ማክሰኞ መጋቢት
17/2005 የምሕረት ዓመት
“. . . በዚህም ዓለም ተስፋን
አጥታችሁ ከእግዚአብሔርም ተለይታችሁ ያለ ክርስቶስ ነበራችሁ፡፡ አሁን ግን እናንተ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁ በክርስቶስ ደም ቀርባችኋል፡፡”
(ኤፌ. 2÷12)
ምድራችን ሰዎች ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላት የሚራወጡባት አደባባይ ናት፡፡
ከትንሽ እስከ ትልቅ ሁሉ ለፍላጎቱ ከእንባ ጀምሮ እስከ ሞት ድረስ ዋጋ ሲከፍልም እንመለከታለን፡፡ በተገኘው አጋጣሚና በቻለው መጠን ሁሉም ሀዘኑን በደስታ፣ ሁከቱን በሰላም፣
ማጣቱን በማግኘት፣ ውርደቱንም በክብር ለመለወጥ ጥረት ያደርጋል፡፡ አቅም እምቢ ቢል እንኳ አሳብ ይፍጨረጨራል፡፡ ሰው ሁሌና ሁሉ
እንደማይሞላ መረዳቱ አያሳርፈውም፡፡ እንዲያውም ከፊት ይልቅ ጥማቱ እየጨመረ ይመጣል፡፡ ነገር ግን በዚህ ዓለም የሚኖረንንን ሩጫ
መጨረሻው ምን እንደሆነ ስንፈትሸው ከሥጋ ስኬት የዘለለ ሆኖ አናገኘውም፡፡ ብዙ ሰው ከደህና ቤተሰብ አለመወለዱ፣ አድጎ በተሻለ የኑሮ ደረጃ ላይ ራሱን
አለማግኘቱ፣ ከባልንጀሮቹ እኩል በሥጋ ነገር አለመለወጡ፣ በዚህ ዓለም ነገሮች የተደላደለ ነገር በሕይወቱ ብዙ ጉድለት መኖሩ የብቻ
አሳብ አጀንዳው፤ የሰው ፊት የወሬ ርዕሱ ነው፡፡
የእግዚአብሔር ቃል ስለ ሰው ልጆች ትልቅ ጉዳት ሲናገር ግን “ያለ ክርስቶስ ነበራችሁ” ይላል፡፡
ሐዋርያው በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን ክርስቲያን ለሆኑ የኤፌሶን ምእመናን “ነበራችሁ” በማለት የሆነላቸው ነገር ከነበሩበት ኑሮ
ምን ያህል የላቀና እንደ አዲስ መፈጠር እንደ ሆነ ያስረዳል፡፡ ሰው ተስፋን ካጣ የመኖር ትልቅ ኃይሉን አጣ ማለት ነው፡፡ ሀብትና
ቁሳቁስ፣ ሥልጣንና ክብር ኖሮን ተስፋችን ከሞተ ግን ሕይወት ትቀጥ ዘንድ በቂ አቅም ታጣለች፡፡ ተስፋ ሁለነገራችን የተያያዘበት ሰንሰለት ነው፡፡ ሰው ተስፋው ከተቆረጠ ሕይወት እንድትቀጥል ዕድል
የለውም፡፡ በባሰ ነገር ላይ ተቀምጠን የተሻለ የምንጠብቀው ተስፋ ስለምናደርግ ነው፡፡ የሰውን ኃጢአተኝነት ተከትሎ የመጣው ቀላል
የማይባል ውድቀት እንዲሁም የእግዚአብሔር ፍርድ ነው፡፡ በሰው ሕይወት ውስጥ የዔደን ገነትን ለቅቆ ከመውጣት ጋር በተያያዘ ብርቱ
ተስፋ ነበር፡፡ ያም መዳናችን ነው! ብዙዎች ሳያዩ የተስፋውን ቃል በማመን ከዚህ ምድር አልፈዋል፡፡ እኛ ግን እንዲህ ያለውን መዳን
ከዚህ ምድር ጀምሮ እንድናጣጥም ጌታ ረድቶናል፡፡