Tuesday, November 18, 2014

የጸናውን ማሰብ


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
                        
ኅዳር 8 ቀን 2007 የምሕረት ዓመት

       በአንድ ሰው ውስጥ ያለው ትልቁ ኃይል ‹‹አሳብ›› እንደ ሆነ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ በብርቱ የምናስበውን ያንን የመሆን ዕድላችን ሰፊ ስለሆነ፤ ሰው አስተሳሰቡ መጠበቅ እንዳለበት ይመከራል፡፡ የእግዚአብሔር ቃል የእውነተኛ አሳብ እውነተኛ ምንጭ ነው፡፡ እምነት ከመስማት ከሆነ የምንሰማውና የምንስማማው እውነተኛ አሳብ አለ ማለት ነው (ሮሜ. 10÷17)፡፡ ያም አሳብ ከዘላለም የሆነው የእግዚአብሔር አሳብ ነው (ኤፌ. 3÷11)፡፡
      
       ቃሉ ‹‹በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ›› (መክ. 12÷1) እንደሚል፤ የጽናት ደጀኑ እግዚአብሔርን ማሰብ ነው፡፡ በጉብዝናችሁ ዘመን የቆማችሁለት አሳብ ከሌለ ማንኛውም አሳብ ይጥላችኋል፡፡ የተሰበሰባችሁበት ዘላለማዊ ጥላ ከሌለም፤ የጊዜው ያባዝናችኋል፡፡ በወጣትነታችሁ የያዛችሁት እውነት ከሌለ ሐሰት ይገዛችኋል፡፡ በምቾቶቻችሁ ውስጥ ያጌጣችሁበት ጽድቅ ከሌለ ርኩሱ ይሸፍናችኋል፡፡ በጤና ጉብዝና፤ በእውቀት ጉብዝና፤ በሀብት ጉብዝና፤ በወዳጅ ጉብዝና እግዚአብሔርን ካልመረጣችሁ፤ ለእግዚአብሔር ካልቆረጣችሁ ዓለም ያሰላቻችኋል፡፡

       አሳብ ከየትኛውም ልማድ በላይ ነው፡፡ አሳባችን በልማዶቻችን ላይ የበላይ ካልሆነ፤ ለልማድ ባሪያ መሆናችን የተገለጠ ነው፡፡ በሕይወታችሁ ውስጥ ስታስቧቸው ደስታን የሚፈጥሩላችሁና ብርታት የሚሆኗችሁን ሰዎች ወይም ሁኔታዎች እስቲ ወደ አእምሮአችሁ አምጡና በወረቀት ላይ አስፍሯቸው፡፡ በመቀጠልም በተቻለ መጠን  ምክንያታችሁን አንድ በአንድ ለመጥቀስ ሞክሩ፡፡