Wednesday, April 10, 2013

ሰቆቃወ ፍቅር



እሮብ ሚያዝያ 2/2005 የምሕረት ዓመት

    የሠላሳ ሁለት ዓመት እድሜ ያላት ሲሴሊያ ከባለቤቷ አዳም ጋር በፍቅር ያሳለፈችውን ጊዜ በቀላሉ ልትረሳው፣ በሰዎች የማጽናኛ ቃል ልታልፈው፣ እንደ አሮጌ ኑሮ ቆጥራው አዲስ ምዕራፍ ልትጀምር አቅም አልነበራትም፡፡ የሞተው ባለቤትዋ ስርዓተ ቀብሩ እንዳበቃ ከመቃብር አውጥታ በአልጋዋ ላይ በማስተኛት ለሁለት ዓመታት ያህል ቀን አብራው በመዋል፣ ሌሊቱን አብራው በማደር አሳልፋለች፡፡ የባሏ እስትንፋስ የተቋረጠ ቢሆንም እርሷ ለእርሱ የነበራት ፍቅር ሕያውነት ግን ቀጥሏል፡፡

    ስለ እርሱ ስትናገርም “አዳምን ምን ጊዜም ቢሆን አልረሳውም፡፡ በአካል ቢሞትም ልቤ ላይ ግን ሕያው ነው፡፡ እርሱ በጣም አስደናቂ ሰው ነበር፡፡ አጽሙን ከእኔ ጋር በማኖሬ ተጽናንቻለሁ፡፡ ፍቅሬንም ተወጥቻለሁ፡፡” በማለት ነበር፡፡ በመጨረሻ ግን የባለቤቷን አጽም ወደ መቃብሩ በመመለስ ሄንሪ የተባለ ሰው አግብታለች (ትንግርት መጽሔት፣ ግንቦት/ሰኔ 1985፣ ገጽ 5)፡፡

    አንዳንድ ሰዎች ፍቅር ልክ እንደ እቅፍ አበባ ለሌላው የሚሰጥ ነገር እንደ ሆነ ሲያስቡ ሌሎች ደግሞ በላይህ ላይ የተጣለ የማይረባ ግን ደግሞ የጠነከረ ኃይል ነው በማለት ይስማማሉ፡፡ ፍቅር ግን ልንሰጠው የምንችለው ማንኛውም ነገር አይደለም፡፡ ፍቅር ራሱ ሌሎች ነገሮችን እንድንሰጥ የሚያስችለን ከፍተኛ ግፊት ነው፡፡ ጥንካሬን፣ ኃይልን፣ ነፃነትንና ሰላምን ለሌሎች እንድንሰጥ የሚረዳን ጉልበት ፍቅር ነው፡፡

    ከዚህ አሳብ በመነሣት ፍቅር ውጤት ሳይሆን መንስዔ፣ ወራጅ ሳይሆን ምንጭ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ስለዚህ ከፍቅር የተነሣ የማንሰጥ ከሆነ፣ ከፍቅር የተነሣ ይቅር የማንል ከሆነ፣ ከፍቅር የተነሣ የማንራራ ከሆነ፣ ከፍቅር የተነሣ ለእውነት የማንኖር ከሆነ በእኛ ያለው የፍቅር ኃይል ተዳክሟል አልያም ሞቷል ማለት ነው፡፡ በሕይወት ውስጥ እጅግ የከበረውና ቀዳሚው ነገር ሌላውን ማፍቀር ነው፡፡ በማስከተልም በሕይወት ውስጥ እጅግ የከበረው ነገር በሌላው መፈቀር ነው፡፡ በመጨረሻ እጅግ የከበረው ነገር ከላይ የተመለከትናቸው ሁለቱ በእኩል ጊዜ መሆን ሲችሉ ማለትም ባፈቀሩት ሰው ሲፈቀሩ ነው፡፡

      የሰው ፍቅር ልዩ ልዩ ቢሆንም የእግዚአብሔር ፍቅር አንድ መሆኑ ዘመን የማይሽረው መጽናኛችን ነው፡፡ እግዚአብሔር እኛን እንዴት እንደወደደን መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር “እንዲሁም ዓለም አንተ እንደላከኝ በወደድከኝም መጠን እነርሱን እንደወደድካቸው ያውቃሉ” (ዮሐ. 17÷23) ይላል፡፡ እግዚአብሔር እኛን የወደደን ፃድቅ፣ የዋህና ትሁት የሆነውን እስከ መስቀል ሞትም የታዘዘውን አንድ ልጁን በወደደበት ፍቅር ነው፡፡ ለዚህም ነው እግዚአብሔር ሲወድ የሰውን ማንነት ታሳቢ አድርጎ አይደለም የምንለው፡፡ መልክና ቁመና፣ ሀብትና ሥነ ምግባርን ግምት ውስጥ በማስገባት አልያም ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጥ ሰውን መውደድ የሰው ፍቅር እንጂ የእግዚአብሔር አይደለም፡፡

      ፍቅር የሰውን ልማድ ይሻገራል፡፡ ጥሙን ሳያረካ፣ ርሀቡን ሳያጠግብ፣ መሻቱን ሳይሞላ አይዝልም፡፡ ከንቱ በሆነው በዚህ ዓለም መለፍለፍ ውስጥ ያለው የማይሰለች አጓጊ ወሬ ፍቅር ነው፡፡ ደመ ነፍስ በሆኑ እንስሳት ውስጥ እንኳ ይህ ኃይል መታየቱና መሥራቱ ምንኛ ድንቅ ነው! አብዛኛውን ጊዜ መልካም በምንላቸው ነገሮች ውስጥ ምቾትን ብቻ እናስተውላለን፡፡ ሰው እግዚአብሔርን ተከትሎ መራብ መቸገር፤ ማዘን መከፋት የለበትም የሚለው ሙግት ምንጩ ይኸው አመለካከት ነው፡፡ በዓለም ሳለን መከራ እንዳለብን ግን እናውቃለን (ዮሐ. 16÷33)፡፡ አፍቅረን ካፈቀርነው ጋር፣ ደክመን ከደከምንለት ነገር ጋር፣ ዋጋ ከፍለን ከለፋንለት ነገር ጋር ላንኖር ወይም የእኛ ላይሆን ይችላል፡፡ ሰው ባይነጥቀን እንኳ ሞት ተናጥቆን ይሆናል፡፡ ምድር በብዙ ፍትሐዊ ባልሆኑ ነገሮች የተሞላች ናት፡፡ ከዚህም የተነሣ ዓለም በብዙ ሙሾና ለቅሶ፤ ሰቆቃና እንግልት እረስርሳለች፡፡ 


       ባሏ የሞተባት መበለት መቃብር ስፍራ ላይ እየወደቀች እየተነሣች “አራተኛ ባሌ ነበር” በማለት ልክ እንደ ትኩስ ሬሣ፣ እንደ መጀመሪያ ወዳጇ ታለቅሳለች፡፡ አለፍ ብለው የቆሙ በእድሜ ጠና ያሉ ግን ደግሞ ባል የሚባል ያላገቡ ሴት “ሕይወት እኮ ፍትሐዊ አይደለችም” አሉ፡፡ ጠንከር አድርገውም ንግግራቸውን ቀጠሉ “እርሷ የምትቀብራቸው ባሎች አግኝታለች፡፡ እኔ ግን አንዱን እንኳ ማግኘት ተስኖኛል” በማለት ስቅስቅ ብለው አለቀሱ፡፡ እግዚአብሔርን ከምናማርርበት ነገር አንዱ አግኝቶ ማጣት ነው፡፡ አስተውለነው ከሆነ እንኳን የጊዜውን ይህችን ምድር እንኳ በዘላቂነት ጥለናት እንሄዳለን፡፡ ነበርኩና ነበረኝ የሰው ታሪክ ነው፡፡ መበለቲቱ ፍቅራቸውን አግኝታ፣ ያላቸውን ተካፍላ፣ ፍቅሯን ገልጣላቸው ስለ ተለዩአት ባሎች ነው የምታነባው፤ እኚህ በእድሜ የገፉ ሴት ደግሞ ባዶ ስለ ሆነው የሕይወታቸው ስፍራ፣ ምንም የባል ፍቅር አስተናግዶ ስለማያውቀው  ልባቸው ነው የሚመረሩት፡፡ እነዚህ ሰዎች ዛሬም ምድራችን ላይ ተጎራብተው አሉ፡፡ ሰውን የለኝም ብቻ ሳይሆን ነበረኝም ያስለቅሰዋል፡፡ እንዲያውም እንዲኖሩን ከምንፈልጋቸው ነገሮች በላይ እንዲኖሩልን የምንፈልጋቸው ነገሮች ዋጋ ያስከፍሉናል፡፡ ታዲያ የጓጓንለትና የደከምንለት ነገር አልበረክትላችሁ ሲለን ኑሮአችንን ሰቆቃ ይወርሰዋል፡፡

    ከፍቅር ጋር የተያያዘው ሰቆቃ ደግሞ የቋጥኝን ያህል ይከብዳል፡፡ አንዳንዴም አፅም ማቀፍ ያስከጅላል፡፡ በዚህ ዓለም ከፍቅር ጋር የተገናኙ የሰው ታሪኮችን ስንመለከት ልብን የሚነኩ ገጠመኞችን እናያለን፡፡ በመግቢያችን ላይ ለሁለት ዓመት የባለቤቷን አፅም አቅፋ ስለኖረች ሴት ታሪክ ስናነብ መደመም እንደሞላባችሁ እገምታለሁ፡፡ እስቲ ከምኞቷ ወገን ሆነን እንመልከት፡፡ ያ የምትወደው፣ ከትቢያ አውጥታ የታቀፈችው፣ የዛሬውን መጥፎ ሽታ ሳይሆን ያለፈውን የተወደደ የመዓዛ ሽታ አስባ ጎኑ ያደረችውን ባሏን እግዚአብሔር ቢያስነሣው ምን የምታደርግ ይመስላችኋል? (ሮሜ. 4÷25)፡፡

    በበድኑ የታቀፈችውን፣ ግዑዝ ሆኖ ፍቅሯን የገለጠችለትን በእውን ዳግም ብታገኘው ምን ይሆናል ብላችሁ ታስባላችሁ? አብዛኛውን ጊዜ ላለን ነገር የበለጠ ጥንቃቄ የሚኖረን እንደምናጣው ስናስብ ነው፡፡ እውነተኛ ወዳጅን ማጣት የእግር እሳት ነው፡፡ የወደዱትን አጥተው፣ ያፈቀሩትን ከስረው፣ የተጠነቀቁለትን ተነጥቀው የዘወትር ለቀስተኛ የሆኑ ብዙ ናቸው፡፡ ቤታቸውን የሀዘን ድባብ ያጠላበት፣ ወጥተው ገብተው የሚቆዝሙ፣ ዛሬን ሞተው ትላንትን በትዝታ የሚኖሩ፣ ከወዳጅ መቃብር ፊት ቆመው እንደ ሕያው ቆጥረውት የሚያወጉ ዕለቱን በፍቅር ሙሾ አሟሽተው፣ ትዝታን ሲጋግሩ ውለው፣ አመሻሹን በእንባ የሚከድኑ፣ የፍቅራቸው ትርፍ ሰቆቃ የሆነባቸው ወገኖች ልብ ይነካሉ፡፡

    የምትወደውን በሞት ያጣች አንዲት አፍቃሪ ሴት መቃብሩ ላይ፡- “ሰውነቴን እንደ ፋኖስ አድርጌ፣ ለስላሳውን ልቤን ክር በማድረግ፣ በለጋ ፍቅሬ የዘይት መዓዛ ሞልቼ፣ በሥፍራህ ሌትና ቀን አበራለሁ” በማለት ጽፋለች፡፡ የተወዳጁ ዋጋ ምን ያህል ትልቅ ነው? ሞት ለያቸው እንጂ ይህንን የጠነከረ ፍቅር ምን ይበጥሰው ነበር? ደግሞ እንጠይቅ እንዲህ የተባለለት ሰው በሕይወት እያለ ምን ዋጋ ከፍሎ ይሆን? ለዚህ ፍቅር የሚመጥን፣ ከመቃብር ባለፈ የሚያስወድድ፣ ለቋሚው ተርፎ የሚያሳርፍ ፍቅር ነበረውን? ከዚህም በላይ ብዙ ነገሮችን ልንጠይቅ እንችላለን፡፡ ዋጋ ያስከፈሉ እንጂ የከፈሉ፣ ያሳደዱ እንጂ የተሰደዱ፣ የተቀበሉ እንጂ የሰጡ፣ የቀሙ እንጂ የተዉ አፍቃሪዎችን እንኳን እግዚአብሔር ምድሪቱም ተርባለች፡፡ በላይ በሰማይ፣ በታች በምድር አንድ እውነተኛና ተግባራዊ ደግሞም ለሕዝቡ ሁሉ የሚበቃ ፍቅር ግን አለ፡፡ ትናንሽ አይነት የፍቅር መገለጫዎች እንኳን ሳይቀሩ በዓይነ ሕሊና ይታሰባሉ፡፡ በእንደዚህ አይነቱ የጉዞ ግንኙነት ውስጥ ለማሳለፍ የትኛውም ጊዜ አይረዝምም፡፡ በፍቅር ለመግባባት የትኛውንም ርቀት ማቋረጥ ፈጽሞ ከባድ አይሆንም፡፡ በተለይ እስከ ሞት የወደደንን ጌታ!! 

      “በፊታቸው የምታደርገው ሥርዓት ይህ ነው፡፡ ዕብራዊ ባሪያ የገዛህ እንደ ሆነ ስድስት ዓመት ያገልግልህ በሰባተኛውም በከንቱ አርነት ይውጣ፡፡ ብቻውን መጥቶ እንደ ሆነ ብቻውን ይውጣ፣ ከሚስቱ ጋር መጥቶ እንደ ሆነ ሚስቱ ከእርሱ ጋር ትውጣ፡፡ ጌታው ሚስት አጋብቶት እንደ ሆነ ወንዶች ወይም ሴቶች ልጆች ብትወልድለት ሚስቱና ልጆችዋ ለጌታው ይሁኑ እርሱም ብቻውን ይውጣ፡፡ ባሪያውም፡- ጌታዬን ሚስቴን ልጆቼንም እወድዳለሁ አርነት አልወጣም ብሎ ቢናገር ጌታው ወደ ፈራጆች ይውሰደው ወደ ደጁም ወደ መቃኑ አቅርቦ ጆሮውን በወስፌ ይብሳው ለዘላለምም ባሪያው ይሁን” (ዘፀ. 21÷1-6)፡፡

       የእግዚአብሔር ቃል  ብሉይ ኪዳን ጥላ፣ አዲስ ኪዳን  አካል፣ ብሉይ ኪዳን ትንቢት፣ አዲስ ኪዳን ፍፃሜ፣ ብሉይ ኪዳን ዘር፣ አዲስ ኪዳን መከር፣ ብሉይ ኪዳን ቃል፣ አዲስ ኪዳን ትርጓሜ እንደ ሆነ በግልጥ ያስረዳናል፡፡ እግዚአብሔር ለእስራኤል ሥርዓት ያደርግላቸው ዘንድ ሙሴን ባዘዘበት በዚህ የዘፀአት ክፍል ውስጥ በጥላነት የተቀመጠ አካላዊ እውነት እናገኛለን፡፡ እውነትን ለመቀበል ልባቸው ክፍት የሆነ ሰዎች ሁሉ በግልጥ እንደሚያስተውሉት የዘፀአት መጽሐፍ ከባርነት ነፃ የመውጣት፣ የማምለጥና የመሻገር መጽሐፍ ነው፡፡

       በዘፍጥረት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እስራኤል በግብፅ ባርነት ስር እንደተያዙ እናነባለን፡፡ በጠቅላላው የሰውን ታሪክ ስንመለከት ደግሞ ሰው ባለ መታዘዝ ምክንያት ከዔደን ገነት ተባርሮ በዚህ ዓለም ገዥ ዲያቢሎስ ቀንበር ስር እንደተጨነቀ በዚሁ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እናነባለን፡፡ እስራኤል እንደዚያ  ካለው የሰው ጭቆና ነፃ የወጡት በዘፀአት መጽሐፍ ውስጥ ነው፡፡ ከባርነት የተላቀቁበትን መንገድ ስንመለከት የፋሲካው በግ ታርዶ፣ የቤታቸው መቃንና ጉበን ደም ተቀብቶ፣ ከሞት መልአክ ሕይወታቸው ተርፎ ነው፡፡ በአዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች እንደዚህ ወዳለው ክብር የተሸጋገርንበት ምሥጢር እንደ እስራኤል ሁሉ ለእኛም ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዶ ነው (1 ቆሮ. 5÷7)፡፡

    በዘፀአት ምዕራፍ አሥራ ሁለት ላይ ሕዝበ እስራኤል ከሞት ያመለጡበት በግ ፍቅሩ ምን ይመስል እንደ ነበር ምዕራፍ ሃያ አንድ ላይ እንመለከታለን፡፡ በእርግጥ ያ በግ በሸላቾቹ ፊት ዝም ያለ፣ እያወቀ እንደ አላዋቂ የተቆጠረ፣ ገዥ ሆኖ ሳለ እንደ ሎሌ የተጎተተ፣ መሠዊያውን ተሸክሞ ሊሰዋ የሄደ መሥዋዕት ነው፡፡ ሰዎች ሁሉ መዳንን ያገኙ ዘንድ መብቱን ወድዶ የተቀማ፣ እጁን ዘርግቶ ራሱን ያስረከበ ነው፡፡ የብሉይ ኪዳን ትልቅ ጥያቄ “የመሥዋዕቱ በግ ወዴት ነው?” (ዘፍ. 22÷7) የሚል ሲሆን፤ የአዲስ ኪዳን ትልቅ መልስ ደግሞ “እነሆ የእግዚአብሔር በግ” (ዮሐ. 1÷36) የሚል ነው፡፡ ያ ዕብራዊ ባሪያ የሚስቱን ታማኝነትና ፍቅር፣ የልጆቹን ሥነ ምግባርና ጽናት እንደ ቅድመ ሁኔታ ሳያስቀምጥ በጸጋው “እወድዳለሁ” እንዳለ ክርስቶስ እንደ ቤተ ክርስቲያን ማኅበረ ምዕመናንን፤ እንደ ልጅ እያንዳንዳችንን ሳይገባን በጸጋው (የማይገባ ስጦታ) ወዶናል፡፡

    ያ ዕብራዊ ባሪያ ራሱን ለድህነት ጥግና ለመከራ ኑሮ ደም እስከማፍሰስ ሰጥቶ ሚስቱንና ልጆቹን በተግባር እንደ ወደደ ክርስቶስ ለሙሽራይቱ ቤተ ክርስቲያንና ለልጆቹ ደምን እስከማፍሰስ ዋጋ ከፍሏል (የሐዋ. 20÷28)፡፡ ያ ዕብራዊ ባሪያ ጆሮውን በወስፌ እንደ ተበሳ ደግሞም እንዲህ ያለው ውርደት በአደባባይ ላይ እንደ ሆነበት ክርስቶስ ቀራንዮ ላይ በእጅ በእግሩ ችንካር አልፎበት የእሾህ አክሊል ደፍቶአል፡፡ ስቀለው . . ስቀለው . . በሚል የግፈኞች ጩኸት ታጅቦ ደፋ ቀና ብሏል፡፡ በዚህም ነፍሱን እስከ መስጠት በዘላለም ፍቅር ወድዶናል (ዮሐ. 15÷13)፡፡

    አንድ አፍቃሪ ሲናገር፡- “እግረ መንገዴን ሳልፍ በየመደብሮቹ እጅግ የሚያምሩና የሚያስደንቁ ስጦታዎችን አየሁ፡፡ ገንዘብ ሊገዛቸው የሚችሉ ወርቅና ጌጣ ጌጦች እንዲሁም በውድ ዋጋ የሚተመኑ አልባሳት ልብንም ዓይንንም በሚማርክ መልኩ ተቀምጠዋል፡፡ እኔ ግን ከእነዚህ ውብ ስጦታዎች አንዱም የለኝም፡፡ ነገር ግን በልብሽ የከበረ ስፍራ የምታኖሪው እኔም እጅግ ዋጋ የምሰጠውን ነገር ስጦታ አድርጌ እሰጥሻለሁ፡፡ ዝገት የማይነካው፣ ማንም መውሰድ የማይችለው የተወደደ ነው፡፡ እንዲህ ያለው የከበረ ነገር የትኛውም መደብር አይገኝም፡፡ በመጪው ጊዜ ሁሉ አብሮሽ የሚዘልቅ ጽኑና እውነተኛ የሆነው ክቡር ስጦታዬ ፍቅሬ ነው” አለ፡፡ ለእውነተኛ ፍቅር ትክክለኛው ምላሽ እውነተኛ ፍቅር ብቻ ነው፡፡

    ክርስቶስ እኛን ለማዳን የባሪያን መልክ መያዝ፣ በሰው ምሳሌ መሆን፣ ራሱን ባዶ ማድረግና ማዋረድ አስፈልጎታል (ፊል. 2÷7)፡፡ እርሱ ሊያገለግል (ባሪያ ሊሆን)፣ ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ ሊሰጥ መጥቶአል (ማቴ. 20÷28)፡፡ መለኮት በሰው ላይ ያለውን የፍትህ ጥያቄ ከሦስቱ አካላት ማለትም አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ አንዱ አካል ወልድ ሰው ሆኖ (የሕማም ሰው ሆነ) አሟላ፡፡ የሰውን የፍትህ ጥያቄ ሰው ያሟላ ይሆናል፡፡ የእግዚአብሔርን ግን ማን ሊያሟላ ይችላል? በእርግጥም መልሱ መለኮታዊነት ያለው፣ በሥጋ የተገለጠ፣ ፍፁም ሰው ፍፁም አምላክ የሆነ እርሱ ክርስቶስ ነው የሚል ይሆናል (ማቴ. 16÷16)፡፡ ማዳን የእርሱ ነው! 

      አይሁድ ክርስቶስን ከሰቀሉትና ከሞተ በኋላ እጅግ ይጨነቁ እንደ ነበር ከወንጌላት እንረዳለን (ማቴ. 27÷62-66)፡፡ እንዲያውም መቃብሩ ላይ አትመው ጠባቂዎች አኑረዋል፡፡ ጠላት እንኳን ተነሥቷል የሚለው ቃል ይቅርና ሞቷል የሚለው ያሸብረዋል፡፡ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ወደ ጲላጦስ ተሰብስበው ደቀ መዛሙርቱ በሌሊት መጥተው እንዳይሰርቁት ለሕዝቡም ከሙታን ተነሣ እንዳይሉ በማለት መላ እንዲፈልግ እንዳስረዱት እናነባለን፡፡ በሌላ በኩል ደቀ መዛሙርቱን ስንመለከት ደግሞ ተስፋ በመቁረጥ ስሜት ውስጥ ሆነው ወደ ቀደመ ተግባራቸው ሲመለሱ እንመለከታለን፡፡

      “እንዳይሰርቁት” የሚለው አገላለጽ ጌታ ዋጋው ምን ያህል ውድ እንደ ሆነ በጥቂቱ ያስረዳል፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ጋር የነበረው ስሜት ግን ከዚህ በተቃራኒ ነበር፡፡ እነዚያ ከበድኑ እንኳ ትርፍ እንዳለ ሲያስቡ፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን የተነገራቸውን ተስፋ እንኳ መጠበቅ ተስኖአቸው ነበር፡፡ መዳን የሆነልን እኛ የአዳኛችንን ማንነት ከምንረዳው በላይ ጠላት እንዴት እንደዳንን ማስተዋሉ መደነቅን ይሞላል፡፡ በእርግጥም እኛ ከምንረዳው በላይ ጠላት ይረዳዋል፡፡ ከምን እንዳመለጥን፣ ምን እንደተደረገልን፣ ምን ያህል ዋጋ እንዳለን ጠላታችን አሳምሮ ያውቀዋል፡፡

      ጌታ ሞቶ የነበረ ሕያውም የሆነ ፊተኛና መጨረሻ ነው (ራዕ. 2÷8)፡፡ ሞተ ብለን የምናዝንለት፣ የምናነባለት፣ የምንቆጭለት፣ የምንታቀፈው በድን አይደለም፡፡ እርሱ ከሙታን መካከል ተለይቶ የተነሣ፣ ከሙታንም በኵር ነው (ሉቃ. 24÷5፤ ቆላ. 1÷18)፡፡ እንወደው፣ እናከብረው፣ እንመካበትና እንኖርለት ዘንድ እርሱ ጌታ ለዘላለም ሕያው ነው፡፡ አሁን በእርሱ ሕያውነት ሐሴት እናደርጋለን፡፡ ያቺ ሴት ባሏ ከመቃብር የተነሣ ቢሆን ኖሮ በበድኑ ካሳየችው ፍቅር በላይ ባፈቀረችው፣ እንደ ጌጥ ይዛው በዞረች፣ ላለፈ ላገደመው ባወራችለት ነበር፡፡ ግን አማራጭ ስላልነበራት በበድኑ ደስ ለመሰኘት ሞክራለት፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሙሽራዋ በዝግ መቃብር ሞትን ድል አድርጎ የተነሣ፣ ሞት ሆይ መውጊያህ፣ ሲኦል ሆይ ድል መንሣትህ የታለ? እያለች ከፊት ይልቅ አብዝታ የምትወደው ነው፡፡ በፍቅር የምታየው፣ በፍቅር የምታወራው፣ በፍቅር የምትገልጠው፣ በፍቅር የምትመካበት ባለ ድል ነው፡፡ ዛሬ ግን እንደዚያ አይደለም፡፡ ብዙዎች በስሙ መጠራት፣ በክብሩ መነገር፣ በኃይሉ መወደስ ደስ የማይሰኙበት፤ በስሙ እንጀራ እየበሉ በስሙ የማይታመኑበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ የአፍ አማኞች የልብ ነቃፊዎች ስፍራን የያዙበት ጊዜ ቢኖር ይህ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ሰምና ወርቅ የመድኃኒዓለም ፍቅር ነው፡፡

    ያ በሥጋው ወራት ከቦታ ወደ ቦታ እንደ ነዳይ የተንከራተተው ጌታ ዛሬም በወንጌሉ እየተገፋ፣ የጸብና የልዩነት ምክንያት እየተደረገ፣ በሰዎች ልብ ሸንጎ ፊት እየቆመ ነው፡፡ ሐዋርያው “ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌል ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን” (ገላ. 1÷8) እንዳለ እንኳን የሰው የመላእክትም ስብከት የታረደው በግ ነው፡፡ ጌታ ለእኛ ላሳየው ፍቅር የሰጠነው ምላሽ ምንድነው? ያ ፍቅር ዛሬ አላዘነምን? ያ ችንካር ያለፈበት እጅ፣ የደም ላብ ያላበው ፊት ትዝ አይላችሁምን? እንድንኖርለት ሞቶልን፤ ለሞተልን መኖር ከብዶናልና ጌታ ይራራልን፡፡      

    ሰቆቃወ ኤርምያስን ስናጠና ብዙ የተደረገለት፣ እግዚአብሔር የረዳው፣ በወጀብና በአውሎ መንገድ የሰጠው ሕዝብ በድፍረት እግዚአብሔርን እንዳሳዘነ ደግሞም የተሰጠውን ቃል ኪዳን በማፍረስ በበረከት አምላክ ላይ ዐመፅ እንደ ተፈፀመ በዚህም ምክንያት የመጽሐፉ ክፍል በእንባና በሙሾ እንደተፃፈ እንረዳለን፡፡ ክፍሉ በሰቆቃና በሀዘን የሚጀምር ቢሆንም የሚያጠናቅቀው ግን በንስሐ ነው፡፡ ነቢዩም እያነባ ሕዝቡን የጋበዘው ለንስሐ ነበር፡፡ በዚህ በጸጋው ዘመን ጌታ እንደ ብሉይ ኪዳኑ በመዓት እያስፈራራ ሳይሆን በምሕረት እየጠራ ንስሐ ግቡ ይለናል፡፡ በኤርምያስ ሰቆቃና ሐዘን ሕዝቡ ከዘላለም ሞት አላመለጠም፡፡ በክርስቶስ መከራና ሞት ግን ታሪክ ተለውጧል፡፡ የሰው ልጆች ኑሮም በውበቱ ተጊጧል፡፡ በዚህም ዘመን ያ የቀራንዮ ፍቅር ያነባል፡፡ ሕይወታችንን ተጠማሁ እያለ ይጮሃል፡፡ ኑ ሕይወት ይሁንላችሁ ይላል፡፡ እርሱ ጌታ የተስፋ፣ የፍቅር፣ የታማኝነት፣ የደኅንነት ጌታና ባለቤት ነው፡፡ ነቢዩ ኤርሚያስ በሰቆቃው ስለ እግዚአብሔር መልካምነት ተርኮ የሕዝቡን ልብ ለማለዘብ እንደ ሞከረ ሁሉ እንደ ነዳይ ለተቆጠረው ትልቅ ፍቅር ይሸነፉ ዘንድ ክርስቶስን ወደ ሰዎች ልብ ማድረስ የተገባ ነው፡፡

ምንጭ፡- የፍቅር ሰምና ወርቅ፣ ዲያቆን ኢዮብ ይመር፣ ገጽ 10

3 comments:

  1. Eyobie tsegawen tabesaleh teberek

    ReplyDelete
  2. esu eko new bewedajoche bet yekoselekut kusel yalen ...yedengelmareyam lej new meto yemiyasaregenem abet yezen gize yedengel mareyam deseta endet des yelale ...kedusane melaket des yebelachu ... haya aratu kehanate semay des yebelachu ...kedusan tsdekan semaetat des yebelachu ...ene hateyategnaw yezan gize endet yehon ... dengel behulu des yebelesh... cher yegetemen

    ReplyDelete
  3. Bear in mind these simple pointers when you're choosing your promise rings and you'll have a symbol of your relationship
    to wear and enjoy. A solitaire diamond has, for a extended time, been related
    to engagement rings as well as a coming big event. As emerald
    is an expensive gem they usually come in shapes
    that help in retaining maximum weight from raw stone.

    Take a look at my page; promise rings opinions

    ReplyDelete