Wednesday, August 15, 2012

የግያዝ ዓይኖች


             
         ከሆነብን በላይ የሆነውን የምንተረጉምበት፣ ከሰማነው በላይ ያደመጥነውን የምንረዳበት፣ ከመጣው ፈተና በላይ መከራውን የምናስተናግድበት መንገድ ጽናታችንንም ሆነ መብረክረካችንን ይወስነዋል፡፡ ልጅ እያለን በጨለማ ስንሄድ አንዱ ዛፍ እንደ ብዙ ዛፍ፣ አንድ ድምጽ ልክ እንደ ብዙ ውኃዎች ድምጽ፣ አንድ ሰውም እንደ ትንሽ መንጋ ሆኖ ይታየን ነበር፡፡ በብዛት ብቻ ሳይሆን በኃይልም የምንረዳበት መንገድ ከሆነው በእጅጉ የተጋነነ ነው፡፡ የቅጠል መተሻሸት፣ የነፋስ ሽውታ፣ የሌሊት ወፍ ድምጽ ልክ እንደ አንበሳ ግሳት፣ እንደ ነብር ፍጥነት፣ እንደ ዲያብሎስ ትጋት ተቆጥሮ ልባችን ይሸነፍበታል፡፡ በሕይወታችን ድንግዝግዝ ነገር ሲበዛ አጥርቶ ማየት ከባድ ነው፡፡ በልኩም መረዳት አስቸጋሪ ነው፡፡ ከከበበን ብዙ መፍትሔ ይልቅ ጥቂት ችግራችንን እሽሩሩ ማለት ይቀናናል፡፡
         በአካል ካደግን፣ በአእምሮ ከበሰልን፣ የኑሮ ተግዳሮቶችን መጋፈጥ ከጀመርን በኋላ የምንፈተነው የሆነውን በሆነው ልክ ማየት ባለመቻል ነው፡፡ መከራ አይለመድም፡፡ የሕይወት ዘመን እንግዳ፤ የየማለዳው አዲስ ነው፡፡ ሰው ወድዶ አለመደሰት ይችላል፡፡ አለመፈተን ግን ከቶ አይችልም፡፡ በደስታ ላይ በርን መዝጋት ይቻላል፤ ችግር ግን የተዘጋውንም ጥሶ ይዘልቃል፡፡ የምስራቹን አልቀበልም ያሉ ዛሬ የበዪ ርሀብተኛ፣ የአዋቂ መሀይም፣ የብልጥ ተላላ፣ የዘናጭ ታራዥ፣ የትጉህ ብኩን ሆነዋል፡፡ ጌታ ግን በተዘጋው ደጅ የሚያልፍ መፍትሔ አለው፡፡ እርሱም “ሰላም ለእናንተ ይሁን” (ዮሐ. 20÷19) አላቸው፡፡
       በማንኛውም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሰይጣን የሚዘጋቸው፤ ሥጋም መጋረጃ ሆኖ የሚከልላቸው ነገሮች ይኖራሉ፡፡ እምነት ግን ከተዘጋው ባሻገር ማየት ነው፡፡ ከሚታየው አልፎ የማይታየውን መመርመር ነው፡፡ ከሥጋ ሁኔታ ወደ መንፈሳዊው ሁኔታ፤ ከዚህ ዓለም አሳብ ወደ ሰማያዊው አሳብ ከፍ ማለትም ነው፡፡ እምነት ከሥጋ አይን ልኬት፣ ከጆሮ የመስማት ደረጃ፣ ከአካልም የመስራት ኃይል በላይ ነው፡፡ ግዙፉን ጎልያድ በአንድ እዚህ ግባ በማይባል ብላቴና ፊት ያሳነሰው እምነት ነው፡፡ ለአሥሩ ሰላዮች በከነዓን የሚኖሩትን ሕዝብ ያገነነው ደግሞም ለእስራኤል ማኅበር ፍርሃትን እንዲያወሩ ያደረገው የእምነት ማነስ ነው፡፡ እነርሱም ሲናገሩ “በዓይናችን ግምት እንደ አንበጣዎች ነበርን ደግሞ እኛ በዓይናቸው ዘንድ እንዲሁ ነበርን አሉ” (ዘኁ. 13÷33)፡፡ እግዚአብሔር ደግሞ  ”“እኔ ሕያው ነኝና በጆሮዬ እንደተናገራችሁት እንዲሁ በእውነት አደርግባችኋለሁ” (ዘኁ. 14÷28) አለ፡፡ እንደ ቃሉም ሁሉን በሚችል አምላክ ፊት ያጉረመረሙት በሙሉ በምድረ በዳ ሞቱ፡፡
       በመጽሐፈ ነገሥት ካልዕ ምእራፍ 6 ላይ የሶርያ ንጉሥ ከእስራኤል ጋር ሊዋጋ ወደ ሕዝቡ እንደመጣ እናነባለን፡፡ ንጉሡም ፈረሶችንና ሰረገሎችን እጅግም ጭፍራ ሰደደ በሌሊትም መጥተው ከተማይቱን ከበቡ፡፡ የእግዚአብሔር ሰው ኤልሳዕ ሎሌ የሆነው ግያዝም “ጌታዬ ሆይ ወዮ ምን እናደርጋለን?” አለው፡፡ ግያዝ እንዲህ ሊናገር የቻለው ኤልሳዕ እንደሚያይ ማየት ባለመቻሉ ነው፡፡ የኤልሳዕ ዓይኖች ግን ከተማይቱን በከበቡት የሶርያ ንጉሥ ጭፍሮችና ድቅድቅ በሆነው ጨለማ ላይ ሳይሆን ያረፉት ከከበባቸው ሠራዊት በላይ በሆነው እግዚአብሔር ላይ ነበር፡፡ “ክርስቶስን ተመልከቱ” (ዕብ. 3÷2)!
       በኑሮ ውስጥ ብዙ የሚከቡን ነገሮች አሉ፡፡ የዚህ ዓለም ከንቱ አሳብ፣ የሰይጣን ውጊያ፣ የሕይወት ውጣውረድ፣ ድካምና ኃጢአት እነዚህ ሁሉ በዙሪያችን ያሉ የዕለት ከዕለት ፈተናዎች ናቸው፡፡ እምነት ግን ከሁኔታ ባላይ መኖር የምንችልበት ኃይል ነው፡፡ በእምነት ዓይን ፊት የማይቀልና የማያንስ ነገር የለም፡፡  ተወዳጆች ሆይ እኛ በኑሮ ሠልፍ ላይ ያለን ዓይን የግያዝ አይነት ነው ወይስ የኤልሳዕ? በዙሪያችን ያለው ችግር ወይስ ከእኛ ጋር ያለው እግዚአብሔር ነው የሚበልጥብን? ችግር ተኮፍሶ መፍትሔው ካነሰ ውጤቱ እንደ ሎሌው መፍራት ነው፡፡ ነቢዩ ዳዊት “መክበቡንስ ከበቡኝ በእግዚአብሔርም ስም አሸነፍኋቸው” (መዝ. 117÷11) ይላል፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን ደግሞ  “የእግዚአብሔር ስም የጸና ግንብ ነው ጻድቅ ወደ እርሱ ሮጦ ከፍ ከፍ ይላል” (ምሳ. 18÷10) ይለናል፡፡ ከዚህ ዓለም ጥበብ የእግዚአብሔር ሞኝነት እጅግ እንደሚበልጥ ስናስተውል በአባትና ልጅ የተናገሩት እነዚህ ቃላት ለልባችን ይጠጋሉ፡፡
         የእግዚአብሔር መቻል የማይቻለውንም ይጠቀልላል፡፡ እርሱ እንዲያደርግልን የምንፈልገውን ሁሉ ቢያደርግልን እንኳ መቻሉ እዚያ ጋር አይቆምም፡፡ ከዚያም በብዙ ያልፋል፡፡ ኢዮብ ስለ እግዚአብሔር መቻል “ሰሜንን በባዶ ስፍራ ላይ ይዘረጋል ምድሪቱንም በታችዋ አንዳች አልባ ያንጠለጥላል ውኆችን በደመናዎቹ ውስጥ ያስራል ደመናይቱም ከታች አልተቀደደችም፡፡ . . . . ይህም የሰማነው ነገር ምንኛ ጥቂት ነው!” (ኢዮ. 26÷7) በማለት ይናገራል፡፡ በእርግጥም ሰማያት በመንፈሱ ውበት ያገኙበት፣ ምድር ከተግሣጹ የተነሣ የምትደነግጥለት፣ ስሙን ሰምቶ ሞት የሚብረከረክለት፣ ክብሩን አይተው ቀላያት የሚሰነጣጠቁለት ጌታ ሁሉን ያደርግ ዘንድ እንዴት አይችልም? አባቱን እንደሚገባ ያልተረዳው ልጅ የአባቱን አቅም በሁኔታ፣ በሰውና በቦታ መገደቡ የሚደንቅ ሊሆን አይችልም፡፡ እግዚአብሔርን የምናርፍበት በእምነት የተረዳነውን ያህል ነው፡፡  
            ግያዝ በእግዚአብሔር ፊት እንደ አገልጋይ ቢኖርም እግዚአብሔርን ግን እንደሚያገለግል ባሪያ አልተረዳውም፡፡ እግዚአብሔርን እንደሚያገለግል ተገልጋዩን መረዳት በሚያጸድቅና በሚኮንን በእርሱ ፊት ለመቆም ቀዳሚው ነገር ነው፡፡ ግያዝ እግዚአብሔር ለሶርያው ንጉሥ አለቃ ንዕማን የሰጠውን ደኅንነትና የገለጠውን ኃይል ተመልክቶአል፡፡ ዳሩ ግን በሶርያ ወታደሮች ፊት በእምነት እንዲቆም አላስቻለውም፡፡ አልዓዛር ከመሞቱ በፊት ማርያም በጌታ እግር ስር ቁጭ ብላ እንደተማረች ቃሉ ይነግረናል (ሉቃ. 10÷38)፡፡ ነገር ግን አልዓዛር ከሞተ በኋላ ማርያም በጌታ እግር ስር እንደተማረ ስትመልስ አናያትም፡፡ በሀዘን ሠልፍ ፊት አይኖችዋ ልክ እንደ ግያዝ ያሉ ነበሩ፡፡ ጌታ ግን አላት ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ በእኔ የሚያምን ቢሞት እንኳን ሕያው ነው፡፡ (ዮሐ. 11÷25)
       ችግር ወደ ሕይወታችን ሲመጣ “በኤልሳዕ ዙሪያ ያሉት የእሳት ፈረሶችና ሰረገሎች ተራራውን ሞልተውት ነበር” የሚለውን ማስተዋል ያቅተናል፡፡ ከሶርያ ጭፍሮች መክበብ በላይ በኤልሳዕና በሎሌው ዙሪያ ያሉት ይበልጡ ነበር፡፡ በግልጥ የምናየው በሥጋና በመንፈስ ሠራዊት መካከል ያለ ልዩነት ነው፡፡ በሰማያዊ ኃይልና በምድራዊ አቅም መካከል የነበረ ፍጥጫ ነው፡፡ በእምነትና በራስ ትምክህት መካከል በግልጥ የሚስተዋል ልዩነትም ነበር፡፡ ግያዝ በመንፈስ ከማስተዋል ይልቅ በሥጋ ለመዳኘት የቀረበ ነበር፡፡ ከሰማዩም ይልቅ የምድሩ የቀረበው ነበር፡፡ እግዚአብሔር ግን የብላቴኖችን ዓይን ይከፍታል፡፡ “የቃልህ ፍቺ ያበራል ሕፃናትንም አስተዋዮች ያደርጋል” (መዝ. 119÷130)፡፡
        ተወዳጆች ሆይ በዙሪያችሁ ካሉት ጠላቶች ይልቅ ወዳጆቻችሁ ብዙ ናቸው፡፡ ከከበባችሁ ችግር የከበባችሁ መፍትሔ ይበልጣል፡፡ ከሚወረወረው ቀስት ከሚበረው ፍላፃ ይልቅ እንደ ጋሻ የከበበን እውነት ኃያል ነው፡፡ የምትኖሩበት አገርና መንደር ላልተመቻችሁ እግዚአብሔር በተኩላና በእባብ ላይ ያጫማል፡፡ ባርነት ላንገሸገሻችሁ፣ የሰው ፊት ለጠቆረባችሁ፣ ነፃነት ብርቱ ናፍቆት ለሆነባችሁ እግዚአብሔር አንበሳውንና ዘንዶውን ያስረግጣል፡፡ ጌታ ያለማመንን ቅርፊት ከልባችን ላይ ያንሣ፣ በዓይናችን ላይ ያለውን የኃጢአት ሞራ ይግፈፍ፡፡ ሁሉም የሚያየው ገደል በሆነበት ዘመን ተራራው ላይ ያለውን ከፍታ፣ ከትንሽ እስከ ትልቅ በራደበት በዚህ ጊዜ በዙሪያችን ያለውን የእሳት ሠራዊትና መንፈሳዊ ኃይል በእምነት እንድናስተውል ጸጋ ይብዛልን፡፡                               

2 comments: