ሐሙስ ነሐሌ 2/ 2005 የምሕረት ዓመት
“እሸትና ቆንጆ አይለፍ ብላችሁ፤
ይኸው ወንዱ አለቀ ሴቶቹ ቆማችሁ፡፡”
ክረምቱን ተከትሎ መሬትን የሚያረሰርሰው ዝናብ በመካከላችን ምን ትሠራለህ? በሚል ይመስላል እኔንም ያቀዘቅዘኛል፡፡ ከአገልግሎት
ወጥቼ ታክሲ የምጠብቅበት ቦታ ላይ ከዚህ ዶፍ የሚሸሽገኝን አንዳች ነገር በመናፈቅ የሚርገፈገፍ ሰውነቴን፣ የሚንቀጠቀጥ ከንፈሬን፣
ኩምትር ጭምድድ ያለ ፊትና መዳፌን እያሻሸሁ ቆሜ አለሁ፡፡ ታዲያ አንድ ታክሲ አጠገቤ መጥቶ ድቅን አለ፡፡ በር ተከፍቶ ወራጆች
ሲወርዱ አንዲት ልጅ ዓይኔ እየተመለከተው ያለውን፣ ጎኗ የነበረ የማውቀውን፣ አንድ ወጣት እየተሳደበች ወረደች፡፡ እርሱም ከውስጥ
ሆኖ መልስ እየሰጠ ስለ ነበር ሴቲቱ እንደመሄድ እያለች ተመልሳ ትሳደባለች፡፡ እኔም ወደ ታክሲው ውስጥ ለመግባት እየሞከርኩ “በቃ
ተዪው . . . ለመሆኑ ምን አድርጎሽ ነው?” አልኳት፡፡ እርሷም “እንኳን ጠየከኝ!” በሚል ስሜት “ጠይቆኝ ነዋ!” ብላ መንቀር
መንቀር እያለች መንገዱን አቋርጣ ወደ መንገዷ ሄደች፡፡ በታክሲው ውስጥ የቀረው ሕዝብ ሰምቶ ኖሮ አንድ ጊዜ ሳቃቸውን ለቀቁት፡፡
የማውቀውም ልጅ ተሸማቀቀ፡፡ ታዲያ ወደ ውስጥ ገብቼ ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝን ነገር ተናገረ፡፡ እርሱም፡-
“ምን እባክህ እሸትና ቆንጆ አይታለፍም ብዬ እርሜን የክረምቱን ብርድ መርሻ ብላከፍ ስድቤን ጠጣሁ” ብሎ ፈገግ አለ፡፡
በማኅበረሰባችን መካከል ከሚነገሩ ልማዳዊ ብሒሎች መካከል “እሸትና ቆንጆ አይታለፍም” የሚለው በክረምቱ ወቅት ተዘውታሪ
አባባል ነው፡፡ መቼም የተረትና ወግ፣ የስነ ቃልና የአበው ብሒል ባለ ጠጎች መሆናችን እሙን ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ተዘውታሪ
አባባሎችና ተረቶች በሰብእና አቀራረጽ ላይ ሊኖራቸው የሚችለውን አዎንታዊና አሉታዊ ተጽእኖ ማስተዋል መቻል ተገቢ ነው፡፡ ምክንያቱም
እንደነዚህ ያሉት በቀላሉ ወደ ሰው ጆሮ ብቻ ሳይሆን ወደ ሰዎች ልብ ዘልቀው የመግባት፣ ኮርኩሮ ስሜትን የመንካት አቅማቸው ከፍተኛ
ስለሆነ ነው፡፡ ድሮ ድሮ በገጠር አካባቢ (ምናልባት አሁንም ጭምር) ሁኔታው በሚጠይቀው መንገድ የተለያዩ አባባሎችን መናገር ልማድ
ነበር፡፡ ለምሳሌ ሥራ ላይ ሲሆኑ የበለጠ የሚያተጋ፣ የታመቀ ኃይልን ተግባር ላይ ለማዋል የሚያበረታ አባባል ይነገራል፡፡ በሐዘን
ላይ ደግሞ የሚያጽናና፣ ያለፈውን ትቶ ለፊቱ የሚያሳስብ፣ ለሞተው ቆርጦ ለቆመው የሚያዝን ስነ ቃል ይመዘዛል፡፡ በተለይ ቅኔያዊ
የሆኑ ንግግሮች መሞካሻም መዳሚያም በመሆናቸው ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ፡፡
መልካም ንግግር ጸብን ለማብረድ፣ በጎውን ለመከወን፣ የባሰውን የተሻለ ለማድረግ፣ ክፉውን በበጎ ለመለወጥ ትልቅ ኃይል
ነው፡፡ እውነትን መሰረት ያደረጉ አባባሎችም ማኅበራዊ ግንኙነትን ቅመም ሆነው የማጣፈጥ አቅም አላቸው፡፡ ዳሩ ግን እውነትን የሚያራክሱ፣
ለሐሰት ዘብ የቆሙ፣ የሰውን ንቃተ ሕሊና የሚያዳክሙ፣ ለነውር የሚያደፋፍሩ አባባሎች ሲሰሙ ምንም የሚመስሉ፤ ሲስተዋሉ ግን ክፉ
ተጽእኖአቸው የፈጠጠ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ከዚህም መካከል ቆንጆ ሁሉ የማይታለፍበት ከእሸት ጋር በንጽጽር የሚነገረው አባባል
አንዱ ነው፡፡ እንግዲህ ከዚህ ተነሥቶ ነው ገጣሚው፡- “እሸትና ቆንጆ አይለፍ ብላችሁ፤ ይኸው ወንዱ አለቀ ሴቶቹ ቆማችሁ፡፡” ያለው፡፡
ነውርን የሚያደፋፍሩ፣ ስነ ምግባር አልባ ኑሮን የሚያበረታቱ፣ ለራስ ያለን ግምት የሚያኮስሱ ተረትና አባባሎችን አጢነን ከሆነ በርካታ
ናቸው፡፡ ከማስታውሰው መካከል “እስከ ትመጽእ መርዓትከ ተክዝ በዓማትከ” የሚለው አባባል ሁልጊዜ ይገርመኛል፡፡ ሰውየው ሚስቱ ጋር
እስከሚደርስ ወይም እስከትመጣ ድረስ በአማቱ እየተደሰተ (ጠይሞ) እንዲቆይ የሚያደፋፍር ምክር አዘል ማጽናኛ እንደ ሆነ እንደ እኔ
የገረማቸው አባት አስረድተውኛል፡፡
ዛሬ ዛሬ በዚህ ትውልድ መካከል መነሻቸውና ምንጫቸው በውል የማይታወቁ ነገር ግን ሰው እየተቀባበለ ጥቅም ላይ የሚያውላቸው
አባባሎች በርከት እያሉ መጥተዋል፡፡ አብዛኞቹ አባባሎች ደግሞ ፆታን ማዕከል አድርገው ብሽቀትና መተቻቸት፣ ማራከስና ማጣመድ ላይ
የተመሰረቱ መሆናቸው መገረማችንን ያጦዘዋል፡፡ በተለይ በሴቶችና በወንዶች መካከል የሚኖረውን የፍቅር ግንኙነት ተመርኩዘው የሚወረወሩ
አባባሎች ሰውን የመግዛትና የመቆጣጠር አቅማቸው ያየለ እንደ መሆኑ ከቃሉ አልፎ ተግባሩን ማየት የተለመደ ነው፡፡ በእኛ አገር ማኅበረሰቡ ጥቅም ላይ ያዋላቸው
አባባሎች በዕለት ከዕለት የሰዎች ኑሮና ግንኙነት ላይ ሊኖራቸው የሚችለውን ተጽእኖ በቀጥታ የተጠና ጥናት ለማግኘት ያደረኩት ሙከራ
ባይሳካም፤ ትዝብቴንና የነጮቹን ሰነድ አገላብጬ ያገኘሁት ነገር ግን የተጽእኖውን ከባድነት ያመላክታል፡፡ በወጣቱ ላይ ለሚታየው
የሞራል ውድቀትና የስነ ምግባር ብልሽት በእውነት ሚዛን ያልተመዘኑ አባባሎቻችን እየታየ ላለው ውድቀት አስተዋጽዖ አድርገዋል፡፡
ልብ ብለን ከሆነ ለአንዳንድ መጥፎ ድርጊታቸው ብዙ ሰዎች ተረት መተረትና አባባል መናገር ይቀናቸዋል፡፡ ሊበቀሉ ካሰቡ “የወጋ ቢረሳ
የተወጋ አይረሳም” ይላሉ /ውድ አንባብያን በዚህ ብሎግ ላይ “የተወጋ ሲረሳ” የሚለውን ጽሑፍ እንድታነቡት እንጋብዛለን/፡፡ ደግሞ
በሰዎች መልካም አለመሆን ላይ አንዳች ክፉ ነገር ሲደርስ “ድሮም ክፉ ነበርክ ክፉ አዘዘብህ፤ እንደ ገና ዳቦ እሳት ነደደብህ”
ይሉታል፡፡ ይህም በሰው ውድቀት የሰውን መርካት ያስረዳናል፡፡
ወደ ቆንጆና እሸት ስንመለስ በዚህ ክረምት በየመንገዱ ዳር ቁጭ ብለው የበቆሎ እሸት ሲጠብሱ አልያም ሲቀቅሉ የምናስተውላቸውን
ወገኖች ወደ አእምሮአችን ያመጣልናል፡፡ አንዳንዶቹማ ልጅ ታቅፈው አልያም ጎናቸው አስቀምጠው ስለሚሠሩ የአዛኝ ሰው አንጀት ይበላሉ፡፡
ብርድና ዝናቡን ተቋቁመው፣ ዓይናቸው ከአላፊና አግዳሚው ጋር እየተንከራተተ እንደ ቀናቸው ሸጠው ወደ ቤት ይመለሳሉ፡፡ ገዢም ጠጋ
ብሎ “እሸትና ቆንጆ” እያለ የበቆሎ እሸቱን ከመንገድ ዳር ገዝቶ እቤት ወደምትቆየው የሰው እሸት ይዞ ይሄዳል፡፡ ሌላው ደግሞ የበቆሎውንም
የሰውንም እሸት መንገድ ዳር ገዝቶ ይሄዳል፡፡ ይህ ሕይወቱን በዓላማ ሳይሆን በአጋጣሚ የሚመራን ሰው ሊያሳየን ይችላል፡፡ ለራዕዩ
ሳይሆን ላየው የሚሸነፍ፣ በደረሰበት ወድቆ የሚተኛ፣ ለነገ የማያስብ የቅርብ አዳሪ! እውነተኛ ነዋሪ ከደግና ከክፉ የሚመርጥ ብቻ
አይደለም፡፡ ጥሩን ከጥሩም ይመርጣል፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ምንነት ስናጠና ከምንረዳቸው ነገሮች አንዱ ከበጎም መካከል የሚመረጥ እንዳለ
ነው፡፡ ለምሳሌ፡- “በእስያም ቃሉን እንዳይናገሩ መንፈስ ቅዱስ ስለ ከለከላቸው በፍርግያና በገላትያ አገር አለፉ” (የሐዋ.
16÷6) የሚል ቃል እናነባለን፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል መመስከርና ማስተማር መቼም ቢሆን ክፉ ተግባር ሆኖ አያውቅም፡፡ ነገር ግን
መንፈስ ቅዱስ እንዳያስተምሩ ከለከላቸው የሚል እናነባለን፡፡ የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደ ሆነ ሲገባን የምንታዘዘው ክፉውን በመተው
ብቻ አይደለም፡፡ ጥሩውንም በመተው እንጂ፡፡ በዚህ ምድር ላይ ብናደርጋቸው መልካም የሆኑ ተግባራት አሉ፡፡ ዳሩ ግን እግዚአብሔር
በተሻለ ልንሠራውና ለእርሱ ክብርን ልናመጣበት በምንችለው እንድንተጋ ይፈልጋል፡፡ የጸጋ ስጦታ ልዩ ልዩ የሆነበትም መንገድ ይኸው
ነው፡፡ ሁሉ ዓይን ቢሆን የእጅን ማን ይሠራዋል? ሁሉ ጆሮ ቢሆንስ የአፍን ማን ይናገራል? እግዚአብሔር በመልካም ውሳኔዎቻችን ላይ
ጌታ ነው፡፡ እንድናልፈው ያዘዘንን ማለፍ መታዘዝ ነው፡፡ ቆንጆም ይታለፋል እሸቱን ግን ብሉ!
- ይቀጥላል -
ሁሉ ዓይን ቢሆን የእጅን ማን ይሠራዋል? ሁሉ ጆሮ ቢሆንስ የአፍን ማን ይናገራል? እግዚአብሔር በመልካም ውሳኔዎቻችን ላይ ጌታ ነው፡፡ Let God be with all of us!
ReplyDeleteገዢም ጠጋ ብሎ “እሸትና ቆንጆ” እያለ የበቆሎ እሸቱን ከመንገድ ዳር ገዝቶ እቤት ወደምትቆየው የሰው እሸት ይዞ ይሄዳል፡፡ ሌላው ደግሞ የበቆሎውንም የሰውንም እሸት መንገድ ዳር ገዝቶ ይሄዳል፡፡ ይህ ሕይወቱን በዓላማ ሳይሆን በአጋጣሚ የሚመራን ሰው ሊያሳየን ይችላል፡፡ ለራዕዩ ሳይሆን ላየው የሚሸነፍ፣ በደረሰበት ወድቆ የሚተኛ፣ ለነገ የማያስብ የቅርብ አዳሪ! እውነተኛ ነዋሪ ከደግና ከክፉ የሚመርጥ ብቻ አይደለም፡፡ ጥሩን ከጥሩም ይመርጣል፡፡......zis is really fantastic advise which help us to choose the best from the good. be blessed!
ReplyDeleteየእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደ ሆነ ሲገባን የምንታዘዘው ክፉውን በመተው ብቻ አይደለም፡፡ ጥሩውንም በመተው እንጂ
ReplyDelete