ማክሰኞ መጋቢት
17/2005 የምሕረት ዓመት
“. . . በዚህም ዓለም ተስፋን
አጥታችሁ ከእግዚአብሔርም ተለይታችሁ ያለ ክርስቶስ ነበራችሁ፡፡ አሁን ግን እናንተ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁ በክርስቶስ ደም ቀርባችኋል፡፡”
(ኤፌ. 2÷12)
ምድራችን ሰዎች ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላት የሚራወጡባት አደባባይ ናት፡፡
ከትንሽ እስከ ትልቅ ሁሉ ለፍላጎቱ ከእንባ ጀምሮ እስከ ሞት ድረስ ዋጋ ሲከፍልም እንመለከታለን፡፡ በተገኘው አጋጣሚና በቻለው መጠን ሁሉም ሀዘኑን በደስታ፣ ሁከቱን በሰላም፣
ማጣቱን በማግኘት፣ ውርደቱንም በክብር ለመለወጥ ጥረት ያደርጋል፡፡ አቅም እምቢ ቢል እንኳ አሳብ ይፍጨረጨራል፡፡ ሰው ሁሌና ሁሉ
እንደማይሞላ መረዳቱ አያሳርፈውም፡፡ እንዲያውም ከፊት ይልቅ ጥማቱ እየጨመረ ይመጣል፡፡ ነገር ግን በዚህ ዓለም የሚኖረንንን ሩጫ
መጨረሻው ምን እንደሆነ ስንፈትሸው ከሥጋ ስኬት የዘለለ ሆኖ አናገኘውም፡፡ ብዙ ሰው ከደህና ቤተሰብ አለመወለዱ፣ አድጎ በተሻለ የኑሮ ደረጃ ላይ ራሱን
አለማግኘቱ፣ ከባልንጀሮቹ እኩል በሥጋ ነገር አለመለወጡ፣ በዚህ ዓለም ነገሮች የተደላደለ ነገር በሕይወቱ ብዙ ጉድለት መኖሩ የብቻ
አሳብ አጀንዳው፤ የሰው ፊት የወሬ ርዕሱ ነው፡፡
የእግዚአብሔር ቃል ስለ ሰው ልጆች ትልቅ ጉዳት ሲናገር ግን “ያለ ክርስቶስ ነበራችሁ” ይላል፡፡
ሐዋርያው በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን ክርስቲያን ለሆኑ የኤፌሶን ምእመናን “ነበራችሁ” በማለት የሆነላቸው ነገር ከነበሩበት ኑሮ
ምን ያህል የላቀና እንደ አዲስ መፈጠር እንደ ሆነ ያስረዳል፡፡ ሰው ተስፋን ካጣ የመኖር ትልቅ ኃይሉን አጣ ማለት ነው፡፡ ሀብትና
ቁሳቁስ፣ ሥልጣንና ክብር ኖሮን ተስፋችን ከሞተ ግን ሕይወት ትቀጥ ዘንድ በቂ አቅም ታጣለች፡፡ ተስፋ ሁለነገራችን የተያያዘበት ሰንሰለት ነው፡፡ ሰው ተስፋው ከተቆረጠ ሕይወት እንድትቀጥል ዕድል
የለውም፡፡ በባሰ ነገር ላይ ተቀምጠን የተሻለ የምንጠብቀው ተስፋ ስለምናደርግ ነው፡፡ የሰውን ኃጢአተኝነት ተከትሎ የመጣው ቀላል
የማይባል ውድቀት እንዲሁም የእግዚአብሔር ፍርድ ነው፡፡ በሰው ሕይወት ውስጥ የዔደን ገነትን ለቅቆ ከመውጣት ጋር በተያያዘ ብርቱ
ተስፋ ነበር፡፡ ያም መዳናችን ነው! ብዙዎች ሳያዩ የተስፋውን ቃል በማመን ከዚህ ምድር አልፈዋል፡፡ እኛ ግን እንዲህ ያለውን መዳን
ከዚህ ምድር ጀምሮ እንድናጣጥም ጌታ ረድቶናል፡፡
በባርነት ውስጥ ያለ ሰው ጥያቄው ዳቦ፣ ልብስና መጠለያ ሊሆን አይችልም፡፡
ብቸኛ ሙግቱ ነፃነት ነው፡፡ በቅኝ የተገዙ ሕዝቦች ነፃነት ምን ማለት እንደሆነ ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ እንዲህ ባለው አስጨናቂ ዘመን
ግን ተስፋ ትልቁ መሳሪያቸው ነበር፡፡ ያሠራቸው እንዳሰራቸው፣ ያስጨነቃቸው እንዳስጨነቃቸው፣ ጨለማው እንደ ጨለመ፣ ፈተናው እንደ
ፈተነ አይቀጥልም! አንድ ቀን የነፃነት ጎሕ ይቀዳል የሚል የማይናወጥ
ተስፋ ሰንቀው ነበር፡፡ በዕለት ከዕለት ኑሮአችን ውስጥ የተለያዩ የሕይወት ሠልፎች ያጋጥሙናል፡፡ እነዚህ ከሚጎዱን በላይ ግን ተስፋ
መቁረጣችን ይጎዳናል፡፡ ትንሹን የሚያገዝፈው ፍርሃታችን አቅም ይነሣናል፡፡ ቃሉ በዚህ ዓለም ተስፋን አጥታችሁ እንደሚል ሰው ከእግዚአብሔር
ከተለያየ ለመኖር የሚያጓጓውን ትልቅ ኃይል አጥቶአል ማለት ነው፡፡
ሐዋርያው እንደሚነግረን ከእግዚአብሔር ጋር መለያየት ያለ ክርስቶስ
መሆን ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር እውነተኛ ሕብረት ማድረግ ደግሞ በክርስቶስ ደም መቅረብ ነው፡፡ በዚህ መሰረት መራቅ ያለ ክርስቶስ
መሆን፤ መቅረብ ደግሞ በክርስቶስ መሆን ነው፡፡ ተወዳጆች ሆይ ለእናንተ ጉድለትና ጉዳት የሆነው ነገር ምንድነው? በባልንጀራ አለመከበባችሁ፣
ወዳጅ አለማፍራታችሁ ወይስ ከመብልና ከልብስ ጋር የተያያዘው ነገር? የቱ ነው ለእናንተ ጉዳት? ጎደለኝ የምትሉትስ ነገር? በዚህ
ዓለም ነገር ስኬት ላይ አለመድረሳችሁን ነውን? በእርግጥም የብዙዎቻችን ትግል ከዚህ ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ ይህንን ጽሑፍ ስጽፍ
ለልቤ ሸክም የሆኑብኝ ነገሮች ነበሩ፡፡ እናም ቆም ብዬ አሰብኩ፡፡ ሕሊናና ልቤን እንደ ወረቀትና እስክርቢቶ ተጠቅሜ እንዳላጣቸው
የተጠነቀኩላቸውን፣ የገንዘብ ሳይሆን የሕሊና፣ የላይ ሳይሆን የልብ ዋጋ ያስከፈሉኝን ነገሮች ለራሴ ግልጽ ለማድረግ ሞከርኩ በእርግጥ
ያለ እነዚህ መኖር አልችልምን? ስልም ራሴን ጠየኩ፡፡ ወደ ሕይወታችን ብዙ ነገሮች ይመጣሉ፡፡ ያለ እነርሱ መኖር እንደማንችል እስኪሰማን
ምናልባት ሰዎች ከሆኑ ደግሞ እስኪሰማቸው ድረስ የጠበቀ ነገር እንፈጥራለን፡፡ ዳሩ ግን የቱንም ያህል ስሜታችን ቢጠነክር ሞት ይፈታዋል፡፡
ከእግዚአብሔር መራቅ ግን የሞት ሞት ነው፡፡ አንዳንዴ ሰዎች ያለ አንተ/አንቺ መኖር አልችልም ብለው ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ ኖረው
ግን አይተናቸዋል፡፡ እግዚአብሔርን እንደ እግዚአብሔርነቱ ያልተገናኙት ግን ዘመናቸው በቁም ሞት ፈጅተዋል፡፡ ከእግዚአብሔርም ፍርድ
በታች ናቸው፡፡
ከበደል በኋላ ሰው ወደ እግዚአብሔር መቅረብ የሚችለው በክርስቶስ ደም እንደ ሆነ ቅዱሳት መጻሕፍት በአንድነት ያረጋግጣሉ፡፡
ስርየት ደም መፍሰስን ተከትሎ የሚመጣ እንደ መሆኑ አንድ ሰው ለኃጢአቱ አንድ ጊዜ የፈሰሰውን የክርስቶስ ደም በእምነት የኃጢአቴ
ስርየት ብሎ እስካላመነ ድረስ ወደተወደደው የአባትና የልጅ ሕብረት ሊገባ አይችልም፡፡ እግዚአብሔር ጻድቅ ስለ ሆነ ጽድቁ ኃጢአትን
ይቀጣል፡፡ ከዚህም የተነሣ ለሰው ኃጢአት ዋጋ ሳይቀበል የመዳን ምስራች ወደ ሰው ልጆች ሊደርስ ከቶ አልተቻለም፡፡ በቀደመው ኪዳን
ብዙ መሥዋዕቶች ለእግዚአብሔር እንደተሠዉ ከዘሌዋውያን መጽሐፍ እንረዳለን፡፡
አንድ ሰው በእግዚአብሔር ፊት ሲቆም በእርሱና ሁሉን በሚችል አምላክ መካከል መሥዋዕት ይሠዋል፡፡ ሰው በራሱ እግዚአብሔር
ፊት መቆም ስለማይችል ምትክ የሚሆን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ያቀርባል፡፡ ያለ መሥዋዕት እግዚአብሔር ፊት መቆም ከእግዚአብሔር ቁጣ
ጋር ፊት ለፊት መግጠም ነው፡፡ በአዲሱ ኪዳን አብ ሰዎችን ሁሉ ወደ ክብር የጠራው ልጁን ለውርደት ሰጥቶ እንደ ሆነ እንረዳለን፡፡
በብሉይ ኪዳን ያለ መሥዋዕት እግዚአብሔር ፊት ሞገስ ማግኘት እንደማይቻል ሁሉ በአዲሱም ኪዳን ሰው ያለ ክርስቶስ ተቀባይነት ሊኖረው
አይችልም፡፡ “ነውር የሌለው ሆኖ በዘላለም መንፈስ ራሱን ለእግዚአብሔር ያቀረበ” (ዕብ. 9÷14) ነቅ የሌለው መሥዋዕት እርሱ
ነውና፡፡ በደሙ ቤዛነታችንን አግኝተናል፡፡
ጌታ በራዕይ መጽሐፍ ውስጥ ለሰምርኔስ ቤተ ክርስቲያን
ሲናገር፡- “መከራህንና ድህነትህን አውቃለሁ ነገር ግን ባለ ጠጋ
ነህ” (ራዕ. 2÷9) ይላል፡፡ እግዚአብሔር የምቾቶቻችን አልያም የፈተናዎቻችን አምላክ ሳይሆን የእኛ አምላክ ነው፡፡ እኛ በምንም
አይነት ሁኔታ ውስጥ ልናልፍ እንችላለን፡፡ እግዚአብሔር ግን ያው ነው፡፡ በደስታችን ከእኛ ጋር እንዳለ የተሰማን ጌታ በመከራችንም
ከእኛ ጋር ነው፡፡ የሰው አቅም በደስታና በሀዘን ውስጥ ተለዋዋጭ ቢሆንም የእግዚአብሔር ኃይል ግን ከፍና ዝቅ አይልም፡፡ ሰው ሁኔታን
የሚሻገር ወዳጅነት፣ ባልንጀርነት፣ ትዳር፣ ታማኝነት፣ ፍቅር አይኖረው ይሆናል፡፡ እግዚአብሔር ግን የታመነ ነው፡፡
እርሱ
ክርስቶስ ፈተናዎቻችንን ያውቃል፡፡ ስለ ስሙ የምናሳየውን ቅናት፣ ስለ ክብሩም የምንተጋውን ትጋት ያውቃል፡፡ የሰምርኔስ ቤተ ክርስቲያን
በከፋ ድህነት ውስጥ ሆና የእግዚአብሔር ጸጋ ግን በኃይል ይሠራባት ነበር፡፡ እውነተኛው ድህነት ስለ እኛ ወድዶ ራሱን ድሀ ያደረገው
ክርስቶስ ከሌለን ነው፡፡ ለአንድ ሰው ትልቁ ጉዳት ያለ ክርስቶስ መሆን ነው (ኤፌ. 2÷12)፡፡ እርሱ ያልነበራት ደግሞም አስወጥታ
ክርስቶስን በውጪ ያቆመችው የሎዶቅያ (የሰው ግዛት) ቤተ ክርስቲያን ሀብታምና ባለ ጠጋ እንደ ሆነች ታስብ ነበር (ራዕ.
3÷17)፡፡ በደጅ ቆሞ ያንኳኳ የነበረው ጌታ ግን ጎስቋላና ምስኪን፣ ድሀና ዕውር፣ የተራቆተችም እንደሆነች ተናግሯታል፡፡ በእግዚአብሔር
ፊት እኛ ስለ እኛ የምንናገረው ሳይሆን እግዚአብሔር ስለ እኛ የሚናገረው ብቻ ልክ ነው፡፡
የሰው ድህነትና መራቆት ያለ ክርስቶስ መሆኑ ነው፡፡ ያለ እርሱ መሰብሰብ መበተን፣ መጠጣት
መጠማት፣ መመገብ መራብ፣ መልበስ መታረዝ፣ መጠበብ ስንፍና ነው፡፡ ወደ ውስጥ ያላስገባነውን አየር አንተነፍስም፡፡ ክርስቶስ ወደ
ውስጣችን ካልገባ በእኛ የሌለውን የዘላለም ሕይወት ለሌሎች ልንሰጣቸው አንችልም፡፡ እውነተኛ ክርስቲያኖች ለሚድኑት የሕይወት ሽታ
ናቸው፡፡ የሰምርኔስ (ከርቤ/መራራ) ቤተ ክርስቲያን ብርና ወርቅ፣ ምቾትና ዝና ባይኖራትም
የሕማም ሰው፣ ደዌንም የሚያውቀው ክርስቶስ ግን ነበራት፡፡ በመከራ ውስጥም የጸናች ነበረች፡፡ የመጀመሪያይቱ ቤተ ክርስቲያን ብርና
ወርቅ ያልነበራት፤ ዳሩ ግን የፍቅር ሰምና ወርቅ ኢየሱስ የነበራት ነበረች (የሐዋ. 3÷5)፡፡ የሎዶቅያ ቤተ ክርስቲያን “አንድም
ስንኳ አያስፈልገኝም” እስክትል ባለ ሀብትና ባለ ዝና ነበረች፡፡ ዳሩ ግን ጌታ በውጪ ተዘግቶበት ያንኳኳ ነበር፡፡ በውስጥ ያለውን
ስፍራ የሰው ልብ ተቆጣጥሮት ነበር፡፡ የክርስቶስ ልብ እንዲኖረን ተጠርተን እንደ ልባችን ከመኖር መንፈስ ቅዱስ ይጠብቀን፡፡ በክርስትናው
ዳኝነት ውስጥ ሰው ስለ እራሱ አልያም ሌሎች ስለ እኛ የሚናገሩት
ሳይሆን ጌታ የሚለው ብቻ እውነተኛ ነው፡፡
በጌታ ፊት
ሰምርኔስ ባለ ጠጋ ስትሆን፤ ሎዶቅያ ደግሞ ድሀና የተራቆተች ነበረች፡፡ በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት መካከል
እንዲህ ያለውን ልዩነት የፈጠረው ምንድነው? የመሚለው ጥያቄ መልስ በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በሰምርኔስ ቤተክርስቲያን
በስተውስጥ የነበረ ሲሆን፤ የሎዶቅያ ቤተ ክርስቲያንን ስንመለከታት ግን ራስ የሆነውን ጌታ አስወጥታ በር ዘግታበታለች፡፡ እርሱም
ደጁን ክፈችልኝ እያለ ይመታል፡፡ ከዚህ ዓለም የምንለይበት ትልቅ አሳብ ክርስቶስ ነው፡፡ ቃሉ፡- “ልጁ ያለው ሕይወት አለው”
(1 ዮሐ. 5÷12) ይላል፡፡ ባለ ጠጋው ጌታ ደጃፋችንን ማንኳኳቱ፤ ወዳጅ ልሁናችሁ፣ በማዕድ አብሬአችሁ ልቀመጥ ማለቱ ምንኛ ድንቅ
ነው? በመንፈስ ድሆች የሆኑ ሁሉ በራቸውን ይከፍታሉ፡፡ ከዘላለም ጌታ ጋር ለዘላለም ሐሴት ያደርጋሉ፡፡ ወደ እርሱ የገባውን ከቶ
የማያወጣ፣ መሰማሪያ የሚሰጥ፣ የሚያስወጣና የሚያስገባ፣ የዳዊት መክፈቻ ያለው የሚከፍት የሚዘጋም የሌለ፣ የሚዘጋ የሚከፍትም የሌለ
ቅዱስና እውነተኛ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እርሱ ይብዛላችሁ!!
Amen. Tsegawen Yabezalachehu
ReplyDelete