Wednesday, June 26, 2013

የንጉሥ እልልታ


                          እሮብ ሰኔ 20/2005 የምሕረት ዓመት

“በያዕቆብ ላይ ክፋትን አልተመለከተም፡፡ በእስራኤልም ጠማምነትን አላየም፡፡ አምላኩ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነው፡፡ የንጉሥም እልልታ በመካከላቸው አለ (ዘኁ. 23÷21)”

         በምድሪቱ ላይ መኖርን የታደሉ ሰዎች ሁሉ አንዱ ከሌላው ጋር አብሮ በመኖር ውስጥ ያለውን ጣዕምና ምሬት በአግባቡ ያውቃሉ፡፡ እንደ ሰው እንዲኖሩን ከምንፈልጋቸው ቁሳቁሶች በላይ ሰዎች በዙሪያችን መኖራቸው እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ አውራኝና ደስ ይበለኝ፤ አናግሪኝና እንቅልፍ ይውሰደኝ የሚሉ ሰዎችን ሳስባቸው አንዳችን በሌላችን ላይ ሊኖረን የሚችለውን አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተጽእኖ አስተውላለሁ፡፡ እስቲ ለመኖር እንድትጓጉ፣ ለመሥራት እንድትተጉ፣ በፍቅር እንድትመላለሱ፣ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም እንድትኖሩ በምክርና በምሪት የተጉላችሁን ሰዎች አስቧቸው፡፡ በምታምኑት አምላክ ስምም ባርኳቸው፡፡

         ሰዎች ከእኛ ጋር መሆናቸው፣ በሀዘንና በደስታ ዙሪያችንን መክበባቸው ምንኛ ግሩም ነው? አንዳንዴ አፋችንን ሞልተን በመተማመን የምንደገፍባቸው ሰዎች እንኳ በቁጥር ብዙ ናቸው፡፡ ታዲያ እንደማይጥሉን ተማምነን በመንገድ የተካካዱን፣ ላንለያይ በቃል ኪዳን ተሳስረናቸው በጥላቻ የተቆራረጡን፣ ብዙ ጠብቀንባቸው የውኃ ሽታ የሆኑብን የዚያኑ ያህል ናቸው፡፡ በእርግጥም ሰውን ክንድ ማድረግ እርግማን ነው (ኤር. 17÷5)፡፡ የእግዚአብሔር ኪዳን ግን የማይሻገረው የለም፡፡ ክንዱ የዘላለም ዋስትና ነው፡፡ እርሱ ከእኛ ጋር ያለው ኪዳን በደም የሆነ ነው፡፡ ሁኔታዎች ቢቀያየሩ፣ ነገሮች እንደ ነበሩ ባይቀጥሉ፣ የሰዎችን ብርታት ድካም ቢፈራረቀው፣ ጠላት ለእልልታ አፉን ቢያሰፋ፣ ከሥጋና ከደም አልቆ ቢቆረጥ ተስፋ እርሱ እግዚአብሔር ያውና ሕያው ነው፡፡ እውነቱ በሰዎች እውነተኛነት ላይ፣ ጽድቁ በሰው ጽድቅ ላይ፣ ቅድስናው በሰዎች ቅድስና ላይ የተመሰረተ አይደለም፡፡ እርሱ ሁሉን የሚቀድስ ቅዱስ፣ የሚያጸድቅ ፃድቅ፣ የምናውቅበት ሀቅ ነው፡፡


        ከኦሪት መጻሕፍት መካከል የመቆጠር ክፍል የሆነውን የዘኁልቍ መጽሐፍ ስንመለከት እግዚአብሔር እንደ ሁል ጊዜው ሁሉ መደነቅን የምንሞላበት፣ ክብሩን አሻግረን የምናይበት፣ ከነገዎቻችን የሚያልፍ የዘላለም ዋስትናን የምናስተውልበትን እውነት ይነግረናል፡፡ የእግዚአብሔር ሕዝብ በምድረ በዳ ነው፡፡ ለዚያም ሕዝብ በሚታይ ሁኔታ በረሃው ላይ ንጉሥ የለውም፡፡ በየመንገዳቸው ሁሉ የጠላት ዓይነት፣ ስልትና ተጽእኖ መልኩን እየቀያየረ ያስጨንቃቸዋል፡፡ ከርሃብና ጥም፣ ከስደትና ድካም በላይ መንፈሳዊ ውጊያ ፈተናቸው ነበር፡፡ በዚህ ሁሉ ጠላት በእግዚአብሔር ነገር ላይ ስልቱን ምን ያህል እንደሚቀያይርና ግልጽ ከሆነው አካሄድ በላይ ስውር ወጥመዱ ምን ያህል ብርቱ እንደ ሆነ መገንዘብ እንችላለን፡፡

        እስራኤል በግብፅ እያሉ የነበረባቸው መንፈሳዊ ፈተና እግዚአብሔርን አታምልኩ የሚል ነበር፡፡ መመለክ የባሕርዩ የሆነ፣ ይህንንም ከማንም ጋር የማይጋራ፣ በአማልክት መካከል ብቻውን አምላክ የሆነ እግዚአብሔር በበረታች ክንድ ሕዝቡን ከጨቋኝ ገዥ እጅ አላቆ የአምልኮ ነፃነትን ለሕዝቡ አወጀ፡፡ ዳሩ ግን ባህር ተከፍሎለት ከተሻገረው የእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር ስልቱን የቀየረ ጠላትነትና ውጊያ አብሮ ተሻገረ፡፡ እስራኤል በእግዚአብሔር ፊት ላሳዩት መንፈሳዊ ውድቀት ከሚጠቀሰው ምክንያት አንዱ ድብልቅ ሕዝብ ነው “ደግሞም ሌላ ብዙ ድብልቅ ሕዝብ መንጎችና ላሞችም እጅግ ብዙም ከብቶች ከእነርሱ ጋር ወጡ” (ዘፀ. 12÷38)፡፡

        ታዲያ እስራኤል ምድረ በዳውን እንደ ጀመሩ ጠላት እንደ ግብፅ እግዚአብሔርን አታምልኩ በማለት ሳይሆን ”አምልኩ ግን ቀላቅላችሁ አምልኩ” በሚል ዓይነት ማኅበሩን በድብልቅ አምልኮ ፈተነው፡፡ በዘመናት እንዳየነው ሰይጣን ከእግዚአብሔር ጋር ተቀላቅሎ ክብርን መቀበሉ ቅር አሰኝቶት አያውቅም፡፡ እግዚአብሔር ግን ይህንን ያደርግ ዘንድ ዓመፀኛ አይደለም፡፡ ብቻውን አምላክ ነውና ብቻውን ይመለክ ዘንድ ይፈልጋል፡፡ ደግሞም በእውነት ይገባዋል፡፡ እግዚአብሔር የደከመለት ሕዝብ ጣዖት እያመለከ አንዴ አስታሮትን ሌላ ጊዜ በኣሊምን እየተከተሉ ለእግዚአብሔር ጀርባቸውን ሰጡት፡፡ ዛሬ ክርስቲያን አትሁኑ የሚል ፈተና በብዛት ባይታይም ዳሩ ግን ጠላት የክርስትናውን እውነት ከሰው ወግና ብልሃት፣ ልብ ወለድና ሐሰት ጋር ቀላቅሎታል፡፡ በእውነትና በመንፈስ የሚመለከውን እግዚአብሔር ሰዎች በሥጋ ብልሃት እንዲፈልጉት ጠላት አትግቷቸዋል፡፡

         ቤተ ክርስቲያን ልክ እንደ ጴርጋሞን ጠባይ ከዓለም ጋር ጋብቻን አድርጋለች፡፡ ሙሽራዋን ክርስቶስን ወሽማበታለች፡፡ በአደባባይ መከበሪያዋ፣ በጓዳ መጽናኛዋ፣ በስውር መዋቢያዋ፣ በዓለም ፊት ሞገሷ ከክርስቶስ ያነሰ ነገር ሆኗል፡፡ ክርስትናን ከዓለም መለየት እስኪያቅት ድረስ በገዛ ደሙ የዋጃት ቤተ ክርስቲያን በዚህ ዓለም ስርዓት ተጽእኖ ስር ወድቃለች፡፡ በእርግጥም የክርስትናው ቋሚ ፈተና ድብልቅ ነገር ነው፡፡ በሰዎች ደረጃም ቢሆን እግዚአብሔርን ደባልቀው ማምለክ ያልከበዳቸው ብዙ ናቸው፡፡ እውነተኛውን ከእውነት ካነሰ ነገር ጋር ቀላቅሎ መመስከርና መኖር የዘመናችን ክርስትና ነው፡፡ እንደነዚህ ያሉቱ የእግዚአብሔር ነገር ብቻ አልበቃ ብሏቸው ወደ ራሳቸው ነገር ዝቅ ያሉ ናቸው፡፡ እግዚአብሔር ያስደስተኛል ያለው ቸል ተብሎ ሰዎች ያስደስተዋል ብለው በሚያስቡት መንገድ እየሄዱ ነው፡፡ ስንወጣ ተቆርጦ ያልቀረ፣ አብሮ የወጣ፣ ከዓለም ወደ ክርስትናው የተሻገረ ነገር የመንፈሳዊ ሕይወት ብርቱ ተግዳሮት ነው፡፡ የእግዚአብሔርን ውለታ የሚያስረሳ፣ ከዘላለም ወዳጅ የሚያቆራርጥ፣ ከምድሩ አቆራኝቶ ከሰማይ የሚያፋታ ድብልቅ ሕዝብ ለእስራኤል ፈተናቸው ነበር፡፡ ለእናንተስ?

         የእግዚአብሔርን አሳብ ከዓለም አሳብ፣ የእግዚአብሔርን አገዛዝ ከዓለም አገዛዝ፣ የሰማዩን ስርዓት ከዚህ ዓለም ስርዓት ጋር የመደባለቅ አካሄድ በእግዚአብሔር ፊት ፍርድ ከሚጠብቃቸው ነገሮች መካከል ነው፡፡ ነህምያ ለሁለተኛ ጊዜ የኢየሩሳሌምን ቅጽር በጎበኘበት ክፍል ከእስራኤል ጋር ድብልቅ ስለ ሆነው ሕዝብ ቃሉ ሲናገር “በዚያም ቀን የሙሴን መጽሐፍ በሕዝቡ ጆሮ አነበቡ አሞናውያንና ሞዓባውያንም ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ ለዘላለም እንዳይገቡ የሚል በዚያ ተገኘ። የእስራኤልን ልጆች በእንጀራና በውኃ ስላልተቀበሉአቸውና ይረግማቸው ዘንድ በለዓምን ስለ ገዙባቸው ነው ነገር ግን አምላካችን እርግማኑን ወደ በረከት መለሰው። ሕጉንም በሰሙ ጊዜ ድብልቁን ሕዝብ ሁሉ ከእስራኤል ለዩ።” (ነህ. 13÷1-3) ይላል፡፡

         በሕጉ መጽሐፍ ውስጥ ተገኘ የተባለው የኦሪት ዘዳግም ምእራፍ ሰባት ክፍል ነው፡፡ በዚህ ክፍል እግዚአብሔር ሕዝቡ ከአሞናውያንና ከሞዓባውያን ጋር እንዳይደባለቁ፣ ቃል ኪዳን እንዳያደርጉ፣ ጋብቻ እንዳይመሰርቱ አዝዞአል፡፡ ስለዚህም ምክንያቱ “ለአምላክህ ለእግዚአብሔር አንተ ቅዱስ ሕዝብ ነህና በምድር ፊት ከሚኖሩ አሕዛብ ሁሉ ይልቅ ለእርሱ ለራሱ ሕዝብ ትሆንለት ዘንድ አምላክህ እግዚአብሔር መረጠህ።” የሚለው ፍቅር ነበር፡፡ ነገር ግን በዚህ ክፍል ላይ እንደምንመለከተው የእግዚአብሔር ሕዝብ ተደባልቆ ጋብቻ መስርቶ እንኳን ኑሮአቸው ቋንቋቸው ሌላ ሆኖ ነበር፡፡ ልጆቻቸው የአዛጦንን ቋንቋ አቀላጥፈው እየተናገሩ የአይሁድን ቋንቋ ስተውት ነበር፡፡ በዚህም በደል ውስጥ ካህኑ ኤልያሴብን ጨምሮ ሌሎች አገልጋዮችም ነበሩበት፡፡ የአገልግሎት ግቡ ሰውን ከሞተለት ጌታ ጋር ማገናኘት ነው፡፡ በምንም አይነት መልኩ በእግዚአብሔር ስም የእኛ ቃልና ግብር ባሪያ የምትሆነ ነፍስ ልትኖር አይገባም፡፡ አይሁድ የአዛጦን፣ የአሞንና የሞዓብን ሴቶች እንዲያገቡ ካደፋፈራቸው ምክንያት አንዱ የእግዚአብሔር አገልጋዮች ድፍረት ነው፡፡ እንዲህ ያለው መደባለቅ ግን በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ አልነበረውም፡፡

         ቤተ ክርስቲያን እንደ እግዚአብሔር ቃል መመላለስን ካልተለማመደች ኑሮም ቋንቋም የዓለም ይሆናል፡፡ ለሌሎች ጥያቄ መልስ መሆኗ ይቀርና የጥያቄው አንድ አካል ትሆናለች፡፡ ለዚህ ዓለም ችግሮች መፍትሔ መሆኗም ይቀርና ችግሩን የሚያባብስ ተጨማሪ ችግር ትሆናለች፡፡ ተወዳጆች ሆይ የዘመናችን ክርስትና ተግዳሮቱ ድብልቅ እንደ ሆነ አስተዋላችሁን? 


                                                ይቀጥላል

2 comments:

  1. I don't have a word to say Just one, Let Jesus Christ Bless You Richly.

    ReplyDelete
  2. geta yibarkachihu gize siten sile betekirstiyanachin yeminweyayibet gize lay endalen yisemagnal. ahun fetenaw Egziabherin atimenu bemalet aydelem.........

    ReplyDelete