ማክሰኞ የካቲት 5/ 2005 የምሕረት ዓመት
በአንድ ምሽት በአላባማ አደባባይ አንዲት ጥቁር አሜሪካዊት ሴት
በብርቱ ከሚዘንበው ንፋስ የቀላቀለ ዝናብ ራሷን ለማስጠለል እየጣረች ሊፍት የሚሰጣት ሰው በመፈለግ ቆማለች፡፡ ጉልበቶቿ እየተብረከረኩ፣
ንፋስ እያንገዳገዳት፣ በድንግዝግዝ አጥርታ ለማየት እየሞከረች የሚያልፈውን ሁሉ መኪና እጇን ዘርግታ እርዳታ ትጠይቃለች፡፡ ብዙዎች
ለተማጽኖዋ ምላሽ ሳይሰጡ ሄዱ፡፡ አንዳንዶቹም ከለሯን እያዩ “ይበልሽ” አይነት ገላምጠዋትና የመንገዱን ዳር ውሃ እየረጩባት አለፉ፡፡
በመኪናዋ ብልሽት ምክንያት እንዲህ ላለ ጉስቁልና መዳረጓና እንደ እርሷ ሰው የሆኑ ሰዎች ሊረዱዋት አለመቻላቸው አበሳጫት፡፡ ድንገት
ግን ጭብጥ ብላ በቆመችበት አንድ ነጭ ወጣት በ1960ዎቹ የነበረውን ግጭትና በመካከላቸው የተፈጠረውን ልዩነት እንደማያውቅ ሆኖ
መኪናውን ፊት ለፊትዋ አቆመ፡፡ ከሞቀው ውስጠኛ ክፍል ወደ ቀዝቃዛው ወርዶ ሁኔታዋ የሚጠይቀውን ያህል እረዳት፡፡
በተረበሸና በተጣደፈ ስሜት ውስጥ ብትሆንም ከልብ አመስግናው
አድራሻውን ተቀብላ ተለያዩ፡፡ ታዲያ ከሳምንት በኋላ የዚህ ሰው ቤት ተንኳኳ፡፡ በሩን ሲከፍት በስጦታ መጠቅለያ የተሸፈነ ውድ ዕቃ
ደጃፉ ላይ ተመለከተ፡፡ ከጎኑ ደግሞ ልዩ ማስታወሻ የሚል ፖስታ ተቀምጦአል፡፡ በውስጡም ያለው መልእክት እንዲህ ይላል፡- “በዚያች
ምሽት፣ በዚያ አውራ ጎዳና፣ እንደዚያ ባለ ሁኔታ ውስጥ አንድ ትልቅ
ትምህርት በልቤ ላይ አስቀምጠሃል፡- “ሁሉ እንደማይከፋ ተረዳሁ” የአንተ መድረስ እኔን ከጨለማና ከብርድ መታደግ ብቻ ሳይሆን ባለቤቴ
በሞትና በሕይወት መካከል ሳለ ከአልጋው አጠገብ ሆኜ እንድረዳው አድርጎኛል፡፡ ከሁሉ በላይ “ሰው ሁሉ ክፉ” እንዳልሆነ ተረድቼብሃለሁና
ብሩክ ሁን”!