Wednesday, June 5, 2013

የሚያስመካ እኔነት


                                እሮብ ግንቦት 29/2005 የምሕረት ዓመት

         እግዚአብሔር ለሙሴ “ያለና የሚኖር እኔ ነኝ” ብሎ ያህዌ የሚለውን ስሙን በብሉይ ኪዳን እንደ ገለጠለት ከቃሉ እንረዳለን (ዘፀ. 3÷14)፡፡ ጌታ ደግሞ ለአይሁድ ሲናገር፡- “አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ (እኔ ነኝ)” (ዮሐ. 8÷58) በማለት አምላክ የሆነ የአምላክ ልጅ መሆኑን አስረዳቸው፡፡ እርሱ ጌታ፡-
1. በልቶ አለመጥገብ በሚስተዋልበት፣ ሰው ከብዙ እንጀራው ጋር ሆኖ በጠኔ በሚሰቃይበት በዚህ ዓለም ምድረ በዳ ውስጥ የማይቋረጥ እንጀራ ኢየሱስ ነው፡፡ ለርሀባችን መጥገብ ልኩ ይህ እንጀራ ነው፡፡ ለሕይወት ዋስትናን፣ ለዕድሜ ልምላሜን፣ ለትጋታችን ፍፃሜን የሚሰጥ እንዲህ ይላል፡-
Ø “የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ” (ዮሐ. 6÷35)!

2. ምድሪቱ ላይ ፀሐይ ስትወጣና ስትጠልቅ ማየት ልባችን በተለየ ሁኔታ የማያስተውለው ልምምድ ነው፡፡ ዳሩ ግን በብዙ ሰዎች ልብ ላይ ፀሐይ ብርሃኗ ስፍራን አላገኘም፡፡ የጭፍን አስተሳሰብና የጭፍኖች ተግባር ምድሪቱን ማስጨነቁም ከዚህ ገሀድ የተነሣ ነው፡፡ ሰው ውጫዊ አካባቢው ቢጨልም፣ የእጁ ሥራ መኖሪያ ቤቱን ጨለማ ቢሞላው ሻማ ይለኩሳል፡፡ ሰው ግን ከልቡ ጨለማ ጋር እስከ ሞት ለሞኖር መቁረጡ ምንኛ ያሳዝናል? ዙሪያ ገባው ለጨላለመባችሁ፣ የጠራ የነፃ አልታይ ላላችሁ፣ ዓይን ፈጥጦ ልብ ለታወረባችሁ ጨለማን የሚያጋልጠው፣ ከዚህ እስራት ለዘላለም የሚፈታው እንዲህ ይላል፡-

Ø “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ” (8÷12)!

3. ለዓለም ሁሉ ኃጢአት የመሥዋዕት በግ ሆኖ ራሱን ያቀረበው ጌታ የወዳጅ ልክ ነው፡፡ ወዳጅነት ሁሉ በእርሱ ይለካል፡፡ የፍቅር ሚዛን እርሱ ነው፡፡ የመውደዱ ፍፃሜ እኛን በእርሱ መጠቅለል ነው፡፡ በእውነተኛ ፍቅር እጮኛውን የሚወድ ባል የልብ ናፍቆቱ ሴቲቱን መጠቅለል(የብቻ) ነው፡፡ እርሱ የልቡን እልፍኝ፣ የሰማይን ደጆች የከፈተልን ነው፡፡  በዚህ ምድር ላይ ብዙ የተዘጉብን ነገሮች ይኖራሉ፡፡ አንዳንዴ መኖራችንን የሚወስኑልን ነገሮች እስኪሆኑ ድረስ በተስፋ መቁረጥ እንሞላለን፡፡ ክርስቶስ ግን ለእኛ ማንም የማይዘጋው በር አለው፡፡ የማንም ጣልቃ ገብነትና ሰብቅ እርሱን አያስጨክነውም፡፡ በጎቹን የሚወድድ፣ በስስት ዓይንና በፍቅር ልብ የሚመለከተን እንዲህ ይላል፡-


Ø “እኔ የበጎች በር ነኝ” (10÷7)!

4. መሰማራትና መሰብሰብ ለእንስሳት ብቻ እንደ ሆነ እናስብ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ነቢዩ ዳዊት ሰውም መሰማራት እንደሚያስፈልገው “በለምለም መስክ ታሰማራኛለህ” በማለት አስረድቶናል፡፡ በእርግጥም ጌታ ያሰማራን፡፡ ያ ለመንጋው የሚራራ፣ ያ ነፍሱን ስለ በጎቹ አሳልፎ የሚሰጠው፣ ያ የእረኞች አለቃ ያሰማራን፡፡ ያ ከእንባችን ጋር እንባ፣ ከቁስላችን ጋር ቁስል፣ ከስደታችን ጋር ስደት፣ ከመጠላታችን ጋር ጠላት፣ ከጩኸታችን ጋር ጩኸት ያለው ያ የናዝሬቱ ኢየሱስ፣ የሕማም ሰው ያሰማራን፡፡ በጎቹን ከጠላት ታግሎ የሚያስመልጥ፣ መሰማሪያን የሚሰጥ፣ መውጣትና መግባትን በማያንቀላፋ ትጋት የሚጠብቅ እንዲህ ይላል፡-

Ø “መልካም እረኛ እኔ ነኝ” (10÷11)!

5. ሕያውነት ያለና የሚንቀሳቀስ ነገር መጠሪያ ነው፡፡ ሕይወትን ከተቀባዮቹ ከእኛ አንፃር ሳይሆን ከሰጪው ፈጣሪ አንፃር መመልከት ብንችል ዋጋዋን እናስተውላለን፡፡ እውነትም ሰው ለነፍሱ ምን ዋጋ ይሰጣል? ቤዛ የሆነን፣ ነፍሳችንን የተዋሳት አንዱ መድኃኒት ኢየሱስ ይባረክ፡፡ ለእርሱ ሞት መጨረሻ፣ የሰው ኑሮ መደምደሚያ አይደለም፡፡ የእኛ ጌታ መፍትሔነቱ ሞትንም ይጠቀልላል፡፡ እንደሞተብን ለሚሰማን ነገር ሁሉ ሕይወትን የሚዘራ ሕይወት እርሱ ነው፡፡

       ከሁሉ በሚበልጥ የትንሣኤ ኃይል በሁኔታዎች ላይ ድልን የሚያጎናጽፍ ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ፣ መቃብርን ያራቆተው ትምክህት ኢየሱስ ነው፡፡ አላዛርን ከሙታን መካከል የቀሰቀሰ፣ የእህት ዘመዶቹን እንባ ያበሰ፣ ማራዋን ቢታንያ በእልልታ ያጥለቀለቀ ትንሣያችን እርሱ ነው፡፡ የሞትን መውጊያ የሰበረ፣ የሲኦልን ድል መንሳት ያንበረከከ እስትንፋስ ሕይወታችን ነው፡፡ የትንሣኤያችን በኩር፣ የባርነታችን ነፃ አውጪ፣ የበደላችን ካሳ፣ የጽድቃችን ማረጋገጫ እንዲህ ይላል፡-

Ø “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ” (11÷25)!

6. የዘላለም ሞት የተፈረደብንን የዘላለም ሕይወት የሰጠን የዘላለም መድኃኒት ነው፡፡ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የነበረውን የጸብ ግድግዳ  ያፈረሰው ኢየሱስ በምድር ያሉ ሁሉ ከሰማዩ የሚገናኙበት መንገድ ነው፡፡ ክርስቲያን ወደ ክብር የሚደርሰው ክብራችን በሆነው ክርስቶስ ነው፡፡ ሰዎች ወደ ጽድቅ የሚደርሱት ጽድቃቸው በሆነው ኢየሱስ ነው፡፡ ወደ እረፍት የመድረስ ምስጢር በላይ በሰማይ በታች በምድር ያለውን ሁሉ በሚጠቀልል ጌታ ነው፡፡

       መንገዱ የእውነት ዋስትና ያለው የማያሳስትም ነው፡፡ የማወቅን ጥማት የሚያረካ፣ የረከሰውን ከቅዱሱ መለየት የሚያስችል፣ መንፈስን ሁሉ የምንመረምርበት ድፍረት ይህ እውነት ነው፡፡ ያለዚህ እውነት ሰው በአቋም አይኖርም፡፡ ለዘላለም ነገር አይቆርጥም፡፡ ከሚታየው ባለፈ መመልከት አይችልም፡፡ ይህ እውነት የሕይወት ቃል ነው፡፡ እርሱ ጌታ የሕይወት ቃል ያለው ነው፡፡ ሕይወት መኖር ነው፡፡ የኑሮ ዋስትና ኢየሱስ ነው፡፡ እርሱ ያለው ሕይወት አለው፡፡ እርሱ ያለው ከሁሉ የበለጠው አለው፡፡ እርሱ ያለው ማትረፊያ አለው፡፡ እርሱ ያለው ትንሣኤ አለው፡፡ እርሱ ያለው የዘላለም መኖሪያ አለው፡፡ እርሱ ያለው በማዕበል ውስጥ ፀጥታ አለው፡፡ እርሱ ያለው በሁኔታዎች ላይ ድል አለው፡፡ እርሱ ያለው ወደ ሰማይ መድረስ አለው፡፡ የማወቅ ልክ እውነተኛ፣ የመኖር ኃይል ሕያው፣ መድረስን የሚሰጥ ፍኖት እርሱ እንዲህ ይላል፡-

Ø “እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ” (14÷6)!

7. የቅርንጫፎች ዋስትና ግንዱ ነው፡፡ የማደግ የመለምለም ኃይላቸው ግንዱ ነው፡፡ ያለዚህ ምንም ሊያደርጉ አይችሉም፡፡ ፍሬን በእነርሱ ውስጥ የሚያፈራም እርሱ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ እውነተኛው የወይን ግንድ ነው፡፡ ልብ በሉ! ውሸተኞች አሉ፡፡ ለሞት የሚያሰናዱ፣ ልምላሜን የሚመስሉ፣ ያለ ፍሬ የሚያስቀሩ ለዚህ እውነተኛ ተቃራኒ ናቸው፡፡ የልምላሜ ምስጢር ያለው በዚህ የወይን ግንድ ውስጥ ነው፡፡ በክርስቶስ የሆኑ ሁሉ ትክክለኛ ስፍራቸው በእውነተኛው ግንድ ላይ እውነተኛ ቅርንጫፍ ነው፡፡ በእግዚአብሔር ሰዎች መካከል ልዩነትን የሚፈጥረው በዚህ ግንድ ላይ እንደ ቅርንጫፍ ያፈሩት ፍሬ ነው፡፡ በብዙ ፍሬ የመገለጥ አቅም፣ እንደ ቅርንጫፍ ስፍራን የመያዝ ጉልበት፣ ለሌሎች እንደ ወይን ጣዕም የመሆን ምስጢር የሆነው እንዲህ ይላል፡-

Ø “እውነተኛ የወይን ግንድ እኔ ነኝ” (15÷1)!


        ተወዳጆች ሆይ የነፍስ፣ የሥጋና የመንፈሳችሁ መልስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው፡፡ ለእያንዳንዱ ጥያቄ “እኔ” ማለት የሚችል እርሱ ብቻ ነው፡፡ ካልተመለሱላችሁ ጥያቄዎች ጋር የምትኖሩ እናንተ ሆይ ኢየሱስ መልስ ነው፡፡ ካልተፈቱ እንቆቅልሾች ጋር የምትኖሩ ወገኖች ሆይ ክርስቶስ መፍትሔ ነው፡፡ የዘላለማችሁን ቸል አትበሉ፡፡ ጥበብና ማስተዋል ይብዛላችሁ!!

3 comments:

  1. ተወዳጆች ሆይ የነፍስ፣ የሥጋና የመንፈሳችሁ መልስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው፡፡ ለእያንዳንዱ ጥያቄ “እኔ” ማለት የሚችል እርሱ ብቻ ነው፡፡ ካልተመለሱላችሁ ጥያቄዎች ጋር የምትኖሩ እናንተ ሆይ ኢየሱስ መልስ ነው፡፡ ካልተፈቱ እንቆቅልሾች ጋር የምትኖሩ ወገኖች ሆይ ክርስቶስ መፍትሔ ነው፡፡ የዘላለማችሁን ቸል አትበሉ፡፡

    ReplyDelete
  2. ፍቅር ከመንፈሳዊው እይታ አንፃር ምን ማለት ነው?

    ReplyDelete
  3. Sew wchawiw akababi bichelm egu yeserawn bat chelema bimola shama ylekusal,
    Tadia KLBU chelema gar eskemot menor mngna yasazn?

    ReplyDelete