በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
አርብ ነሐሴ 15
ቀን 2007 የምሕረት ዓመት
እዚያ . . . ኑ ቡና ጠጡ፤
አሉባልታ አድምጡ።
ብዬ ከወዳጆቼ ተሰባስቤ፤
ለወሬ ተሰናድቶ ቀልቤ።
የሰው ሥጋ ስንቋደስ፤
ስንቀቅል ስንጠብስ።
ከፍም የተገናኘው ሸክላ፤
በእሳቱ ነበልባል ሲበላ።
ድንገት . . . እፍ
. . . እፍ . . .
ኧረ ገነፈለ፤
ቡናው ከጀበናው ዘለለ።
እኛ ስናወራ እሳቱ አይሎ፤
ጀበናው የውስጡን አወጣ አግተልትሎ፡፡
እዚህ . . . ኑ ቡና ጠጡ፤
ቃሉን አድምጡ።
ብዬ ወዳጆቼን ሰብስቤ፤
ለቃሉ ተሰናድቶ ቀልቤ።
የሰው ነፍስ ስንናጠቅ፤
ከክፉ ሥራ ስናላቅቅ።
ከፍም የተገናኘው ሸክላ፤
በሳቱ ነብልባል ሲበላ።
ድንገት . . . እሰይ
. . . እሰይ . . .
ገነፈለ፤
ፍቅር ከጀበናው ዘለለ።
ከተሰባሪው ገል ገላ፤
ከእኔነቴ ሸክላ።
የመለኮት እሳት በዝቶ፤
ውስጤን አግሎ አፍልቶ።
እንደ ፈሳሽ ምንጭ፤
ከሰዎች ሲሰራጭ።
የሕይወት ቡና ቢያጠጣ፤
ከሸክላነታቸው ሸክላ ወጣ።
እናንተም የፍቅሩ ቁራሾች፤
የመለኮት እሳት ተካፋዮች።
ከፍቅር ጀበና ገንፍሉ፤
ከሸክላነታችሁ ውጡና ዝለሉ።