Tuesday, March 5, 2013

አሜን እንደ አቀበት




ማክሰኞ የካቲት 26/2005 የምሕረት ዓመት

         የሰዓቱ መገስገስ፣ የሰማዩ  መዳመን፣ የንፋሱ ሽውታ፣ የጀንበርዋ ማዘቅዘቅ፣ ልክ እንደ ገደል ማሚቱ ኑሮዬን ያሳበቀብኝ ያህል ተሰማኝ፡፡ ከጥያቄ ወደበለጠ ጥያቄ፣ ከእንባ ወደ ባሰ እንባ፣ ከፈተና ወደ ብርቱ ፈተና መገላበጤን ልቤ ልክ እንደ ሰው እየታዘበው ለዚህ የተፈጠርኩ ያህል ቆጥሬው የአሳብም የእግርም ጉዞዬን በምሬት ኃይል እገፋለሁ፡፡ ትላንትና ዛሬ፤ ቅድምና አሁን ተጨፍልቀው አንድ ሆነውብኛል፡፡

     ሁሉም ነገር ለምሬት ምክንያት የሆነ ያህል ተሰማኝ፡፡ ከሰው ዘንድ ምክርም ልግስናም ጨርሻለሁ፡፡ የባሰ ነግረው ሊያጽናኑኝ፣ ስለተጎዳ አውርተው ሊጠግኑኝ፣ ከኑሮ ተሞክሮአቸው መክረው ሊመልሱኝ ብዙ ጊዜ ሞክረዋል፡፡ ይህ ግን ችግሬን ለማረሳሳት እንደ ማዳፈኛ ያህል ብቻ ነበር እንጂ ዘላቂ እረፍት አልሰጠኝም፡፡ ከሰው ቃል የእግዚአብሔር ቃል፣ ከሥጋ ለባሽ ማጽናናት የመንፈስ ቅዱስ ማጽናናት፣ ከምድራዊ መፍትሔ የመለኮት ምላሽ እንዲሻል ልቤ ግድ ስላለኝ አሳቡ ከሚሰበክበት፣ ምስጋናው ከሚደርስበት፣ ኃጢአተኛ በምሕረት ከሚመለስበት አደባባይ ለድምፁ ቅርብ፣ ለታዳሚው ሩቅ ሆኜ ጥግ ላይ ቁጭ አልኩ፡፡ የመከራዬ እድሜ እንደተደገፍኩት የጥድ ዛፍ ያህል መሰለኝ፡፡ በዕለቱ የነበረው ሰባኪ “እግዚአብሔር አለ” ሲል ቃሉ ጆሮዬ ጋር ደረሰ፡፡ ሕዝቡ ሁሉ ከፍ ባለ ድምፅ “አሜን!” አሉ፡፡
        
       ባለፉት ልምምዶቼ አሜንታ እንደ እኔ የሚቀለው፣ አፉንም ሞልቶ የሚናገረው አልነበረም፡፡ አሁን ግን እሩቅ እንዳለ የማስበውን እግዚአብሔር ቀርቶ የራሴን ሕልውና እንኳን እጠራጠራለሁ፡፡ እነርሱ እንደ መለሱት ልመልስ፣ እንደተስማሙት ልስማማ ውስጤ ታገለኝ፡፡ እናም ተሸነፍኩ፡፡
         
        የሰዉን ደጋግሞ አሜን ማለት ልቤ ታዘበው፡፡ በእርግጥ የእውነት ከአሳቡ ጋር ተስማምተው ነውን? ብዬ ራሴን በብርቱ ጠየኩ፡፡ ሰባኪው ከብዙ ማብራሪያ በኋላ እንደገና “እግዚአብሔር ፈዋሽ ነው” በማለት ተናገረ፡፡ የጉባኤው ታዳሚ ሁሉ በአንድነት ከፊት ይልቅ አሜን አለ፡፡ እኔ ግን አቅም አጣሁ፡፡ የተረሳሳን ሕመሞቼ እንኳ በአሳብ አገረሹብኝ ያጣሁት እንቅልፍ፣ ፆሙን ያደረው ሆዴ፣ ለአመት በዓል ዳቦ እንደተለኮሰ እሳት የሚነደው ራሴ፣ እያዘዘኝ ያለው ላዘው ያልቻልኩት እንባዬ፣ ውስጤን የሚንጠው ብሶት ብቻ ሁሉም ደቦ ተጠራርተው ፊቴ ላይ ቆሙ፡፡ ለሕዝቡ እንደ ምቹ ሜዳ ለመገስገስ የቀለለው አሜን ለእኔ የማልወጣው ተራራ፣ የማላቋርጠው አቀበት ሆነብኝ፡፡ ወትሮ እንደ ልቤ የምናገረውን በማስተዋል ውስጥ ሆኜ ልናገረው አቅም ከዳኝ፡፡ ለሌሎች የቀለላቸው አሜን እኔን አልቀልሽ አለኝ፡፡  
 
        በተረጋጋ ማንነት፣ በሚማርክ ለዛ፣ በተዋበ ድምፅ ያ ሰባኪ “እግዚአብሔር ተዋጊ ነው” ብሎ ምራቅ የመዋጥን ያህል ዝም አለ፡፡ እኔም ውስጤ ዝም ሲልብኝ ተሰማኝ፡፡ እርሱ ምራቁን ለመዋጥ እኔ ግን እየተገረፈ ዋጥ አድርጋት እንደሚባል ሕፃን በዝምታ ወደ ውስጥ ስቅስቅ ብዬ አነባሁ፡፡ በደካማ ጎኔ ገብተው የፈተፈቱ፣ በቃል በኑሮዬ የተዘባበቱ፣ በነገር ቀስት፣ በአመጽ ፍላፃ እድሜዬን በመከራ የለቀለቁ በየስማቸው ሕሊናዬን ከበቡኝ፡፡ እኔም አሜን አቃተኝ፡፡

        የተበደልኩትን እያሰብኩ፣ በቁስሌ ላይ የተሰደደውን ጦር እያሰላሰልኩ፣ የተዋጉኝን፣ መስመር ያሳቱኝን፣ በዓላማ ያሳደዱኝን፣ ጠግበው እያገሱ ቁራሽ የቀሙኝን፣ በእልፍኝ ተኝተው አጎዛ የነጠቁኝን እያስታወስኩ አሜን እንቢ አለኝ፡፡ እግዚአብሔርንም ከእነዚህ ልደምረው ዳዳኝ፡፡ የተነገረው ቃል ለእኔ ዘብ ሳይሆን ባላንጣ ተደርጎ መሰለኝ፡፡ እርሱ ሲነሣ ጠላቶቹ እንደሚበተኑ ከሰባኪው ማብራሪያ መካከል ደጋግሞ ይታወሰኛል፡፡ ታዲያ እኔ የእጁ ሥራ አይደለሁምን? ፈተና ሲንጠኝ አይገደውምን? በእጁ ለተቦካ ጭቃ፣ በእስትንፋሱ ሕያው ለሆነ ፍጡር ይጨክናልን? ለእኔ የሚነሣው መቼ ነው? የእኔ ጠላቶች የሚበተኑትስ መቼ ነው? ተዋጊ ነው! ሲል እኔን እየተዋጋኝ ይሆን? ብዬ ጠረጠርኩት፡፡ ደግሞ ሌላ ከአሳቤ የሚያባትት ቃል ሰባኪው ተናገረ “እግዚአብሔር ጽድቃችን ነው”፡፡ ጽድቅ ምን ማለት ነበር? አፍታም ሳይቆይ ወዲያው ተመለሰልኝ “እግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት ማግኘት”፡፡

        ሰው ፊት ተቀባይነት ያጣች ምስኪን፣ በእራሷ ውስጥ የጠፋች ብኩን፣ ሸክም የሚያንገዳግዳት ድኩም፣ ኃጢአት የሚንጣት ባዛኝ እንዴት በሰማይ ተቀባይነት ታገኛለች? እግዜር ትቶኝም አይደል እንዲህ ከመከራ ጋር ተለውሼ ከፈተና ጋር ተቦክቼ የምኖር? እውነት ነው! እግዚአብሔር ትቶኛል፡፡ ለልመናዬ ጆሮ፣ ለጥያቄዬ የአንደበት መልስ የለውም፡፡ ድምፄን አውትቼ አዎ የለውም! ስል በሩቅ የሰሙኝ የቀለላቸውን አሜን እያስተጋቡ ገላመጡኝ፡፡ እኔ ግን ትንፋሼ ቁርጥ ቁርጥ እያለ አቀበቱን መጨረስ አቃተኝ፡፡
        በረጅሙ እየተነፈስኩ ጽድቁ ቀርቶብኝ በአግባቡ በኮነነኝ አልኩና ደግሞ የኩነኔ አግባብ ምንድነው? እያልኩ ባልገባኝ መገረም ጀመርኩ፡፡ በጎነት የለኝም፤ በጎነት ከየት አገኛለሁ? በእርሱ ፊት የሚያቆም፣ ሞገስን የሚያሰጥ በእኔ ውስጥ ከቶ ምን ይገኛል? ተስፋ መቁረጥ እንደ ክፉ ባልንጀራ አግድም አየኝ፡፡ ከዚህ የተለየ ዕጣ እንደሌለኝ ለራሴ ነገርኩት፡፡ 
     
       በመጨረሻ ግን ሰባኪው አሜንን ማብራራት ጀመረ፡፡ “አሜን የሆነው፤ የታመነውና እውነተኛው ምስክር የዓለም መድኃኒት ክርስቶስ ኢየሱስ ነው” (ራዕ. 3÷14) አለ፡፡ ጉባኤው በጸጥታ ተዋጠ፡፡ እኔ ግን አሜንታዬን አቀለጥኩት፡፡ ከሰዉ መገረም በላይ እኔ ለእኔ ገረመኝ፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር መስማማት ምን ማለት እንደሆነ ለልቤ ተብራራልኝ፡፡ አቀበት ኑሮዬ ሜዳ ሲሆን፣ ዐለቱ ችግሬ ሲፍረከረክ፣ ጉብታው ስቃዬ ሲናድ፣ ለዘመናት የገዛኝ ሰንሰለት ሲፈታ ተሰማኝ፡፡ እናም በልቤ ተቀኘሁ፡-    

መብዛትና መጉደል በፊትህ ምንድነው
የአንተ ጸጋ ዙፋን ለሁሉም መልስ ነው፡፡
ስንፍና አላወራም በክብርህ ከፍታ
መልስ ነህ ለቤቴ አንተ ካለህ ጌታ፡፡
በእንጀራ አትታማም ሥጋህን ሰጥተሃል
እንደ ዐለት ልብ ውኃ ደምህን አፍስሰሃል፡፡
ማዕረግ ያየ የለም በእቅፍህ እንደኔ
ማለፍ የሌለብህ አንተ ነህ ወገኔ፡፡ አሜን!

5 comments:

  1. Amen!!!!!!!!!! tinfash yemigeza, lib yemineka tsihuf new. awon Eyesus yetiyakewochachin hulu mels new!

    ReplyDelete
  2. AMEN AMEN AMEN!!!

    ReplyDelete
  3. esus ewnetnew gin....





    ReplyDelete
  4. esus ewnet new. gin.....

    ReplyDelete