Friday, August 3, 2012

ለአፍንጫ ጥላ



       አንድ አባት ለሕፃናት በሚገባቸው መንገድ ለማስተማር የተጠቀሙበት ምሳሌ ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ በአገልግሎት ውጤታማ ላለመሆን እንደ ምክንያት ከሚጠቀሱ ነገሮች መካከል በእድሜ ከፋፍሎ አለማስተማር ዋንኛው ነው፡፡ በእርግጥም ይህንን አስተያየት መሮንም ቢሆን ልንቀበለው ግድ ይሆንብናል፡፡ የእግዚአብሔር ቃል በወተትና በአጥንት ደረጃ ለሰዎች እንደሚቀርብ ስናስብ ሕፃናትና አዋቂዎች በአንድነት በተቀመጡበት ጉባኤ ላይ የትኛውን ዓይነት መልእክት ማስተላለፍ እንዳለብን ግራ ያጋባል፡፡ ምክንያቱም ወተት ብናቀርብ አዋቂዎቹን ወደኋላ እንጎትታቸዋለን፤ አጥንት ብናቀርብ ደግሞ ልጆቹን እንገድላቸዋለን፡፡ በዓለም የትምህርት ስርዓት እንኳን ያለውን የማስተማር ሂደት ስንመለከት በእድሜና በተቀራራቢ የማገናዘብ ደረጃ የተከፋፈለ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ተፈጥሮአዊውን ምክንያት የተከተለ ነው፡፡
        ምሳሌያቸው ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነንም አባት ከሁሉም አይነት እድሜ የተውጣጡ ሰዎች (ሕፃን፣ ወጣት፣ ሽማግሌ) ባሉበት ጉባኤ ላይ ተገኝተው በትምህርት ሰዓት ሕፃናቱ ከጨዋታና ከረብሻ ውጪ ምንም ተሳትፎ እንዳልነበራቸው አስተውለው ለልጆቹ ብቻ መልእክት አስተላለፉ፡፡ መልካም አስተማሪ የሚያሰኘው ትምህርትን ማክበድ ሳይሆን በተቻለ መጠን አሳቡ በሰሚው ልብ ውስጥ በግልጽ መቅረት እንዲችል ማስቻል ነው፡፡ ይህ ማለት ግን ቋንቋና የአቀራረብ ዘዴን ማስተካከል እንጂ የእግዚአብሔርን አሳብ ማስተካከል ማለት አይደለም፡፡ አብዛኛውን ጊዜ የምንመለከተው ግን የእግዚአብሔርን አሳብ እንደግል አሳብ አቅልሎ የማቅረብ ሂደት ነው፡፡ እንዲህ ያለው መንገድ እግዚአብሔር የሚለውን ሳይሆን እኛ መናገርና ሕዝቡ መስማት የሚፈልገውን ነገር በአቅርቦት ማርካት ነው፡፡ ይህ ተናጋሪውንና ሰሚውን ደስ ቢያሰኝም በእግዚአብሔር ዓይኖች ፊት ግን ከፍርድ አያመልጥም፡፡
         ታዲያ እኚህ አባት መንጋትና መምሸትን የሚያዘው ማነው? መፍጠርና ማኖርስ ሥልጣኑ የማን ነው? በሚል ጀምረው ክረምትንም የሚሰጥ፣ ዝናምንም የሚያዘንብ እግዚአብሔር እንደሆነ ተናገሩ፡፡ በልጆቹ ፊት ላይ ይነበብ የነበረው ደስታና የ“ተረድተናል” ምላሽ አስገራሚ ነበር፡፡ በማስከተልም ከዝናብ ጋር አያይዘው ስለ ተፈጥሮአችን ለልጆቹ ማውጋት ቀጠሉ፡፡ “እግዚአብሔር አፍንጫችንን ወደ ላይ አድርጎ ቢሠራው ኖሮ ዝናብ ሲዘንብ ትንንሽ የአፍንጫ ጥላ እንገዛ ነበር፡፡ ታዲያ ድሀ ከየት ያመጣ ነበር?” ሲሉ ሕፃናቱን ጨምሮ ሁላችንም ሳቅን፡፡ መልእክቱ ለሕፃናቱ ተብሎ የተነገረ ቢሆንም እንኳን አዋቂዎችንም የመስበር (የመንካት) አቅም ነበረው፡፡ ከዚህ ምን ተረዳችሁ? እግዚአብሔርን ለማመስገን ከበቂ በላይ ምክንያት አልታያችሁም? ትንንሽ የሚመስሉን ነገሮች ለእግዚአብሔር ትልልቅ ምስጋና የያዙ ስውር ምክንያቶች ናቸው፡፡
        የመገብከኝ እግዚአብሔር ተመስገን ስንል ስለጎረስኩበት እጅና ስለጎረሰው አፌ ተመስገን የምንል ስንቶቻችን ነን? ስለሰማነው የምስራች በእግዚአብሔር ደስ ስንሰኝ ስለሰማንበት ጆሮ የምናመሰግን ምን ያህሎቻችን ነን? ለሚያስተውል ሰው መራመድ፣ ማላመጥ፣ መናገር፣ ማየት ቀላል ሊሆን አይችልም? እኛ ምግቡ ብቻ፣ መሬቱ ብቻ ነው የእግዚአብሔር የሚመስለን፡፡ በእርግጥ እንደ ተባለው አፍንጫ ወደ ላይ ቢሆን ኖሮ ለዚህም መፍትሔ አፈላላጊ ይቋቋም ነበር፡፡ ድሀ ደግሞ በጥላ ካልተሸሸገ አፍንጫን በመኪና ማስጠለል ከየት ይመጣል? እግዚአብሔር በማንኛውም ነገር ላይ አዋቂ ነው!
        አስባችሁት ከሆነ እኛ መቃብር እስክንገባ እንኳን በአግባቡ የማናውቀው የሰውነት ክፍሎች ያሉን ሰዎች ነን፡፡ ምግብ መመገብ የጀመርነው ጨጓራ እንደሚፈጭ በማናውቅበት ሰዓት ነው፡፡ ከመተንፈስ ጋር የተዋወቅነው ስለ ልብ ምት የሰናፍጭ ቅንጣት የምታህል እውቀት ሳይኖረን በፊት ነው፡፡ እግዚአብሔር ምን ለምን እንዳደረገ በሙላት ያውቃል፡፡ አንዳንዴ አንዱ የአካል ክፍላችን ከሌላው ጋር ቦታ ቢቀያየር ምን ዓይነት ገጽታ እንደሚኖረን ስናስበው እንደመማለን፡፡ ሰይጣን የእግዚአብሔርን ምስጋና የሚሰርቅበት መንገድ ያለንን አሳንሶ የሌለንን በማብዛት፣ የያዝነውን አደብዝዞ የሌለንን በማጉላት ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ ትበላላችሁ የሚለው ካላረካን ከዚህች አትብሉ ላይ መውደቃችን የተፈተነ እውነት ነው፡፡
        አንድ ትጉህ አመስጋኝና ዋዘኛ ተገናኙ፡፡ ታዲያ ትጉሁ እግዚአብሔር እስራኤልን በኤርትራ ባህር ያሻገረበትን ታሪክ እያሰበ ሁሉን ቻይነቱን ያመሰግናል፡፡ ይህንን የሰማው ዋዘኛ እርሱ አመስጋኙ እንደሚለው ባህር እንዳልነበረና አነስተኛ ጉድጓድ እንደነበረ በመሆኑም ለዚህ ምንም ማመስገን እንደማይገባ ተናገረ፡፡ ትጉሁም አመስጋኝ ከልብ በሆነ ፈገግታ ውስጥ ሆኖ “አሁን ደግሞ የደነቀኝ እግዚአብሔር ፈርዖንና ሠራዊቱን በጠባብ ጉድጓድ ውስጥ ማስጠሙ ነው” በማለት የዋዘኛውን ተቃውሞ ለበለጠ ምስጋና ተጠቀመበት፡፡ እኛ አጥተን የምናማርረውን ምሬት ተርፎአቸው የሚያማርሩ አሉ፡፡ ክርስትናውን ልዩ የሚያደርገው ግን በመብዛት ብቻ ሳይሆን በመጉደልም ውስጥ ለጌታ የምስጋናን ነዶ ማቅረብ መቻሉ ነው፡፡ እኛ አጠገባችን ላለ ነገር ሩቅ፣ ለጨበጥነውም ነገር ስውር ነን፡፡ ስለዚህ ኑሮዬ ይበቃኛልን መለማመድ ለእኛ ከባድ ነው፡፡
         ለዝናም እንጂ ለብርድ፤ ለፀሐይ እንጂ ለሙቀት፣ ለአካል እንጂ ለነፍስ ገበያ ጥላ የለውም፡፡ ልዑል ግን መጠጊያችን ነው፡፡ ሁሉን የሚችል አምላክ ጥላም ማደሪያችን ነው፡፡ ላባዎቹ ይጋርዱናል፡፡ በክንፎቹም በታች ለዘላለም እንተማመናለን፡፡ ምስጋና ይብዛላችሁ! 

1 comment: