Friday, August 14, 2015

ስፍራችሁን ያዙ

(ካለፈው የቀጠለ)
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

አርብ ነሐሴ 8 ቀን 2007 የምሕረት ዓመት

      ‹‹ነጽር ኀበ አይ መካን አዕረጋ ለቤተ ክርስቲያን ዘከመ ይእቲ ኩለን ሰሐባ በጥበብ እምሉዓሌ፡፡ ወክመዝ አዕረጋ ኀበ ልዕልና ዐቢይ÷ ወለዝንቱ ዘውእቱ እምኔነ አንበሮ ዲበ ዝንቱ መንበር÷ ወለነሂ ዓዲ ለቤተ ክርስቲያን ስሐበነ እግዚአብሔር ኀቤሁ በከዊኖቱ ርእሰ ዚአነ እስመ ውስተ መካን ኀበ ሀሎ ርእሰ ህየ ይሄሉ ሥጋ ቤተ ክርስቲያን አካሉ እንደ መሆንዋ መጠን ወዴት ከፍ ከፍ እንዳደረጋት አስተውል፡፡ ከላይ ሆኖ በጥበብ ወደ እርሱ አቀረባት እንደዚህ ወዳለ ክብርም አወጣት ከእኛ ወገን የሆነውን /ከመለኮት ጋር የተወሐደውን/ ትስብእትንም በዚያ ዙፋን በቀኙ አስቀመጠው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የሆንነውን እኛንምርስቶስ ራሳችን በመሆኑ እግዚአብሔር ወደ እርሱ ሳበን÷ ራስ ካለበት ሕዋሳት ይኖራሉና››      

/ሃይማኖተ አበው ዘዮሐንስ አፈወርቅ፤ 67÷39/ 

ሁለተኛው ጭብጥ፤ ከስፍራችን አንፃር በዚህ ዓለም ላይ በሰማይ እንደተሰጠን ስፍራ መመላለስ ነው፡፡ በሰማይ የሆነችው የእግዚአብሔር ፈቃድ በምድር ላይ የምትፈጸመው በቤተክርስቲያን፤ በክርስቶስ ክርስቲያን በሆኑ ምዕመናን ነው፡፡ በዚህ ዓለም ላይ ሰዎች ከፀሐይ በታች ካላቸው ስፍራ አንፃር ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ሐኪሙ እንደ ሐኪም፤ መሐንዲሱ እንደ መሐንዲስ፤ አስተማሪው እንደ አስተማሪ፤ ተማሪው እንደ ተማሪ . . . ሁሉም ሰው በሌሎችም ይሁን በራሱ ካገኘው ስፍራ አንፃር በሰው መካከል ይወጣል ይገባል፡፡
የእግዚአብሔር መንግሥት ልጆች ከሆንን ከመንግስቱ የቃል ኪዳን ሰነድ /መጽሐፍ ቅዱስ/ አንፃር መንፈሳዊ ስፍራችንን ጠብቀን መመላለስ ይገባናል፡፡ ልብ በሉ! እዚህ ጋር እንደሚገባ የሚመላለሰው ሰው መጀመሪያ ስፍራውን እንደ እግዚአብሔር ቃል የያዘው ሰው ነው፤ እርሱም ከእግዚአብሔር ልጅነትን ያገኘ ነው፡፡ መመላለስ ስፍራውን ስለያዝን የሚመጣ እንጂ ፍላጎትና ጥረት የሚያስገኘው አይደለም፡፡
የምንመገበው ሰው ስለሆንን እንጂ ሰው ለመሆን እንዳልሆነ ሁሉ እንደ እግዚአብሔር ልጆች መመላለስ የሚመጣው አስቀድሞ የልጅነትን ስፍራ በመያዝ ነው፡፡ አንበሳ እንደ አንበሳ የሚመላለሰው ተፈጥሮው አንበሳ ስለሆነ ነው፤ በግ እንደ በግ የሚኖረው ተፈጥሮው በግ ስለሆነ ነው፡፡ ሌሎቹም እንዲሁ፡፡ ክርስቶስ ራስ የሆነላት አካሉ፤ ሙሽራዋ የሆነላት ሙሽሪቱ፤ ሊቀ ካህናት የሆነላት ቤቱ፤ ቤተክርስቲያኑ በእግዚአብሔር ልብ ውስጥ እንዳላት መንፈሳዊ ስፍራ፤ በዚህ ዓለም መካከል መመላለስ አለባት፡፡ 
ሐዋርያው ስፍራችሁን ያዙ ካለ በኋላ፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ካገኘንበት መንፈሳዊ ማንነት አንፃር እንድንመላለስ ይነግረናል፡፡ ተወዳጆች ሆይ፤ በክርስቶስ ክርስቲያን በመሆናችን ያገኘነውን ስፍራ እንደሚገባ ባልተረዳንበትና አምነን ባልተቀበልንበት መልኩ እውነተኛ ኑሮ /መመላለስ/ አይጠበቅም፡፡
እንደ ቃሉ መኖርን፤ እንደ ቃሉ ማመን ይቀድመዋል፡፡ ‹‹ጻድቅ በእምነት ይኖራል ተብሎ እንደ ተጻፈ የእግዚአብሔር ጽድቅ ከእምነት ወደ እምነት በእርሱ ይገለጣልና።›› /ሮሜ 1፡17/ እንዲል ቃሉ፤ በእምነት የሚኖረው የጽድቅን ስፍራ የያዘው ሰው ነው፡፡ ጽድቁ የሌለው ሰው የጽድቅ ፍሬን እንዴት ሊያፈራ ይችላል?
    ‹‹እንግዲህ በጌታ እስር የሆንሁ እኔ በተጠራችሁበት መጠራታችሁ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እለምናችኋለሁ›› /ኤፌ. 4፡1/ ይለናል፡፡ ተወዳጆች ሆይ፤ እንዲህ እየተባለ ያለው መንፈሳዊ ስፍራውን የያዘው ክርስቲያን ነው፡፡ እንደሚገባ የሚመላለስበት ጉልበት ያለው ለጥሪው ምላሽ የሰጠ ሰው ነውና፡፡ ክርስትና ጥሪ ነው /1 ጴጥ. 2፡9/፡፡ እግዚአብሔር ባስቀመጠው የተቀመጠ፤ ሥፍራው የሚጠይቀውን ኑሮ እንደሚገባ ለመኖር ኃይል ያገኛል፡፡  
በኤፌሶን መልእክት ውስጥ የምናገኘው ሦስተኛው ጭብጥ በጠላት /ፈተና/ ፊት ከመንፈሳዊ ስፍራችን አንፃር መዋጋትን የተመለከተ ነው፡፡ ‹‹በቀረውስ በጌታና በኃይሉ ችሎት የበረታችሁ ሁኑ።›› /ኤፌ. 6፡10/ ተብለናል፡፡
በክርስትና ሕይወት የፈተና ምንጭ እንደሆኑ ከምንጠቅሳቸው ዋናዎቹ ሥጋ /ባህርዩ/፤ ዓለም /ሥርዓቱ/፤ እና ዲያብሎስ ናቸው፡፡ በዚህ መልእክት ‹‹የዲያብሎስን ሽንገላ መቃወም›› ተብሎ ትኩረት ተሰጥቶበታል፡፡ ኃይልን በሚሰጠን /ፊል. 4፡13/ በክርስቶስ ሁሉን እንችላለን እንጂ የሰው ሕይወት በምድር ላይ ብርቱ ሠልፍ ነው /ኢዮ. 7፡1/፡፡ መንፈሳውያን ብንሆንም ውጊያው መንፈሳዊ ነው፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹በሰይጣን እንዳንታለል፤ የእርሱን አሳብ አንስተውምና።›› /2 ቆሮ. 2፡11/ እንዳለ፤ ክርስቲያን የባላጋራውን ክፉ አሳብ ሊስትና ሊታለል አይገባም፡፡ ጠላት የቱንም ያህል በሽንገላ ቢገለጥ ‹‹ሌባው ሊሰርቅና ሊያርድ ሊያጠፋም እንጂ ስለ ሌላ አይመጣም›› /ዮሐ. 10፡10/ እንደተባለው፤ ዛሬም እንደዚያው ነው፡፡
በእግዚአብሔር ዘንድ ሐሰት የሌለውን ያህል በዲያብሎስም ዘንድ እውነት የለም /ሮሜ 3፡4/፡፡ ሁሉን በሚችል አምላካችን ዘንድ ኃጢአት የሌለውን ያህል በሰይጣንም ዘንድ ጽድቅ የለም፡፡ ወዳጆቼ ሆይ፤ ሰው እንዲህ ወዳለው እውነት እንዴት ይደርሳል? ብላችሁ ታስቡ ይሆናል፡፡ የእግዚአብሔር ቃል በግልጥ እንደሚነግረን፤ ‹‹እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው፤ መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው።›› /ሮሜ 10፡17/ ይለናል፡፡
ሰው የእግዚአብሔርን ቃል ካልሰማ ትክክለኛ እውቀትና እምነት በውስጡ ሊኖር አይችልም፡፡ የምንሰማው ሁሉ እምነት አይሆነንም፡፡ ዓለማችን በብዙ ድምፆች የተበከለች ናት፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ ለመስማት የሰውን ቀልብ ከሚስቡ ነገሮች ጀርባ፤ ጠላት ዲያብሎስ ረጅም ወጥመድን ዘርግቶአል፡፡
ሰው በመስማት የሚያርፈውን ያህል እንደዚያው ሊባዝንም ይችላል፡፡ ሰምተው የተቃኑ ሰምተውም ጠመዋል፡፡ አድምጠው ወደ ሕይወት የተመለሱ፤ አድምጠው ሞትን መርጠዋል፡፡ የሚወራውና ሰው የሚያደምጠው ሁሉ ሕይወት አይሆንም፡፡ ስለ እግዚአብሔር ባሪያዎች እንኳን ‹‹አንተ ግን ሕይወት ለሚገኝበት ትምህርት የሚገባውን ተናገር።›› /ቲቶ 2፡1/ ተብሎአል፡፡ ‹‹አንተ ግን›› ከተባለ፤ ሌሎች ሕይወት የማይገኝበትን ትምህርት በእግዚአብሔር ስም ለሰው ጆሮና ልብ የሚቀልቡ አሉ ማለት ነው፡፡ ተወዳጆች ሆይ፤ እናንተ ግን?  
የፍቅር ሐዋርያው ‹‹ . . ከአብ ዘንድ የነበረውንም፤ ለእኛም የተገለጠውን የዘላለምን ሕይወት እናወራላችኋለን፤›› /1 ዮሐ. 1፡2/ ይለናል፡፡ ልክ ጴጥሮስ ሲናገር ‹‹ከአሥራ አንዱ ጋር ቆመ›› ተብሎ እንደተፃፈ /ሐዋ. 2፡14/፤ እዚህም ጋር ‹‹እናወራላችኋለን›› ተብለናል፡፡ ሐዋርያቱ በአንድ ልብ መካሪ፤ በአንድ ቃል ተናጋሪ ሆነው ያወረሱን መንፈሳዊ ወሬ ‹‹የዘላለም ሕይወት›› ነው፡፡
እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ያለው ኑሮ በዘላለም ላይ የተመሠረተ መሆኑ ደስታችንን ፍጹም ያደርገዋል፡፡ ከምትወዱት ጋር አብራችሁ እንደምትኖሩ ሰምታችሁ ቀጥሎ እድሜው በጣቶቻችሁ ቁጥር ልክ እንደ ሆነ ቢነገራችሁ ምን ያህል ትከፉ? ሰው ከሰው ጋር ላለው ኑሮ ይህንን ያህል ከሳሳ፤ የዘላለም እግዚአብሔር እንዴ አብዝቶ አይናፈቅ?
ከሞት በኋላ ስለተያዘ የሰዎች ቀጠሮ ሰምታችሁ ከሆነ ያ በክርስቶስ የሆነው ነው፡፡ ከሞት በኋላም ስለሚዘልቅ እድር፤ ዕቁብ፤ አክስዮን፤ ስብሰባ . . . አልሰማንም፡፡ ከሞትና ከመቃብር የሚያልፍ ኑሮ ግን ክርስቲያን በመሆናችን አለን፡፡ ‹‹ኢየሱስም፦ ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል›› /ዮሐ. 11፡25/ እንዳለን፤ ክርስትና በዚህ ምድር ላይ በተሰፈረልን ዕድሜ ልክ የሆነ ኑሮ ሳይሆን በዘላለም (መጨረሻ በሌለው) ላይ የቆመ ነው፡፡   
ስናወራውም ዘላለም፤ ስንኖረውም ዘላለም እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ገና ከሞት በኋላ ሳናይ ያመነው እርሱ አይተነው እንድንኖር ቀጠሮ ይዞልናል፡፡ የዘላለም እግዚአብሔር እስካለ ድረስ /ሮሜ 16፡26/፤ የዘላለም ኑሮ አለ፡፡  እመጣለሁ ያለን በእርግጥ ይመጣል /ዮሐ. 14፡3/፡፡
ሐዋርያው ‹‹የዘላለምን ሕይወት እናወራላችኋለን›› በማለት ሰውን ከሞት ወደ ሕይወት /1 ዮሐ. 3፡14/፤ ከድቅድቅ ጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃን /1 ጴጥ. 2፡9/ የሚያሸጋግረውን ወሬ ይነግረናል፡፡ አዎ! የምንሰማው ሁሉ እግዚአብሔርን ወደ ማመን፤ አሳቡንና የልቡን ምክር ወደ መረዳት አያደርሰንም፡፡ የሚቀድሰው እውነት ቃሉ   /ዮሐ. 17፡17/ ግን እግዚአብሔርን ወደ ማወቅና ማመን ያደርሰናል፡፡

‹‹እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት።›› /ዮሐ. 17፡3/ እንደተባለ፤ የዘላለም ሕይወት እውነትን በማወቅና በማመን የሚሆን ነው፡፡ ‹‹ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቶአል›› /ሆሴ. 4፡6/ ተብሏልና፤ ትክክለኛው የእግዚአብሔር እውቀት የሌለው ሰው ለዘላለም ይጠፋል፡፡ ሰው የመዳን እውቀት ከሌለው ወደ መዳን፤ የጸጋው ቃል ከሌለው በጸጋው መኖር እንዴት ይቻለዋል?
                     ‹‹ . . . ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ፤›› /ቆላ. 4፡3/!

No comments:

Post a Comment