Tuesday, November 18, 2014

የጸናውን ማሰብ


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
                        
ኅዳር 8 ቀን 2007 የምሕረት ዓመት

       በአንድ ሰው ውስጥ ያለው ትልቁ ኃይል ‹‹አሳብ›› እንደ ሆነ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ በብርቱ የምናስበውን ያንን የመሆን ዕድላችን ሰፊ ስለሆነ፤ ሰው አስተሳሰቡ መጠበቅ እንዳለበት ይመከራል፡፡ የእግዚአብሔር ቃል የእውነተኛ አሳብ እውነተኛ ምንጭ ነው፡፡ እምነት ከመስማት ከሆነ የምንሰማውና የምንስማማው እውነተኛ አሳብ አለ ማለት ነው (ሮሜ. 10÷17)፡፡ ያም አሳብ ከዘላለም የሆነው የእግዚአብሔር አሳብ ነው (ኤፌ. 3÷11)፡፡
      
       ቃሉ ‹‹በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ›› (መክ. 12÷1) እንደሚል፤ የጽናት ደጀኑ እግዚአብሔርን ማሰብ ነው፡፡ በጉብዝናችሁ ዘመን የቆማችሁለት አሳብ ከሌለ ማንኛውም አሳብ ይጥላችኋል፡፡ የተሰበሰባችሁበት ዘላለማዊ ጥላ ከሌለም፤ የጊዜው ያባዝናችኋል፡፡ በወጣትነታችሁ የያዛችሁት እውነት ከሌለ ሐሰት ይገዛችኋል፡፡ በምቾቶቻችሁ ውስጥ ያጌጣችሁበት ጽድቅ ከሌለ ርኩሱ ይሸፍናችኋል፡፡ በጤና ጉብዝና፤ በእውቀት ጉብዝና፤ በሀብት ጉብዝና፤ በወዳጅ ጉብዝና እግዚአብሔርን ካልመረጣችሁ፤ ለእግዚአብሔር ካልቆረጣችሁ ዓለም ያሰላቻችኋል፡፡

       አሳብ ከየትኛውም ልማድ በላይ ነው፡፡ አሳባችን በልማዶቻችን ላይ የበላይ ካልሆነ፤ ለልማድ ባሪያ መሆናችን የተገለጠ ነው፡፡ በሕይወታችሁ ውስጥ ስታስቧቸው ደስታን የሚፈጥሩላችሁና ብርታት የሚሆኗችሁን ሰዎች ወይም ሁኔታዎች እስቲ ወደ አእምሮአችሁ አምጡና በወረቀት ላይ አስፍሯቸው፡፡ በመቀጠልም በተቻለ መጠን  ምክንያታችሁን አንድ በአንድ ለመጥቀስ ሞክሩ፡፡ 

       አሁንም ደጋግማችሁ በማሰላሰል ተርኳቸው፡፡ በጽሞና አስተውሏቸው፡፡ በእርግጥ እነዚህ ሰዎች ያለ እንከን ነበሩን? ሁኔታዎቻችሁስ ሌላ ሁኔታ አልሻራቸውምን? እነዚያን ጣፋጭ ጊዜያት መራርነት አልተፈራረቃቸውምን? ዛሬም ደግመን ስናስባቸው ደስ በሚለን ምክንያት ውስጥ በጽናት አሉን? ስለ እነርሱ አውርታችሁ ‹‹ግን . . . ›› የለባቸውምን? በመልካም ጀምራችሁ፣ በመልካም አልፋችሁ፣ በመልካም ትጨርሱላቸዋላችሁን? ሰው በብዙ ድካም በጥቂት መልካምነት ለመታሰብ ብቁ፣ ለመደሰት ምክንያት ከሆነን ያለ ጉድለት ያለ፣ ብርታትና ጽናት መኖሪያው የሆነ መልካም፤ በሕይወታችን ብናገኝ ምን ያህል ያሳርፍ ይሆን?
        
        ሐዋርያው ‹‹በነፍሳችሁ ዝላችሁ እንዳትደክሙ ከኃጢአተኞች በደረሰበት እንዲህ ባለ መቃወም የጸናውን አስቡ›› (ዕብ. 12÷3) በማለት በሁኔታዎች መለዋወጥ ውስጥ በጽናት የምንቆምበትን የአሳብ ኃይል ይነግረናል፡፡ ስለ ችግር ካደመጠ ሰው ይልቅ በችግር ውስጥ ያለፈ፣ ስለ ሕመም ከሰማ ሰው ይልቅ ሕማምን የሚያውቅ፣ የተፈተኑትን ከተመለከተ ይልቅ ተፈትኖ ያለፈ፣ መከራችንን በቃልም በኑሮም ቢካፈለን በእጅጉ ብልጫ አለው፡፡ ከብርቱ መሻቶቻችን አንዱ ‹‹ሰዎች ምን አለ የተሰማኝ ለደቂቃ እንኳን በተሰማቸው?›› የሚል ነው፡፡

        ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ‹‹አንተ ባልፈጠርከው ሰው ተሰድበህ ይሆናል፤ እርሱ ፃድቅ የሆነው ግን በፈጠረው አንደበት ተሰደበ፡፡ አንተ ባላበጀኸው እጅ ተመትተህ ይሆናል፤ እርሱ ጌታ ግን በሠራው እጅ ተደበደበ፡፡ አንተ ባልሠራሃቸው ሰዎች መከራ ደርሶብህ ይሆናል፤ እርሱ መድኃኒታችን ግን በመልክና በምሳሌው በፈጠረው ሥጋ ለባሽ መስቀል ላይ ተሰቀለ፡፡ አንተ . . . ›› በማለት ጌታ ከኃጢአተኞች የተቀበለውን መከራ ያስረዳናል፡፡

        በነፍስ ዝሎ ላለመድከም የጸናውን ጌታ ከማሰብ፤ የተሰቀለውን እርሱን ከማስተዋል፤ የሚረዳ ጸጋ ወዳለው ኢየሱስ ከማቅናት የሚሻል አልያም አማራጭ ሆኖ የሚቀርብ ምንም ነገር የለም፡፡ ጌታ ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ ነው /ዕብ 4÷15/፡፡ በምናልፍበት ኑሮ፤ በምንደክምበት ነገር ሊራራል የሚችል፤ እርሱን ማሰብ የጽናት ሁሉ እውነተኛ ምንጭ ነው፡፡ ስለ እኛ ሲል መከራን የተቀበለው ክርስቶስ የመከራዎቻችን መውጫ ነው /1 ቆሮ. 10÷13/፡፡ ጥረት የማያሻግረውን፤ ብልሃት የማይሠራውን፤ ገንዘብ የማያሳልፈውን፤ ወዳጅ የማይጋፈጠውን፤ እናት እንኳን የልጇን ጩኸት የማትሰማበትን፤ ጨለማን ያበራው፣ መራራን ያጣፈጠው፣ ሞትን የሻረው፣ ሕይወትንና አለመጥፋትን ወደ ብርሃን ያወጣው /2 ጢሞ. 1÷11/፤ ሞት ሆይ መውጊያህ የታለ? ያስባለን፤ የሲዖልን ድል መንሣት በሚበልጥ ድል ያሻገረን ኢየሱስ ነው፡፡

        በምንኖርበት ዓለም ሕይወት ብርቱ ሰልፍ ናት /ኢዮ. 7÷1/፡፡ ብርቱ ሰልፍ ከመልክዓ ምድሩ ጋር የተያያዘ እንደ መሆኑ፤ ሥጋ ለባሽ ሁሉ በቋሚነት ይፈተናል፡፡ ተጉዘን ተጉዘን የምናበቃበት የምድር ጥግና የማንረግጠው መሬት እስከሌለ ድረስ ብርቱ ሠልፍ እናስተናግዳለን፡፡ የችግሮቻችን አይነትና ርዕስ ቢለያይም ሰው ሁሉ ይፈተናል፡፡ ብዙዎች ቀብረው የሚያዝኑትን ሀዘን በወዳጅ ተከበው የሚያዝኑ፤ ሌሎች አጥተው የተከፉትን መከፋት አከማችተው የሚከፉትን አለማስተዋል ካልሆነ በቀር ሁሉም ተግዳሮት አለበት፡፡ ጌታም በዓለም ሳለን መከራ እንዳለብን ነግሮናል /ዮሐ. 16÷33/፡፡ ዳሩ ግን ‹‹አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ›› ይለናል፡፡ ከአንዱ ጌታ በቀር እንዲህ ሊናገር የተቻለው ሌላ ማን ነው?
     
        ተወዳጆች ሆይ፤ በምትኖሩበት ሁኔታና ባላችሁበት ቦታ ሆናችሁ፤ ያለ ማቋረጥ ‹‹የጸናውን አስቡ››፡፡ ሰው ሌላ ምንም አስቦ በፊቱ ያለውን ሩጫ በትዕግሥት ሊሮጥና ነውርን ሊንቅ አይችልም፡፡ ሰውን ብታስቡ ወደ ሰው ትጎተታላችሁ፤ ሁኔታን ብትከተሉ በሁኔታው ትዋጣላችሁ፡፡ ጌታን አስቦ በእርሱ ውስጥ መጥፋት (መሰወር) ምንኛ መታደል ነው፡፡ በርኩሰት መካከል ቅድስና፤ በውሸት ዘንድ እውነት፤ በሚጠፋው ፊት ዘላቂው ጽናት የዘላለም እግዚአብሔር ነው /ሮሜ 16÷25/፡፡ መሽቶ እስኪነጋ፤ በክረምት ቢሆን በበጋ እርሱ የታመነ ነው፡፡ ሐዋርያው ያዕቆብ ‹‹በጎ ስጦታ ሁሉ ፍጹምም በረከት ሁሉ ከላይ ናቸው፥ መለወጥም በእርሱ ዘንድ ከሌለ በመዞርም የተደረገ ጥላ በእርሱ ዘንድ ከሌለ ከብርሃናት አባት ይወርዳሉ።›› /ያዕ. 1÷17/ ይለናል፡፡

        የዳዊት መክፈቻ ያለው፤ የሚከፍት የሚዘጋም የሌለ፤ የሚዘጋ የሚከፍትም የሌለ፤ ቅዱስና እውነተኛ በሆነው /ራዕ. 3÷7/ በእርሱ ዘንድ ‹‹መለወጥ›› የለም፡፡ እግዚአብሔር በነቢያቱ አፍ እንዲህ ብሎ እንደተናገረ ‹‹እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም›› /ሚል. 3፥6/፡፡ ዘመናት ቢተካኩ፤ ወቅቶች ቢፈራረቁ ጌታ እግዚአብሔር ከዘላለም እስከ ዘላለም ያው ነው /መዝ. 89÷2/፡፡ የእርሱ አለመለወጥ በጊዜያት ውስጥ ያለውን ጽናት እንድናስተውል ያደርገናል፡፡ ኑሮው በሞት የማይደመደም ሕያው እርሱ ጌታ ከእናንተ ጋር ነው፡፡ ከጊዜ ጋር መጥተው ከጊዜ ጋር ስለሄዱ፤ ለልባችሁም ስብራትና ሀዘንን ስላተረፉላችሁ ብዙ ነገሮች ታስቡ ይሆናል፡፡

        እንዲህ ያለው ሕሊናን የሚያቆስል አሳብ የሚሻረው መለወጥ በሌለበት በጌታችን የበለጠ አሳብ ነው፡፡ ሐዋርያው ‹‹ብዙ ጊዜ በመንገድ ሄድሁ በወንዝ ፍርሃት፣ በወንበዴዎች ፍርሃት፣ በወገኔ በኩል ፍርሃት፣ በአሕዛብ በኩል ፍርሃት፣ በከተማ ፍርሃት፣ በምድረ በዳ ፍርሃት፣ በባሕር ፍርሃት፣ በውሸተኞች ወንድሞች በኩል ፍርሃት፣ ነበረብኝ፤ በድካምና በጥረት ብዙ ጊዜም እንቅልፍ በማጥት በራብና በጥም ብዙ ጊዜም በመጦም በብርድና በራቁትነት ነበርሁ›› (2 ቆሮ. 11÷26) በማለት በሚለዋወጡ ሁኔታዎች ውስጥ እንዳለፈ ይነግረናል፡፡ ዳሩ ግን ‹‹ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬ እስከ ለዘላለምም ያው ነው።›› /ዕብ. 13÷8/፡፡

       ወዳጆቼ ሆይ፤ ዓለሙንና በእርሱ ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ እርሱ የሰማይና የምድር ጌታ ነውና /ሐዋ. 17÷24/ በቦታ አይወሰንም፡፡ በዚህ ነው፤ ሲባል በዚያ አይጎድልም፡፡ በዚያ አለ፤ ሲባልም በዚህ አይታጣም፡፡ በእርሱ ዘንድ ብቻ በመዞር የተደረገ ጥላ የለም፡፡ እኛንም ሁኔታዎቻችንንም ስፍራ ይወስነናል፡፡ እግዚአብሔር ግን ከእኛም ከሁኔታውም በላይ ነው፡፡ እንዲህ ተብሎ እንደተፃፈ፤ ‹‹ከላይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው፤ ከምድር የሚሆነው የምድር ነው የምድሩንም ይናገራል። ከሰማይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው።›› /ዮሐ. 3÷31/፤ እርሱ የማይሞላው ክፍተት፤ የማይገኝበት ሽሽግ፤ የማያስተውለው ስውር፤ እጁ የምታጥርበት ሩቅ፤ የማይመረምረው ጥልቅ የለም፡፡ እግዚአብሔርን ከወሰነው እርሱ እግዚአብሔር አይደለም /ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ/፡፡
 
       ለምድሪቱ የምትወጣው ፀሐይ አንድ ናት፡፡ ዳሩ ግን በሌላ ስፍራ ብርሃን ሲሆን፤ በአንዱ ስፍራ ደግሞ ጥላ ይሆናል፡፡ አገር ቤት ሲጨልም አውሮፓ ይጠራል፡፡ ዓይኖቻችን በሚያስተውሉት ብርሃን ዘንድ በመዞር የተደረገ ጥላ አለ፡፡ በእምነት በምናስተውለው እግዚአብሔር ብርሃንነት ዘንድ ግን እንዲህ አይሆንም፡፡ እኛ አካላችን ባለበት እልፍ ብሎ ጥላችን ይስተዋላል፡፡ ጥላው የሸፈነውን አካል፤ አካል ያዳረሰውን ጥላ አይሞላውም፡፡ ለእርሱ ለአምላካችን መገኘቱ የማይሞላው ምን አለ? አካሉ አንሶ ጥላው የሚሸፍነው ውስንነት በጌታ ዘንድ ከቶ የለም፡፡ የእኛ አካል ስፍራ ቢቀይር እግዚአብሔር መገኘቱ በዚያም አለ፡፡ እውነተኛ አምላክ የሆንክ አንተ አባታችን ሆይ፤ መለወጥና ጥላ በአንተ ዘንድ የሌለ ጽኑ መጠጊያችን አንተ ነህ፡፡

       ዮሴፍ ወንድሞቹ በግፍ ለእስማኤላውያን አካሉን ከሸጡት በኋላ፤ ግብፅ ደግሞ ነፍሱን የምትሸጥ ገጠመችው /የጲጥፋራ ሚስት/፡፡ ዮሴፍ ለጽድቅ መወገኑ፤ ከሕያው እግዚአብሔር ጋር መቆሙ ያስከተለውን መከራ በትዕግሥት ተቀበለ /ዕብ. 12፥4/፡፡ የሚስቱን ቃል የሰማው አባወራ ዮሴፍን ወደ ግዞት ቤት አገባው /ዘፍ. 39፥19/፡፡ የእግዚአብሔር ባሪያ በዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ ውስጥ የጸናውን እግዚአብሔር ያስብ ነበር፡፡ ከመለኮት የሆነውም ራዕይ እንዲፈፀም በልቡ ይታመን ነበር፡፡ ነገር ግን ዮሴፍ በግዞት ቤት ሳለ የጠጅ አሳላፊዎችን አለቃ ሕልም በፈታ ጊዜ ‹‹በጎ ነገር በተደረገልህ ጊዜ እኔን አስበኝ፥ ምሕረትንም አድርግልኝ፥ የእኔንም ነገር ለፈርዖን ነግረህ ከዚህ ቤት አውጣኝ›› /ዘፍ. 40፥14/ አለው፡፡

       ዮሴፍ በባዕድ ምድር ሞገስ የሆነውን፤ ከወንድሞቹ ቁርጥ ሞት የታደገውን፤ በግብፃዊው ቤት ላይ የሾመውን፤ ከሚስቱም መሴሰን ያስመለጠውን እግዚአብሔር ማሰብ ቸል ብሎ፤ ሰው እንዲያስበውና እንዲታደገው ከጀለ፡፡ ጌታ እንዲህ ካለውም ያድነን፡፡ እግዚአብሔር ያወራን ሰዎች ሰው አውርቶን፤ ጌታ የመራን ሰዎች ሥጋና ደም ተናግሮን ከመለኮት አሳብ ዝቅ ካልን ይህ ስንፍና ነው፡፡ ጌታ ግን አመፀኛ አይደለም፡- ‹‹ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ አይደለምና።›› /ዕብ. 6፥10/፡፡ ዮሴፍ ተስፋ ስላደረገው የጠጅ አሳላፊዎች አለቃ ‹‹የጠጅ አሳላፊዎች አለቃ ግን ዮሴፍን አላሰበውም፥ ረሳው እንጂ›› ተብሎ በምዕራፉ መጨረሻ ላይ እናነባለን፡፡ የሁሉም ዓይን ተስፋ የሚያደርገው እግዚአብሔር ግን ከዮሴፍ ጋር ነበረ፡፡ የጸናው ጌታ ያጽናን!
         
       ሐዋርያው ‹‹በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይሁን።›› /ፊል 2÷5/ ይለናል፡፡ በመከራና በፈተና ውስጥ ስናልፍ ትልቅ ጉልበት በክርስቶስ የነበረው አሳብ ነው፡፡ ኃይልን የሚሰጥ፤ ለመኖር ጉልበት የሚሆን፤ በወጀብና በአውሎ መንገድ የምናገኝበት አሳብ የጸናው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው!
                                               ‹‹ . . . ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ፤›› /ቆላ. 4፡3/!

No comments:

Post a Comment