ማክሰኞ ጥር 28/2005 የምሕረት ዓመት
በመጀመሪያው
ክፍል ንባባችን በጋብቻው ቀን ትታው ዕጩ ባሏን በሰው ሁሉ ፊት እንደማታገባው ነግራው ስለሄደች ሴት አውርተን ነበር፡፡ ወደ ዛሬው
አሳብ ከመሸጋገራችን በፊት ያለፈውን ጥያቄ እንመልስላችሁ፡፡ ሴቲቱ ጥላው እንድትሄድ ምክንያት የሆናት ነገር ምን መሰላችሁ? በእጮኝነት
አብረው ባሳለፉባቸው ጊዜያት ሁሉ መደበኛ ፊርማው ምን ይመስል እንደነበር ስለምታውቅ የጋብቻቸው ቀን የፈረመው ፊርማ ትልቅና ደማቅ
በመሆኑ ይህም ከሁል ጊዜው የተለየ አዲስ በመሆኑ ምክንያት ነው፡፡ ይህ ለብዙዎቻችን ስሜት አይሰጥ ይሆናል፡፡ ዳሩ ግን ለዚህች
ሴት ትልቅ መልእክት ነበረው፡፡ የመጀመሪያው “በዚህ ሰው ውስጥ የማላውቀው አዲስ ጠባይ አለ ማለት ነው” የሚል ሲሆን፤ ሁለተኛው
ደግሞ “በትዳር ውስጥ ሊያሳየኝ ያለውን አምባገነናዊ አባወራነት የሚጠቁም ነው” የሚል ይሰኛል፡፡ በዚህ ሰው እውነተኛ ጠባይ ላይ
የተደረገ በቂ ጥናት ይኑር አይኑር ባናውቅም በዚህች ሴት ስነ ልቦና መሠረት ግን የእጮኛዋ ጊዜ ጠብቆ ፊርማ መለወጥ ትልቅ መልእክት
አስተላልፎላታል፡፡
የብዙ ባለ ትዳሮች አንዱ ሙግት “አዲስ ጠባይ” ነው፡፡ ካገባሁት
በኋላ አዲስ ሆነብኝ፣ የማልላመደው ጠባይ ገጠመኝ የሚል ሮሮ፡፡ ነገር ግን ምን ያህል ሰዎች ናቸው ከጋብቻ በፊት በሚኖረው አብሮነት
(በተአቅቦ) እንደሚገባ የሚተያዩት? በሰውየው ከሚሸሸገው ጠባይ በላይ በእኛ አለማስተዋል ምክንያት በቸልታ የሚታለፍ የተገለጠ ጠባዩ
ይበልጣል፡፡ በሕብረት ውስጥ ሁሉንም ማጥራት ባይቻልም ቢያንስ ችግሮቹን በአግባቡ ለይቶ ማወቅ ባያሳርፍ እንኳ ያዘጋጃል፡፡ ነገር
ግን ስሜታችንን ብቻ እያዳመጥን ቸል የማይባሉ ነገሮችን (ትንንሾቹን ጨምሮ) ብንዘነጋቸው ዋጋ መክፈላችን አይቀሬ ነው፡፡ ከዚህ
በታች የሳይኮሎጂ ባለ ሙያ የሆነ አንድ ወንድም የላከልንን እናስነብባችኋለን፡፡
Commitment intimacy
Passion
“ፍቅር በሳይኮሎጂ እይታ
ስለ ፍቅር መጽሐፍ ቅዱስ፣ የተለያዩ ባለ ሙያዎች እንዲሁም ግለሰቦች
ብዙ ብለዋል፤ እኛም ብዙ ሰምተናል ብዙ ብልናል፡፡ ለዛሬ ግን የሳይኮሎጂ ባለ ሙያዎች ስለ ፍቅር የሰጡትን ሙያዊ ትንታኔ ከራሳችን
ነባራዊ ሁኔታ ጋር እያነጻጸርን እንመለከታለን፡፡ ከብዙዎቹ የስነ ልቦና ባለ ሙያዎች መካከል ግልጽ በሆነና በማያሻማ ሁኔታ ስለ
ፍቅር ትንታኔ የሰጠ ባለ ሙያ ስተርንበርግ ይባላል፡፡ ይህ ባለ ሙያ እንደሚነግረን አንድ ሰው እየተሰማው ያለው ስሜት ፍቅር ይሁን
አልያ ተራ ስሜት ማወቅ የሚቻለው እነዚህ ሦስት የፍቅር መሰረታዊያን
መኖር ሲችሉ ነው፡፡ እነዚህ የፍቅር መሰረታዊያን ምን ምን ናቸው? በማለት ስንዘረዝራቸው፡ -
1. Commitment (አዕምሮአዊ ዝግጁነት)፡- ማለት ሰዎች ለሚወዱት ሰው
ማንኛውንም አይነት መሥዋዕትነት ለመክፈል ያላቸው አእምሮዊ ዝግጁነት
ነው፡፡ ይህንን ነገር ስንመለከት ቀለል ያለ ነገር መስሎ ሊሰማን ይችላል፡፡ ነገር ግን እኛን የሚቆጣጠር የሰውነታችን አካል አዕምሮአችን
በመሆኑ አዕምሮአችን ያላሰበበትን እና ያልተቀበለውን ዝግጁነት በተግባርም ሆነ በቃል ማሳየት አይቻልም፡፡ ያለ ዝግጅት ደስታውም
መርዶ ነው እንዲሉ አእምሮአዊ ዝግጅት ማድረግ ላመንበት ነገር ልንከፍል ያለውን ዋጋ ይወስነዋል፡፡ ስለዚህ ስለ ፍቅር ስታስቡ አእምሮአዊ
ዝግጅትን ትኩረት ልትሰጡበት አግባብ ነው፡፡
2. Intimacy (ጥልቅ የሆነ የስሜት መናበብ)፡- ይህን ቃል ብዙውን ጊዜ ሰዎች
ሲጠቀሙበት እንሰማለን፡፡ ይህ ማለት በሁለት የሚዋደዱ
ሰዎች መካከል ያለ አንዱ የአንዱን ስሜት የመረዳት፣ የመጠበቅ ከፍ ሲልም ከቃላት በዘለለ መልኩ በስሜት መደጋገፍን ያጠቃልላል፡፡
በፍቅር ውስጥ አንዱ ሌላውን የሚረዳበት መንገድ በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡ የመግባባት መስመሩም ይኸው ነው፡፡ መገናዘብ ባለበት ሁኔታ
አለመግባባቶች ስፍራቸው ትንሽ ነው፡፡ አብዛኛው ጭቅጭቅ ጥልቅ የሆነ የስሜት አለመናበብ የሚያመጣውም ጭምር ነው፡፡
3. Passion (ጥልቅ የሆነ ስሜትን በተግባር መግለጥ )፡- ስሜት ቃሉ ራሱ እንደሚያስረዳው
በተግባርና በቃላት ካልተገለጠ በቀር ከሚሰማው ሰው ውጪ ሌሎች ሊያውቁትና ሊረዱት አይችሉም፡፡ ስለዚህ ለምንወዳቸው ሰዎች ስሜቶቻችንን
በቃላትና በድርጊት መግለጽ ያስፈልጋል፡፡ የሚገለጽበት መንገድ በቃል እወድሃለሁ/እወድሻለሁ ብሎ በቃል ከመግለጽ ጀምሮ በድርጊታዊ
መቀራረቦችንም ያጠቃልላል፡፡ እነዚህን የፍቅር መሰረታዊያን መሰረት
በማድረግ የተለያዩ አይነት የፍቅር አይነቶችን ለመመልከት እንሞክራለን፡-
v Liking፡- በዚህ
አይነቱ ፍቅር ውስጥ Intimacy (ጥልቅ የሆነ የስሜት መናበብ)
ብቻ እንጂ አዕምሮአዊ ዝግጁነትም (Commitment) ሆነ ጥልቅ የሆነ ስሜትን በተግባር መግለጥ (Passion)
አይገኝበትም፡፡ ይህ አይነቱ ፍቅር በብዙ መልኩ በተለምዶ የአይን
ፍቅር ከሚባለው ጋር ይመሳሰላል፡፡ በዚህ አይነት ስሜት ውስጥ ያሉ ሰዎች መውደዳቸውን በስሜቶቻቸው ለመግለጽ ይሞክራሉ፡፡ ይህ አይነቱ
የመውደድ ስሜት ዘላቂ አይደለም፡፡
v Infatuate love፡- ይህንን አይነቱን ስሜት የፍቅር አይነት ብሎ ለመጥራት በጣም አስቸጋሪ
ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ስሜትን በተግባር ከመግለጽ ባለፈ ምንም አይነት አዕምሮአዊ ዝግጁነትም (Commitment) ሆነ Intimacy ( ጥልቅ የሆነ የስሜት መጋራት የለውም፡፡ ይህ
ጊዜያዊ የሆነ ፍትወትን ለማርካት የሚደረግ ሩጫ እንጂ ዘላቂ ለሆነ ግንኙነት አይጨነቅም፡፡ እንዲህ ያለውን “ተቀብሎ ሸሽ” ልንለው
እንችላለን፡፡ ጥልቀት የለውምና እድሜ አይኖረውም፡፡
v Romantic love:- በዚህ አይነቱ ፍቅር ውስጥ ጥልቅ የሆነ የስሜት መናበብና (Intimacy)
ይህንንም ስሜት በተግባር መግለጽ ቢኖርም ዳሩ ግን ለሚወዱት ሰው መሥዋዕትነትን ለመክፈል የሚያስችል ምንም አይነት አዕምሮአዊ
ዝግጁነት (Commitment) የለም፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው ሰዎች ከጋብቻ ውጭ ያላቸው ግንኙነት ነው፡፡
v Companionate love:- ይህን አይነቱን ፍቅር ለመረዳት ረጅም ጊዜ በትዳር አብረው
የቆዩና ልጆች የወለዱ ባለ ትዳሮችን መመልከት በቂ ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ አዕምሮአዊ ዝግጁነትም (Commitment) ሆነ ጥልቅ የሆነ የስሜት መጋራትና መረዳዳት (Intimacy) ቢኖርም በተግባር የሚገለጽ ነገር ግን አይኖርም፡፡ ለዚህም ነው ብዙ ሰዎች ተጋብተው
ልጅ ከወለዱ በኋላ አንድ አልጋ ላይ ተኝተው “አይተዋወቁም” ጥናቶችም
እንደሚያሳዩት ለብዙዎች ትዳር መፍረስ ዋነኛው መንስኤ እንዲህ ያለው ምክንያት ነው፡፡
v Consummate love:- እንግዲህ ደስተኛ፣ ስኬታማና ፍሬያማ የሆነ የፍቅር ግንኙነት
እንዲኖራቸው የሚፈልጉ ሰዎች ማንኛውንም አይነት መሥዋዕትነት ለመክፈል የሚያስችል አዕምሮአዊ ዝግጁነት (Commitment) ፣ ጥልቅ
የሆነ የስሜት መናበብና (Intimacy) ጥልቅ የሆነ ስሜትን በተግባር መግለጥ (Passion)
የሚችል ፍቅር አስፈላጊ ነው፡፡”
በሄኖክ
ኃይሉ (የሳይኮሎጂ ባለ ሙያ)
የእውነተኛ ፍቅር ምክንያቱ እራሱ ፍቅር ብቻ ነው። አፍቃሪው ከተፈቃሪው በምላሽ የሚጠብቀው ነገር የለም። ተፈቃሪው ምንም አይነት ሕፀፅ /ጉድለት/ ቢኖርበት አፍቃሪው በሚሰጠው ፍቅር አይቆጭም። ተፈቃሪው የተሰጠውን ፍቅር አቃሎ ወይም ዘንግቶ በደል ቢበድል እንኳ አፍቃሪው ልፋቴ ከንቱ ቀረ ብሎ አይቆጭም። ፍቅር መስጠትን እንጂ መቀበልን ሂሳብ ውስጥ አያስገባምና። አፍቃሪው ሁል ጊዜ የሚጨነቀው ስለ ተፈቃሪው እንጂ ስለ እራሱ አይደለም።
ReplyDeleteይህን ፍቅር የምንማረው እራሱ ፍቅር ከሆነ ከእግዚአብሔር ነው።