Sunday, September 11, 2016

ከይሳኮር የሚበልጥ


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን


እሑድ መስከረም 1 ቀን 2009 የጸጋ ዓመት
      ቀጣዩን (የሚሆነውን) የማወቅ ጉጉት በማንኛውም ሰው ውስጥ ያለ የጋራ ፍላጎት እንደ ሆነ ይስተዋላል፡፡ ምንም እንኳ ‹‹ነገ ለራሱ ይጨነቃልና፤ ለነገ አትጨነቁ፤ ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል›› (ማቴ. 6፡34) ተብሎ በቅዱሱ መጽሐፋችን የተጻፈ ቢሆንም፤ ምድር ብርቱ ሠልፍ አላትና በክርስትናችንም እንዲህ የምናውቀውን ቃል መታዘዝ ጭንቅ ይሆናል፡፡ ደግሞ ቀጣዩ ምን ይሆን?፤ ኖሬ ምን ይገጥመኛል? የሚሉ ጥያቄዎች፤ ‹‹አይመጣምን ትተሽ ይመጣልን አስቢ›› አይነት አባባሎች . . ወዘተ፤ ሰው በቀጣዩ ላይ ያለው ሥጋት ከፍተኛ መሆኑን ያሳብቃሉ፡፡
      በመጽሐፍ ቅዱሳችን የመጀመሪያ ክፍል ‹‹ያዕቆብ ልጆቹን ጠርቶ እንዲህ አለ፡- በኋለኛው ዘመን የሚያገኛችሁን እንድነግራችሁ ተሰብሰቡ፡፡›› (ዘፍ. 49፡1-28) ተብሎ ተጽፎአል፡፡ የብዙዎች አባት አብርሃም፤ ሳቅ የሆነውን ይስሐቅን ወለደ፤ እርሱ ደግሞ አሰናካይ የሆነውን ያዕቆብን ወለደ፡፡ ያዕቆብ ከእርሱ ከራሱ በሆነው ብልጣ ብልጥነት ብዙ ዘመኑን የደከመ ቢሆንም በጎልማስነቱ ጊዜ ከአምላክ ጋር ታገለ፤ አልቅሶም ለመነው (ሆሴ. 11፡4)፡፡ እግዚአብሔር ያዕቆብን ስሙን ለእግዚአብሔር የሚዋጋ ሲል እስራኤል አለው፡፡ ያዕቆብ ከእግዚአብሔር ጋር ትክክለኛ ግንኙነት ወደ ማድረግ የመጣው ከስሙ መቀየር ጋር ተከትሎ ሆነ፡፡ ይህም በቀጣይ ኑሮው ላይ ግልጽ ለውጦችን አምጥቶአል፡፡

      መድኃኒታችን ኢየሱስ ለአገልግሎቱ ሾሞ፤ ታማኝ አድርጎ የቆጠረውን ሐዋርያ ጳውሎስ (1 ጢሞ. 1፡12) አስቀድሞ የነበረውን ስም በመቀየር (ሐዋ. 9)፤ ታናሽ የሚለውን የስም ፍቺ ይዞ ለጌታ ምርጥ ዕቃው ሆኗል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ስምን ከተግባራዊ ባህርይ ጋርም ያያይዘዋል፡፡ በእርግጥም ዙሪያችንን አጥርተን ብናይ ስም በባህርይ ላይ ያለውን ተጽእኖ በግልጽ ልናይ እንችላለን፡፡ ሰው ዘመኑን በብዛት የሚሰማው የራሱን ስም ነውና፡፡ ወላጆች ለልጆች የስም ስያሜ ሲያወጡ፤ ልጆችም በወጣላቸው ስያሜ ሲጠሩ ማስተዋልና ለዚያ መጠንቀቅ ተገቢ ይሆናል፡፡


      ‹‹በኋለኛው ዘመን›› የሚለው ወደኋላ ያለፈውን ሳይሆን የፊቱን የሚያመለክት ጊዜ ጠቋሚ አገላለጽ ነው፡፡ በተመሳሳይ መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያው ጴጥሮስ በኩል ‹‹በኋለኞች ዘመናት .  . ›› (1 ጢሞ. 4፡1) ሲል እናነባለን፡፡ ይህም ጸሐፊው ከነበረበት ዘመን የወደፊቱን የሚያሳይ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ያዕቆብ ወደ እርሱ ለተሰበሰቡት ለአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ልጆቹ፤ የሚሆነውን ነገራቸው፤ ባረካቸውም፡፡ ስለ መጀመሪያ ልጁ ሮቤል ሲናገር ‹‹ . . እንደ ውኃ የምትዋልል ነህ አለቅነት ለአንተ አይሁን . . ›› ይለዋል፡፡ በሥነ አመራርና በአስተዳደር ክህሎት ትምህርቶች ውስጥ ከመጽሐፍ ቅዱስ የሚመዘዘው አንዱ ማጣቀሻ በዚህ ስፍራ ላይ ያነበብነው ነው፡፡ ‹‹እንደ ውኃ መዋለል›› መወሰን፤ መጨከን አለመቻልን ያመለክታል፡፡ ሰው ከግል ማንነቱ ጀምሮ፤ ቤተሰብና አገር እስከ ማስተዳደር የሚያልፍባቸው ውሳኔውን የሚጠይቁ ግልጽ የኑሮ መስመሮች ውስጥ ያልፋል፡፡ አግባብ የሆኑ ውሳኔዎችን ያለ መወሰን አንዱና ትልቁ ምክንያት ደግሞ እንደ ውኃ የሚዋልለው የሰው ባህርይ ነው፡፡
      ተወዳጆች ሆይ፤ ውሳኔ ካልተሰጠባቸው ወረቀቶች ጀምሮ የውሳኔ ያለህ! የሚሉ ግንኙነቶች ምን ያህል ሊሆኑ እንደሚችሉ ጥቂት ለማሰብ ሞክሩ፡፡ ከአንዱ እጅ ወደ ሌላው እጅ ሲገላበጡ አፈር የመሰሉ ማመልከቻዎች፤ ከአንዱ አእምሮ ወደ ሌላው አእምሮ ሲመላለሱ የተረሱ ጉዳዮች፤ እንደ ውኃ በሚዋልሉ አለቅነት በማይገባቸው ሰዎች ጭምር የተበደሉ አይደሉምን?፤ የእውነት ዳኛ እግዚአብሔር (መዝ. 7፡11) ውሳኔዎቻችሁን በሚጠይቁ ነገሮቻችሁ ሁሉ ላይ መከናወንን ይስጣችሁ፡፡ ያዕቆብ እንዲሁ ለሌሎቹ ልጆቹ እየተናገረ በቁጥር 14 ይሳኮር ጋር ይደርሳል፡፡ ‹‹ይሳኮር አጥንተ ብርቱ አህያ ነው፤ በበጎች ጉረኖም መካከል ያርፋል፡፡ ዕረፍትም መልካም መሆኗን አየ፤ ምድሪቱም የለማች መሆንዋን፤ ትከሻውን ለመሸከም ዝቅ አደረገ፤ በሥራም ገበሬ ሆነ፡፡›› ይለዋል፡፡ ብርቱ፤ በበጎች መካከል ያረፈ፤ መልካም የሆነውን የተመለከተ፤ ለሸክም ዝቅ ያለ ገበሬ፤ ይሳኮር፡፡ ኦ! ይህ ምንኛ ደስ የሚል ማንነት ነው፡፡
      ስለ ይሳኮር ልጆች ደግሞ ‹‹እስራኤልም የሚገባውን ያደርግ ዘንድ ዘመኑን የሚያውቁ ጥበበኞች ሰዎች የይሳኮር ልጆች አለቆች ሁለት መቶ ነበሩ፤ ወንድሞቻቸውም ሁሉ ይታዘዙአቸው ነበር፡፡›› (1 ዜና. 12፡32) እንደተባለ፤ በዚህ ክፍል ደግሞ የሚገባውን ስለ ማድረግ፤ ዘመንን ከማወቅና ከጥበብ ጋር ይሳኮር የተነሣበትን ሁኔታ እናያለን፡፡ ከሰው ቀጣዩን የማወቅ ፍላጎት ጋር በተያያዘ አብሮ የሚታሰበው ጉዳይ ሊሆንና ሊመጣ ላለው ነገር በቂ የሆነ ኃይልና ጥበብ የማግኘት ጉዳይ ነው፡፡ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ትክክለኛ መፍትሔ ይዞ የመገኘት ጉዳይ ለማንም የምንጊዜም አሳብ ነው፡፡
     ከመጀመሪያው ንባብ ኃይልና ትህትና፤ ከሁለተኛው ንባብ ደግሞ እውቀትና ጥበብን በዋናነት ልንመለከት እንሞክራለን፡፡ ይሳኮር ‹‹አጥንተ ብርቱ አህያ›› ተብሏል፡፡ አህያ ስድብ ሳይሆን የአህያ ስሟ ነው፡፡ እርግጫውን  ትተን ስሙን ከብርታት ጋር ማያያዝ ጥቅሱ የሚለውን በትክክል ለመረዳት አስፈላጊ ነው፡፡ ይሳኮር ተግባሩን እንደሚገባ ስለ ማድረግ፤ ወንድሞቹም እንዲሁ እንዲመላለሱ ብርቱና ኃያል ነው፡፡ ደግሞ ከኃይል ጋር ትከሻውን ለመሸከም ዝቅ ያደረገ ነበር፡፡ ኃይል በተሳሳተ መንገድ በተተረጎመባት የአሁኗ ዓለም፤ ኃይልን ከትህትና ጋር አስተባብሮ የሚገባውን በእግዚአብሔር ፊት ማድረግ መቻል በማንኛውም ዘመን የየዕለት ሁኔታዎች ውስጥ በድል የሚያሻግር ነው፡፡  
     ወደ አዲስ ኪዳን አሳብ ልውሰዳችሁ፤ ‹‹በዚህም ሥርዓት በሚመላለሱ ሁሉ ላይ በእግዚአብሔር እስራኤልም ላይ ሰላምና ምሕረት ይሁን›› (ገላ. 6፡16) ተብለናል፡፡ አሜን! ከቀደመው ኪዳን ክፍሎች ጋር ተጨማሪ የአሳብ ድልድይ ለመፍጠር ደግሞ ‹‹ዘመኑን እየዋጃችሁ በውጭ ባሉቱ ዘንድ በጥበብ ተመላለሱ›› (ቆላ. 4፡5) የሚለውን ምክር ልብ እንላለን፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ጸጋ ከሕግ፤ ከመጠን ይልቅ እንደሚበልጥ በሞገተበት መልእክቱ እውነተኞች ክርስቲያኖችን ‹‹የእግዚአብሔር እስራኤል›› ሲል ይጠራቸዋል፡፡ ነገሩ ‹‹በግልጥ አይሁዳዊ የሆነ አይሁዳዊ አይደለምና በግልጥ በሥጋ የሚደረግ መገረዝም መገረዝ አይደለምና . . ›› (ሮሜ 2፡28) እንደተባለው ነው፡፡ 
      በመጣው ዘመን እንዴት እንድንመላለስና የሚገባውን እንድናደርግ ለእግዚአብሔር እስራኤል ወንድሞቹ የሚታዘዙት ይሳኮር ወዴት አለ?ብለን መጠየቅ እንችላለን፡፡ መውጣት መግባታችንን በኃይልና በትህትና፤ ደግሞ በእውቀትና በጥበብ ይሆን ዘንድ በመካከላችን እንዲህ ያለ ማን አለ?ሰው ለራሱ እንኳ የሚበቃ ምክር ባጣበት በጽድቅ የሚመክር፤ መጨካከን የኑሮ ከፍታ በሆነበት የፍቅር ልብ የማያልቅበት፤ በዚህ ዓለም ጥበብ እሽቅድድም ብልጫ ሰው በተጠመደበት የሚበልጥ ጥበበኛ፤ የእውቀት ብዛት የተግባር ማነስ በሚታይበት በቃል በኑሮ የበረታ፤ ኃይል ለማንሣት ሳይሆን ለመጣል በሆነበት የሚያድን ኃይል፤ ትህትና እንደ መበለጥና መሞኘት በሚቆጠርበት ሁሉን የሚሸከም ማን ይሆን?
 
     ተመሳሳይ ነገሮች መሐል ልዩ የሆነ አንድ እንደሚፈልግ ሰው ኃጢአት የሰውን ታሪክ ምንም ልዩ የማይገኝበት ተመሳሳይ አድርጎታል (ሮሜ 3፡23)፡፡ ዳሩ ግን ‹‹ . . በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ›› (ዕብ. 2፡14 እና 15) ተብሎ እንደተጻፈ፤ ሰው የሌለው ሁሉ ያለው ክርስቶስ ከኃጢአት በቀር እኛን መስሎ ወደዚህ ዓለም መጥቶአል (1 ጢሞ. 1፡15)፡፡ ወንድሞች ብሎ ሊጠራን ያላፈረው (ዕብ. 2፡13)፤ ፍጹም ሰውም የሆነው ወልድ ከይሳኮር የሚበልጥልን ዘመኑን የምናውቅበትና የምንመላለስበት ጥበብ፤ ትሁትና ኃይል ነው፡፡ ስለ ትህትና ቢሆን የባሪያን መልክ የያዘ፣ ራሱን ባዶ ያደረገ፣ ራሱን ያዋረደና ለመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ነው (ፊል. 2፡7)፤ ደግሞ ስለ ኃይል ቢሆን እርሱ የኃይል ሁሉ ምንጭ ነው፡፡ ‹‹ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ›› (ፊል. 4፡13) ተብሎ እንደተጻፈ፤ በእያንዳንዱ ዘመን በመዋረድ ቢሆን በመብዛት፤ በመጥገብ ቢሆን በመራብ፤ በመብዛት ቢሆን በመጉደል ክርስቶስ ሁሉን የሚያስችል በቂ ኃይላችን ነው፡፡
      ‹‹ . . የተሰወረ የጥበብና የእውቀት መዝገብ ሁሉ በእርሱ ነውና፡፡›› (ቆላ. 2፡3) ክርስቶስ የዘመኑን መልክ የምንለይበት እውቀት፤ ለዚያም የሚሆን የኑሮ ጥበብ ነው፡፡ በዚህ ዓመት ደግሞ ምን ይሆን? በክርስቶስ ክርስቲያን ለሆኑ ጭንቀት ሊሆን አግባብ አይደለም፡፡ ለማዳን የሆነው የእግዚአብሔር ኃይል፤ ልጁ ኢየሱስ አለ (ሮሜ 1፡16፤ 1 ቆሮ. 1፡24)፤ የዋህ እና በልቡ ትሑት የሆነው የነፍሳችን ዕረፍት ከእኛ ጋር ነው (ማቴ. 11፡29)፡፡ ሰዎችን ሁሉ የሚያውቅ፤ ስለ ማንም ምስክር የማያሻው የእውቀት ጥግ ማወቃችን ነው (ዮሐ. 2፡23)፡፡ የዚህች ዓለም ጥበብ በእግዚአብሔር ፊት ሞኝነት እንደ ሆነ ግልጥ ያደረገልን ክርስቶስ ጥበባችን ነው (1 ቆሮ. 3፡18)፡፡ ስለዚህ ‹‹ . . የኃይሉ ታላቅነት ከእግዚአብሔር እንጂ ከእኛ እንዳይሆን ይህ መዝገብ በሸክላ ዕቃ ውስጥ አለን›› (2 ቆሮ. 4፡7)፡፡ 
      ‹‹ . . በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና፡፡›› (ማቴ. 18፡20) እንዳለን፤ ቤተ፡ ክርስቲያን በምድር እንደ ሕያው እግዚአብሔር መንግሥት የሚገባውን እንድታደርግ ወንድሞቹ የሚታዘዙት ክርስቶስ በመካከላቸው ነው፡፡ ዘመኑ እንደ ይሳኮር ባለው የአህያ ጉልበት አይታለፍም፤ ትከሻውን ለሸክም ዝቅ እንዳደረገው እንደ እርሱም ትህትናና ታታሪነት አይከናወንም፤ ደግሞም በዚያ እውቀት ሊታወቅና እንደዚያ ጥበብ ተጠበን ልናልፈው አንችልም፡፡ ዳሩ ግን የሚበልጠው በሰው መካከል ሰው ሆኖ መጥቶአል፡፡ ከእርሱ የሚበልጥ፤ እንደ እርሱም ያለ ወደፊት አይመጣም፡፡ ዘመኑን በክርስቶስ!     
ለቤተ ፍቅር ቤተ ሰዎቻችን፤ እንኳን ለአዲስ ዓመት እግዚአብሔር አደረሳችሁ!

‹‹ . . . ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ፤›› /ቆላ. 4፡3/!

No comments:

Post a Comment