Friday, April 20, 2012

የጠወለጉ መንገደኞች


        ከሕይወት ትርጉም አንዱ ሕይወት ጉዞ ናት የሚለው ነው፡፡ የምንኖርበትን ዓለም በማስተዋል ከተመለከትነው ሁሉም ነገር በጉዞ ላይ ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ ጥናት እያደረጉ እንደሆነ የሚታመንባቸው ምሁራንም በዚህ አሳብ መስማማታቸው ይነገራል፡፡ የእኛንም ሕይወት ስንቃኘው እውነታው ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ ትውልድ ይመጣል ትውልድ ይሄዳል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ግን ሰው ጉዞውን በአግባቡ እንዲያጠናቅቅ በቂ ዝግጅት አስፈላጊ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ጉዞው ፈታኝ ይሆንና ስንቅ ሊያልቅመዛል ሊከሰት መጠውለግ ሊመጣ ይችላል፡፡ በክርስትና ውስጥም የሚሆነው እንዲሁ ነው፡፡
         የእግዚአብሔርን ቃል እንሰማለን በሰማነው እናምናለን በዚህም በእውነት መሰረት ላይ እንተከላለን፡፡ ዕለት ዕለት ከዚሁ የሕይወት ቃል ጋር በሚኖረን የጠበቀ ሕብረት በመለምለም ራስ ወደ ሆነው ጌታ እናድጋለን፡፡ (ኤፌ. 4÷15) ሰው ከእግዚአብሔር አሳብና ከተሰጠው ተስፋ እየራቀከማመን እየዘገየ ሲሄድ መጠውለግ ይመጣል፡፡ ዓለም የምስራች የሰማው ሞት በሞት የተዋጠውመቃብር ባዶውን የታየው፣ የኃጢአት ዋጋ የተከፈለው፣ ጽድቃችን የታወጀው፣ የሰዱቃውያን እምነት ፉርሽ የሆነው፣ የክርስትናው ትልቅ ኃይል የተገለጠው ክርስቶስ ከሙታን መካከል ተለይቶ በመነሣቱ ነው፡፡ የክርስቶስ ትንሣኤ የእምነታችን መሰረትና ብርታት ነው፡፡ ኢየሱስ ከሙታን መካከል ተለይቶ ከተነሣ በኋላ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱ ከኢየሩሳሌም ወደ ኤማሁስ እየሄዱ ስለሆነው ነገር ሁሉ እርስ በእርሳቸው እየተነጋገሩና እየመረመሩ በመንገድ ሳሉ ጌታ በመካከላቸው እንደተገኘ ወንጌላዊው ሉቃስ ጽፎልን እናነባለን፡፡ (ሉቃ. 24÷13-35) ኤማሁስ በኢየሩሳሌም አቅራቢያ የሚገኝ ከተማ ሲሆን ዛሬ ከኢየሩሳሌም በስተሰሜን ርቀው የሚገኙ ሦስት ከተሞች ቀድሞ ኤማሁስ በሚል ስያሜ በአንድነት ይጠሩ እንደነበር ይታሰባል፡፡ የቀለዮጳም ቤት በዚያው እንደነበር ይታመናል፡፡
          ከሰው ብርቱ መሻት አንዱ የፊቱን ቀድሞ ማወቅ ነው፡፡ ነገዎቻችንን ከሚያበላሹብን ነገሮች ምክንያቶች መሐል ስለ ነገ ቀድመን የማወቅ ፍላጎታችን (መጨነቃችን) ተጠቃሽ ነው፡፡ ጌታ ግን “ነገ ለራሱ ይጨነቃልና ለነገ አትጨነቁ” (ማቴ. 6÷34)” ይላል፡፡ ስላመለከትነው ጉዳይ አፈፃጸም፣ ስለጠየቅነው መሻታችን ምላሽ፣ ስላሳየነው ትጋት ውጤት ቀድመን ማወቅ የሚያስችል አቅም ባይኖረንም እንገምታለን፡፡ አንዳንዴም ከግምታችን በመነሣት ወደ ተግባር እንሸጋገራለን፡፡ እግዚአብሔር ግን አይገምትም ደግሞም አይገመትም፡፡ እርሱ ነገዎቻችንን ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ከተናገረው የሚቀር፣ ከወሰነው የሚዛነፍ፣ ከልኬቱ የሚጎልና የሚተርፍ የለም፡፡ በተለይ በመከራ ውስጥ ስናልፍ መፈተናችን ስፋትና ርዝማኔው ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅ እንጓጓለን፡፡ እግዚአብሔር ግን ሁሉን ያውቃል፡፡
        ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሁላችንም ኃጢአት በመስቀል ላይ ከመሞቱ አስቀድሞ አሥራ ሁለቱንም ደቀ መዛሙርት ወደ እርሱ አቅርቦ፡-“እነሆ ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን ስለ ሰው ልጅም በነቢያት የተፃፈው ሁሉ ይፈጸማል፡፡ ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታልና ይዘብቱበትማል ያንገላቱትማል ይተፉበትማል ከገረፉትም በኋላ ይገድሉታል በሦስተኛውም ቀን ይነሣል (ሉቃ. 18÷34)” አላቸው፡፡ ወደ ፊት ሊሆን ያለውን አስቀድመው ማወቅ ለማይችሉት ደቀ መዛሙርት እንዲህ ያለው የኢየሱስ ንግግር ምንኛ ፍቅርን የተሞላ ነው? አዳምን በእርሱ መልክና (እውቀት፣ ጽድቅ፣ ቅድስና) ምሳሌ (ወኪል ገዥነት) ፈጥሮ በዔደን ገነት ካስቀመጠው በኋላ ከዚህ አትብላ ብቻ አላለውም፡፡ ይልቁንም መብላቱ (አለመታዘዝ) የሚያስከትለውንም ውጤት አብሮ ነገረው፡፡(ዘፍ. 2÷17) ወላጆች ብዙ ጊዜ ልጆቻቸውን እንዳያጠፉ እንጂ ጥፋታቸው የሚያስከትለውን ለመንገር ዝንጉዎች ናቸው፡፡ ትዕዛዛቸው እንጂ ቅጣታቸው በልብ የተሰወረ ነው፡፡
        ኢየሱስ ክርስቶስ ሊሆን ያለውን እስከ መጨረሻው ለወደዳቸው ተናገረ፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ግን ከነገራቸው ምንም አላስተዋሉም ከአፉ የወጣውም ቃል ተሰውሮባቸው ነበር፡፡ ይህንን አለመረዳታቸው ደግሞ ትንሣኤውን በጽናትና ከእምነት በሆነ ድፍረት እንዳይጠባበቁና ፈጥነው እንዳይቀበሉ መሰናክል ሆኖባቸዋል፡፡ ቀለዮጳ (Whom tradition identifies as the brother of Joseph, Mary's husband, and thus Jesus' uncle) እና ሉቃስ (The unnamed follower who, according to tradition, is the evangelist Luke himself)1 እኛ ግን እስራኤልን እንዲቤዥ ያለው እርሱ እንደሆነ ተስፋ አድርገን ነበርበማለት ተስፋ መቁረጣቸውን አንጸባርቀዋል፡፡ እግዚአብሔር በብርሃን የነገረንን በጨለማ፣ በፀጥታ ውስጥ የነገረንን በመከራ፣ በደስታ የነገረንን በሀዘን ውስጥ ከተጠራጠርነው ውጤቱ እየጠወለጉ መሄድ፣ ወደ ፊት (ኢየሩሳሌም) ሳይሆን ወደ ኋላ (ኤማሁስ) መመለስ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም እንደሚመጣ ወዳዘጋጀልንም ስፍራ እንደሚወስደን የነገረንን ተስፋ ምን ያህሎቻችን በናፍቆትና በእርግጠኝነት እንጠባበቀው ይሆን? እነ ቀለዮጳ ተስፋቸው ስለተናደ እርስ በእርሳቸው የሚነጋገሩትና የሚመረምሩት ነገር ከመጠውለግ አልታደጋቸውም፡፡
         ሰው በተስፋው ከዛለ ምንም የሚያቆመው ነገር የለም፡፡ በጴጥሮስ ፊት አውራሪነት ደቀ መዛሙርቱ ሰው በማጥመድ ፈንታ ዓሣ ወደ ማጥመድ ተግባራቸው የተመለሱት ጌታ የሰጠውን የተስፋ ቃል ባለማስተዋልና ባለመጽናታቸው ጠንቅ ነው፡፡ (ዮሐ. 21÷1-14) ነገር ግን ሌሊቱን ሙሉ በመጠውለግ (በድካምና በሀዘን)አሳልፈዋል፡፡ አዝኖ መንገድ ምን ያህል አድካሚ ነው? የኤማሁስ መንገደኞች ወደ መቃብሩ ማልደው ስለሄዱና የጌታን ሥጋ ስላጡ “ሕያው ነው” የሚል የመላእክትን ራዕይ እንዳዩ፣ ከወንድሞችም መሐል ወደ መቃብሩ ሄደው የእህቶችን ቃል እውነተኛነት እንዳረጋገጡ ቀርቦ ለጠየቃቸው ጌታ አስረድተውታል፡፡ ነገር ግን የተስፋውን መፈጸም እንዳይቀበሉ አለማስተዋል ጋርዶባቸዋል፡፡ አለማስተዋል ደግሞ ከማመን አዘግይቶአቸዋል፡፡ ከማመን መዘግየት ደግሞ አጠውልጓቸዋል (ሀዘንና ምሬት)፡፡
እናንተ የማታስተውሉ + ልባችሁ ከማመን የዘገየ = እየጠወለጋችሁ ስትሄዱ
          የእኛ ድካም እግዚአብሔርን ከመሥራት አለመከልከሉ ለልባችን የዘወትር መደመም ነው፡፡ የእነርሱ መጠውለግ ታላቁ መምህር ከሙሴና ከነቢያት ጀምሮ ከታላቁ መጽሐፍ ታላላቅ ቁም ነገሮችን እያብራራ ብዙ በረከቶችን ወደ ሰዎች ልብ እንዲያደርስና እንዲተረጉም ምክንያት ሆኗል፡፡ ተወዳጆች ሆይ የትኛውም ድካማችን እግዚአብሔርን እንዳይሠራ አያግደውም፡፡“እርሱም፡-ጸጋዬ ይበቃሃል ኃይሌ በድካም ይፈጸማልና አለኝ፡፡ እንግዲሕ የክርስቶስ ኃይል ያድርብኝ ዘንድ በብዙ ደስታ በድካሜ ልመካ እወዳለሁ” (2ቆሮ. 12÷9)፡፡ ጌታ መጠውለጋችንን አለመጸየፉ፣ በድካማችንም አለመራቁ ምንኛ ድንቅ ነው? የእርሱ መገኘት መጠውለጋችንን ያለመልመዋል፡፡ እርሱ በእግዚአብሔርና በሕዝቡ ሁሉ ፊት በሥራና በቃል ብርቱ የሆነ ጌታ ነው፡፡ ቀለዮጳና ሉቃስ ጌታ ጭንካር ባለፈበት እጁ እንጀራውን ባርኮና ቆርሶ ሲሰጣቸው ትንሣኤና ሕይወት የሆነውን መድኃኒት አስተዋሉት፡፡ በመንገድም ሳሉ ከአፉ በሚወጣው የጸጋ ቃል ልባቸው ይቃጠል (ይነካ) እንደነበር አስታወሱ፡፡ በመጠውለግ ወጥተው በመለምለም ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፡፡

ለመለምለም፡-
1. ማስተዋል፡- ሰውን ከእንስሳ ጋር የሚያተካክለው ጠባይ አለማስተዋል ነው፡፡ ማስተዋል ያለመቻል ውጤቱ ደግሞ ጥፋት ነው፡፡ (ሆሴ. 4÷6) በፊታችን የተገለጠውን እውነት ካልተረዳነው ለነፍሳችን ጥቅም የሚሆን ነገር አይኖርም፡፡ ማስተዋል ንባብ ሳይሆን ትርጓሜ ነው፡፡ ስለዚህ መንፈሳዊ ሙቀት ልምላሜ እንዳይለየን ወደ ጥልቁ ፈቀቅ ማለት አለብን፡፡
2. ለማመን መፍጠን፡- ለብዙዎቻችን ከመሥራት ይልቅ ማመን ቀላል ነው፡፡ ለትሩፋት መሰረቱ ግን ጠንካራ እምነት ነው፡፡ የሰናፍጭ ቅንጣት ታህል እምነት ተራራን ማሸሽ ከቻለች ይህ እንዲኖረን መትጋት እንዴት ቀላል ሊሆን ይችላል? በተረዳነው የእግዚአብሔር ነገር ለማመን ቀጠሮ አይያዝም፡፡ ብዙ የተደከመባቸው የከበረውንም እውነት የሰሙ ነገር ግን በልዩ ልዩ ምክንያት ከማመን የዘገዩ ዛሬ ያመነቱበት ሐቅ ነገ በዘላለም ሸንጎ ፊት የሚያቆምም እንደሆነ አለማስተዋላቸው ልብን ያቆዝማል፡፡ ከእግዚአብሔርን ቃል ይበልጥ እየተረዳን በመጣን ቁጥር ከቃሉ ባለቤት ጋር የበለጠ ሕብረት ለማድረግ ጉጉታችን ይጨምራል፡፡ እምነት ደግሞ ለዚህ መሰረቱ ነው፡፡ ከማመን መዘግየት እየሄዱ መጠውለግን ያስከትላል፡፡
3. በተስፋ መጽናት፡- ተስፋ ተስፋ ያደረግነውን ስናገኘው የሚጠናቀቅ ነው፡፡ ጌታ በተዘጋው ደጅ አልፎ በመካከል በመቆም “ሰላም ለእናንተ ይሁን” በማለት የትንሣኤውን ተስፋ ፈጽሟል (ዮሐ.20÷19)፡፡ እሰቀላለሁ ብሎ የተሰቀለልን፣ ልሙትላችሁ ብሎ የሞተልን፣ እነሣለሁ እንዳለ በዝግ መቃብር በኃይልና በሥልጣን የተነሣ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ በኑሮአችንም የሚሆነው እንዲሁ ነው፡፡ እግዚአብሔር ካለው የሚስቀርብን ከከለከለንም የሚያደርግልን የለም፡፡ ሰይጣን ከብርታት ወደ መዛል የሚያደርሰን የተሰጠንን የተስፋ ቃል እንድንጠራጠረው በማድረግ ነው፡፡ ተወዳጆች ሆይ ጌታ የታመነ ነውና በተስፋ ጽኑ፡፡ ማስተዋል ይብዛልን!!














       

       











          1. St. Athanasius Orthodox Academy, The Orthodox Study Bible New Testament and Psalms,1993, Page 201, USA.

No comments:

Post a Comment