እሮብ ሰኔ
20/2005 የምሕረት ዓመት
“በያዕቆብ ላይ ክፋትን አልተመለከተም፡፡ በእስራኤልም ጠማምነትን አላየም፡፡
አምላኩ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነው፡፡ የንጉሥም እልልታ
በመካከላቸው አለ (ዘኁ. 23÷21)”
በምድሪቱ ላይ መኖርን የታደሉ ሰዎች ሁሉ አንዱ ከሌላው ጋር አብሮ በመኖር ውስጥ ያለውን ጣዕምና ምሬት በአግባቡ ያውቃሉ፡፡
እንደ ሰው እንዲኖሩን ከምንፈልጋቸው ቁሳቁሶች በላይ ሰዎች በዙሪያችን መኖራቸው እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ አውራኝና ደስ ይበለኝ፤
አናግሪኝና እንቅልፍ ይውሰደኝ የሚሉ ሰዎችን ሳስባቸው አንዳችን በሌላችን ላይ ሊኖረን የሚችለውን አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተጽእኖ
አስተውላለሁ፡፡ እስቲ ለመኖር እንድትጓጉ፣ ለመሥራት እንድትተጉ፣ በፍቅር እንድትመላለሱ፣ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም እንድትኖሩ በምክርና
በምሪት የተጉላችሁን ሰዎች አስቧቸው፡፡ በምታምኑት አምላክ ስምም ባርኳቸው፡፡
ሰዎች ከእኛ ጋር መሆናቸው፣ በሀዘንና በደስታ ዙሪያችንን መክበባቸው ምንኛ ግሩም ነው? አንዳንዴ አፋችንን ሞልተን በመተማመን
የምንደገፍባቸው ሰዎች እንኳ በቁጥር ብዙ ናቸው፡፡ ታዲያ እንደማይጥሉን ተማምነን በመንገድ የተካካዱን፣ ላንለያይ በቃል ኪዳን ተሳስረናቸው
በጥላቻ የተቆራረጡን፣ ብዙ ጠብቀንባቸው የውኃ ሽታ የሆኑብን የዚያኑ ያህል ናቸው፡፡ በእርግጥም ሰውን ክንድ ማድረግ እርግማን ነው
(ኤር. 17÷5)፡፡ የእግዚአብሔር ኪዳን ግን የማይሻገረው የለም፡፡ ክንዱ የዘላለም ዋስትና ነው፡፡ እርሱ ከእኛ ጋር ያለው ኪዳን
በደም የሆነ ነው፡፡ ሁኔታዎች ቢቀያየሩ፣ ነገሮች እንደ ነበሩ ባይቀጥሉ፣ የሰዎችን ብርታት ድካም ቢፈራረቀው፣ ጠላት ለእልልታ አፉን
ቢያሰፋ፣ ከሥጋና ከደም አልቆ ቢቆረጥ ተስፋ እርሱ እግዚአብሔር ያውና ሕያው ነው፡፡ እውነቱ በሰዎች እውነተኛነት ላይ፣ ጽድቁ በሰው
ጽድቅ ላይ፣ ቅድስናው በሰዎች ቅድስና ላይ የተመሰረተ አይደለም፡፡ እርሱ ሁሉን የሚቀድስ ቅዱስ፣ የሚያጸድቅ ፃድቅ፣ የምናውቅበት
ሀቅ ነው፡፡