Thursday, August 22, 2013

እሸትና ቆንጆ (ካለፈው የቀጠለ)


                                
                               ሐሙስ ነሐሌ 16/ 2005 የምሕረት ዓመት

“ውበትህ ከሰው ልጆች ይልቅ ያምራል ሞገስ በከንፈሮችህ ፈሰሰ ስለዚህ እግዚአብሔር ለዘላለም ባረከህ” (መዝ. 44÷2)::

         ኑሮአችንን ትዝብት ላይ ስንጥለው “ሁሉ አያምልጠኝ” ይሆንብናል፡፡ ከዚህም የተነሣ እንዳያልፉን ዋጋ የምንከፍልባቸው ነገሮች ሁሉ ሕይወታችንን የሚቀራመቱና እድሜያችንን የሚሻሙ ኃይሎች ይሆናሉ፡፡ ሰው የሚኖረው ለተያዘበት ለዚያ ነገር ነውና፡፡ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ያሉ ወላጆች ልጃቸው ሲያድግ ምን ሊሆን እንደሚችል አሳሰባቸው፡፡ ስለዚህም ከወዲሁ የልጁን የነገ ማንነት ለማወቅና የልጃቸውን ቀጣይ ሕይወት ለማስተካከል ፈተና ሊፈትኑት ወሰኑ፡፡ በአንድ ጠረጴዛ ላይ የተወሰኑ ብሮች፣ ውድ የሆነ የመጠጥ አይነት፣ የሙዚቃና ዳንስ ጥበብ የሚያስተምሩ መጻሐፎች እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ ደረደሩ፡፡ በመቀጠልም ታዳጊ ልጃቸው ወደ ክፍሉ እንዲገባ በማድረግ በፊቱ ከሚመለከታቸው የተለያዩ ነገሮች አንዱን እንዲመርጥ በመጠባበቅ በስውር ይከታተሉት ጀመር፡፡

         እንደ ቤተሰቡ አስተሳሰብ ብሩን ከመረጠ የቢዝነስ ሰው፣ መጠጡን ከወሰደ ጠጪና አባካኝ፣ የሙዚቃና ዳንስ መጽሐፉን ከመረጠ ዘፋኝ፣ መጽሐፍ ቅዱሱን ካነሣ ደግሞ የእምነት መምህር እንደሚሆን ተማምነው ነበር፡፡ ልጅ ወደ እነዚህ ነገሮች ተጠግቶ ምርጫውን በጉጉት ተሰውረው የሚከታተሉትን እናትና አባት በሚያስደንቅ ሁኔታ ቀስ እያለ ከሁሉም አንሥቶ ቀኝና ግራ እጁን በመሙላት ቤቱን ለቀቀ፡፡ ከዚህ በኋላ ወላጅ አባት ወደ ሚስቱ ጠጋ ብሎ “የእግዚአብሔር ያለህ! ልጃችን ያለ ጥርጥር ለሁሉም ይሆናል”አላት፡፡    

         ለሰው ሕይወት አደገኛው ነገር “ምንም መሆን አልችልም” እና “ሁሉንም መሆን እችላለሁ” የሚሉ ሁለት አሳቦች ናቸው፡፡ ሰው ወደዚህ ምድር የመጣው ከነመምረጥ አቅሙ ጋር ከሆነ፤ አልያም ነፃ ፈቃድ አለን ካልን የምንኖረው እየመረጥን ነው፡፡ ከሁሉም ማንሣት ልክ እንደማይሆን ሁሉ ምንም አለማንሣትም እንዲሁ ነው፡፡ ልከኛ ኑሮ የቱን ይዞ የቱን መተው እንዳለብን ማወቅ ነው፡፡ ወደ ሠርግ ቤት ስንሄድ በአንድ ጠረጴዛ ላይ ልዩ ልዩ የምግብ ዓይነቶች ተደርድረው እንመለከታለን፡፡ አስተውለነው ከሆነ እንደዚህ ያለው አቀራረብ አንድ መልእክት አለው፡፡ እርሱም “መርጠህ አንሣ” የሚል ነው፡፡ ነገር ግን ሰዎች ከሁሉም አንሥተው ሰሃናቸው ተጨንቆ ወደ መቀመጫቸው ይሄዳሉ፡፡ እንደነዚህ ያሉቱ ልዩ ልዩ የሆነውን እንደ አንድ ወጥ ለመጨለፍ ጥረት የሚያደርጉ ናቸው፡፡ ታዲያ እንደዚህ ያለው መስገብገብ ዘግየት ብሎ ከበዪነት ወደ ተመልካችነት፣ ከተጠቃሚነት ወደ አባካኝነት ያሻግራል፡፡

         ሕይወትም ልክ እንደ ሠርግ ቤቱ ግብዣ ናት፡፡ ከሁሉም ልናነሣ አግባብ አይሆንም፡፡ የምንመርጠውን የምናስተውል ልከኛ መራጮች መሆን ያስፈልገናል፡፡ ወደዚህ የተመጠነ ኑሮ ለመምጣት ደግሞ “ሁሉ አያምልጠኝ” ከሚል እብሪተኝነት መላቀቅ አለብን፡፡ አንዳንድ ሰዎች እነርሱ ያልወጠወጡት ወጥ እንደሚጎረና፣ እነርሱ ያልተገኙበት እቅድ እንደማይሳካ፣ እነርሱን ያላካተተ ተግባር እንደሚከሽፍ ያምናሉ፡፡ የሰዎችን ድርሻና የመሥራት አቅምም ቶሎ አይቀበሉም፡፡ ከዚህ የተነሣ ራሳቸውን ሁሉም ቦታ የመፈለግ አባዜ ይጠናወታቸዋል /ልክ እንደ ጆከር/፡፡

         ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክታቱ ውስጥ አጉልቶ የሚያንጸባርቀው ነገር ቢኖር “አንድ አሳብ” የሚለውን ነው፡፡ እርሱ ለብዙ አሳብ የኖረ አልነበረም፡፡ ለአንዱ ለዚያ የክርስቶስ አሳብ ግን የኖረ ብቻ ሳይሆን የሞተም ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ስለ ጸጋ ስጦታ በተናገረበት ክፍል ላይ “የጸጋም ስጦታ ልዩ ልዩ ነው መንፈስ ግን አንድ ነው” ይላል (1 ቆሮ. 12÷4)፡፡ ጸጋ ለቤተ ክርስቲያን (ምእመናን) መታነጽ አንዱ መንፈስ ቅዱስ ለሰው የሚሰጠው ስጦታ ነው፡፡ ያመኑቱ እንዲጸኑ፤ ያላመኑቱ ወደ ማመን እንዲደርሱ የምንተጋበት ማትረፊያ ነው፡፡ ልዩ ልዩ የሚለው አገላለጽ አንዱ የሚያከናውነውን ሌላው እንደማያደርገው የሚያመላክት አሳብን የያዘ ነው፡፡ ልክ የአካል ክፍሎቻችን የየራሳቸው ውበትና ተግባር እንዳላቸው ሁሉ ማለት ነው፡፡

         የአካል ክፍሎቻችንን ስናስተውላቸው ለዘመናት የተሰጡበትን ዓላማ ያለ መሰልቸት ሲፈጽሙ እናያቸዋለን፡፡ አፍንጫ ማሽተት መሮት መስማት የጀመረበት፣ ዓይን ማየት ታከተኝ ብሎ መናገር የፈለገበት፣ እጅም መጨበጥ ሰለቸኝ ብሎ ሊረግጥ የዳዳበት ዘመን የለም፡፡ ለተሰጣቸው ለአንዱ ተግባር ተሰጥተው ይኖራሉ፡፡ ለሁሉም መሆን አንችልም! የምንሆንለት ግን አለ፡፡ ሁሉም ሰው የበለጠ ውጤታማ ሊሆንበትና በተሻለ ሁኔታ ሊያከናውነው በሚችለው ተግባር ላይ መሰማራቱ የሚመጣውን ውጤት ማኅበራዊ ያደርገዋል፡፡ ጆሮ ሎቲ ማንጠልጠል ቢፈልግ ዓይን ይመርጣል፣ እግር ይሄዳል፣ አፍ ግዢው ላይ ይግባባል፣ እጅ ለማስጌጥ ይራዳል . . . በመጨረሻ ግን አካል ይሞገሳል፡፡

         ኑሮአችን ውስጥ ከእያንዳንዱ ትጋት ጀርባ ያለው መሻት በልጦ መታየት አልያም አንሶ አለመታየት ስለሆነ “አይታለፍም” የሚለው መፈክር ሁልጊዜ ያስተጋባል፡፡ እንዲህ ያለው አባባል በተግባራዊ ሁኔታ ለእሸትና ቆንጆ ብቻ የሚውል አይደለም፡፡ ሰዎች እንደ ዋዛ የማያልፏቸው ብዙ ከንቱ ነገሮች አሉ፡፡ ይህ ዓለም ያስጌጣቸው፣ ከፍታ የሰጣቸው፣ የሰዎች ሽሚያ የከበባቸው ነገሮች እንዳያልፉን የምንናጥባቸው ናቸው፡፡ የዚህ ዓለም አንዱ ማጃጃያ ውበት ነው፡፡ ተረታችን እንኳ “ሲያዩት ያላማረ . . . ” የሚል ነው፡፡ የዕብራውያን ፀሐፊ “ኢየሱስ ክርስቶስን ተመልከቱ” (ዕብ. 3÷1) በማለት ሰው ሁሉ “አይለፈኝ” የሚለውን ውበት ያመላክተናል፡፡ መቼም ይህ ሁሉ ወገን ቀን ከሌሊት የሚፍጨረጨረው ለምንድን ነው? ብለን ስንጠይቅ ከጌታ አንፃር ስንዳኘው “ባነሰው ለመርካት” የሚል ምላሽ እናገኛለን፡፡

         ጌታ የዓይናችን ማረፊያ፣ በልተነው ብርዱን ማለፊያ እሸት ነው፡፡ ዝናብ እየዘነበ፣ ብርዱም እየበረታ፣ ሰማዩም እየጠቆረ ሲመጣ ጥላቸውን ይዘው እሸት የሚጠብሱ ወገኖች ጌታን እንድናስበው በብዙ የሚረዱን ናቸው፡፡ ስቃይና ፈተና በላያችን ሲወርድ፣ የመከራ ኃይልና ብርታቱ ሙቀታችንን ሲያቀዘቅዘው፣ የሁኔታ መጥቆርና የቀን መክፋፋት ሲከበን አዎ! ሁሉን የምንረሳበት፣ ውስጣዊ ሙቀታችን የሚመለስበት ሲመሽ ታርዶ የተጠበሰው መሥዋዕት ኢየሱስ ነው! እርሱ ውበታችን የሆነበትን መንገድ ስንመረምር “መልክና ውበት የለውም፤ ባየነውም ጊዜ እንወድደው ዘንድ ደም ግባት የለውም፡፡ የተናቀ ከሰውም የተጠላ የሕማም ሰው ደዌንም የሚያውቅ ነው” (ኢሳ. 53÷2-3) ተብሎለት ነው፡፡ ደመ ግቡን ማንም ይወድደዋል፡፡ ጌታ ግን እንወድደው ዘንድ ደም ግባት አልባ ሆኗል፡፡ እኛ ወደ ክብር የመጣንበት መንገድ የእርሱ መናቅና መጠላት፣ ሕማም መልበስና ደዌን ማወቅ ነውና፡፡

         እሸት በእሳት ተጠብሶ፣ እንደ ወተት ያለ ውበቱ ጠቁሮ፣ ተንገላቶና ተሰቃይቶ ወደ ሰው ለመብል እንዲደርስ ለእግዚአብሔር እንደ ተወደደ መሥዋዕት ራሱን ያቀረበ፣ ሥጋዬ ብሎ ብሉኝ፣ ደሜ ብሎ ጠጡኝ ያለ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እስራኤል በአብ የትእዛዝ ቃል በብሉይ ኪዳን ተጠብሶ የበሉት ፋሲካ፣ የግብጽን ጨለማ ያመለጡበት የብርሃን ዓምድ፣ የሞት መልአክ እንዲያልፋቸው የሆነበት ደም፣ ነውር የሌለበት ጠቦት፣ ሲመሽ ያረዱት በግ ኢየሱስ ነው (ዘጸ. 12)፡፡ በእርግጥም ክርስትና የማናልፈው እሸትና ቆንጆ አለው፡፡ ነቢዩ በመዝሙሩ “ውበትህ ከሰው ልጆች ይልቅ ያምራል ሞገስ በከንፈሮችህ ፈሰሰ ስለዚህ እግዚአብሔር ለዘላለም ባረከህ” በማለት ስለ ክርስቶስ ውበት የተናገረበትን ክፍል ስናስብ ውበት ላጣነው ለእኛ እውነተኛው ውበታችን ማን እንደ ሆነ ያስረዳናል፡፡ ነቢዩ ኤርሚያስ ደግሞ እግዚአብሔር “በውኑ ቆንጆ ጌጥዋን ወይስ ሙሽራ ዝርግፍ ጌጥዋን ትረሳለችን? ሕዝቤ ግን የማይቈጠር ወራት ረስቶኛል” (ኤር. 2÷32) ያለበትን አሳብ ያቀርብልናል፡፡          


         ጌታ እንኳን ከኑሮው ከከንፈሩም ቃል ሞገስ ይፈስስ ነበር፡፡ ቆንጆ ያሰኘን ጌጥ፣ ለሙሽራይቱ ቤተክርስቲያን ዝርግፍ ጌጥ ክርስቶስ ነው፡፡ በእርሱ ሕይወት አለ፡፡ ሕይወትም ትበዛለች፡፡ ይህ እንዲበዛልን የመጣው ጌታ አይለፈን፡፡ ሰው የሰው ነገር አልፎት ከተቆጨ ሕይወት የሆነ መድኃኒትን ቸል ማለት እንዴት አያስቆጭም? ለሚያልፈው ተሽቀዳድሞ ለሚዘልቀው መቦዘኑ ምነው አይሰማው? ከበቆሎ እሸት ወደ ቆንጆ፤ ከቆንጆም ወደ እሸት ስትገላበጡ ለቤዛ መሥዋዕት የሆነልንን እሸት፣ ደም ግባት አልባ ሆኖ የወደደንን ሕይወት ጌታ እንዳታልፉት ልብ አድርጉ፡፡ ክረምቱን በእርሱ አሳብ እንድንሻገር ጸጋ ይብዛልን!! 

Thursday, August 8, 2013

እሸትና ቆንጆ


                                ሐሙስ ነሐሌ 2/ 2005 የምሕረት ዓመት



“እሸትና ቆንጆ አይለፍ ብላችሁ፤ ይኸው ወንዱ አለቀ ሴቶቹ ቆማችሁ፡፡”

       ክረምቱን ተከትሎ መሬትን የሚያረሰርሰው ዝናብ በመካከላችን ምን ትሠራለህ? በሚል ይመስላል እኔንም ያቀዘቅዘኛል፡፡ ከአገልግሎት ወጥቼ ታክሲ የምጠብቅበት ቦታ ላይ ከዚህ ዶፍ የሚሸሽገኝን አንዳች ነገር በመናፈቅ የሚርገፈገፍ ሰውነቴን፣ የሚንቀጠቀጥ ከንፈሬን፣ ኩምትር ጭምድድ ያለ ፊትና መዳፌን እያሻሸሁ ቆሜ አለሁ፡፡ ታዲያ አንድ ታክሲ አጠገቤ መጥቶ ድቅን አለ፡፡ በር ተከፍቶ ወራጆች ሲወርዱ አንዲት ልጅ ዓይኔ እየተመለከተው ያለውን፣ ጎኗ የነበረ የማውቀውን፣ አንድ ወጣት እየተሳደበች ወረደች፡፡ እርሱም ከውስጥ ሆኖ መልስ እየሰጠ ስለ ነበር ሴቲቱ እንደመሄድ እያለች ተመልሳ ትሳደባለች፡፡ እኔም ወደ ታክሲው ውስጥ ለመግባት እየሞከርኩ “በቃ ተዪው . . . ለመሆኑ ምን አድርጎሽ ነው?” አልኳት፡፡ እርሷም “እንኳን ጠየከኝ!” በሚል ስሜት “ጠይቆኝ ነዋ!” ብላ መንቀር መንቀር እያለች መንገዱን አቋርጣ ወደ መንገዷ ሄደች፡፡ በታክሲው ውስጥ የቀረው ሕዝብ ሰምቶ ኖሮ አንድ ጊዜ ሳቃቸውን ለቀቁት፡፡ የማውቀውም ልጅ ተሸማቀቀ፡፡ ታዲያ ወደ ውስጥ ገብቼ ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝን ነገር ተናገረ፡፡ እርሱም፡- “ምን እባክህ እሸትና ቆንጆ አይታለፍም ብዬ እርሜን የክረምቱን ብርድ መርሻ ብላከፍ ስድቤን ጠጣሁ” ብሎ ፈገግ አለ፡፡

      በማኅበረሰባችን መካከል ከሚነገሩ ልማዳዊ ብሒሎች መካከል “እሸትና ቆንጆ አይታለፍም” የሚለው በክረምቱ ወቅት ተዘውታሪ አባባል ነው፡፡ መቼም የተረትና ወግ፣ የስነ ቃልና የአበው ብሒል ባለ ጠጎች መሆናችን እሙን ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ተዘውታሪ አባባሎችና ተረቶች በሰብእና አቀራረጽ ላይ ሊኖራቸው የሚችለውን አዎንታዊና አሉታዊ ተጽእኖ ማስተዋል መቻል ተገቢ ነው፡፡ ምክንያቱም እንደነዚህ ያሉት በቀላሉ ወደ ሰው ጆሮ ብቻ ሳይሆን ወደ ሰዎች ልብ ዘልቀው የመግባት፣ ኮርኩሮ ስሜትን የመንካት አቅማቸው ከፍተኛ ስለሆነ ነው፡፡ ድሮ ድሮ በገጠር አካባቢ (ምናልባት አሁንም ጭምር) ሁኔታው በሚጠይቀው መንገድ የተለያዩ አባባሎችን መናገር ልማድ ነበር፡፡ ለምሳሌ ሥራ ላይ ሲሆኑ የበለጠ የሚያተጋ፣ የታመቀ ኃይልን ተግባር ላይ ለማዋል የሚያበረታ አባባል ይነገራል፡፡ በሐዘን ላይ ደግሞ የሚያጽናና፣ ያለፈውን ትቶ ለፊቱ የሚያሳስብ፣ ለሞተው ቆርጦ ለቆመው የሚያዝን ስነ ቃል ይመዘዛል፡፡ በተለይ ቅኔያዊ የሆኑ ንግግሮች መሞካሻም መዳሚያም በመሆናቸው ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ፡፡