Tuesday, February 12, 2013

ሁሉ አይከፋም


                                ማክሰኞ የካቲት 5/ 2005 የምሕረት ዓመት

          በአንድ ምሽት በአላባማ አደባባይ አንዲት ጥቁር አሜሪካዊት ሴት በብርቱ ከሚዘንበው ንፋስ የቀላቀለ ዝናብ ራሷን ለማስጠለል እየጣረች ሊፍት የሚሰጣት ሰው በመፈለግ ቆማለች፡፡ ጉልበቶቿ እየተብረከረኩ፣ ንፋስ እያንገዳገዳት፣ በድንግዝግዝ አጥርታ ለማየት እየሞከረች የሚያልፈውን ሁሉ መኪና እጇን ዘርግታ እርዳታ ትጠይቃለች፡፡ ብዙዎች ለተማጽኖዋ ምላሽ ሳይሰጡ ሄዱ፡፡ አንዳንዶቹም ከለሯን እያዩ “ይበልሽ” አይነት ገላምጠዋትና የመንገዱን ዳር ውሃ እየረጩባት አለፉ፡፡ በመኪናዋ ብልሽት ምክንያት እንዲህ ላለ ጉስቁልና መዳረጓና እንደ እርሷ ሰው የሆኑ ሰዎች ሊረዱዋት አለመቻላቸው አበሳጫት፡፡ ድንገት ግን ጭብጥ ብላ በቆመችበት አንድ ነጭ ወጣት በ1960ዎቹ የነበረውን ግጭትና በመካከላቸው የተፈጠረውን ልዩነት እንደማያውቅ ሆኖ መኪናውን ፊት ለፊትዋ አቆመ፡፡ ከሞቀው ውስጠኛ ክፍል ወደ ቀዝቃዛው ወርዶ ሁኔታዋ የሚጠይቀውን ያህል እረዳት፡፡
          በተረበሸና በተጣደፈ ስሜት ውስጥ ብትሆንም ከልብ አመስግናው አድራሻውን ተቀብላ ተለያዩ፡፡ ታዲያ ከሳምንት በኋላ የዚህ ሰው ቤት ተንኳኳ፡፡ በሩን ሲከፍት በስጦታ መጠቅለያ የተሸፈነ ውድ ዕቃ ደጃፉ ላይ ተመለከተ፡፡ ከጎኑ ደግሞ ልዩ ማስታወሻ የሚል ፖስታ ተቀምጦአል፡፡ በውስጡም ያለው መልእክት እንዲህ ይላል፡- “በዚያች ምሽት፣ በዚያ አውራ ጎዳና፣ እንደዚያ ባለ ሁኔታ  ውስጥ አንድ ትልቅ ትምህርት በልቤ ላይ አስቀምጠሃል፡- “ሁሉ እንደማይከፋ ተረዳሁ” የአንተ መድረስ እኔን ከጨለማና ከብርድ መታደግ ብቻ ሳይሆን ባለቤቴ በሞትና በሕይወት መካከል ሳለ ከአልጋው አጠገብ ሆኜ እንድረዳው አድርጎኛል፡፡ ከሁሉ በላይ “ሰው ሁሉ ክፉ” እንዳልሆነ ተረድቼብሃለሁና ብሩክ ሁን”!

          ኑሮ ሁለት ጫፍ እንዳለው የሁላችንም ልብ ይስማማበታል፡፡ ማግኘትና ማጣት፣ መወደድና መጠላት፣ መክበርና መዋረድ፣ ማዘንና መደሰት ሁሉም ሰው የሚነካቸው ሁለት ጠርዞች ናቸው፡፡ የዚህን ዓለም አኗኗር ሚዛናዊ የሚያደርገው ነገር ቢኖር ይህ ይመስለኛል፡፡ በሕይወታችን ፈተና ብቻ ሳይሆን ፈታኞችም ይፈራረቃሉ፡፡ በኑሮአችን ድካም ብቻ ሳይሆን አድካሚዎችም ይለዋወጣሉ፡፡ በመንገዳችን ክፋት ብቻ ሳይሆን ክፉዎችም ይመጣሉ፡፡
          ሰው መሆንን ቀላል ከማያደርጉት ነገሮች አንዱ ከፈተናው ጋር ብቻ ሳይሆን ከፈታኙም ጋር ትግል ግድ መሆኑ ነው፡፡ የሕይወት ፈተና በአንድ ክፍል ውስጥ ለአንድ ሰዓት የምንገጥመው የትምህርት ፈተና ዓይነት አይደለም፡፡ ምድሪቱን ከተቀላቀልንበት ጊዜ አንስቶ እስከ መጨረሻዋ የእድሜያችን ህቅታ ድረስ የምንጋፈጠው የእድሜ ልክ እንጂ፡፡
          የአሳብ ጮራ ሲደበዝዝ፣ የልብ ጓዳ ሲጨላልም፣ እግር ከመሄድ፤ እጅ ከመሥራት ሲዝል፣ ጆሮ የሚሰማው ፍርሃት፣ አፍንጫ የሚያሸተው ርኩሰት ሲሆን፤ የመከራ ደመና ሲያጉረመርም፣ የፈተና ዶፍ ሲወርድ፣ ውስጥ ሲንዘፈዘፍ፣ የወዳጅ ድምጽ ሲርቅ፣ የጎረቤት እርዳታ ሲሟጠጥ፣ ያየን ሁሉ ሲያልፈን፣ የቀረበን ሁሉ ሲጸየፈን፣ የዘረጋነው መዳፍ ሲሰበሰብ፣ የተስፋ ዓይን ሲከደን፣ የውስጣችን ብርታት ሲናድ፣ እኔነት ሲቀልጥ፣ በዚያ ጨለማ ውስጥ ብርሃን፣ በዚያ የማያቋርጥ ዝናብ ውስጥ ጥላ፣ በዚያ በሚያንገዳግድ ማዕበል ውስጥ ጸጥታ፣ ጭው ባለው ምድረ በዳ ውስጥ መሪ እግዚአብሔር ነው፡፡  
         እግዚአብሔር ወዳጅ ብቻ ሳይሆን የወዳጅም ዋስትና ነው፡፡ ብዙዎቻችን የትምህርት ደረጃችን፣ የሥራችን ዓይነት፣ የመግባባት ችሎታችን፣ ሰዎችን የማቅረብና የመማረክ ጥበባችን በወዳጅ እንደሚከበን፣ ክፉዎችን ከሕይወታችን እንደሚያጠራልን እናስባለን፡፡ ዳሩ ግን እውነታው ከዚህ የራቀ ነው፡፡ አንዳንዴ እንኳን ጥረታችን አሳባችን የማያቃቸው ሰዎች ለእኛ ሲሟገቱ፣ ከከረመ ባልንጀራ በላይ ሕይወት እስከ መስጠት ሲታመኑ አስተውለን ከሆነ በእውነትም ጌታ የዚህም ዋስትና ነው፡፡ ሰዎችንም እውነተኛ ባልንጀራ የምናደርግበት መንገድ ክርስቶስ ነው፡፡  
         ሰው ለጥላቻው በቂ ምክንያት፣ ለክፋቱ ሚዛን የሚደፋ መነሻ ባይኖረውም በዚህ ውስጥ ካለው ሥጋዊ ደስታ ልቡን አላራቀም፡፡ እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ በመጎዳት የምትመላለሱ ሁሉ ትላንት በሆነው፣ ዛሬ በተፈጠረው፣ ቅድም በሆነባችሁ ነገር ሊመጡ ያሉትን ቀናት እንዲሁም ይዘውት የሚመጡትን ነገር አትኮንኑ፡፡ የመቃብር ሥፍራው እንኳ በግዢ የነበረው የእግዚአብሔር ሰው አብርሃም በዘፍጥረት አሥራ አምስት ላይ አምላኩ እግዚአብሔር በቃሉና በራዕዩ ሲገናኘው እናነባለን፡፡ እንዲህ ሲል፡- “አብራም ሆይ አትፍራ እኔ ለአንተ ጋሻህ ነኝ ዋጋህም እጅግ ታላቅ ነው” (ዘፍ. 15÷1)፡፡
         አብርሃም እንዲህ ያለውን የማጽናናት ቃል የሰማው ከድል ሲመለስ ነው፡፡ ሁላችንም ልንል እንደምንችለው ከድል የተመለሰን ሰው እንዴት አትፍራ ይሉታል? ኮሎዶጎምርንና ከእርሱ ጋር የነበሩትን ነገሥታት ወግቶ የተመለሰን ባለ ጀብዱ እንዴት ጋሻህ ነኝ ይሉታል? ሁላችንም ግልጽ ሊሆንልን የሚገባ አንድ እውነት አለ፡፡ እግዚአብሔር እያንዳንዳችን የምንመፃደቅበትን በጎነት ቢያጥበው ስንት እድፍ ይወጣው ይመስላችኋል? ልብ በሉ እያልኩ ያለሁት ኃጢአታችንን አይደለም፡፡ መልካምነቴ የምንለውን እንጂ፡፡
          አዎ! ሰማያት እንኳ በፊቱ ንፁሕ አይደሉም፡፡ መላእክትንም ስንፍና ይከሳቸዋል፡፡ የሰው ብርታት እግዚአብሔር ፊት እንዲህ ያለ መጽናናት ይፈልጋል፡፡ በብዙ ምርኮ ተምነሽንሾ፣ ከብቱንም ሁሉ አስመልሶ፥ ደግሞም ወንድሙን ሎጥን፣ ሴቶችንና ሕዝቡን መለሰ። አብርሃም ግን እግዚአብሔርን “ምንን ትሰጠኛለህ? እኔም ያለ ልጅ እሄዳለሁ። በቤቴ የተወለደ ሰው ይወርሰኛል” በማለት ከሰው የተሸሸገውን በእግዚአብሔር ዘንድ የታወቀውን ፍርሃቱን ደግሞም የውስጡን ሽንፈት ሁሉን በሚችል አምላክ ፊት አመነ፡፡
         እግዚአብሔር ፈገግታችን ውስጥ ያለውን እንባ፣ መትጋታችን ውስጥ ያለውን ሥንፍና፣ ድላችን ውስጥ ያለውን ሽንፈት፣ መልካምነታችን ውስጥ ያለውን ድካም አሳምሮ ያውቃል፡፡ በማይረዱን ፊት እንደተረዳ፣ በማያዝኑልን ዘንድ እንዳልተጎዳ መስለን እንቀርብ ይሆናል፡፡ አልያም ለጠሉን ጥላቻ፣ ለናቁን ንቀት፣ ለሰደቡን ርግማን ስናሰናዳ ተጠምደን ይሆናል፡፡ ተወዳጆች ሆይ ጌታ ሁሉን ያውቃል፡፡ አብርሃም እግዚአብሔርን ስለ አንድ ልጅ ሲያወራው እግዚአብሔር ደግሞ አብርሃምን እንደ ሰማይ ከዋክብት ስለሚበዛ ዘር ያወራው ነበር፡፡
          እግዚአብሔር ያውራን! እኛ ብናወራ ስለ ብቸኝነት፣ እኛ ብናወራ ስለ ከፉብን፣ እኛ ብንናገር ስለ ቀን ጨለማ፣ እኛ ብንተርክ ስለ ጉዳት፣ እኛ ብንራቀቅ ሥጋት፣ እኛ ብንጠበብ ልፋት፣ እኛ ብንተጋ ልፋት እረ እግዚአብሔር በታሪካችን ይግባ፡፡ በእኛና በፍርሃት፣ በእኛና በብቸኝነት፣ በእኛና ባለ ማስተዋል፣ በእኛና በከበዱብን ነገሮች መሐል እግዚአብሔር ይቁም፡፡ አብርሃም ጥቂቱን ለምኖ እግዚአብሔር ብዙ አደረገለት፡፡ የሚቆጠርልን ጽድቅ እንዲ የምናስቆጥረው ጽድቅ አለመኖሩን መረዳት ከአጉል ታይታ ይሰውራልና እናስተውል፡፡
         አብርሃም የዕለቱ እንኳ በደንብ ያልገባው፣ በራሱ እድሜ ሊሆን ያለውን ነገር በቅጡ የማያውቅ ሰው ነበር፡፡ እግዚአብሔር ግን አብርሃም ከሞተ በኋላ ስለ ሕዝቡ መማራክ፣ በግብጽ ባርነት ለ400 ዓመት መቀመጥ፣ በእግዚአብሔር ፈራጅነት ስለ ሕዝቡ አርነት መውጣት ይነግረው ነበር፡፡ በእውነት እግዚአብሔር እንደሚያይ ማየት የጥያቄዎቻችን ሁሉ መልስ ነው፡፡ ዋጋ እንደሌለው የተሰማውን አብርሃም እግዚአብሔር ዋጋህ ነኝ አለው፡፡ እግዚአብሔር አዋቂ ነው፡፡ ከሚያውቀው የምናውቀው ምንኛ ጥቂት ነው?
         እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር ቃል ኪዳን ያደረገው ፀሐይ በገባችና ታላቅ ጨለማ በሆነ ጊዜ ነው፡፡ እግዚአብሔር በጨለማዎቻችን መሐል ብርሃን አለው፡፡ በመራራዎቻችን መሐል ጨው አለው፡፡ የቱንም ያህል በከፋባችሁ ነገር ውስጥ ያለ መፍትሔ የማይተዋችሁ እግዚአብሔር የታመነ ነው፡፡ በአዲስ ኪዳን እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ቃል ኪዳን ያደረገው ፀሐይ ጠልቃ፣ ምድር በጨለማ ተወርሳ፣ የእግዚአብሔር ልጅ መስቀል ላይ ተሰቅሎ ነው፡፡ ዛሬም ጨለማውን ሰንጥቆ፣ ጭጋግና ዝናቡን አቋርጦ እጅግ ካማረው ምቹ ስፍራ ዝቅ ብሎ፣ ሁኔታችን በሚጠይቀው ልክ የሚረዳን ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፡፡ እርሱ ካላችሁ ሁሉና ሁሌ አይከፋም፡፡ ከሰው ብቻ ሳይሆን ከራሳችንም ሽሽት የሚሰውር ጥላ እግዚአብሔር ስሙ ይቀደስ፡፡

4 comments:

  1. Geta Abezeto Tsegawen yabezalachu ke'zeh yeblet endeteseru behalu cehelt yeberetachu hunu. tebareku

    ReplyDelete
  2. Geta Eyesus abzito Yebarkeh !!

    ReplyDelete
  3. betammmmmmmmmmmmmmmmm tebarek !!!!!!!!!!!!!!!!!!!

    ReplyDelete