Friday, December 25, 2015

መልእክት ኀበ ፊልሞና፡፡(2)

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!


አርብ ታኅሣሥ 15 ቀን 2008 የምሕረት ዓመት

(መልእክት ወደ ፊልሞና)

‹‹እምጳውሎስ ሙቁሐ ለኢየሱስ ክርስቶስ፡ (ኤፌ. 3፡1)››!

           መጽሐፍ ቅዱሳችሁን ከመክፈታችሁ፤ እንዲሁም የመልእክቱን ክፍል ከመግለጣችሁ አስቀድሞ አብ፤ ወልድ፤ መንፈስ ቅዱስ፤ አንድ አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ማስተዋልን እንዲሰጣችሁ፤ እንዲሁም ከመልእክቱ ልትረዱ የሚገባችሁን ሁሉ መቀበል እንድትችሉ በቅዱስ መንፈሱ በኩል እንዲረዳችሁ በመንፈስና በእውነት በመገዛት ጸልዩ፡፡ ተወዳጆች ሆይ፤ ከዚህ በኋላ መልእክቱን ቃል በቃል በጥንቃቄና በእርጋታ አንብቡት፤ ይህንንም በመደጋገም አድርጉት፡፡

የመልእክቱ ዳሰሳ፡-

o   ‹‹ተቀብለህ ለዘላለም እንድትይዘው . . ›› /ቁ. 15/ የመልእክቱ ዋና አሳብ ሲሆን፤ ለመልእክቱ ‹‹የዘላለም መያያዝ›› ብለን ርእስ ልንሰጠው እንችላለን፡፡ ሐዋርያው ለፊልሞና ‹‹እንደ ባልንጀራ ብትቆጥረኝ እንደ እኔ አድርገህ ተቀበለው›› /ቁ. 17/ በማለት ይጠይቃል፡፡

o   መልእክቱ ከሐዋርያው ከጳውሎስ መልእክታት በጣም አጭሩ መልእክት ሲሆን፤ ሐዋርያው በእስር ቤት ሆኖ ከጻፋቸው ከፊልጵስዩስ፤ ከቆላስይስ እና ከኤፌሶን መልእክታት መካከል አንዱ ሲሆን፤ ይዘቱ ግን የተለየ ነው፡፡


o   ሐዋርያው ከጻፋቸው መልእክታት መካከል ለሦስት ሰዎች (ግለሰቦች) የጻፋቸው አራት መልእክታት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እነዚህም፡- አንደኛ ጢሞቴዎስ፤ ሁለተኛ ጢሞቴዎስ፤ ቲቶ እና አሁን እያጠናነው ያለነው የፊልሞና መልእክት ናቸው፡፡ መልእክቱን ወደራሳችሁ አቅርባችሁ፤ ለእናንተ እንደተላከ በመቁጠር ብታነቡት በእጅጉ ትጠቀማላችሁ፡፡

o   በመልእክቱ አሳብ ውስጥ ቁልፍ የሆኑ (ትኩረት የሚሰጣቸው) ቃላትን እናገኛለን፡፡ እነዚህም፡- ክብር፤ ቸርነት፤ ጥንቃቄ፤ ወዳጅ፤ ፍቅር፤ ትህትና፤ ጥበብ፤ ግልጽ የሆነ ንጽህና (ቅድስና)፤ ከዚህ በመነሣት የመልእክቱን ይዘት ‹‹ትህትናን የተላበሰ መልእክት›› እንደሆነ እናስተውላለን፡፡ ተወዳጆች ሆይ፤ በዚህ መልእክት ውስጥ ችግር ፈቺ የሆነውን ክርስትና ለመመልከት ሞክሩ፡፡

o   መልእክቱ ባለ ሀብት የነበረው የቆላስይስ ክርስቲያን እና የሐዋርያው የጳውሎስ ቅርብ ወዳጅ የፊልሞና ባሪያ አናሲሞስ (ጠቃሚ፤ ዋጋ ያለው ማለት ነው) ከጌታው ወደ ሮም ኮብልሎ መጥፋቱ፤ በኋላም በክርስቶስ ክርስቲያን ሆኖ ወደ አሳዳሪው መመለሱን ማእከል ያደረገ ‹‹የእርቅ›› ደብዳቤ ነው፡፡ ተወዳጆች ሆይ፤ ጥሩ የማይባለውን አጋጣሚ ጌታ አንድን ነፍስ ወደ ክብር ለማምጣት እንዴት ለበጎ እንደ ተጠቀመበት አስተውሉ፡፡

o   መልእክቱ የ‹‹እርስ በርስ መዋደድን›› /ዮሐ. 13፡34/ አዲስ ትእዛዝ መሰረት ያደረገው የክርስትና ኑሮ የፍቅር ገጽታ ምን እንደሚመስል በተግባር የሚያስረዳ ሲሆን፤ በዓለም ላይ የሰዎች ባርነት (ስቃይን ጭምር የተሞላ) ተስፋፍቶ በነበረበት የሐዋርያት ዘመን ባሪያን አስመልክቶ የተጻፈ ብቸኛው መልእክት ነው፡፡ በዚህም ክርስትና የባርነትን ችግር ለመፍታት ያለውን የላቀ መንገድ የሚያሳይ ጽሑፍ ሆኖ ጥቅም ላይ ውሏል፡፡

o   ሐዋርያው በቆላስይስ መልእክቱ ላይ ‹‹ከእናንተ ከሆነውና ከታመነው ከተወደደውም ወንድም ከአናሲሞስ . . ›› /ቆላ. 4፡9/ ብሎ እንደጻፈው፤ ፊልሞና በቆላስይስ የሚኖር ባሪያ አሳዳሪና ቤተክርስቲያኒቱም (የምእመናን ስብስብ) በቤቱ የነበረች እንደሆነ፤ እንዲሁም የፊልሞና መልእክት እና የቆላስይስ መልእክት በተመሳሳይ ጊዜ የተጻፉና የተላኩ መሆኑን እንረዳለን፡፡ በዚህ ክፍል መሰረት መልእክቱ የተላከው ‹‹በአናሲሞስና በቲኪቆስ›› እጅ ነው፡፡    


 የመልእክቱ አከፋፈል፡-

·       መንፈሳዊ ሰላምታ (ከቁ. 1 – 3)
·       የፊልሞና እምነትና ፍቅር እውቅና (ከቁ. 4 – 7)
·       አናሲሞስን ስለመቀበል የተሰጠ ትኩረት (ከቁ. 8 – 21)
·       የማጠቃለያ ስንብት (ከቁ. 22 – 25)

‹‹የተወደደና አብሮ የሚሠራ››

         የክርስቶስ ኢየሱስ እስር የሆነው ጳውሎስ በእምነት ወንድሙ ከሆነ ከጢሞቴዎስ ጋር፤ የመልእክቱን ተቀባይ ፊልሞናን የገለጸበት ደስ የሚያሰኝ አገላለጽ ነው፡፡ ሐዋርያው በሌሎች መልእክቶቹ (ለምሳሌ፡- አንደኛ ቆሮንቶስ) ተቀባዮቹ ጋር ችግር እንዳለ እንኳ እያወቀ መልእክቶቹን የሚጽፍበት መነሻ በአዎንታዊ ነገሮች የተሞላ ነበር፡፡ ፊልሞና ቀጣዮቹን የጽሑፍ ክፍሎች እንዴት ባለ መንፈሳዊ ሙቀት ሊያነባቸው እንደሚችል ልብ በሉ፡፡ ስለ ችግሮች ከማውራታችን አስቀድሞ ለማመስገን የሚሆነንን ብዙ ምክንያት ማየቱ የግንኙነት እጅግ መልካሙ ጎን ነው፡፡

          እጅግ ከሚወደን ሰው የሚመጣ ምስጋና ቀርቶ ወቀሳም ለጥቅማችን ይሆንልናል፡፡ እኛ ለሌሎች የምንናገርበት፤ ሌሎችም የእኛን የሚሰሙበት ልብ የጤናማ ግንኙነት ወሳኝ ቦታ ነው፡፡ ‹‹እኛ ግን የክርስቶስ ልብ አለን›› /1 ቆሮ. 2፡16/ ተብሎ እንደተጻፈ፤ በዚህ ልብ ሆነን የምንናገረውም የምንሰማውም ነገር መቀባበልን ያመጣል፡፡ ሐዋርያው ‹‹ . . ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም . . . ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና›› /ገላ. 3፡28/ እንዳለ፤ መልእክቱ አንድነትን የሚያጎላ አሳብ የያዘ ነው፡፡

         ‹‹ለአገልግሎቱ ሾሞኝ ታማኝ አድርጎ ስለ ቆጠረኝ ኃይል የሰጠኝን ክርስቶስ ኢየሱስን ጌታችንን አመሰግናለሁ . . ›› /1 ጢሞ. 1፡12/ የሚለው ሐዋርያ፤ ‹‹በጌታ እስር›› /ኤፌ. 4፡1/ መሆኑን ደግሞ ይገልጻል፡፡ አገልግሎት ልዩ ልዩ፤ ጌታ ግን አንድ ስለሆነ (1 ቆሮ. 12፡5)፤ ልዩ ልዩ በሆነ አገልግሎት የሚገለገለው ጌታ ክርስቶስ ነው /ቆላ. 3፡24/፡፡ ሐዋርያው ስለ ወንጌል አገልግሎት ወንጌልን ለማስፋት (ለማዳረስ) በሮም እስር ቤት እንዳለ ለፊልሞና ያስታውሰዋል፡፡ በእርግጥም እስራቱ ስለ ክርስቶስ ብቻ ነበር (ፊል. 1፡13)፡፡

         ሐዋርያው ፊልሞና የተወደደና አብሮ ሠራተኛ እንደሆነ እውቅና ሲሰጥ እንመለከታለን፡፡ ይህንን ሥራ በተመለከተ ለፊልጵስዩስ በተጻፈው መልእክት ላይ ‹‹ወንጌልን በመስበክ አብራችሁ ስለ ሠራችሁ›› /ፊል. 1፡5/ የሚል አገላለጽ ስለምናነብ፤ ፊልሞናም በወንጌል ‹‹መሰበክ›› አገልግሎት ጠንካራ ሠራተኛ እንደሆነ ማሰብ እንችላለን፡፡ በትንሽዋ እስያ ዛሬ ቱርክ ተብላ በምትጠራው ከተማ ውስጥ የነበረችው የቆላስይስ ቤተክርስቲያን ‹‹በቤቱ የነበረች ጉባኤ›› እንደመሆኗ፤ በእስር ላይ ከነበረው ጳውሎስና በዚያም አብሮት ከነበረ የመንፈስ ወንድሙ ጢሞቴዎስ ጋር ፊልሞናም አብሮ ሠራተኛ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡

         በመልእክቱ ጸሐፊና በሌሎች አገልጋይ ወንድሞች፤ እንዲሁም በቤቱ ባለችው ቤተክርስቲያን (ማኅበረ ምእመናን) ዘንድ የተወደደ የሆነው ፊልሞና መወደዱን የሚጨምር ጥያቄ በሐዋርያው መልእክት ውስጥ ይቀርብለታል፡፡ አናሲሞስን ‹‹እንደ ተወደደ ወንድም ተቀብለህ ለዘላለም ያዘው›› የሚል ብርቱ መልእክት ለፊልሞና፡፡ በዚህም ከባሪያና ከአሳዳሪ የሚሻል (የሚበልጥ) ግንኙነትን እንመለከታለን፡፡

          በአናሲሞስና በፊልሞና መካከል የነበረው ግንኙነት የባሪያና የአሳዳሪ እንደመሆኑ ‹‹ከዘላለም ባነሰ መሰረት›› ላይ የነበረ ግንኙነት እንደነበር እናውቃለን፡፡ ዳሩ ግን ‹‹በእምነት በኩል ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁና . . ›› /ገላ. 3፡26/ ተብሎ እንደተጻፈ፤ አሁን የሚኖራቸው ግንኙነት በክርስቶስ ኢየሱስ በሆነው የዘላለም ሕይወት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ሁለቱም ወንድማማች የአንዱ እግዚአብሔር ልጆች ናቸው፡፡

         በሥጋ በመወለድ በጊዜያዊ ትስስር የሚዛመዱን እንዳሉ፤ እንዲሁ መንፈስ ከሆነው ከእግዚአብሔር በመወለዳችን የማይጠፋ የዘላለም ትስስር አለን (ዮሐ. 1፡13)፡፡ በሥጋ የሆነው ቤተሰብ ሰንሰለት በሞት ሲበጠስ (ላይቀጥል ሲቋረጥ)፤ ብንሞት እንኳ ሕያዋን በምንሆንበት (ዮሐ. 11፡25) ትንሣኤና ሕይወት በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን የሚሻገር ኅብረት አለን፡፡ በአሁኑ ዓለም ከዘላለም መቀባበል ያነሱ ብዙ ግንኙነቶች ቢኖሩን፤ ሁሉም ሊያልፉ የተቀጠሩ ናቸው (1 ቆሮ. 7፡31)፡፡

         እጅግ የተወደዳችሁ ወዳጆቼ፤ ጊዜ ወስዳችሁ ስለ ግንኙነቶቻችሁ አስቡ፡፡ በክርስቶስ ክርስቲያን ከሆንበት እውነት የሚበልጥ ምን መጠጋጋት ሊኖር ይችላል? የዛሬ ጥናታችንን በአንድ አሳብ እንፈጽም፤ በቤታችሁ ሠራተኞችን ቀጥራችሁ የምታሠሩ ክርስቲያን ቤተሰቦቼ ሁላችሁ፤ ስለ ዘላለም ሕይወት ታስቡላቸዋላችሁን? የለፉበትን እንኳን ለመስጠት የሚፈተኑ፤ ከሰው ቆጥረው እንደ ሰው (እንደ ክርስቲያን ቀርቶ) እንኳ የማያዩአቸውን፤ አሠሪዎቻቸው በዋናው ምግብ ጠግበው እየታመሙ፤ በትራፊው የሚቀኑባቸውን ልናስተውል እንችላለን፡፡ እስቲ! ለዘላለማቸውም (ስለ ወንጌል) አስቡላቸው፡፡ እናስተውል!!     
                              ‹‹ . . . ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ፤›› /ቆላ. 4፡3/!

ማሳሰቢያ መልእክቱን በማጥናት የምትከታተሉ መጽሐፍ ቅዱስ እና የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት (በመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር የተዘጋጀ) እንዲኖራችሁ እመክራለሁ፡፡ ለቀጣዩ ክፍሉን በደንብ አንብቡ!

No comments:

Post a Comment