እሮብ ሚያዝያ 9/2005 የምሕረት ዓመት
ለዛሬ ለምንነጋገርበት ነገር መነሻ አሳብ የሆነችኝ አያቴ ናት፡፡ መቼም ስለ አያት ሲነሣ ብዙ ነገር በአእምሮአችሁ ላይ
ድቅን እንደሚል እገምታለሁ፡፡ በተለይም በአያት ያደጉ ልጆች በብዙ እንክብካቤና ስስት ስለሚያድጉ የእናትን ፍቅር በሚተካከል ደረጃ
ፍቅርን ተመግበዋል ተብሎ ይታሰባል፡፡ እንዲያውም ሞልቀቅ የሚሉ ሰዎችን በአያት እጅ እንዳደጉ መገመት የተለመደ ነው፡፡ እንደ የልጅ
ልጅ ስናስብ አያት ብዙ ነገር ነው/ናት፡፡ ሚስት ከባሏ ጋር ብትጣላ ለልጆችዋ የአደጋ ጊዜ መሰብሰቢያና የአባወራው ማስፈራሪያ አያት
ናት/ነው፡፡ አባት ሚስቱ ብትጎረምስበት፣ ልጆቹን አስታቅፋው እንደ ልቧ ብትሄድ አልያም በሞት ብትለየው ቅድሚያ መፍትሔው አያቱ
ናት፡፡ ከዚህ የተነሣ ብዙ ጊዜ ወላጆች ቢሞቱ ልጅ የማሳደግ ግዴታው በሕይወት ባሉ አያቶች ላይ ሲወድቅ ማስተዋል ብርቅ አይደለም፡፡
አንዳንድ ትዳሮችን ስንመለከት ደግሞ በአያት ቁጥጥር ስር የሚተዳደሩ ናቸው፡፡ አጣምረውም አለያይተውም ሊያኖሩ የሚችሉበት አቅም
አንዳንድ አያቶች ውስጥ እንመለከታለን፡፡ ጠልተው ሊያስጠሉ፤ ወድደው ሊያስወድዱ፣ ተናግረው ሊታመኑ ይችላሉ፡፡
ስለ አያት ለምን አነሣሁ መሰላችሁ? የእኔ አያት እንደ ብዙ አያቶች ሁሉ ኃይለኛና አይበገሬነቷ ትዝታ ጭሮብኝ ነው፡፡
በምንድነው አይበገሬነቷ? ብላችሁ ብትጠይቁኝ አያቴ በታመመች ቁጥር የሕክምና ባለ ሙያ ጋር እንድትሔድ በቤትም በጎረቤትም ተለምና
በጄ አለማለቷ ነው፡፡ እንኳን በታወቀውና በግልጹ ቀርቶ በተሰወረውም ሕመሟ ከሐኪም ዘንድ መፍትሔ አትፈልግም፡፡ እንደ ምንም አስገድደን
ለመውሰድ በምናደርገው ሙከራ እንኳ ገና ክፉና ደጉን እንዳለየ ሕፃን የምታሰማው ጩኸት ልብም እግርም ይይዛል፡፡ ታዲያ ምን እንዲሻል
ብንጠይቃት ጓሮ ለብዙ ዘመን ስትንከባከበው፣ ውኃ ስታጠጣው፣ ፍግ ስትመግበው የኖረ፤ እርሷም ልክ እንደ ወላጆችዋ በቅብብሎሽ ከእሷ
ዘንድ በደረሰው ቦታ ላይ የጸደቀ ቅልብ (ይጠብቃል) ምች መድኃኒት ቆርጣችሁ አምጡልኝ ትላለች፡፡ ለእሷ በሽታ ከዚህ የበለጠ መፍትሔ
የለም፡፡ ምክንያቱም እሷና ምች መድኃኒቷ አብረው ዘመን የተሻገሩ፣ ከየትኛውም መድኃኒት በበለጠ የተላመዱ እንዲሁም በቅርብ ዘወር
ብላ የሚገናኙ ናቸው፡፡ ስትናገር፡-“ከዛሬ ሐኪምና መድኃኒት እኔ ጓሮ ያለችው ምች መድኃኒት ትበልጣለች” ትላለች፡፡ ስለዚህ እምቢታዋ
ልክ እንዳላይደለ ቢገባንም አያት ስለሚከበር፣ ስለሚፈራ፣ መብት ስለማይጣስ ያለችውን አርሰንና አሽተን እናጠጣታለን፡፡
አንዳንዴ መለስ ሌላ ጊዜ ደግሞ ቀለስ እያለች በገዛ እጇ ተንጣ ኖራለች (የዛሬን አያድርገውና)፡፡ ስለ ሕክምና ጥቅም፣
ለችግሯ ስለሚሆን መፍትሔ ያለ ማቋረጥ እንነግራታለን፡፡ ዳሩ ግን የአያቴ ምች መድኃኒት የሞት መድኃኒት ያክል ነበር፡፡ እዚያ ሔጄ
አንዴ ኪኒን ሌላ ጊዜ መርፌ ከምቀለብ የማይዋጥም የማይወጋም “የሚጠጣ ምች መድኃኒቴ ፍቱን ነው” እያለች ታስቀናለች፡፡ አያቴ በተረቷና
በወጓ ሁሉ ምች መድኃኒቷ ትነሣለች፡፡ የእሷን ምች መድኃኒት የሚያጥላላ አልያም የሚያራክስ ውጉዝ ከመ አርዮስ ይባላል፡፡ እንግዲህ
አያቴና ምች መድኃኒቷ ግብአተ መቃብራቸው የተፈፀመው እንዲህ ባለ ፍቅር ውስጥ እያሉ ነው፡፡ ዛሬ ሰዎች አያትህ ምን ሆና ነው የሞተችው
ሲሉኝ ምች መድኃኒቷ አታሏት እላቸዋለሁ፡፡ በእርግጥም በእርሷ የሆነው ይኼው ነው፡፡ ሰው እንዴት ሰው በተከለው ይታለላል?