Wednesday, April 17, 2013

የአያቴ ምች መድኃኒት



                                      እሮብ ሚያዝያ 9/2005 የምሕረት ዓመት

          ለዛሬ ለምንነጋገርበት ነገር መነሻ አሳብ የሆነችኝ አያቴ ናት፡፡ መቼም ስለ አያት ሲነሣ ብዙ ነገር በአእምሮአችሁ ላይ ድቅን እንደሚል እገምታለሁ፡፡ በተለይም በአያት ያደጉ ልጆች በብዙ እንክብካቤና ስስት ስለሚያድጉ የእናትን ፍቅር በሚተካከል ደረጃ ፍቅርን ተመግበዋል ተብሎ ይታሰባል፡፡ እንዲያውም ሞልቀቅ የሚሉ ሰዎችን በአያት እጅ እንዳደጉ መገመት የተለመደ ነው፡፡ እንደ የልጅ ልጅ ስናስብ አያት ብዙ ነገር ነው/ናት፡፡ ሚስት ከባሏ ጋር ብትጣላ ለልጆችዋ የአደጋ ጊዜ መሰብሰቢያና የአባወራው ማስፈራሪያ አያት ናት/ነው፡፡ አባት ሚስቱ ብትጎረምስበት፣ ልጆቹን አስታቅፋው እንደ ልቧ ብትሄድ አልያም በሞት ብትለየው ቅድሚያ መፍትሔው አያቱ ናት፡፡ ከዚህ የተነሣ ብዙ ጊዜ ወላጆች ቢሞቱ ልጅ የማሳደግ ግዴታው በሕይወት ባሉ አያቶች ላይ ሲወድቅ ማስተዋል ብርቅ አይደለም፡፡ አንዳንድ ትዳሮችን ስንመለከት ደግሞ በአያት ቁጥጥር ስር የሚተዳደሩ ናቸው፡፡ አጣምረውም አለያይተውም ሊያኖሩ የሚችሉበት አቅም አንዳንድ አያቶች ውስጥ እንመለከታለን፡፡ ጠልተው ሊያስጠሉ፤ ወድደው ሊያስወድዱ፣ ተናግረው ሊታመኑ ይችላሉ፡፡

          ስለ አያት ለምን አነሣሁ መሰላችሁ? የእኔ አያት እንደ ብዙ አያቶች ሁሉ ኃይለኛና አይበገሬነቷ ትዝታ ጭሮብኝ ነው፡፡ በምንድነው አይበገሬነቷ? ብላችሁ ብትጠይቁኝ አያቴ በታመመች ቁጥር የሕክምና ባለ ሙያ ጋር እንድትሔድ በቤትም በጎረቤትም ተለምና በጄ አለማለቷ ነው፡፡ እንኳን በታወቀውና በግልጹ ቀርቶ በተሰወረውም ሕመሟ ከሐኪም ዘንድ መፍትሔ አትፈልግም፡፡ እንደ ምንም አስገድደን ለመውሰድ በምናደርገው ሙከራ እንኳ ገና ክፉና ደጉን እንዳለየ ሕፃን የምታሰማው ጩኸት ልብም እግርም ይይዛል፡፡ ታዲያ ምን እንዲሻል ብንጠይቃት ጓሮ ለብዙ ዘመን ስትንከባከበው፣ ውኃ ስታጠጣው፣ ፍግ ስትመግበው የኖረ፤ እርሷም ልክ እንደ ወላጆችዋ በቅብብሎሽ ከእሷ ዘንድ በደረሰው ቦታ ላይ የጸደቀ ቅልብ (ይጠብቃል) ምች መድኃኒት ቆርጣችሁ አምጡልኝ ትላለች፡፡ ለእሷ በሽታ ከዚህ የበለጠ መፍትሔ የለም፡፡ ምክንያቱም እሷና ምች መድኃኒቷ አብረው ዘመን የተሻገሩ፣ ከየትኛውም መድኃኒት በበለጠ የተላመዱ እንዲሁም በቅርብ ዘወር ብላ የሚገናኙ ናቸው፡፡ ስትናገር፡-“ከዛሬ ሐኪምና መድኃኒት እኔ ጓሮ ያለችው ምች መድኃኒት ትበልጣለች” ትላለች፡፡ ስለዚህ እምቢታዋ ልክ እንዳላይደለ ቢገባንም አያት ስለሚከበር፣ ስለሚፈራ፣ መብት ስለማይጣስ ያለችውን አርሰንና አሽተን እናጠጣታለን፡፡

          አንዳንዴ መለስ ሌላ ጊዜ ደግሞ ቀለስ እያለች በገዛ እጇ ተንጣ ኖራለች (የዛሬን አያድርገውና)፡፡ ስለ ሕክምና ጥቅም፣ ለችግሯ ስለሚሆን መፍትሔ ያለ ማቋረጥ እንነግራታለን፡፡ ዳሩ ግን የአያቴ ምች መድኃኒት የሞት መድኃኒት ያክል ነበር፡፡ እዚያ ሔጄ አንዴ ኪኒን ሌላ ጊዜ መርፌ ከምቀለብ የማይዋጥም የማይወጋም “የሚጠጣ ምች መድኃኒቴ ፍቱን ነው” እያለች ታስቀናለች፡፡ አያቴ በተረቷና በወጓ ሁሉ ምች መድኃኒቷ ትነሣለች፡፡ የእሷን ምች መድኃኒት የሚያጥላላ አልያም የሚያራክስ ውጉዝ ከመ አርዮስ ይባላል፡፡ እንግዲህ አያቴና ምች መድኃኒቷ ግብአተ መቃብራቸው የተፈፀመው እንዲህ ባለ ፍቅር ውስጥ እያሉ ነው፡፡ ዛሬ ሰዎች አያትህ ምን ሆና ነው የሞተችው ሲሉኝ ምች መድኃኒቷ አታሏት እላቸዋለሁ፡፡ በእርግጥም በእርሷ የሆነው ይኼው ነው፡፡ ሰው እንዴት ሰው በተከለው ይታለላል?    
  

        አያቴ በሕይወት ሳለች በውርስ በተቀበለችው መሬት ላይ ብዙ ምች መድኃኒት ተክላ ትሸጥ እንደ ነበር አስታውሳለሁ፡፡ እንዲያውም የሞተች ቀን ብዙ ሰው ሙሾ ያወጣው “ባለ ምች መድኃኒቷ” እያለ ነው፡፡ የአንዳንዶች እንባ የፈሰሰውም “ያስለመድሽን ቀረ” በሚል ስሜት ነው፡፡ ግን ብቻ አያቴ ሞታለች፡፡ የተመካችበት፣ በእጇ ተክላ ያጸደቀችው መድኃኒቷ አባብሎ መቃብር አውርዷታል፡፡ ለሰው ይበቃል ያለችው እሷን ማቆም ተስኖት እንደምትኖር እየተሰማት ሞታለች፡፡ አያቴ ችግሯ መድኃኒት እንቢ ማለቷ ብቻ አይደለም፡፡ ያለባትንም በሽታ በውል አለመረዳቷ ጭምር እንጂ፡፡ ስለዚህ የራሷ ባለ ሙያ ሆና መቃብር ወርዳለች፡፡ የእጅ አያስጥል ይሏችኋል ይኼ ነው፡፡

        ሊቃውንቱ አምስት ሺ አምስት መቶ ዘመን የሰው አቅም የተፈተሸበት እንደ ሆነ ይናገራሉ፡፡ ሰው በፈጠረው አምላክ ላይ ለፈፀመው በደል መፍትሔው ራሱ ተበዳዩ እንደ ሆነ እስኪረዳና እኔነቱ እስኪንጠፋጠፍ ድረስ ጊዜው በቂ ነበር፡፡ ነገር ግን ሰው ከፍጥረቱ የቁጣ ልጅ እንዲሁም በበደልና በኃጢአቱ ሙት ከሆነበት ታሪክ በራሱ መውጣት አልቻለም፡፡ ሕጉ ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋል፤ የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሏቸዋል ሲል ሰው ደግሞ ጽድቃችን የመርገም ጨርቅ ሆነ በማለት የሰው ዘር ሁሉ የእግዚአብሔርን ክንድ (ኢየሱስ ክርስቶስ) ወደሚናፍቅበት ሁኔታ ውስጥ ገብቶአል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሁለት ጽድቅ ይናገራል፡፡ አንዱ የሰው ጽድቅ ሲሆን ሌላው ደግሞ የእግዚአብሔር ጽድቅ ነው (ሮሜ. 10÷3)፡፡

        የሰው ጽድቅ ሰው በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት ለማግኘት ለራሱ የሚያቆመው ሲሆን የእግዚአብሔር ጽድቅ ደግሞ ሰው በእርሱ ፊት ተቀባይነትን ያገኝ ዘንድ እግዚአብሔር ለሰው ሁሉ ያቆመው ጽድቅ ነው፡፡ ሰው መልካም በሚለው በራሱ ሥራ እስኪያፍር ድረስ ሕጉ የሰውን አቅምና ትምክህት ከንቱ አደረገው (ያዕ. 2÷10)፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ጽድቁን ወደ ምድር ላከ፡፡ እርሱም የሚወደው ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ሰው ምን ጊዜም ራሱ ለተከለውና ለተንከባከበው ነገር ሲሸነፍለት፣ ለእውነተኛው መፍትሔና መድኃኒት ትኩረት ሲነፍግ እርሱ አያቴን ነው፡፡ አያቴ የምትንከባከበው ምች መድኃኒቷን ብቻ አልነበረም፡፡ ጤና አዳምም ነበራት፡፡ አንዴ በሻይ ሌላ ጊዜ በቡና ታጣጥመዋለች፡፡ ከዚህም ባለፈ አፍንጫዋ ስር ሽጣ ታሻትተዋለች፡፡ ደግሞ ሲያሰኛት በጆሮና በፀጉሯ መሐል ሰክታ ትታይበታለች፡፡ አንድ ቀን ከልብ የምትወዳቸው አንዲት ጎረቤታችን ስሟን ጠርተው ወዳጄ የአዳም ዘር ሁሉ ጤና “ኢየሱስ ነው” አሏት፡፡ እንዲህ ያለው ንግግር ለአያቴ የማይዋጥ መራራ ነው፡፡

        የዘላለምን ሞት ያስከተለው የአዳም በሽታ ኃጢአት ነው፡፡ ከዚህም የከፋ በሽታ የለም፡፡ ሁሉ በራሳቸው መንገድ ይድኑ ዘንድ ስለማይችሉ እግዚአብሔር የድኅነት መንገዱን ገለጠ፡፡ ሰዎች ለዚህ መገለጥ ፈጣንና ቁርጥ ምላሽ ሲሰጡ የዘላለምን ሕይወት ይወርሳሉ፡፡ የአዳም መፍትሔ ሰውን ሊያድን ሰው የሆነው ክርስቶስ ነው (ዕብ. 1÷1-3)፡፡ ማስተዋል ይብዛላችሁ!

1 comment:

  1. የዘላለምን ሞት ያስከተለው የአዳም በሽታ ኃጢአት ነው፡፡ ከዚህም የከፋ በሽታ የለም፡፡ ሁሉ በራሳቸው መንገድ ይድኑ ዘንድ ስለማይችሉ እግዚአብሔር የድኅነት መንገዱን ገለጠ፡፡ ሰዎች ለዚህ መገለጥ ፈጣንና ቁርጥ ምላሽ ሲሰጡ የዘላለምን ሕይወት ይወርሳሉ፡፡ የአዳም መፍትሔ ሰውን ሊያድን ሰው የሆነው ክርስቶስ ነው (ዕብ. 1÷1-3)፡፡

    ReplyDelete