Saturday, October 4, 2014

ብዙ ኃይል


                            መስከረም 24 ቀን 2007 የምሕረት ዓመት

‹‹በጻድቅ ሰው ቤት ብዙ ኃይል አለ፤ የኃጥእ ሰው መዝገብ ግን ሁከት ነው።›› 
(ምሳ. 15÷6)፡፡

         በሰው ልጆች አኗኗር ውስጥ ኃይል እጅግ አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ በኃይል እጦትና እጥረት ሰዎች ያለ መብራት በጨለማ ይሄዳሉ፤ ያልበሰለ በጥሬው ይበላሉ፡፡ ሰዎች በአቅም ማነስ ምክንያት ለተግባር ብዙ ይቸገራሉ፡፡ ኃይል የማይገባበት የኑሮ ክፍል የለም፡፡ ብዙ ነገሮች በብዙ ኃይል ጭምር የሚተገበሩ ናቸው፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ በመንፈሳዊው ዓለም ስላለው ከፍተኛ ኃይል ይነግረናል፡፡ ጠቢቡ በዘመኑ ያስተዋለውን ባካፈለበት በዚህ ክፍል ላይ ጻድቅ ቤት ውስጥ ብዙ ኃይል እንዳለ ሲነግረን፤ በኃጢአተኛ መዝገብ ውስጥ ግን ሁከት አለ ይለናል፡፡

        ጠቢቡ ጻድቅና ኃጥእን፤ ቤትና መዝገብን፤ ኃይልና ሁከትን እነዚህን ሁለት ነገሮች ከሰው አንፃር በንጽጽር አቅርቦልናል፡፡ ጽድቅ የሚለው አገላለጽ በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነትን ያገኘ እውነተኛ ማንነትን ሲያሳይ፤ ኃጥእ የሚለው አገላለጽ ደግሞ ከእግዚአብሔር ጋር ጸብ ውስጥ ያለና መንገድ የሳተ  ማንነትን ያመላክተናል፡፡ ቤት ልንኖርበትና ልንጠለልበት ያለንበትን ክልል ሲያሳይ፤ መዝገብ አንድ ሰው የሚሰበስበውን የሚያኖርበትን ስፍራ ያመለክተናል፡፡ ብዙ ኃይል የሚለው አገላለጽ ጽድቅ የሚለውን አዎንታዊ ቃል ተከትሎ የመጣ እንደ መሆኑ በዚያው መንገድ የምንመለከተው ብርቱ ነገር ሲሆን፤ ሁከት ደግሞ የደፈረሰ ያልጠራ፤ ሰላም የሌለበትን ነገር ያስረዳናል፡፡


       በቀደመው ኪዳን ‹‹ጽድቅና ኃጢአት›› መካከል ያለውን ልዩነት በግልጽ የምናስተውልበት፤ ውጤቱንም በግልጥ የምናይበት ሆኖ ከቀረበልን ነገር ዋናው ‹‹ኃይል›› ነው፡፡ ምድሪቱ ላይ ሰዎች በብዙ ነገራቸው ላይ ኃይልን አብዝተው ይሻሉ፡፡ አቅም ያጣንባቸው ነገሮች ሁሉ አንዳች ኃይልን ለመናፈቅ በቂ ምክንያት ነው፡፡ በዙሪያችን ብዙ የአቅም ማነሶችን እናስተውላለን፡፡ በጤና በኩል፤ በመብል በኩል፤ በሰላም በኩል፤ በደስታ በኩል ወገኖች በጥያቄ ተሞልተው ልብ እንላለን፡፡ ሰዎች መፍትሔን ይሻሉ፡፡ በሰለለና በዛለባቸው ነገር ላይም ምላሽን ይናፍቃሉ፡፡

        በምንኖርበት ዓለምና በሥጋ ለባሽ ላይ ሰዎች መደገፋቸው፤ የሚያልፈውንም ክንድ ማድረጋቸው ከሥጋት ወደ በለጠ ፍርሃት ውስጥ እየጨመራቸው ተጨንቀዋል፡፡ ዳሩ ግን በመዝሙር እንዲህ ተጽፎአል፤ ‹‹እግዚአብሔርን እንዲህ በሉት። ሥራህ ግሩም ነው፤ ኃይልህ ብዙ ሲሆን ጠላቶች ዋሹብህ።›› /መዝ. 65÷3/፡፡ ቀና ብልን የምናየው ሰማይ፤ ዝቅ ብለን የረገጥነው ምድር እንደ መጎናጸፊያ እስኪጠቀለል ድረስ ጠላት ዲያቢሎስና መልእክተኞቹ የሚዋሹበት ብዙ ኃይል አለ፡፡ እግዚአብሔር ብዙ ኃይል ነው፡፡ በሌላ ስፍራ መዝሙረኛው ‹‹ኃይሌም ዝማሬዬም እግዚአብሔር ነው፤ እርሱም መድኃኒት ሆነልኝ›› /መዝ 117፣14/ ይላል፡፡ ተወዳጆች ሆይ፤ የእልልታና የመድኃኒት ድምፅ በጻድቃን ድንኳን ነው፡፡

        እግዚአብሔር ያለን ብዙ ኃይል ነው፡፡ ምድሪቱ ላይ ብዙ ገንዘብ፤ ብዙ ሥልጣን፤ ብዙ እውቀት፤ ብዙ ጦር፤ ብዙ ብልሃት እንዳላቸው የምናስባቸው ሁሉ ከኃይለኛው አምላካችን፤ ከእግዚአብሔር ክንድ በታች ናቸው፡፡ ስለ አምላካችን ክንድ፡ ‹‹በክንድህ ብርታት እንደ ድንጋይ ዝም አሉ›› / ዘፀ 15፣16/ ተብሎ ተጽፍአል፡፡ ማን እንደ እግዚአብሔር?

       በጌታ የተወደዳችሁ፤ በውስጣችን ላለው ዝለት፤ በዙሪያችን ለምናስተውለው ተስፋ መቁረጥ ‹‹በጻድቅ ቤት›› የተባለውን ልብ በሉ፡፡ በክርስቶስ ክርስቲያን የተሰኛችሁ፤ አብርሃም በጸደቀበት በዚያው መንገድ ጽድቅን ያገኛችሁ፤ ያላችሁን አስተውሉ፡፡ በእናንተ ዘንድ ብዙ ኃይል አለ፡፡ ችግርን አልፎ፤ መከራን አልፎ፤ ሀዘንን አልፎ፤ መለያየትን አልፎ፤ በሽታን አልፎ የሚሠራ ኃይል፤ ሁሉን ያደርግ ዘንድ ቻይ የሆነ አሳቡም ይከለከል ዘንድ ከቶ የማይቻል የእስራኤል ቅዱስ እግዚአብሔር ስሙ ብሩክ ይሁን፡፡ ሰዎች በእጃቸው ሥራ፤ በአስተሳሰባቸው ብልሃት፤ በወገናቸው ትጋት በሚደረፉበት በዚህ የዘመን ማብቂያ እናንተ በእግዚአብሔር መተማመንን ልማድ አድርጉ፡፡

        ሰይጣን ዛሬም ይዋሻል፡፡ የዘመን ርዝማኔ ትምህርት እንደማይሆን ከሰይጣን በላይ አብነት የለም፡፡ እርሱ ውሸትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል /ዮሐ 8፣44/፡፡ በእግዚአብሔር ብዙ ኃይል ላይ ጠላት የማይቋረጥ ዘመቻን ከፍቷል፡፡ መጽናናትን ከእግዚአብሔር ስትሹ፤ ዕረፍትን ከሕያው አምላክ ስትናፍቁ፤ የጉዳዮቻችሁን መከናወን፤ የጉድለቶቻችሁን ሙላት ስትጠባበቁ ጠላት ዲያብሎስ ‹‹አይችልም››ን ወደ ጆሮአችሁ ይዞ ይመጣል፡፡ እርሱ ጌታ ባለ ብዙ ኃይል ነው፡፡ የጻድቅ ቤት በዚህ የተሞላ ነው፡፡ እውነተኛ ክርስቲያኖች የገዛ መንገዳቸው ያመጣውን ነገር ሳይሆን የእግዚአብሔርን ኃይልና ማዳን በኑሮአቸው የሚለማመዱ ናቸው፡፡

       እናንተ የምታምኑ ሆይ፤ በኃጥእ መዝገብ አትቅኑ፡፡ በዚህ የሠሩባት የማታ ማታ ሕይወትን ከስረዋልና፡፡ እግዚአብሔር የሁከት አምላክ አይደለም፡፡ የአመፀኞች መዝገብ ለዚህ ዓለም ስርዓትና መሻት እንደ ማጣፈጫ ቢሆንም፤ የክርስቶስ የሆኑቱ ከዚህ እድል ፈንታ የላቸውም፡፡ በእግዚአብሔር ጽድቅ ጥላ ስር የሆኑ ሁሉ ባለ ብዙ ኃይል ናቸው፡፡ እርሱም የዘላለም አምላክ እግዚአብሔር ነው፡፡ ይህንን ኃይል ከብዙ የኑሮአችን ክፍል ጋር አያይዘን ልናየው እንችላለን፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ክንድ በተለያዩ ሁኔታዎች ላይ በሉዓላዊነት ሲገለጥ እናስተውላለን፡፡ እኔ ግን ለዚህ ዝግጅት ማየት የፈለኩት ከማዳኑ ጋር የተያያዘውን ነው፡፡

       ‹‹በወንጌል አላፍርምና፤ አስቀድሞ ለአይሁዳዊ ደግሞም ለግሪክ ሰው፥ ለሚያምኑ ሁሉ የእግዚአብሔር ኃይል ለማዳን ነውና›› /ሮሜ 1፣16/፡፡ እግዚአብሔር ኃይሉን ለማዳን መጠቀሙ ድንቅ ነው፡፡ በዙሪያችን ሰዎች በአቅማቸው ያላቸውን ነገር ለጥፋትና ለሌሎች ውድቀት ሲያውሉት ማየት ልብን ያሳዝናል፡፡ ለነገሩ ትንሽ ያላት እንቅልፍ የላትም አይደል ነገሩ፡፡ ከእግዚአብሔር አንፃር የዚህ ዓለም ቀዳሚ ባለጠጋም የተረቱ ሰለባ ነው፡፡ እግዚአብሔር ይችላል፡፡ ተስፋችሁን ሊቀጥል፤ ከገባችሁበት መከራ ሊያወጣ ይችላል፡፡ የመረረባችሁን ሊያጣፍጠው፤ የጠመመባችሁን ሊያቀናው እርሱ ይችላል፡፡ ከሞትና ከሲዖል ኃይል የሚያድን ኃይል እርሱ ጌታ ነው፡፡ ሰዎች ባላቸው ብዙ ነገር ሊወጡ የማችሉት ብርቱ ጠላት ዲያቢሎስ የዚህ ዓለም ገዥ በሆነበት ሁኔታ፤ እግዚአብሔር ብቻ ያድናል፡፡

        ስለማናፍርበት ነገር ማውራት እንዴት ደስ ያሰኛል፡፡ ዓለሙ በብዙ የሚያሳፍር ወሬና የቅሌት ኑሮ የተጨናነቀ ነው፡፡ ወንጌላችን በዚህ የጨለማ ድቅድቅ መሐል ብርሃን፤ አልጫ በሆነው ነገር ላይ ጨው ነው፡፡ እናንተ እውነተኞች ሆይ፤ ከፀሐይ በታች የዚህ ዓለም ስርዓት ትኩረትና ከፍታ የሚሰጠው ነገር እናንተ ቤት የለ ይሆናል፡፡ ዳሩ ግን ልብ በሉ፤ ሰዎች ሁሉ የሚድኑበት፤ መቃብርን አልፈው ሕያው የሚሆኑበት፤ ከከንቱ ኑሮ የሚገላገሉበት፤ ከሞተ ሥራ ሕሊናቸው የሚነፃበት ኃይል በእናንተ ውስጥ አለ፡፡ ይህንን ብልሃት አያገኘውም፡፡ ሀብትና ንብረት አይገዛውም፡፡ ሥልጣንና ጉልበት አስሮ አያመጣውም፡፡ የልብ እምነት ግን ከዚህ ብዙ ኃይል ጋር ያስተሳስራል፡፡


       ወዳጆቼ፤ ይህንን ዓለም በምን ታሸንፉታላችሁ፡፡ ትብታብና ሰንሰለቱ፤ ጭፍራና ሠራዊቱ ርኩስ መንፈስ የሆነ፤ ሊሰርቅና ሊያርድ ሊያጠፋም የሚተጋውን ክፉ እንዴት ትሻገሩታላችሁ? እንዲህ ካለው ባላጋራ መዳን በሌላ በማንም የለም /ሐዋ 4፣12/፡፡ ‹‹እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁድ ማሰናከያ ለአሕዛብም ሞኝነት ነው፥ ለተጠሩት ግን፥ አይሁድ ቢሆኑ የግሪክ ሰዎችም ቢሆኑ፥ የእግዚአብሔር ኃይልና የእግዚአብሔር ጥበብ የሆነው ክርስቶስ ነው።›› (1 ቆሮ. 1÷23-24)፡፡

4 comments:

  1. ወዳጆቼ፤ ይህንን ዓለም በምን ታሸንፉታላችሁ? good.

    ReplyDelete
  2. Hayil yeegziabiher new madanim yenigusu

    ReplyDelete
  3. በኃጥእ መዝገብ አትቅኑ

    ReplyDelete
  4. Bizu hayile. Wow des yilal tebareku

    ReplyDelete