሀብትም አፍም አያመጡትም፡፡ ፍቅር ግን ሁሉንም ሊገዛ የሚችልበት ጉልበት አለው፡፡ ምንም እንኳን ሰው የእግዚአብሔርን ልጅ ከዙፋኑ የሚያወርድ ፍቅር ባይኖረውም ጌታን ለመስቀል ሞት ያበቃው ግን እርሱ ለእኛ ያለው ትልቅ ፍቅር እንደሆነ እናውቃለን፡፡ ስለዚህ ፍቅር እንኳን ምድራዊውን ሀብትና የአፍ ብልሃት ይቅርና የጥበብና የማስተዋል ደግሞም የማይጨረስ ባለጠግነት ባለቤት የሆነውን ጌታ መግዛት (ማሸነፍ) የቻለው ፍቅር ነው፡፡
          ማን ያግባሽ? ለሚለው ጥያቄ ምላሽ መሆን ያለበት “እውነተኛ ፍቅር ያለው” የሚለው ትልቅ መልስ እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ለአንድ ቤት መቆም የመሰረቱን ያህል ወሳኝ ነገር የለም፡፡ ፍቅር መሰረታችን በሚሆንበት የትኛውም ጥምረት ዘላቂነት መከተሉ የተረጋገጠ ነው፡፡ ስለዚህ ለጥያቄው ትክክለኛ መልስ መስጠት ካለብን ስለ ፍቅር መናገር ብቻ ሳይሆን መኖርም አለብን፡፡
                                                                     መዓዛ